በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!

 ምዕራፍ 16

ለአምልኮ መሰብሰብ

ለአምልኮ መሰብሰብ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ስብሰባዎቻችንን እንዴት እንደጀመርን እና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ መመርመር

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ ለመበረታታት አንድ ላይ ተሰብስበው ነበር። ሆኖም ጠላቶቻቸውን ስለፈሩ በሮቹን ቆልፈዋቸዋል። በዚህ መሃል ኢየሱስ በመካከላቸው በመገለጥ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ሲላቸው ፍርሃታቸው ቀለል ብሎላቸው መሆን አለበት። (ዮሐንስ 20:19-22ን አንብብ።) ቆየት ብሎም ደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተሰብስበው ሳለ ይሖዋ በእነሱ ላይ መንፈስ ቅዱስን አወረደ። ይህም ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን የስብከት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል እንደሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም!—ሥራ 2:1-7

2. (ሀ) ይሖዋ ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ብርታት የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው? (ለ) የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንና “ የቤተሰብ አምልኮ” የሚለውን በገጽ 175 ላይ የሚገኝ ሣጥን ተመልከት።)

2 እኛም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን ያጋጠሟቸው ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። (1 ጴጥ. 5:9) አንዳንዶቻችን የሰው ፍርሃት ያስጨንቀን ይሆናል። እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ለመጽናት ይሖዋ የሚሰጠው ብርታት ያስፈልገናል። (ኤፌ. 6:10) ይሖዋ እንዲህ ያለውን ብርታት ለመስጠት በአብዛኛው የሚጠቀመው በስብሰባዎቻችን አማካኝነት ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ ትምህርት የምናገኝባቸው ሁለት ሳምንታዊ ስብሰባዎች አሉን፤ እነዚህም የሕዝብ ስብሰባና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን የተባለው በሳምንቱ መሃል የምናደርገው ስብሰባ ናቸው። * ከዚህም በተጨማሪ አራት ዓመታዊ ስብሰባዎች አሉን፤ እነሱም የክልል ስብሰባ፣ ሁለት የወረዳ ስብሰባዎች እንዲሁም የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ናቸው። ይሁንና በሁሉም ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዘመናችን የሚካሄዱት ስብሰባዎች የተጀመሩት እንዴት ነው? ለስብሰባዎች ያለን አመለካከት ስለ እኛ ምን ያሳያል?

መሰብሰብ ያለብን ለምንድን ነው?

3, 4. ይሖዋ ከሕዝቡ ምን ይጠብቃል? ምሳሌ ስጥ።

3 ከጥንት ጀምሮ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ እሱን ለማምለክ እንዲሰበሰቡ መመሪያ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1513 ዓ.ዓ. ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር ሕጉን የሰጠ ሲሆን ይህ ሕግ ሳምንታዊውን ሰንበት ያካትት ነበር፤ ሰንበት የተሰጠው በዚያ ዕለት እያንዳንዱ ቤተሰብ ይሖዋን እንዲያመልክና ስለ ሕጉ እንዲማር ነው። (ዘዳ. 5:12፤ 6:4-9) እስራኤላውያን ይህን ትእዛዝ በሚጠብቁበት ወቅት ቤተሰቦች እርስ በርስ የጠበቀ ግንኙነት ይኖራቸው ነበር፤ ከዚህም ሌላ ብሔሩ በአጠቃላይ በመንፈሳዊ ንጹሕና ጠንካራ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ  ሕዝቡ ይሖዋን ለማምለክ አዘውትረው እንዲሰበሰቡ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጨምሮ የአምላክን ሕጎች ችላ ሲሉ የእሱን ሞገስ ያጡ ነበር።—ዘሌ. 10:11፤ 26:31-35፤ 2 ዜና 36:20, 21

4 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌም እንመልከት። በየሳምንቱ በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። (ሉቃስ 4:16) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ የሰንበትን ሕግ እንዲያከብሩ ባይጠበቅባቸውም አዘውትረው የመሰብሰብ ልማዳቸውን አልተዉም። (ሥራ 1:6, 12-14፤ 2:1-4፤ ሮም 14:5፤ ቆላ. 2:13, 14) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በእነዚያ ስብሰባዎች ላይ ትምህርትና ማበረታቻ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ በጸሎት፣ በሚሰጡት ሐሳብና በመዝሙራት አማካኝነት ለአምላክ የምስጋና መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።—ቆላ. 3:16፤ ዕብ. 13:15

