ውድ የመንግሥቱ አስፋፊ

ብሩክሊን የሚገኘው ቤቴል ቤተሰብ አባል እንደሆንክ አድርገህ አስብ፤ ወቅቱ ጥቅምት 2, 1914 ዓርብ ጠዋት ሲሆን ቁርስ ላይ በተለመደው ቦታህ ተቀምጠህ የወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስልን መምጣት እየተጠባበቅህ ነው። በድንገት የመመገቢያ አዳራሹ በር ተከፈተና ወንድም ራስል ገባ። ሁልጊዜ እንደሚያደርገው፣ ሳይናገር ትንሽ ቆም ካለ በኋላ በፈገግታ ተሞልቶ “እንደምን አደራችሁ” በማለት ለሁሉም የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሰላምታ ሰጠ። ከዚያም ጠረጴዛው ጫፍ ላይ ወዳለው ቦታው ሄዶ ከመቀመጥ ይልቅ አጨበጨበና “የአሕዛብ ዘመን ተፈጸመ፤ ነገሥታታቸውም ጊዜያቸው አበቃ!” የሚል አስደሳች ማስታወቂያ ተናገረ። በሰማኸው ነገር በጣም እንደተደሰትህ ከፊትህ ማየት ይቻላል፤ ይህን ቀን ለረጅም ጊዜ በጉጉት ስትጠብቀው ቆይተሃል! በመሆኑም ከመላው የቤቴል ቤተሰብ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በማጨብጨብ በዚህ ዜና መደሰትህን ገለጽህ።

 ወንድም ራስል ይህንን አስደሳች ማስታወቂያ ከተናገረ በርካታ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምን ሲያከናውን ቆይቷል? በጣም ብዙ ነገሮችን አከናውኗል! ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ሕዝቡን ቀስ በቀስ ሲያጠራ እና ሲያሠለጥን ቆይቷል፤ በ1914 በጥቂት ሺዎች ይቆጠሩ የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ዛሬ ወደ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሆነዋል። አንተስ እንዲህ ካሉ ሥልጠናዎች ጥቅም ያገኘኸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

ወንድሞቻችን “በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት እየገሰገሰ ነው” ሲሉ እንሰማለን፤ ደግሞም ይህ ትክክል ነው። ይሁንና ይህን መጽሐፍ በትኩረት ስታነብ እንደምትገነዘበው የይሖዋን ድርጅት የማይታይ ክፍል የሚያመለክተው ይህ ሰማያዊ ሠረገላ ከ1914 አንስቶ በከፍተኛ ፍጥነት ሲገሰግስ ቆይቷል። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማሰራጨት ሲሉ የተለያዩ አዳዲስ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል፤ ለምሳሌ በጋዜጦች፣ መልእክቶችን ይዞ ሰልፍ በመውጣት፣ በተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ በምሥክርነት መስጫ ካርዶች፣ በሸክላ ማጫወቻዎች፣ በሬዲዮ አልፎ ተርፎም በኢንተርኔት አማካኝነት ምሥራቹን አሰራጭተዋል።

ይሖዋ የስብከቱን ሥራ ስለባረከው፣ ማራኪ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በአሁኑ ጊዜ ከ670 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና ለሁሉም ሰው ያለ ክፍያ ማሰራጨት ችለናል። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ፈቃደኛ ሠራተኞች በበለጸጉ አገሮችም ሆነ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን፣ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባቱ ሥራ ይካፈላሉ። በተጨማሪም አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ፣ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች በአደጋው በተጠቁ አካባቢዎች ያሉትን ክርስቲያኖች ወዲያውኑ በመርዳት በእርግጥም ‘ለመከራ ቀን እንደተወለደ ወንድም’ መሆናቸውን ያስመሠክራሉ።—ምሳሌ 17:17

ቀሳውስትና ሌሎች ሰዎች “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር” የሚያሴሩባቸው ጊዜያት አሉ፤ ይሁንና ያደረጉት የተሳሳተ ጥረት “ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳደረገ” በተደጋጋሚ መመልከታችን እምነታችንን የሚያጠናክር ነው።—መዝ. 94:20፤ ፊልጵ. 1:12

ውድ ‘የቤተሰባችን’ አባላት፣ ከእናንተ ጋር አብረን መሥራታችንን እንደ ታላቅ መብት እንቆጥረዋለን። ሁላችሁንም በጣም እንደምንወዳችሁ ልንገልጽላችሁ እንፈልጋለን። ይህ መጽሐፍ መንፈሳዊ ውርሻችሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአድናቆት እንድትመለከቱ እንዲረዳችሁ ጸሎታችን ነው።—ማቴ. 24:45

መልካሙን ሁሉ እንመኝላችኋለን

ወንድሞቻችሁ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል