በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!

 ምዕራፍ 13

የመንግሥቱ ሰባኪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው አደረጉ

የመንግሥቱ ሰባኪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው አደረጉ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ተከታዮቹ ከመንግሥታትና በሕግ ተጠቅመው የስብከቱን ሥራ ለማስቆም ከሚሞክሩ አካላት ተቃውሞ ገጠማቸው

በ33 ዓ.ም. የዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ ብዙም አልቆየም። በኢየሩሳሌም ያለው የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመም ገና ጥቂት ሳምንታት ማለፋቸው ነው። ሰይጣን እርምጃ ለመውሰድ ይህ አመቺ ጊዜ እንደሆነ ሳይሰማው አልቀረም። ጉባኤው እድገት ከማድረጉ በፊት ከሕልውና ውጭ ሊያደርገው ፈልጓል። በመሆኑም ምንም ጊዜ ሳያጠፋ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ላይ እገዳ እንዲጥሉ አደረገ። ሐዋርያት ግን በድፍረት መስበካቸውን በመቀጠላቸው ብዙ ወንዶችና ሴቶች ‘በጌታ አመኑ።’—ሥራ 4:18, 33፤ 5:14

ሐዋርያት “ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ደስ ብሏቸዋል

2 በቁጣ የበገኑት ተቃዋሚዎቻቸው በሐዋርያት ላይ በድጋሚ ጥቃት ሰነዘሩ፤ በዚህ ጊዜ ግን ሐዋርያቱን በሙሉ አሰሯቸው። ይሁንና ሌሊት ላይ የይሖዋ መልአክ የእስር ቤቱን በሮች ከፍቶ አስወጣቸው፤ በመሆኑም ንጋት ላይ መስበካቸውን ቀጠሉ! ሐዋርያቱ እንደገና ተይዘው በገዢዎቹ ፊት የቀረቡ ሲሆን እንዳይሰብኩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመጣሳቸው ገዢዎቹ ከሰሷቸው። ሐዋርያቱም “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በድፍረት መለሱ። ገዢዎቹ ይህን ሲሰሙ በጣም ስለተናደዱ ሐዋርያትን ‘ሊገድሏቸው ፈለጉ።’ ይሁንና ልክ በዚህ ጊዜ ገማልያል የሚባል በሕዝቡ ዘንድ የተከበረ የሕግ አስተማሪ፣ ገዢዎቹን እንዲህ በማለት አስጠነቀቃቸው፦ “በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ያሰባችሁትን ነገር በተመለከተ ልትጠነቀቁ ይገባል። . . . እነዚህን ሰዎች አትንኳቸው፤ ተዉአቸው።” የሚያስገርመው ገዢዎቹ፣ ምክሩን ተቀብለው ሐዋርያቱን ለቀቋቸው። ታዲያ እነዚያ ታማኝ ክርስቲያኖች ምን አደረጉ? ሐዋርያቱ በደረሰባቸው ነገር ሳይበገሩ “ስለ ክርስቶስ ይኸውም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።”—ሥራ 5:17-21, 27-42፤ ምሳሌ 21:1, 30

3, 4. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች ለማጥቃት የትኛውን ዘዴ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት ቆይቷል? (ለ) በዚህና በሚቀጥሉት ሁለት ምዕራፎች ላይ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?

3 በ33 ዓ.ም. ክርስቲያኖች ፍርድ ቤት የቀረቡበት ይህ አጋጣሚ፣ ባለሥልጣናት በክርስቲያን ጉባኤ ላይ የሰነዘሩት የመጀመሪያው ተቃውሞ ቢሆንም የመጨረሻው ግን አይደለም። (ሥራ 4:5-8፤ 16:20፤ 17:6, 7) ዛሬም ቢሆን ሰይጣን በእውነተኛው አምልኮ ተቃዋሚዎች በመጠቀም ባለሥልጣናት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ እንዲጥሉ ለማድረግ ይሞክራል። ተቃዋሚዎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ የተለያዩ ክሶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። ከእነዚህ ክሶች መካከል ‘የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው’ እንዲሁም ‘በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳሉ’ የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ ነጋዴዎች ወይም ሸቀጥ አዟሪዎች  እንደሆንን የሚገልጽ ክስ ተሰንዝሮብን ያውቃል። ወንድሞቻችን ተገቢ እንደሆነ በሚሰማቸው ጊዜ ሁሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ እነዚህ ክሶች ሐሰት መሆናቸውን አረጋግጠዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኝቷል? ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት የተላለፉ የፍርድ ውሳኔዎች በዛሬው ጊዜ አንተን በግለሰብ ደረጃ የሚነኩህ እንዴት ነው? እነዚህ ውሳኔዎች ‘ለምሥራቹ በመሟገትና ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን በማድረግ’ ረገድ አስተዋጽኦ ያበረከቱት እንዴት እንደሆነ መመልከት እንድንችል ፍርድ ቤት የቀረቡ አንዳንድ ጉዳዮችን እስቲ እንመርምር።—ፊልጵ. 1:7

4 በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ የመስበክ መብታችንን ለማስከበር ጥረት ያደረግነው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በሚቀጥሉት ሁለት ምዕራፎች ደግሞ የዓለም ክፍል ላለመሆንና በአምላክ መንግሥት መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር ስንል ጉዳያችንን ፍርድ ቤት በማቅረብ ካደረግናቸው ትግሎች አንዳንዶቹን እንመለከታለን።

የሕዝብን ሰላም አደፍራሾች ወይስ የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች?