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እርስ በርስ ለመበረታታትና ለመተናነጽ ይሰበሰቡ ነበር

5. በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንና በየዓመቱ በምናደርጋቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው? (“ ለአምላክ ሕዝቦች አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዓመታዊ ስብሰባዎች” የሚለውን በገጽ 176 ላይ የሚገኝ ሣጥንም ተመልከት።)

5 በተመሳሳይ እኛም በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንና በየዓመቱ በምናደርጋቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የአምላክን መንግሥት እንደምንደግፍ እናሳያለን፤ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን ብርታት እናገኛለን እንዲሁም እምነታችንን በመግለጽ ሌሎችን እናበረታታለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ በጸሎት፣ በምንሰጣቸው ሐሳቦችና በመዝሙራት አማካኝነት ይሖዋን እናመልካለን። ስብሰባዎቻችንን የምናካሂድበት መንገድ እስራኤላውያንም ሆኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ያደርጉት ከነበረው ይለይ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ስብሰባዎቻችን ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ ዛሬም በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይሁንና በዘመናችን የሚካሄዱት ስብሰባዎች የተጀመሩት እንዴት ነው?

“ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” የሚያነቃቁን ሳምንታዊ ስብሰባዎች

6, 7. (ሀ) የስብሰባዎቻችን ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) የተለያዩ ቡድኖች የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች የሚለያዩት እንዴት ነበር?

6 ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ከአምላክ ቃል ውስጥ እውነትን ለማግኘት ምርምር ማድረግ በጀመረበት ወቅት የእሱ ዓይነት ዓላማ ካላቸው ሰዎች ጋር  የመሰብሰብን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። በ1879 ወንድም ራስል “እኔና በፒትስበርግ ያሉ አንዳንድ ሰዎች አንድ ላይ ሆነን ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመመርመር ስንል መጽሐፍ ቅዱስን የምንማርበት ፕሮግራም አዘጋጅተን ሁልጊዜ እሁድ እሁድ በቋሚነት እንሰበሰባለን” ብሏል። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ይበረታቱ የነበረ ሲሆን በ1881 በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ በየሳምንቱ እሁድና ረቡዕ ስብሰባ ማድረግ ጀምረው ነበር። የኅዳር 1895 መጠበቂያ ግንብ እነዚህ ስብሰባዎች የሚደረጉበት ዓላማ ‘ክርስቲያናዊ ወዳጅነትንና ፍቅርን’ ለማዳበር እንዲሁም “የሐሳብ ልውውጥ” ለማድረግ ብሎም ተሰብሳቢዎቹ እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ለመፍጠር እንደሆነ ገልጿል።—ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።

7 ለበርካታ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድኖች፣ ስብሰባዎችን የሚያካሂዱበት መንገድና የስብሰባዎቹ ብዛት ከቡድን ወደ ቡድን ይለያይ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ1911 የታተመ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኝ አንድ ቡድን የተላከ ደብዳቤ “በየሳምንቱ ቢያንስ አምስት ስብሰባዎችን እናደርጋለን” ይላል። እነዚህን ስብሰባዎች የሚያደርጉት ሰኞ፣ ረቡዕ፣ ዓርብ እና ሁለቱን ደግሞ እሁድ ዕለት ነበር። በ1914 የታተመ ከአፍሪካ የተላከ ሌላ ደብዳቤ ደግሞ “ስብሰባ የምናደርገው በወር ሁለት ጊዜ ሲሆን የምንሰበሰበው ከዓርብ እስከ እሁድ ነው” ይላል። ቀስ በቀስ ግን ስብሰባዎቻችን አሁን ያላቸውን ዓይነት መልክ ያዙ። እስቲ የእያንዳንዱን ስብሰባ ታሪክ በአጭሩ እንመልከት።

8. ቀደም ባሉት ዓመታት የሕዝብ ንግግር ከሚሰጥባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

