የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አንድ ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ ትርጉሙን ሲረዳ ፊቱ በደስታ ሲፈካ ታያለህ። ከዚያም “መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ገነት ሆና በዚያ ለዘላለም መኖር እንደምንችል ይናገራል ማለት ነው?” ብሎ ይጠይቃል። የአገልግሎት ጓደኛህ ፈገግ ብሎ “ያነበብከው ጥቅስ ይህን አያሳይም?” ይለዋል። ተማሪው በአድናቆት ስሜት ተውጦ ራሱን እየነቀነቀ “ከዚህ በፊት ይህን አለማወቄ ይገርማል!” ይላል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት እንደነበር ታስታውሳለህ።

እንዲህ ያለ ተሞክሮ አጋጥሞህ ያውቃል? ብዙዎቹ የአምላክ አገልጋዮች ይህን የመሰለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች፣ የእውነት እውቀት ምን ያህል ውድ ስጦታ እንደሆነ እንድናስታውስ ያደርጉናል! እስቲ ቆም ብለህ አስብ፦ አንተ ይህን ስጦታ ልታገኝ የቻልከው እንዴት ነው? በዚህ ክፍል ውስጥ ይህን ጉዳይ እንመረምራለን። የአምላክ ሕዝቦች እየደመቀ የሚሄድ መንፈሳዊ ብርሃን ያገኙበት መንገድ የአምላክ መንግሥት እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት የአምላክ ሕዝቦች እውነትን እንዲማሩ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።