5. በ1930ዎቹ መገባደጃ አካባቢ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይታሰሩ የነበሩት ለምንድን ነው? በኃላፊነት ላይ የነበሩት ወንድሞች ምን እርምጃ ለመውሰድ አሰቡ?

5 በ1930ዎቹ መገባደጃ አካባቢ በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ በሚገኙ ከተሞችና ግዛቶች በሙሉ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ ለመካፈል የሚያስችላቸው ሕጋዊ ፈቃድ እንዲያወጡ ለማስገደድ ጥረት ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ወንድሞቻችን እንዲህ ያለ ፈቃድ ለማውጣት አላመለከቱም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ፈቃድ በማንኛውም ጊዜ ሊሰረዝ ይችላል፤ ወንድሞቻችን የትኛውም መንግሥት ቢሆን ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሰብኩ ለክርስቲያኖች የሰጣቸውን ትእዛዝ እንዳይፈጽሙ የማገድ ሥልጣን እንደሌለው ተሰምቷቸው ነበር። (ማር. 13:10) በዚህም ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ታሰሩ። በዚህ ጊዜ፣ በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ጉዳዩን ፍርድ ቤት ለማቅረብ አሰቡ። ወንድሞች ይህን ያደረጉት መንግሥት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታቸውን በነፃነት እንዳያራምዱ የጣለው እገዳ ሕጋዊ እንዳልሆነ እንዲታወቅ ለማድረግ በማሰብ ነበር። በ1938 ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ የፍርድ ሂደት እንዲካሄድ መንገድ የከፈተ አንድ ሁኔታ ተፈጠረ። ይህ ሁኔታ ምንድን ነው?

6, 7. የወንድም ካንትዌል ቤተሰብ ምን አጋጠመው?

6 ኒውተን ካንትዌል የተባሉ የ60 ዓመት ወንድም ከባለቤታቸው ከኤስተር እና ሄንሪ፣ ራስልና ጄሲ ከተባሉት ልጆቻቸው ጋር ሚያዝያ 26, 1938 ማክሰኞ ዕለት በከነቲከት በምትገኘው በኒው ሄቨን ከተማ ምሥራቹን ሲሰብኩ ለመዋል አስበው ጠዋት ላይ ከቤታቸው ወጡ። ሁሉም ልዩ አቅኚዎች የሆኑት የዚህ ቤተሰብ አባላት አገልግሎት ሲወጡ የዚያን ዕለት ወደ ቤት ላይመለሱ እንደሚችሉ ያውቁ ነበር። ለምን? ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜያት ታስረው ስለነበር እንደገና ሊታሰሩ እንደሚችሉ ይጠብቁ ነበር። ይሁንና ይህን ማወቃቸው የመንግሥቱን መልእክት ከመስበክ ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም። ቤተሰቡ ወደ ኒው ሄቨን የሄዱት ሁለት መኪኖችን ይዘው ነበር። ወንድም ኒውተን፣ በቤተሰቡ መኪና ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንና ይዘዋቸው የሚንቀሳቀሱትን የሸክላ ማጫወቻዎች የጫኑ ሲሆን የ22 ዓመቱ ሄንሪ ደግሞ የድምፅ ማጉያ የተገጠመለትን መኪና ይነዳ ነበር። ቤተሰቡ የፈራው አልቀረም፤ ሥራቸውን ከጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ፖሊሶች አስቆሟቸው።

7 መጀመሪያ የተያዘው የ18 ዓመቱ ራስል ነበር፤ ቀጥሎም ወንድም ኒውተን እና እህት ኤስተር ተያዙ። የ16 ዓመቱ ጄሲ፣ ወላጆቹና ወንድሙ በፖሊሶች  ተይዘው ሲወሰዱ ከርቀት ይመለከት ነበር። ሄንሪ የሚሰብከው በከተማው ውስጥ በሌላ አካባቢ ስለነበር ጄሲ ብቻውን ቀረ። ያም ቢሆን የሸክላ ማጫወቻውን ይዞ መስበኩን ቀጠለ። ሁለት ካቶሊኮች፣ ጄሲ “ጠላቶች” የተባለውን የወንድም ራዘርፎርድን ንግግር በሸክላ ማጫወቻው እንዲያሰማቸው ተስማሙ። ሆኖም ሰዎቹ ንግግሩን ሲያዳምጡ በጣም ስለተበሳጩ ጄሲን ሊመቱት ፈለጉ። እሱ ግን ምንም ሳይደናገጥ ትቷቸው ሄደ፤ ብዙም ሳይቆይ አንድ ፖሊስ አስቆመው። በመሆኑም ጄሲም ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። ፖሊሶቹ በእህት ኤስተር ላይ ክስ ባይመሠርቱም ወንድም ካንትዌልንና ልጆቹን ከሰሷቸው። ይሁንና በዚያኑ ዕለት በዋስ ተለቀቁ።

8. ፍርድ ቤቱ፣ ጄሲ ካንትዌል ሰላም የሚያደፈርስ ተግባር ፈጽሟል ብሎ የፈረደው ለምንድን ነው?