8 የሕዝብ ስብሰባ። ወንድም ራስል የጽዮን መጠበቂያ ግንብን ማዘጋጀት ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም በ1880 የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የስብከት ጉዞ ማድረግ ጀመረ። (ሉቃስ 4:43) ይህም በዛሬው ጊዜ ለምናደርገው ሕዝባዊ ስብሰባ መንገድ ጠርጓል። መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ያለውን ጉዞ ሲያስተዋውቅ ወንድም ራስል፣ “‘ከአምላክ መንግሥት ጋር ስለተያያዙ ነገሮች’ ንግግር የሚሰጥባቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለማካሄድ” እንደሚፈልግ ገልጿል። በብዙ አገሮች ጉባኤዎች ከተቋቋሙ በኋላ በ1911 እያንዳንዱ ጉባኤ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተናጋሪዎችን በአቅራቢያው ወዳሉ አካባቢዎች እንዲልክ ማበረታቻ ተሰጥቶ ነበር፤ እነዚህ ተናጋሪዎች እንደ ፍርድ እና ቤዛ ባሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስድስት ክፍል ያላቸው ተከታታይ ንግግሮች ያቀርቡ ነበር። አንድ ወንድም ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት ሦስት የተለያዩ ንግግሮችን ካቀረበ በኋላ የሚቀጥሉትን ሦስት ንግግሮች የሚያቀርበውን ሰው ስምና የንግግሮቹን ርዕስ ያስተዋውቃል።

9. ባለፉት ዓመታት በሕዝባዊ ስብሰባ ረገድ ምን ለውጦች ተደርገዋል? ይህን ስብሰባ መደገፍ የምትችለውስ እንዴት ነው?

9 በ1945 መጠበቂያ ግንብ፣ “በወቅቱ ካሉት አሳሳቢ ችግሮች” ጋር የተያያዙ ስምንት ተከታታይ ንግግሮች የሚሰጡበት የሕዝባዊ ስብሰባ ዘመቻ በዓለም ዙሪያ እንደሚካሄድ አስታወቀ። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት፣ ንግግር እንዲያቀርቡ የተመደቡ ወንድሞች ታማኝና ልባም ባሪያ የሰጣቸውን ርዕሰ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ያዘጋጇቸውን ንግግሮችም ያቀርቡ ነበር። በ1981 ግን ሁሉም ተናጋሪዎች የሚያቀርቡት ንግግር ለጉባኤዎች በሚላከው አስተዋጽኦ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ተነገራቸው። * እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ለሕዝብ ንግግር የተዘጋጁ አንዳንድ አስተዋጽኦዎች አድማጮችን የሚያሳትፉ ወይም  በሠርቶ ማሳያ የሚቀርብ ክፍል ያላቸው ነበሩ፤ ከዚያ ዓመት በኋላ ግን መመሪያዎቹ የተስተካከሉ ሲሆን የሕዝብ ንግግሮች በንግግር መልክ ብቻ መቅረብ ጀመሩ። በጥር 2008 ደግሞ የሕዝብ ንግግር የሚቀርብበትን ጊዜ ከ45 ደቂቃ ወደ 30 ደቂቃ በመቀነስ ተጨማሪ ማስተካከያ ተደረገ። የሕዝብ ንግግር የሚቀርብበት መንገድ ቢለዋወጥም አሁንም ቢሆን ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው ንግግሮች በአምላክ ቃል ላይ ያለን እምነት እያደገ እንዲሄድና ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ነገሮችን እንድንገነዘብ እየረዱን ነው። (1 ጢሞ. 4:13, 16) አንተስ ተመላልሶ መጠየቅ ለምታደርግላቸው ሰዎችም ሆነ የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሌሎች ሰዎች እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች እንዲያዳምጡ ሞቅ ያለ ግብዣ ታቀርብላቸዋለህ?

10 የመጠበቂያ ግንብ ጥናት። ዎች ታወር ሶሳይቲ ለጉባኤዎች ንግግር እንዲሰጡና የስብከቱን ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲመሩ የሚልካቸው ፒልግሪም ተብለው የሚጠሩ ወንድሞች መጠበቂያ ግንብ የሚጠናበት ቋሚ ስብሰባ እንዲኖር በ1922 ሐሳብ አቀረቡ። ይህ ሐሳብ በሥራ ላይ ዋለ፤ መጀመሪያ አካባቢ መጠበቂያ ግንብ የሚጠናው በሳምንቱ መካከል ባሉት ቀናት ወይም እሁድ ዕለት ነበር።

የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በጋና፣ 1931

10-12. (ሀ) በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ረገድ ምን ለውጦች ተካሂደዋል? (ለ) ራስህን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብሃል?