8 ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም መስከረም 1938 የወንድም ካንትዌል ቤተሰብ በኒው ሄቨን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀረበ። ወንድም ኒውተን፣ ራስልና ጄሲ ፈቃድ ሳያወጡ የእርዳታ ገንዘብ አሰባስበዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ተፈረደባቸው። ይህን ፍርድ በተመለከተ ለከነቲከት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢባልም ጄሲ ሰላም የሚያደፈርስ ተግባር ፈጽሟል በሚል ክስ ጥፋተኛ ነው ተባለ። ለምን? የተቀዳውን ንግግር ያዳመጡት ሁለቱ ካቶሊኮች፣ ንግግሩ ሃይማኖታቸውን የሚነቅፍ በመሆኑ እንዳስቆጣቸው ፍርድ ቤት ቀርበው በመመሥከራቸው ነው። በድርጅታችን ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ይህን ውሳኔ ለማስለወጥ ሲሉ ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማለትም በአገሪቱ ላለው የመጨረሻው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ።

 9 መጋቢት 29, 1940 የመሃል ዳኛው ቻርልስ ሂዩዝ እና ሌሎች ስምንት ዳኞች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ወንድም ሄይደን ከቪንግተን ያቀረበውን ይግባኝ ማዳመጥ ጀመሩ። * የከነቲከት ግዛት አቃቤ ሕግ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሰላም የሚያደፈርሱ መሆናቸውን ለማሳየት የመከራከሪያ ነጥብ ሲያቀርብ ከዳኞቹ አንዱ “ክርስቶስ ኢየሱስ ያወጀው መልእክት በሰዎች ዘንድ የተጠላ ነበር አይደል?” በማለት ጠየቁት። አቃቢ ሕጉም “አዎን፣ እንዲያውም ካልተሳሳትኩ ኢየሱስ ይህንን መልእክት በማወጁ ምን እንደገጠመው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል” በማለት መለሰ። ይህ ሐቁን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ንግግር ነበር። አቃቤ ሕጉ ሳይታወቀው የይሖዋ ምሥክሮችን ከኢየሱስ ጋር፣ መንግሥትን ደግሞ በኢየሱስ ላይ ከፈረዱት ሰዎች ጋር እየፈረጃቸው ነበር! ፍርድ ቤቱ ግንቦት 20, 1940 በአንድ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደላቸው።

ሄይደን ከቪንግተን (ከፊት መሃል ላይ)፣ ግሌን ሃው (በስተ ግራ) እና ሌሎች ከተፈረደላቸው በኋላ ከፍርድ ቤት ሲወጡ

9, 10. (ሀ) የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከወንድም ካንትዌል ቤተሰብ ጋር በተያያዘ ምን ውሳኔ አስተላለፈ? (ለ) ይህ ውሳኔ አሁንም ድረስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

10 የዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ምን ትርጉም ነበረው? ይህ ውሳኔ ሃይማኖትን በነፃነት የማራመድ መብት እንዲከበር እንዲሁም የፌዴራሉም ሆነ የግዛቱ መንግሥት አሊያም የከተማው አስተዳደር ሃይማኖታዊ ነፃነትን የማገድ መብት እንዳይኖረው አድርጓል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ፣ ጄሲ “የማኅበረሰቡን ሰላም የሚያደፈርስም ሆነ ሥርዓት የሚጥስ . . . ምንም ተግባር እንዳልፈጸመ” ገልጿል። በመሆኑም ውሳኔው የይሖዋ ምሥክሮች በኅብረተሰቡ ሰላምና ጸጥታ ላይ ምንም ዓይነት ስጋት እንደማይፈጥሩ በግልጽ አስቀምጧል። ይህ፣ የአምላክ ሕዝቦች በፍርድ ቤት ያገኙት ታላቅ ድል ነው! ይህ ውሳኔ አሁንም ድረስ የሚጠቅመን እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ጠበቃ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ ያለነው የይሖዋ ምሥክሮች፣ ተገቢ ያልሆነ እገዳ ይጣልብናል ብለን ሳንሰጋ ሃይማኖታችንን በነፃነት የማስፋፋት መብት ያለን መሆኑ በምንኖርበት አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ተስፋ ያዘለ መልእክት ለማካፈል አስችሎናል።”

በመንግሥት ላይ ዓመፅ የሚያነሳሱ ወይስ እውነትን የሚያውጁ?

ኩዊቤክ ለአምላክ፣ ለክርስቶስና ለነፃነት ያላት የመረረ ጥላቻ መላውን ካናዳ የሚያሳፍር ነው

11 በ1940ዎቹ ዓመታት በካናዳ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። በመሆኑም በዚያ የሚገኙ ወንድሞቻችን፣ መንግሥት የአምልኮ ነፃነትን እየተጋፋ መሆኑን ለሕዝብ ለማሳወቅ ሲሉ በ1946 አንድ ትራክት ለማሠራጨት ለ16 ቀናት የቆየ ዘመቻ አካሄዱ። ኩዊቤክ ለአምላክ፣ ለክርስቶስና ለነፃነት ያላት የመረረ ጥላቻ መላውን ካናዳ የሚያሳፍር ነው (እንግሊዝኛ) የተባለውና አራት ገጽ ያለው ይህ ትራክት በኩዊቤክ ግዛት ባሉ ወንድሞቻችን ላይ ቀሳውስት የሚያስነሱትን ዓመፅ፣ ፖሊሶች የሚፈጽሙትን የጭካኔ ድርጊትና ሕዝቡ የሚያደርስባቸውን ስደት የሚያጋልጥ ነው። ትራክቱ “የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም ያለ ሕጋዊ ማስረጃ እየታሠሩ ነው” የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር። አክሎም “በግሬተር ሞንትሪያል በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተሰነዘሩ ወደ 800 ገደማ የሚሆኑ ክሶች አሉ” ብሏል።

12. (ሀ) ትራክቱ ሲሰራጭ ተቃዋሚዎች ምን አደረጉ? (ለ) ወንድሞቻችን ምን ዓይነት ክስ ቀረበባቸው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

12 ቪልነቭ ከተባሉት የሮም ካቶሊክ አቡን ጋር እጅና ጓንት የሆነው የኩዊቤክ አስተዳዳሪ ሞሪስ ዱፕሌሲ፣ ይህ ትራክት በመሰራጨቱ ምክንያት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ “ምሕረት የለሽ ጦርነት” አወጀ። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የቀረቡት ክሶች በእጥፍ በመጨመራቸው ከ800 ወደ 1,600 ደረሱ። አንዲት አቅኚ “ፖሊሶች ብዙ ጊዜ ስለሚያስሩን ምን ያህል ጊዜ እንደታሰርን እንኳ ጠፍቶብን ነበር” ብላለች። ትራክቱን ሲያሰራጩ የተያዙ የይሖዋ ምሥክሮች “በመንግሥት ላይ ዓመፅ የሚያነሳሳና ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ” በማሠራጨት ወንጀል ተከሰሱ። *

13. በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ወንጀል የተከሰሱት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እነማን ናቸው? ፍርድ ቤቱስ ምን ውሳኔ ሰጠ?

 13 በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ወንጀል የተከሰሱት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ወንድም ኤመ ቡሼ እንዲሁም ዢዜል እና ሉሲል የተባሉት ሴቶች ልጆቹ ናቸው፤ የ18 ዓመቷ ዢዜል እና የ11 ዓመቷ ሉሲል ከአባታቸው ጋር የተከሰሱት በ1947 ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች የተከሰሱት ኩዊቤክ ያላት የመረረ ጥላቻ የተባለውን ትራክት ከኩዊቤክ ሲቲ በስተ ደቡብ ባለው እርሻቸው አካባቢ በማሠራጨታቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ሕግ ጥሰው ሰላም እንደሚያደፈርሱ ማሰብ ይከብዳል። ወንድም ቡሼ ትሑትና ገራገር ሰው ነው፤ ማንንም የማይነካና አነስተኛ እርሻውን እያረሰ የሚኖር ሲሆን አልፎ አልፎ፣ በፈረስ በሚጎተት ጋሪው ወደ ከተማ ይሄዳል። ያም ቢሆን እሱም ሆነ ቤተሰቡ በትራክቱ ላይ የተገለጹት በደሎች ደርሰውባቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥላቻ ስለነበረው የወንድም ቡሼ ቤተሰብ ንጹሕ መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ይህ ዳኛ፣ አቃቤ ሕጉ ትራክቱ ጥላቻን እንደሚቀሰቅስ በመግለጽ የወንድም ቡሼ ቤተሰብ ጥፋተኛ እንደሆነ ያቀረበውን ሐሳብ ትክክል እንደሆነ አድርጎ ተቀብሎታል። የዳኛው አመለካከት ጠቅለል ተደርጎ ሲቀመጥ ‘እውነትን መናገር ወንጀል ነው!’ እንደማለት ነው። ወንድም ኤመ እና ዢዜል በመንግሥት ላይ ዓመፅ የሚያነሳሳና ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ በማሠራጨታቸው የተፈረደባቸው ሲሆን ትንሿ ሉሲል እንኳ ወህኒ ቤት ሁለት ቀን ቆይታለች። በመሆኑም ወንድሞች ለካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማለትም በአገሪቱ ላለው የመጨረሻው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ፤ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ተስማማ።

14. በኩዊቤክ ያሉት ወንድሞች ስደት በነበረባቸው ዓመታት ምን ያደርጉ ነበር?

14 በኩዊቤክ የሚገኙት ደፋር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋብ የማይልና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እየተሰነዘረባቸውም የመንግሥቱን መልእክት መስበካቸውን ቀጠሉ፤ ይህም በአብዛኛው ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። የትራክቱ ዘመቻ ከጀመረበት ከ1946 በኋላ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ በኩዊቤክ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ300 ወደ 1,000 አድጓል! *

15, 16. (ሀ) የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንድም ቡሼን ቤተሰብ በተመለከተ ምን ውሳኔ አስተላለፈ? (ለ) ይህ ውሳኔ ለወንድሞቻችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ምን ጥቅም አስገኝቷል?

15 ዘጠኝ ዳኞች ያሉት የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኔ 1950 የወንድም ኤመ ቡሼን ጉዳይ ተመለከተ። ከስድስት ወር በኋላ ይኸውም ታኅሣሥ 18, 1950 ፍርድ ቤቱ እኛን የሚደግፍ ውሳኔ አስተላለፈ። ለምን? ፍርድ ቤቱ፣ የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረበውን የመከራከሪያ ነጥብ አሳማኝ ሆኖ ስላገኘው ነው፤ ጠበቃው “በመንግሥት ላይ ዓመፅ ማነሳሳት” የሚለው አገላለጽ ብጥብጥ መፍጠርን ወይም መንግሥት እንዲለወጥ ለማድረግ ረብሻ ማስነሳትን እንደሚጨምር መግለጹን የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ወንድም ግሌን ሃው ተናግሯል። ትራክቱ ግን “እንዲህ ዓይነት ዓመፅ የሚቀሰቅስ ሐሳብ አልያዘም፤ በመሆኑም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕግን የተከተለ ነው።” ወንድም ሃው አክሎም “ይሖዋ ድል ሲሰጠን መመልከት ችያለሁ” ብሏል። *

16 በእርግጥም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለአምላክ መንግሥት ታላቅ ድል ነበር። ይህ ውሳኔ፣ ‘በኩዊቤክ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት ላይ ዓመፅ የሚያነሳሳና ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ አሰራጭተዋል’ በሚል የቀረቡባቸውን ውሳኔ ያልተሰጠባቸው 122 ክሶች ውድቅ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ፣ የካናዳ ሕዝብና የብሪታንያ የጋራ ብልጽግና አባል አገራት ዜጎች መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ሐሳባቸውን የመግለጽ ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ከዚህም ሌላ ይህ ድል፣ የኩዊቤክ ቤተ ክርስቲያንና  መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ነፃነት ለመንፈግ ያደረጉትን ጥረት የሚያከሽፍ ነው። *

ሸቀጥ አዟሪዎች ወይስ የአምላክ መንግሥት ቀናተኛ አዋጅ ነጋሪዎች?