11 የሰኔ 15, 1932 መጠበቂያ ግንብ ይህ ስብሰባ እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚገልጽ ተጨማሪ ሐሳብ ይዞ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ በቤቴል የሚካሄደውን ጥናት እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ስብሰባውን አንድ ወንድም መምራት እንደሚኖርበት አስታወቀ። ሦስት ወንድሞች በስብሰባው ቦታ ከፊት ቁጭ ብለው አንቀጾቹን እየተፈራረቁ ያነብባሉ። በዚያን ጊዜ የሚጠኑት ርዕሶች ለውይይት የሚረዱ ጥያቄዎች አልነበሯቸውም፤ በመሆኑም ጥናቱን የሚመራው ወንድም አድማጮች በሚጠናው ርዕስ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ ሐሳብ እንዲያቀርብ ተነግሮት ነበር። ከዚያም ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ይጋብዛል። ተጨማሪ ማብራሪያ ካስፈለገ የሚመራው ወንድም “አጭርና ነጥቡ ላይ ያተኮረ” ማብራሪያ እንዲያቀርብ መመሪያ ተሰጥቶት ነበር።

 12 መጀመሪያ አካባቢ እያንዳንዱ ጉባኤ፣ አብዛኞቹ ወንድሞች ማጥናት የሚፈልጉትን የመጠበቂያ ግንብ እትም መርጦ ያጠና ነበር። ይሁንና የሚያዝያ 15, 1933 መጠበቂያ ግንብ ሁሉም ጉባኤዎች በቅርብ የወጣውን እትም እንዲያጠኑ ሐሳብ አቀረበ። በ1937 የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እሁድ እሁድ እንዲካሄድ መመሪያ ተሰጠ። ይህ ስብሰባ አሁን በሚካሄድበት መልክ እንዲከናወን የሚያስችል ተጨማሪ ማስተካከያ በጥቅምት 1, 1942 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጣ። ይህ መጽሔት፣ የጥናት ርዕሶች ባሉበት በእያንዳንዱ ገጽ ግርጌ ጥያቄዎች እንደሚወጡና በጥናቱ ወቅት በእነዚህ ጥያቄዎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስታወቀ። ከዚያም ጥናቱ ከአንድ ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት ገለጸ። በተጨማሪም ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሰጡት ወንድሞች ከአንቀጹ ላይ እያነበቡ ከመመለስ ይልቅ “በራሳቸው አባባል” መልስ እንዲሰጡ የሚያበረታታ ሐሳብ ይዞ ነበር። ዛሬም ቢሆን ታማኝና ልባም ባሪያ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት ዋነኛ ስብሰባ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ነው። (ማቴ. 24:45) ሁላችንም ‘በየሳምንቱ ለሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እዘጋጃለሁ? ከቻልኩ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አደርጋለሁ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።

13, 14. የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለው ታሪክ ምን ይመስላል? ከዚህ ስብሰባ የሚያስደስትህ ምንድን ነው?

13 የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት። ሚሌኒያል ዶውን የተባለው መጽሐፍ የተወሰኑ ጥራዞች ከወጡ በኋላ በ1890ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በሜሪላንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በቦልቲሞር ከተማ የሚኖረው ወንድም ራን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያስችሉ “የዶውን ክበቦች” እንዲቋቋሙ ሐሳብ አቀረበ። አብዛኛውን ጊዜ በግል መኖሪያ ቤቶች የሚካሄዱት እነዚህ ስብሰባዎች የተጀመሩት ለሙከራ ያህል ነበር። ሆኖም እስከ መስከረም 1895 ባለው ጊዜ እንደታየው የዶውን ክበቦች በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ስኬታማ ሆነው ነበር። በመሆኑም በዚያ ወር የወጣው መጠበቂያ ግንብ የእውነት ተማሪዎች በሙሉ ይህን ስብሰባ እንዲያካሂዱ ሐሳብ አቀረበ። መጠበቂያ ግንቡ፣ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ጥሩ አንባቢ መሆን እንዳለበት ገልጾ ነበር። የሚመራው ወንድም፣ አንድ ዓረፍተ ነገር ያነብብና ተሰብሳቢዎቹ ሐሳብ እስኪሰጡ ይጠብቃል። በአንድ አንቀጽ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር አንብቦ ከተወያዩበት በኋላ በአንቀጹ ላይ ያሉትን ጥቅሶች አውጥቶ ያነብባል። ምዕራፉ ሲያልቅ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ያጠኑትን ነገር በአጭሩ ይከልሳሉ።

14 የዚህ ስብሰባ መጠሪያ በተለያዩ ጊዜያት ተቀይሯል። “የቤርያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክበቦች” ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ነበር፤ ይህ ስያሜ የተሰጠው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ይመረምሩ የነበሩትን የቤርያ ሰዎች እንደ ምሳሌ በመውሰድ ነው። (ሥራ 17:11) ከጊዜ በኋላ ይህ ስም ተቀይሮ “የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት” ተባለ። አሁን ይህ ስብሰባ “የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የተለያዩ ቡድኖች በግለሰቦች ቤት መሰብሰባቸው ቀርቶ ሁሉም የጉባኤው አባላት በመንግሥት አዳራሽ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። ባለፉት አሥርተ ዓመታት በዚህ ስብሰባ ላይ የተለያዩ መጻሕፍት፣ ብሮሹሮች ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ተጠንተዋል። ገና ከጅምሩ አንስቶ በዚህ ስብሰባ ላይ የሚገኙ ሁሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይበረታቱ ነበር። ይህ ስብሰባ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ጥልቀት  እንዲኖረው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለዚህ ስብሰባ አዘውትረህ ትዘጋጃለህ? እንዲሁም ተሳትፎ ለማድረግ የምትችለውን ያህል ትጥራለህ?

15. ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተዘጋጀበት ዓላማ ምን ነበር?

15 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት። “የካቲት 16, 1942 ሰኞ ምሽት ላይ የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ ወንድሞች በሙሉ ከጊዜ በኋላ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በተባለው ትምህርት ቤት እንዲካፈሉ ተጋበዙ” በማለት ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እያገለገለ የነበረው ኬሪ ባርበር ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ባርበር ይህ ትምህርት ቤት “ይሖዋ በዘመናችን ካሉት የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ካደረጋቸው ታላላቅ ለውጦች መካከል አንዱ” እንደሆነ ገልጿል። ይህ ትምህርት ቤት ወንድሞች የማስተማርና የስብከት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በመርዳት ረገድ እጅግ ውጤታማ በመሆኑ ከ1943 አንስቶ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ኮርስ (እንግሊዝኛ) የተባለው ቡክሌት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጉባኤዎች ቀስ በቀስ መሰራጨት ጀመረ። የሰኔ 1, 1943 መጠበቂያ ግንብ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተዘጋጀው የይሖዋ ሕዝቦች “ስለ አምላክ  መንግሥት በማወጅ ረገድ የተሻሉ ምሥክሮች ለመሆን ራሳቸውን እንዲያሠለጥኑ” ለመርዳት እንደሆነ ገልጿል።—2 ጢሞ. 2:15

16, 17. ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የምናገኘው ሥልጠና የሚረዳን የንግግር ችሎታችንን ለማሻሻል ብቻ ነበር? አብራራ።

16 መጀመሪያ ላይ ብዙዎች፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ንግግር መስጠት በጣም ከብዷቸው ነበር። አባቱ ከወንድም ራዘርፎርድና ከሌሎች ወንድሞች ጋር በ1918 ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ታስሮ የነበረው ወንድም ክሌይተን ዉድዎርዝ ጁኒየር በ1943 በዚህ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካፈለበት ወቅት ምን እንደተሰማው አይረሳውም። ወንድም ዉድዎርዝ “ንግግር መስጠት በጣም ይከብደኝ ነበር” ብሏል፤ “ምላሴ ይተሳሰር፣ አፌ ይደርቅ እንዲሁም ድምፄ አንዴ እየጎረነነ በሌላ ጊዜ ደግሞ እየሰለለ ያስቸግረኝ ነበር።” ወንድም ዉድዎርዝ የንግግር ችሎታው እየተሻሻለ ሲመጣ ግን በርካታ የሕዝብ ንግግሮችን የማቅረብ መብት አገኘ። ከትምህርት ቤቱ ያገኘው ሥልጠና የንግግር ችሎታውን እንዲያሻሽል ብቻ ሳይሆን የትሕትናን አስፈላጊነትና በይሖዋ መታመን ያለውን ጥቅም እንዲገነዘብ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ዋናው ቁም ነገር ንግግሩን የሚያቀርበው ሰው ማንነት እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ተናጋሪው በደንብ  ከተዘጋጀና በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ከተማመነ ተሰብሳቢዎቹ ደስ ብሏቸው ሊያዳምጡትና ቁም ነገር ሊቀስሙ ይችላሉ።”

17 በ1959 እህቶችም በትምህርት ቤቱ እንዲካፈሉ ተጋበዙ። እህት ኤድና ባወር፣ ይህን ማስታወቂያ የሰማችው በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንደሆነ ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “እህቶች ምን ያህል ተደስተው እንደነበር አልረሳውም። አሁን ተጨማሪ አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል።” ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህት ቤት ለመካፈል የተከፈተውን አጋጣሚ በመጠቀም ከይሖዋ ተምረዋል። ዛሬም በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ አማካኝነት እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ማግኘታችንን ቀጥለናል።—ኢሳይያስ 54:13ን አንብብ።

18, 19. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎት ስንካፈል ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ተግባራዊ ነጥቦች ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በስብሰባዎቻችን ላይ የምንዘምረው ለምንድን ነው? (“ ስለ እውነት መዘመር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

18 የአገልግሎት ስብሰባ። ከ1919 ጀምሮ አገልግሎታችንን በተደራጀ መልኩ ለማከናወን የሚረዱ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር። በወቅቱ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ሁሉም የጉባኤው አባላት ሳይሆኑ ጽሑፎችን በማሠራጨቱ ሥራ በቀጥታ የሚካፈሉት ብቻ ነበሩ። ከ1923 አንስቶ የአገልግሎት ስብሰባ በወር አንድ ጊዜ መካሄድ ጀመረ፤ ሁሉም የጉባኤው አባላት በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት ነበረባቸው። በ1928 ጉባኤዎች በየሳምንቱ የአገልግሎት ስብሰባ እንዲያደርጉ መመሪያ ተሰጣቸው፤ በ1935 ደግሞ ሁሉም ጉባኤዎች የአገልግሎት ስብሰባ ሲያደርጉ ዳይሬክተር (ከጊዜ በኋላ ኢንፎርማንት አሁን ደግሞ የመንግሥት አገልግሎታችን ተብሏል) ላይ የሚወጡትን ነጥቦች እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጣ። ብዙም ሳይቆይ ይህ ስብሰባ፣ ሁሉም ጉባኤዎች በየሳምንቱ ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች አንዱ ሆነ።

19 በዛሬው ጊዜ በአገልግሎት ስንካፈል ልንጠቀምባቸው የምንችል ተግባራዊ ነጥቦች በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ ላይ ይቀርባሉ። (ማቴ. 10:5-13) የስብሰባውን አስተዋጽኦ ለማግኘት ብቁ ከሆንክ ጽሑፉ ሲሰጥህ በደንብ ታጠናዋለህ? የቀረቡትን ነጥቦች በአገልግሎት ላይ ትጠቀምባቸዋለህ?

በዓመት ውስጥ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ስብሰባ

ክርስቲያኖች ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በየዓመቱ ሲሰበሰቡ ቆይተዋል (አንቀጽ 20ን ተመልከት)

20 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን እሱ እስከሚመጣ ድረስ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ አዝዟቸዋል። እንደ ፋሲካ ሁሉ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያም በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። (1 ቆሮ. 11:23-26) በዚህ ስብሰባ ላይ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ። ይህ በዓል፣ ቅቡዓኑን ከክርስቶስ ጋር በአምላክ መንግሥት አብረው ወራሾች የመሆን መብት እንዳላቸው ያስታውሳቸዋል። (ሮም 8:17) ሌሎች በጎች ደግሞ ለአምላክ መንግሥት ንጉሥ ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል።—ዮሐ. 10:16

20-22. (ሀ) የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የምናከብረው ለምንድን ነው? (ለ) በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘትህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