17. አንዳንድ መንግሥታት የስብከቱን ሥራችንን ለመቆጣጠር የሞከሩት እንዴት ነው?

17 እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችም “የአምላክን ቃል [አይሸቃቅጡም]።” (2 ቆሮንቶስ 2:17ን አንብብ።) ያም ሆኖ አንዳንድ መንግሥታት የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠሩ ሕጎችን በመጠቀም አገልግሎታችንን ለመቆጣጠር ይፈልጋሉ። ‘የይሖዋ ምሥክሮች ሸቀጥ አዟሪዎች ናቸው ወይስ የምሥራቹ ሰባኪዎች?’ ከሚለው ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተሰጡ ሁለት የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን እስቲ እንመልከት።

18, 19. በዴንማርክ የሚገኙት ባለሥልጣናት የስብከቱን ሥራ ለማስቆም የሞከሩት እንዴት ነው?

18 ዴንማርክ። እየዞሩ ለመሸጥ የሚያስችል የንግድ ፈቃድ ሳያወጡ የታተሙ ጽሑፎችን መሸጥ ሕገ ወጥ እንደሆነ የሚገልጽ ሕግ ከጥቅምት 1, 1932 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀመረ። ወንድሞቻችን ግን የንግድ ፈቃድ ለማውጣት አላመለከቱም። በሚቀጥለው ቀን፣ አምስት አስፋፊዎች ከዋና ከተማዋ ከኮፐንሃገን 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሮስኪለ የተባለች ከተማ ሲሰብኩ ዋሉ። በቀኑ መገባደጃ ላይ ግን ኦገስት ሌማን የተባለውን አስፋፊ አጡት። ይህ ወንድም ‘ያለ ፈቃድ ዕቃዎችን ሸጧል’ በሚል ታስሮ ነበር።

19 ኦገስት ሌማን ታኅሣሥ 19, 1932 ፍርድ ቤት ቀረበ። ወንድም ሌማን ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ቢሰጥም ምንም ነገር እንዳልሸጠ ተናገረ። ጉዳዩን የተመለከተው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ወንድም ሌማን የተናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ተስማምቷል። ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ “ተከሳሹ . . . ራሱን የሚያስተዳድርበት ገቢ አለው፤ [ጽሑፎችን በመስጠቱ] ምንም ዓይነት ቁሳዊ ጥቅም አላገኘም፤ እንዲህ ዓይነት ጥቅም የማግኘት ሐሳብም አልነበረውም። እንዲያውም በዚህ እንቅስቃሴ መካፈሉ ወጪ እንዲያወጣ አድርጎታል።” ፍርድ ቤቱ፣ ሌማን ያደረገው ነገር “ንግድ ተብሎ ሊፈረጅ” እንደማይችል በመግለጽ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፍ ብይን አስተላልፏል። ይሁንና የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች፣ የስብከቱ ሥራ በመላ አገሪቱ እንዲታገድ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተው ነበር። (መዝ. 94:20) አቃቤ ሕጉ፣ እስከ አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ ይግባኝ አለ። ታዲያ ወንድሞች ምን አደረጉ?

20 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከማየቱ በፊት ባለው ሳምንት፣ በመላው ዴንማርክ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክረው ቀጠሉ። ማክሰኞ ጥቅምት 3, 1933 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አስታወቀ። ወንድም ኦገስት ሌማን ሕግ አለመጣሱን በመግለጽ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ብይን አጸደቀው። ይህ ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበካቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ነበር። ወንድሞችና እህቶች፣ ይሖዋ በፍርድ ቤት ይህን ድል እንዲያገኙ ስላስቻላቸው አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ የስብከት ሥራቸውን ይበልጥ አፋፋሙት። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በዴንማርክ የሚገኙ ወንድሞቻችን መንግሥት ሳያስቸግራቸው አገልግሎታቸውን እያከናወኑ ነው።

በ1930ዎቹ በዴንማርክ የነበሩ ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች

21, 22. የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከወንድም መርዶክ ጋር በተያያዘ ምን ውሳኔ አስተላለፈ?

21 ዩናይትድ ስቴትስ። እሁድ፣ የካቲት 25, 1940 ሮበርት መርዶክ ጁኒየር የተባለ አቅኚና ሌሎች ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች በፔንስልቬንያ ግዛት ፒትስበርግ  አቅራቢያ በምትገኘው ጀኔት ከተማ ሲሰብኩ ተያዙ። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ፈቃድ ሳያወጡ መጽሔቶችን ለሰዎች በመስጠታቸው ተከስሰው ተፈረደባቸው። ጉዳዩ ለዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የተባለ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ጉዳያቸውን ለማየት ተስማማ።

22 ግንቦት 3, 1943 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን መብት የሚያስከብር ውሳኔ አሳለፈ። ይህ ፍርድ ቤት፣ ፈቃድ ማውጣት እንደሚያስፈልግ የሚናገረው መመሪያ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጿል፤ ምክንያቱም ይህ መመሪያ አንድ ሰው “የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የሰጠውን መብት ለመጠቀም ገንዘብ” እንዲከፍል እንደማስገደድ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል። ፍርድ ቤቱ፣ የከተማው አስተዳደር ያወጣው ደንብ ‘የፕሬስ ነፃነትን የሚገድብ እንዲሁም ሃይማኖትን በነፃነት የማራመድ መብትን የሚጋፋ ነው’ በሚል ይህን ደንብ ውድቅ አድርጎታል። ዊልያም ዳግላስ የተባሉት ዳኛ የአብዛኞቹን ዳኞች አመለካከት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “[የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ] በመስበክ ወይም ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን በማሠራጨት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሁለቱንም ነገሮች ያካተተ ነው።” ዳኛው አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ . . . በአብያተ ክርስቲያናት ከሚከናወነው አምልኮና ከመስበኪያ ሰገነት ከሚቀርብ ስብከት ተለይቶ አይታይም።”

23. በ1943 በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች በዛሬው ጊዜ የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

23 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ያለ ውሳኔ ማሳለፉ ለአምላክ ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው። ይህ ውሳኔ እውነተኛ ማንነታችን ይኸውም ክርስቲያን አገልጋዮች እንጂ  ነጋዴዎች አለመሆናችን በግልጽ እንዲታወቅ አድርጓል። የይሖዋ ምሥክሮች በጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲታዩላቸው ካቀረቧቸው 13 ጉዳዮች መካከል በ1943 በዚያ ታሪካዊ ቀን በ12ቱ አሸንፈዋል፤ ከእነዚህ መካከል ከመርዶክ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ይገኝበታል። በቅርብ ጊዜያት ተቃዋሚዎች እኛን ፍርድ ቤት በማቅረብ የመንግሥቱን መልእክት በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት የመስበክ መብታችንን እንደገና ለመጋፋት በሞከሩበት ወቅት፣ ከዓመታት በፊት የተሰጡት እነዚህ የፍርድ ውሳኔዎች መብታችንን ለማስከበር ከፍተኛ እገዛ አድርገውልናል።

“ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል”

24. የአንድ አገር መንግሥት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ ሲጥል ምን እናደርጋለን?

24 የይሖዋ አገልጋዮች፣ መንግሥታት የአምላክን መንግሥት መልእክት በነፃነት የመስበክ መብት ሲሰጧቸው በጣም ደስ ይላቸዋል። ሆኖም የአንድ አገር መንግሥት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ ሲጥል፣ የምንሰብክበትን መንገድ በመቀየር ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመን መስበካችንን እንቀጥላለን። እንደ ሐዋርያት ሁሉ እኛም “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።” (ሥራ 5:29፤ ማቴ. 28:19, 20) የስብከቱ ሥራችንን ሳናቋርጥ፣ በሥራችን ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ይግባኝ ለመጠየቅ ፍርድ ቤት እንሄዳለን። እስቲ እንዲህ ካደረግንባቸው ሁኔታዎች መካከል ሁለቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

25 ኒካራጓ። ሚስዮናዊና የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የሆነው ዶነቫን መንስተርማን ኅዳር 19, 1952 በዋና ከተማው በማናግዋ ወደሚገኘው የኢሚግሬሽን ቢሮ ሄደ። ወንድም ዶነቫን፣ የቢሮው ኃላፊ በሆነው በካፒቴን አርኖልዶ ጋርሲያ ፊት እንዲቀርብ ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር። ካፒቴኑም በኒካራጓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ “ትምህርታቸውን እንዳይሰብኩ እንዲሁም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዳያስፋፉ [መታገዳቸውን]” ለወንድም ዶነቫን ነገረው። እንዲህ ዓይነት እገዳ የተጣለው ለምን እንደሆነ ካፒቴን ጋርሲያ ሲጠየቅ፣ የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን ለማከናወን የሚያስችል ፈቃድ ከመንግሥት እንዳላገኙ እንዲሁም  ኮሚኒስት እንደሆኑ የሚገልጽ ክስ እንደቀረበባቸው ተናገረ። ከሳሾቻችን እነማን ናቸው? የሮም ካቶሊክ ቀሳውስት ናቸው።

በኒካራጓ ያሉ ወንድሞች በእገዳው ወቅት

25, 26. በኒካራጓ ያሉ ወንድሞች ጉዳያቸውን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡ ያደረጋቸው ምን ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? ውጤቱስ ምን ሆነ?

26 ወንድም ዶነቫን፣ ለአስተዳደርና ሃይማኖቶች ሚኒስቴር እንዲሁም ለፕሬዚዳንት አናስታሲዮ ሶሞሳ ጋርሲያ ወዲያውኑ ይግባኝ አለ፤ ይሁንና ይህ ምንም ውጤት አላስገኘም። በመሆኑም ወንድሞች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ ለውጥ አደረጉ። የመንግሥት አዳራሾችን በመዝጋት በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍለው መሰብሰብ የጀመሩ ሲሆን መንገድ ላይ መስበካቸውንም አቆሙ፤ ሆኖም የመንግሥቱን መልእክት ይሰብኩ ነበር። ይህንንም እያደረጉ፣ የተጣለባቸውን እገዳ የሚሽር ፍርድ እንዲሰጣቸው ለኒካራጓ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ። ጋዜጦች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለተጣለው እገዳና ስላቀረቡት አቤቱታ ይዘት በስፋት ያተቱ ሲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለመስማት ፈቃደኛ ሆነ። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ሰኔ 19, 1953 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአንድ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደላቸው። ፍርድ ቤቱ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የሕሊና እንዲሁም እምነትንና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚጋፋ እንደሆነ ገልጿል። በተጨማሪም በኒካራጓ መንግሥትና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ግንኙነት እንደ ቀድሞው መሆን እንዳለበት ትእዛዝ አስተላልፏል።

27. የኒካራጓ ዜጎች በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተደነቁት ለምንድን ነው? ወንድሞችስ ይህን ድል እንዴት ተመለከቱት?