21 ወንድም ራስልና አጋሮቹ የጌታ ራትን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን የተገነዘቡ ሲሆን ይህ በዓል መከበር ያለበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ አውቀው ነበር። የሚያዝያ 1880 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “በፒትስበርግ የምንገኝ ብዙዎቻችን ለበርካታ ዓመታት . . . ፋሲካን [የመታሰቢያውን በዓል] የማክበርና የጌታን ሥጋና ደም ከሚወክሉት ቂጣና ወይን የመካፈል ልማድ አለን።” ብዙም ሳይቆይ ከመታሰቢያው በዓል ጋር ተያይዞ ትላልቅ ስብሰባዎች  መደረግ ጀመሩ። እንዲህ ዓይነት ስብሰባ እንደተካሄደ የሚገልጸው የመጀመሪያው መረጃ በ1889 ስለተካሄደው ስብሰባ የሚያወሳው ሲሆን በዚህ ወቅት 225 ተሰብሳቢዎችና 22 ተጠማቂዎች ነበሩ።

22 በዛሬው ጊዜ የመታሰቢያውን በዓል በትልቅ ስብሰባ ወቅት የማናከብር ቢሆንም በመንግሥት አዳራሹ አሊያም በተከራየነው አዳራሽ ውስጥ የጌታ ራትን ስናከብር በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ሁሉ እንዲገኙ እንጋብዛቸዋለን። በ2013 በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ከ19 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተገኝተዋል። በመታሰቢያው በዓል ላይ የመገኘት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በዚህ ቅዱስ ምሽት በዓሉን አብረውን እንዲያከብሩ የመጋበዝ ታላቅ መብት አለን! አንተስ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ብዙ ሰዎችን ለመጋበዝ በየዓመቱ የቻልከውን ያህል ጥረት ታደርጋለህ?

አመለካከታችን ምን ይጠቁማል?

23 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ለአምልኮ እንዲሰበሰቡ የተሰጣቸውን መመሪያ እንደ ሸክም አይቆጥሩትም። (ዕብ. 10:24, 25፤ 1 ዮሐ. 5:3) ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ለአምልኮ ወደ ይሖዋ ቤት መሄድ ይወድድ ነበር። (መዝ. 27:4) በተለይ ደግሞ አምላክን ከሚወድዱ ሰዎች ጋር መሰብሰብ ያስደስተው ነበር። (መዝ. 35:18) የኢየሱስን ምሳሌም እንውሰድ። ልጅ እያለም እንኳ አባቱ ወደሚመለክበት ቦታ የመሄድ ልባዊ ፍላጎት ነበረው።—ሉቃስ 2:41-49

ለመሰብሰብ ያለን ጉጉት የአምላክ መንግሥት ምን ያህል እውን እንደሆነልን ያሳያል

24. በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታችን ምን አጋጣሚዎች ይከፍትልናል?

24 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ይሖዋን እንደምንወድድና የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማነጽ እንደምንፈልግ እናሳያለን። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት ዜጎች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ለመማር እንደምንጓጓ እናሳያለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ሥልጠና በዋነኝነት የምናገኘው ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎች ነው። ከዚህም ሌላ ስብሰባዎቻችን የአምላክ መንግሥት በዛሬው ጊዜ እያከናወናቸው ካሉት ሥራዎች ሁሉ በጣም አስፈላጊ በሆነው ሥራ ይኸውም ሰዎችን የንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉና በማሠልጠኑ ሥራ በጽናት ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ችሎታና ብርታት ይሰጡናል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) በእርግጥም አንድ ላይ ለመሰብሰብ ያለን ጉጉት የአምላክ መንግሥት በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እውን እንደሆነልን የሚያሳይ ነው። እንግዲያው ስብሰባዎቻችንን ምንጊዜም ከፍ አድርገን እንመልከታቸው!

^ አን.2 በየሳምንቱ ከምናደርጋቸው የጉባኤ ስብሰባዎች በተጨማሪ እያንዳንዱ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ፣ የቤተሰብ አምልኮ ወይም የግል ጥናት ለማድረግ ጊዜ እንዲመድብ ይበረታታል።

^ አን.9 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ180 በላይ የሕዝብ ንግግር አስተዋጽኦዎች ተዘጋጅተዋል።