27 የኒካራጓ ዜጎች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፍ ውሳኔ በማሳለፉ ተደነቁ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ቀሳውስቱ ከፍተኛ ተሰሚነት ስለነበራቸው ፍርድ ቤቱ ከእነሱ ጋር ላለመጋጨት ይጠነቀቅ ነበር። በተጨማሪም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ ኃይል ስለነበራቸው አብዛኛውን ጊዜ ፍርድ ቤቱ የባለሥልጣናቱን ውሳኔ የሚቃወም ብይን ማስተላለፍ ይከብደው ነበር። ወንድሞቻችን ይህን ድል ያገኙት ንጉሣቸው ጥበቃ ስላደረገላቸው እንደሆነ እርግጠኞች በመሆን መስበካቸውን ቀጠሉ።—ሥራ 1:8

28, 29. በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በዛየር ምን ያልተጠበቀ ለውጥ ተከሰተ?

28 ዛየር። በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ፣ አሁን የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ በምትባለው በዛየር 35,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በአገሪቱ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚከናወኑት እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ቅርንጫፍ ቢሮው አዳዲስ ሕንፃዎች መገንባት ጀመረ። ታኅሣሥ 1985 በዋና ከተማዋ በኪንሻሳ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ 32,000 ልዑካን የከተማዋን ስታዲየም ሞሉት። ብዙም ሳይቆይ ግን ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ። በዚያ የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ምን አጋጠማቸው?

29 ከኩዊቤክ ካናዳ የመጣውና በዱፕሌሲ የግዛት ዘመን የነበረውን ስደት የቀመሰው ወንድም ማርሴል ፊልቶ በወቅቱ ዛየር ውስጥ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለግል ነበር። ወንድም ፊልቶ ምን እንደተከናወነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በዛየር ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ሕጋዊ እንዳልሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ መጋቢት 12, 1986 ደረሳቸው።” በእገዳው ደብዳቤ ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ፈርመውበታል።

30 በሚቀጥለው ቀን በአገሪቱ የሬዲዮ ጣቢያ “ከአሁን በኋላ [በዛየር] ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ አንሰማም” የሚል ማስታወቂያ ተነገረ። ወዲያውኑ ስደት ተነሳ። የመንግሥት አዳራሾቻችንን አፈራረሷቸው፤ እንዲሁም ወንድሞቻችን ይዘረፉ፣ ይያዙና ወደ ወህኒ ይወርዱ ብሎም ይደበደቡ ጀመር። የይሖዋ ምሥክሮች  ልጆች እንኳ ታሰሩ። ጥቅምት 12, 1988 መንግሥት የድርጅታችንን ንብረት ወረሰው፤ እንዲሁም ሲቪል ዘብ ተብሎ የሚጠራ የሠራዊቱ ክፍል የቅርንጫፍ ቢሮውን ንብረት ተቆጣጠረው። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ጉዳዩን ለፕሬዚዳንት ሞቡቱ ይግባኝ ቢሉም ምንም ምላሽ አላገኙም። በዚህ ጊዜ የቅርንጫፍ ኮሚቴው አባላት “ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ እንበል ወይስ የሚሆነውን በትዕግሥት እንጠብቅ?” የሚለው ከባድ ውሳኔ ተደቀነባቸው። ሚስዮናዊና በወቅቱ የአገሪቱ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ የነበረው ወንድም ቲመቲ ሆልምስ “ጥበብና መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር አልን” በማለት ተናግሯል። የኮሚቴው አባላት ጉዳዩን በጸሎት ካሰቡበት በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ይህ ትክክለኛው ጊዜ እንዳልሆነ ወሰኑ። በመሆኑም ትኩረታቸውን ወንድሞችን በመንከባከብና የስብከቱ ሥራ የሚቀጥልበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ አደረጉ።

“ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንደሚቀይር ማየት ችለናል”

31 በዚህ ሁኔታ ዓመታት አለፉ። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና ረገብ እያለ መጣ፤ በአገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ይበልጥ መከበር ጀመረ። የቅርንጫፍ ኮሚቴው አባላት፣ የተጣለባቸውን እገዳ በተመለከተ ወደ ዛየር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት ጊዜው እንደደረሰ ተሰማቸው። የሚገርመው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ለመስማት ፈቃደኛ ሆነ። ከዚያም ጥር 8, 1993 ይኸውም ፕሬዚዳንቱ በሥራችን ላይ እገዳ እንዲጣል ካዘዙ ከሰባት ዓመት ገደማ በኋላ ፍርድ ቤቱ፣ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወሰደው እርምጃ ከሕጉ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ወሰነ፤ በመሆኑም እገዳው ተነሳ። ይህ ውሳኔ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! ዳኞቹ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ውሳኔ ውድቅ ያደረጉት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነው! ወንድም ሆልምስ እንዲህ ብሏል፦ “ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንደሚቀይር ማየት ችለናል።” (ዳን. 2:21) ይህ ድል የወንድሞቻችንን እምነት አጠናክሯል። ወንድሞች፣ ንጉሡ ኢየሱስ ተከታዮቹ መቼና እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው እንዲያውቁ በመርዳት እንደመራቸው ተሰምቷቸዋል።

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ያሉ ወንድሞች ይሖዋን የማምለክ ነፃነት በማግኘታቸው ተደስተዋል

31, 32. የዛየር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምን አስደናቂ ውሳኔ አስተላለፈ? ይህስ ለወንድሞቻችን ምን ጥቅም አስገኝቷል?

 32 እገዳው ሲነሳ ቅርንጫፍ ቢሮው ሚስዮናውያንን እንዲያስመጣ፣ አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ እንዲገነባ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲያስገባ ተፈቀደለት። * በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሳዊ ደኅንነት እንዴት ጥበቃ እንደሚያደርግ መመልከታቸው በጣም አስደስቷቸዋል!—ኢሳ. 52:10

“ይሖዋ ረዳቴ ነው”

33. በፍርድ ቤት ካደረግናቸው ሙግቶች መካከል አንዳንዶቹን በአጭሩ መመልከታችን ምን ትምህርት አስገኝቶልናል?

33 በፍርድ ቤት ካደረግናቸው ሙግቶች መካከል አንዳንዶቹን መመልከታችን ኢየሱስ “ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ” በማለት የገባውን ቃል እየፈጸመ እንደሆነ ያረጋግጥልናል። (ሉቃስ 21:12-15ን አንብብ።) ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲል በዘመናችንም እንደ ገማልያል ያሉ ሰዎችን ያስነሳባቸው ወይም ደፋር የሆኑ ዳኞችና ጠበቆች ከፍትሕ ጎን እንዲቆሙ ያነሳሳባቸው ጊዜያት አሉ። ይሖዋ የተቃዋሚዎቻችንን መሣሪያ አዶልዱሟል። (ኢሳይያስ 54:17ን አንብብ።) ተቃውሞ የአምላክን ሥራ ሊያስቆም አይችልም።

34. በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች ይህን ያህል አስደናቂ የሆኑት ለምንድን ነው? እነዚህ ድሎችስ ምን ያረጋግጣሉ? (“ የስብከቱ ሥራ እንዲቀጥል ያደረጉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ያገኘናቸው ታላላቅ ድሎች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

34 በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች ይህን ያህል አስደናቂ የሆኑት ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማሰብ ሞክር፦ የይሖዋ ምሥክሮች በኅብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ወይም ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አይደሉም። በምርጫ አንካፈልም፤ ፖለቲካዊ ዘመቻዎችን አንደግፍም ወይም በፖለቲካ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር አንሞክርም። ከዚህም ሌላ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የቀረቡት የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኛውን ጊዜ “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ናቸው። (ሥራ 4:13) በመሆኑም ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ፣ ፍርድ ቤቶቹ ኃያል በሆኑት ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተቃዋሚዎቻችን ላይ በመፍረድ ከእኛ ጎን እንዲቆሙ የሚያነሳሳቸው ምንም ምክንያት የለም። ያም ቢሆን ፍርድ ቤቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ለእኛ ፈርደውልናል! በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች “በአምላክ ፊት ሆነን እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር በመተባበር” እንደምንመላለስ ያረጋግጣሉ። (2 ቆሮ. 2:17) እንግዲያው እኛም ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” እንላለን።—ዕብ. 13:6

^ አን.9 በከሳሽ ካንትዌል እና በተከሳሽ ከነቲከት ግዛት መካከል የተካሄደው ክርክር፣ ወንድም ሄይደን ከቪንግተን ወንድሞችን ወክሎ በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ከቀረበባቸው 43 ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ነው። ወንድም ሄይደን በ1978 አንቀላፍቷል። የወንድም ሄይደን ባለቤት፣ እህት ዶሮቲ በ2015 በ92 ዓመታቸው እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት አገልግለዋል።

^ አን.12 ይህ ክስ በ1606 በወጣ ሕግ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ሕግ መሠረት፣ አንድ ሰው የተናገረው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ ፍርድ ቤቱ ጥላቻን የሚያስፋፋ እንደሆነ ከተሰማው ግለሰቡ ጥፋተኛ ነው ብሎ ሊፈርድ ይችላል።

^ አን.14 በ1950 በኩዊቤክ 164 የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበሩ፤ ከእነዚህም መካከል 63ቱ የጊልያድ ምሩቃን ሲሆኑ እነዚህ ክርስቲያኖች በኩዊቤክ ከባድ ተቃውሞ እንደሚጠብቃቸው ቢያውቁም የተሰጣቸውን ምድብ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል።

^ አን.15 ወንድም ግሌን ሃው፣ ከ1943 እስከ 2003 ድረስ በካናዳም ሆነ በሌሎች አገሮች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ፍርድ ቤት በመቅረብ የተሟገተ ጥበበኛና ደፋር ጠበቃ ነበር።

^ አን.16 ይህን ጉዳይ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 22, 2000 ንቁ! ከገጽ 18-24 (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ውጊያው የአምላክ እንጂ የእናንተ አይደለም” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.32 ሲቪል ዘቡ ከጊዜ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮውን ለቅቆ የወጣ ቢሆንም በሌላ ቦታ ላይ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቷል።