በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!

 ምዕራፍ 22

መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል

መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

አምላክ ከሰው ልጆችና ከምድር ጋር በተያያዘ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ የአምላክ መንግሥት ይፈጽማል

አንድ ታማኝ ወንድም ውሎው አድካሚና በውጥረት የተሞላ ቢሆንም ወደ ጉባኤ ስብሰባ መጥቷል። በቀላሉ የማይረካው አለቃው ሲያጉላላው ውሏል፤ እንዲሁም ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት ተፈታታኝ ስለሆነበት ውጥረት ፈጥሮበታል፤ የባለቤቱ መታመምም አስጨንቆታል። የመክፈቻው መዝሙር ሲጀምር ግን ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ በመሆኑ እፎይታ ተሰማው። መዝሙሩ የሚያወሳው በገነት ውስጥ ስለምናገኘው ሕይወት ነው፤ ስንኞቹ ይህንን ተስፋ በዓይነ ሕሊናው እንዲስል እንዲሁም እዚያ እንዳለ አድርጎ እንዲያስብ የሚያበረታቱ ናቸው። ወንድም ይህን መዝሙር በጣም ይወደዋል፤ መዝሙሩን ከቤተሰቡ ጋር ሲዘምረውም በተጨነቀው ልቡ ውስጥ ተስፋ ያብባል።

1, 2. (ሀ) ምድር ገነት እንደምትሆን ያለን ተስፋ ብሩህ ሆኖ እንዳይታየን እንቅፋት የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ምን ሊረዳን ይችላል?

2 አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ብዙዎቻችን እንዲህ ይሰማናል። ይሁንና በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ የምንመራው ሕይወት ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን ያለን ተስፋ ብሩኅ ሆኖ እንዳይታየን እንደሚያደርግ እሙን ነው። የምንኖረው ከገነት ፍጹም ተቃራኒ በሆነና “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) ታዲያ ተስፋችን እውን ሆኖ እንዲታየን ምን ሊረዳን ይችላል? የአምላክ መንግሥት በቅርቡ መላውን የሰው ዘር እንደሚገዛ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ይሖዋ ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል በጥንት ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹ ሲፈጸሙ ያዩአቸውን አንዳንድ ትንቢቶች እስቲ እንመልከት። ቀጥሎም እነዚህም ሆኑ እንደ እነዚህ ያሉ ሌሎች ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በዚህ መንገድ እምነታችንን ካጠናከርን በኋላ እነዚህ ትንቢቶች ከወደፊቱ ተስፋችን ጋር በተያያዘ ምን ትርጉም እንዳላቸው መጨረሻ ላይ እናያለን።

ይሖዋ በጥንት ጊዜ ቃሉን የፈጸመው እንዴት ነው?

3. በባቢሎን በግዞት የነበሩትን አይሁዳውያን ያጽናናቸው የትኛው ተስፋ ነው?

3 በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በባቢሎን በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ለማሰብ ሞክር። አብዛኞቹ አይሁዳውያንም ሆኑ ወላጆቻቸው፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ የኖሩት በግዞት ሲሆን ሕይወታቸው በጣም አስቸጋሪ ነበር። ባቢሎናውያኑ፣ በይሖዋ ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት ያፌዙባቸው ነበር። (መዝ. 137:1-3) ታማኝ አይሁዳውያን በባቢሎን ባሳለፏቸው አሥርተ ዓመታት ሁሉ ከይሖዋ ጋር ተጣብቀው እንዲቀጥሉ የረዳቸው፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመልሳቸው የሰጠው  አስደሳች ተስፋ ነው። ይሖዋ በዚያ የሚኖረው ሁኔታ አስደናቂ እንደሚሆን ቃል ገብቷል። እንዲያውም ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ የተመለሰችውን የይሁዳን ምድር ከኤደን የአትክልት ስፍራ ማለትም ከገነት ጋር አነጻጽሯታል! (ኢሳይያስ 51:3ን አንብብ።) እነዚህ ተስፋዎች የተሰጡበት ዓላማ በአምላክ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ሊያድር የሚችለውን ጥርጣሬ በሙሉ ማስወገድና ሕዝቡ ተስፋው እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንዲሆኑ መርዳት እንደሆነ ጥያቄ የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ አንዳንድ ትንቢቶችን እንመልከት።

4. ይሖዋ፣ በትውልድ አገራቸው ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደማይኖር ለአይሁዳውያን ማረጋገጫ የሰጣቸው እንዴት ነው?

4 ያለ ስጋት መኖር። በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን የሚመለሱት ቃል በቃል ወደ ገነት ሳይሆን ለ70 ዓመታት ባድማ ሆኖ ወደ ቆየ ሩቅ አካባቢ ነበር፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ይህን አገር ፈጽሞ አይተውት አያውቁም። በጥንት ዘመን በዚያ አካባቢ እንደ አንበሳ፣ ተኩላና ነብር የመሳሰሉ አራዊት በብዛት ይገኙ ነበር። ቤተሰብ ያለው አንድ ሰው ‘ሚስቴና ልጆቼ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከል የምችለው እንዴት ነው? በጎቼንና ከብቶቼንስ ከአደጋ መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢያስብ የሚያስገርም አይደለም። በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘው አምላክ የገባው ቃል አይሁዳውያኑን ምን ያህል አጽናንቷቸው እንደሚሆን አስበው። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ፣ ማራኪ በሆነው በዚህ ትንቢት አማካኝነት ግዞተኞቹም ሆኑ ከብቶቻቸው ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ማረጋገጫ ሰጥቷል። አንበሶች ገለባ እንደሚበሉ የሚገልጸው ሐሳብ እነዚህ አራዊት የአይሁዳውያኑን ከብቶች እንደማይበሉባቸው ያመለክታል። ታማኝ አይሁዳውያን እንዲህ ያሉትን አራዊት የሚፈሩበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ተመልሰው በሚሄዱበት የይሁዳ ምድር፣ በምድረ በዳውም ሆነ በጫካዎች ውስጥ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደማይኖር ቃል ገብቷል።—ሕዝ. 34:25

5. ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን፣ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አትረፍርፎ እንደሚያቀርብላቸው እንዲተማመኑ ያደረጓቸው የትኞቹ ትንቢቶች ናቸው?

5 ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮችም ሊነሱ ይችላሉ። አይሁዳውያኑ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ይመጡባቸው ይሆናል፦ ‘ወደ ትውልድ አገራችን ስንመለስ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ምግብ ማቅረብ እችል ይሆን? የት እንኖራለን? ሥራስ አገኝ ይሆን? የምሠራው ሥራ በማረኩን ሰዎች ቀንበር ሥር ሆኜ ከምሠራው አሰልቺ ሥራ የተሻለ ይሆን?’ እንደ እነዚህ ለመሳሰሉት ጥያቄዎችም ይሖዋ በመንፈስ መሪነት ባስጻፋቸው ትንቢቶች አማካኝነት መልስ ሰጥቷል። ይሖዋ፣ ታዛዥ የሆኑት ሕዝቦቹ ምንጊዜም ዝናብ እንደሚያገኙና በዚህም የተነሳ ምድሪቱ “የተትረፈረፈና ምርጥ” የሆነ ምርት እንደምትሰጥ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 30:23) መኖሪያንና ሥራን በተመለከተም ይሖዋ ስለ ሕዝቦቹ እንዲህ ብሏል፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም።” (ኢሳ. 65:21, 22) በእርግጥም በብዙ መንገዶች ሲታይ ሕይወታቸው አረማዊ በሆነችው በባቢሎን በግዞት ከሚመሩት ሕይወት በእጅጉ የተሻለ ይሆናል። ይሁንና አሁን ላሉበት የግዞት ሕይወት ስለዳረጋቸው ከባድ ችግርስ ምን ማለት ይቻላል?

6. የአምላክ ሕዝቦች በምርኮ ከመወሰዳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ምን ዓይነት የጤና ችግር ነበረባቸው? ይሖዋ ከግዞት ለሚመለሱት አይሁዳውያን ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል?

6 መንፈሳዊ ጤንነት። የአምላክ ሕዝቦች በምርኮ ከመወሰዳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ ታምመው ነበር። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ስለ ሕዝቡ ሲናገር “መላው ራስ ታሟል፤ መላው ልብም በበሽታ ተይዟል” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 1:5) ሕዝቡ ይሖዋ ለሚሰጣቸው ምክር ጆሮ ባለመስጠታቸውና  እሱ የሚሰጣቸውን የእውቀት ብርሃን ላለማየት ዓይናቸውን በመጨፈናቸው በመንፈሳዊ ሁኔታ ዓይነ ስውርና መስማት የተሳናቸው ሆነው ነበር። (ኢሳ. 6:10፤ ኤር. 5:21፤ ሕዝ. 12:2) አይሁዳውያኑ ከግዞት ከተመለሱም በኋላ ይኸው ችግር ከቀጠለ ያለ ስጋት መኖር እንዴት ይችላሉ? እንደገና የይሖዋን ሞገስ አያጡም? ይሖዋ “በዚያ ቀን፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመጽሐፉን ቃል ይሰማሉ፤ የዓይነ ስውራኑም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ” በማለት የሰጠው ተስፋ ይህ እንደማይሆን ዋስትና ይሰጣል። (ኢሳ. 29:18) አዎን፣ ይሖዋ ተግሣጹን ተቀብለው ንስሐ የገቡትን ሕዝቦቹን በመንፈሳዊ ይፈውሳቸዋል። ሕዝቡ እሱን መስማታቸውንና መታዘዛቸውን እስካልተዉ ድረስ ይሖዋ ሕይወት ሰጪ የሆነውን መመሪያና እውቀት መስጠቱን ይቀጥላል።

7. አምላክ በግዞት ለነበሩት ሕዝቦቹ የገባው ቃል የተፈጸመው እንዴት ነው? ይህስ የእኛን እምነት የሚያጠናክረው እንዴት ነው?

7 ታዲያ ይሖዋ ቃሉን ጠብቆ ይሆን? ታሪክ መልሱን ይሰጠናል። ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ያለ ስጋት፣ ሁሉ ነገር ተትረፍርፎላቸውና መንፈሳዊ ጤንነት አግኝተው መኖር ችለዋል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ ከእነሱ በኃይልም ሆነ በቁጥር ከሚበልጡት ጎረቤቶቻቸው ጠብቋቸዋል። አራዊትም የአይሁዳውያኑን ከብቶች አልበሉባቸውም። እርግጥ ነው፣ እነዚያ አይሁዳውያን ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና እንደ እነዚህ ያሉ ነቢያት እንደ ገነት ያለ ሁኔታ እንደሚኖር የጻፏቸው ትንቢቶች ሙሉ በሙሉ ሲፈጸሙ አላዩም፤ ያም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች ሲፈጸሙ ያዩአቸው ትንቢቶች አስደሳች ከመሆናቸውም ሌላ በወቅቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ አድርገዋል። እኛም ይሖዋ በዚያ ወቅት ለነበሩ ሕዝቦቹ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ ስናሰላስል እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። እነዚያ ትንቢቶች መጀመሪያ ላይ በተወሰነ መጠን ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው አስደሳች ከነበረ ሙሉ በሙሉ ሲፈጸሙ ደግሞ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? እስቲ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን እንዳደረገልን እንመልከት።

ይሖዋ የገባውን ቃል በዘመናችን እየፈጸመ ያለው እንዴት ነው?

8. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩት በምን ዓይነት “አገር” ውስጥ ነው?

8 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ቃል በቃል አንድ ብሔር አላቋቋሙም፤ የሚኖሩትም ቢሆን በአንድ አገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የአንድ መንፈሳዊ ብሔር አባል ናቸው፤ ይህ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ይባላል። (ገላ. 6:16) ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑት አጋሮቻቸውም በመንፈሳዊ “አገር” ይኸውም ይሖዋ አምላክን በአንድነት በሚያመልኩበት ክልል ውስጥ ከእነሱ ጋር ይኖራሉ። ይህ አምልኮ መላው ሕይወታቸውን ይነካል። (ዮሐ. 10:16፤ ኢሳ. 66:8) ይሖዋ የሰጠን “አገር” ምንድን ነው? መንፈሳዊ ገነት ነው። አምላክ እንደ ኤደን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር የገባው ቃል በዚህ ገነት ውስጥ በመንፈሳዊ ሁኔታ አስደናቂ ፍጻሜውን አግኝቷል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

9, 10. (ሀ) በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው? (ለ) በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሰላም እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

9 ያለ ስጋት መኖር። በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ የዱር እንስሳትም ሆኑ ሰዎችና የቤት እንስሶቻቸው ተስማምተውና በሰላም እንደሚኖሩ ማራኪ በሆነ መንገድ ይገልጻል። ታዲያ ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜ አግኝቷል? አዎን! ቁጥር 9 እነዚህ ፍጥረታት ጉዳት ወይም ጥፋት የማያደርሱበትን ምክንያት ሲገልጽ “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን  ምድርም በእርግጥ በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” ይላል። ‘የይሖዋ እውቀት’ የእንስሳትን ባሕርይ ሊለውጥ ይችላል? አይችልም። ልዑሉን አምላክ በማወቃቸውና እንደ እሱ ሰላማዊ መሆን የሚችሉበትን መንገድ በመማራቸው ሕይወታቸው የሚለወጠው ሰዎች ናቸው። ዛሬ ባለንበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይህ ትንቢት አስደሳች በሆነ መንገድ ሲፈጸም የምናየው ለዚህ ነው። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ያሉት የክርስቶስ ተከታዮች ኃይለኝነት የሚንጸባረቅበትንና እንደ አውሬ ያለ ባሕርያቸውን አስወግደው ከመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በሰላምና በስምምነት መኖር እንዳለባቸው እየተማሩ ነው።

10 ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ መጽሐፍ ላይ ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ይኸውም እንዲህ ዓይነት አቋም ለመያዝ ምክንያት ስለሆነን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብና የአምላክ ሕዝቦች ገለልተኛ በመሆናቸው ስለደረሰባቸው ስደት ተመልክተናል። ታዲያ በዓመፅ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ፣ የሞት ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም እንኳ በማንኛውም ዓይነት የዓመፅ ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ አባላት ያሉት “ብሔር” መኖሩ የሚያስገርም አይደለም? የመሲሐዊው ንጉሥ ተገዢዎች ኢሳይያስ የገለጸው ዓይነት ሰላም እንዳላቸው የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደናቂ ማስረጃ ነው! ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:34, 35) በጉባኤው ውስጥ ክርስቶስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያው’ በመጠቀም ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰላማዊ፣ አፍቃሪና ገር እንዲሆኑ በትዕግሥት እያስተማራቸው ነው።—ማቴ. 24:45-47

11, 12. በዛሬው ጊዜ ያለውን ዓለም እያጠቃው ያለው ምን ዓይነት ረሃብ ነው? ይሖዋ ለሕዝቦቹ የተትረፈረፈ ምግብ የሚያቀርብላቸው እንዴት ነው?

 11 ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። ዓለም በመንፈሳዊ ረሃብ እየተሠቃየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “‘እነሆ፣ በምድሪቱ ላይ ረሃብ የምሰድበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፤ ‘ረሃቡ የይሖዋን ቃል የመስማት ረሃብ እንጂ ምግብን የመራብ ወይም ውኃን የመጠማት አይደለም።’” (አሞጽ 8:11) የአምላክ መንግሥት ዜጎችስ ተመሳሳይ ረሃብ አጋጥሟቸው ይሆን? ይሖዋ፣ በሕዝቡና በጠላቶቹ መካከል የሚኖረውን ልዩነት ለመግለጽ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ።” (ኢሳ. 65:13) አንተስ እነዚህ ቃላት ሲፈጸሙ ተመልክተሃል?

12 መንፈሳዊ ምግብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና ጥልቀቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ወንዝ በተትረፈረፈ ሁኔታ እየቀረበልን ነው። በመንፈሳዊ ረሃብ በተጠቃው በዚህ ዓለም ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱት ጽሑፎቻችን እንዲሁም በቪዲዮዎችና በድምፅ በተቀረጹ ነገሮች፣ በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ብሎም በድረ ገጻችን አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ምንጊዜም እንደማይቋረጥ ኃይለኛ ጅረት እየጎረፈልን ነው። (ሕዝ. 47:1-12፤ ኢዩ. 3:18) ይሖዋ የተትረፈረፈ ነገር እንደሚሰጠን የገባው ቃል በሕይወትህ ውስጥ በየዕለቱ ሲፈጸም በማየትህ አትደሰትም? ታዲያ በየዕለቱ ከይሖዋ ማዕድ ትመገባለህ?

ጉባኤዎቻችን በመንፈሳዊ በደንብ እንድንመገብ፣ ከስጋት ነፃ እንድንሆንና ጤናሞች እንድንሆን ይረዱናል

13. ይሖዋ የዕውሮች ዓይን እንደሚገለጥና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮ እንደሚከፈት የገባው ቃል ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው?

13 መንፈሳዊ ጤንነት። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ሆነዋል። (2 ቆሮ. 4:4) ክርስቶስ ግን በዓለም ዙሪያ ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ ነው። አንተስ የዕውሮች ዓይን ሲገለጥና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮ ሲከፈት ተመልክተሃል? ሰዎች ትክክለኛውን የአምላክ ቃል እውነት በማወቃቸው፣ በአንድ ወቅት እውነትን እንዳያዩና እንዳይሰሙ አድርገዋቸው የነበሩትን ሃይማኖታዊ ውሸቶች ሲተዉ ከተመለከትህ የሚከተለው ትንቢት ሲፈጸም አይተሃል ማለት ይቻላል፦ “በዚያ ቀን፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመጽሐፉን ቃል ይሰማሉ፤ የዓይነ ስውራኑም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ።” (ኢሳ. 29:18) በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ፈውስ እያገኙ ነው። ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥቶ ከእኛ ጋር በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ይሖዋን የሚያመልክ እያንዳንዱ ሰው ይሖዋ የሰጠው ተስፋ ለመፈጸሙ ሕያው ማስረጃ ነው!

14. እምነታችንን የሚያጠናክረው በምን ላይ ማሰላሰላችን ነው?

14 የዚህ መጽሐፍ እያንዳንዱ ምዕራፍ፣ በዚህ የመጨረሻው ዘመን ክርስቶስ ተከታዮቹን በእውነተኛ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ እያኖራቸው እንዳለ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ይዟል። በዚህ መንፈሳዊ ገነት አማካኝነት በረከት ስለምናገኝባቸው በርካታ መንገዶች ምንጊዜም እናሰላስል። ይህን ስናደርግ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል።

“መንግሥትህ ይምጣ”

15. ምድር ገነት እንደምትሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ መላዋን ምድር ገነት የማድረግ ዓላማ ነበረው። አዳምንና ሔዋንን በገነት ያስቀመጣቸው ሲሆን ልጆች ወልደው ምድርን  እንዲሞሏት እንዲሁም በላይዋ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ እንዲንከባከቡ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍ. 1:28) አዳምና ሔዋን ግን ከሰይጣን ጋር ተባብረው በማመፅ ዘሮቻቸው ሁሉ አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን እንዲወርሱ አደረጉ። ያም ቢሆን የአምላክ ዓላማ ፈጽሞ አልተቀየረም። የተናገረው ቃል ምንጊዜም ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። (ኢሳይያስ 55:10, 11ን አንብብ።) በመሆኑም የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን እንደሚሞሏት እንዲሁም እንደሚገዟት ማለትም ገነት በሆነችው ምድር ላይ ያሉትን የይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ በፍቅር እንደሚንከባከቧቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በግዞት ለነበሩት አይሁዳውያን እንደ ገነት ያለ ሁኔታ እንደሚኖር የተነገሯቸው ትንቢቶች በዚያ ወቅት ሙሉ በሙሉ ይፈጸማሉ! ይህ እንዴት እንደሚሆን ለማየት የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት።

16. መጽሐፍ ቅዱስ በገነት ውስጥ ያለ ስጋት እንደምንኖር የሚገልጸው እንዴት ነው?

16 ያለ ስጋት መኖር። በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘው አስደሳች ትንቢት በመጨረሻ ቃል በቃል የተሟላ ፍጻሜውን ሲያገኝ እንመለከታለን። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲሁም ልጆች በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ከስጋት ነፃ ሆነው መንቀሳቀስ ይችላሉ። ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ለሌሎች ስጋት አይፈጥሩም። በመላዋ ምድር ላይ እንደ ልብህ መሆን ይኸውም በወንዞች፣ በሐይቆችና በባሕሮች ውስጥ መዋኘት ብሎም በተራሮችና በሣር በተሸፈኑ ሜዳዎች ላይ ያለ ምንም ስጋት መቦረቅ የምትችልበት ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ቀኑ መሸ ብለህ የምትፈራበት ምክንያት አይኖርም። በሕዝቅኤል 34:25 ላይ ያለው ሐሳብ ፍጻሜውን ስለሚያገኝ የአምላክ ሕዝቦች “በምድረ በዳ ያለ ስጋት [መኖር]፤ በጫካዎችም ውስጥ [መተኛት]” እንኳ ይችላሉ።

17. የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር በሚገዛበት ወቅት ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር አትረፍርፎ እንደሚሰጠን እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

17 ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። ድህነት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ረሃብ ወይም እርዳታ የማይኖርበት ጊዜ ይታይህ። በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኙት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ መሲሐዊው ንጉሥ ለተገዢዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሁሉ እንደሚያቀርብላቸው ማረጋገጫ ይሆነናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በጥቂትና ዳቦና ዓሣ በሺዎች የሚቆጠሩ የተራቡ ሰዎችን መመገቡ እንዲህ ያሉ ትንቢቶችን መፈጸም እንደሚችል የሚያሳይ ናሙና ይሆናል። (ማቴ. 14:17, 18፤ 15:34-36፤ ማር. 8:19, 20) የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር በሚገዛበት ወቅት እንደሚከተለው ያሉ ትንቢቶች ቃል በቃል ይፈጸማሉ፦ “መሬት ላይ ለምትዘራው ዘር ዝናብ ይሰጥሃል፤ ምድሪቱም የምታፈራው እህል የተትረፈረፈና ምርጥ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ ሰፊ በሆነ የግጦሽ መስክ ይሰማራሉ።”—ኢሳ. 30:23

18, 19. (ሀ) በኢሳይያስ 65:20-22 ላይ የሚገኘው ትንቢት ለአንተ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ዕድሜያችን “እንደ ዛፍ ዕድሜ” የሚሆነው በምን መንገድ ነው?

18 በዛሬው ጊዜ ምቹ መኖሪያ ቤት ወይም አርኪ ሥራ ማግኘት ለብዙዎች የማይታሰብ ነገር ነው። ምግባረ ብልሹነት በተስፋፋበት በዚህ ዓለም ብዙዎች ለረጅም ሰዓት በትጋት ቢሠሩም እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው የሚያገኙት ጥቅም በጣም ትንሽ እንደሆነና ሥራቸው የሚያስገኘው ትርፍ ሁሉ የሚገባው ሀብታምና ስግብግብ ወደሆኑት ሰዎች ኪስ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የሚከተለው ትንቢት በዓለም ዙሪያ ሲፈጸም ምን ዓይነት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል አስብ፦ “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። እነሱ በሠሩት ቤት ሌላ ሰው አይኖርም፤ እነሱ የተከሉትንም ሌላ ሰው አይበላውም። የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፤ የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም  በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።”—ኢሳ. 65:20-22

19 ዕድሜያችን “እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል” ሲባል ምን ማለት ነው? በአንድ ግዙፍ ዛፍ አጠገብ ቆመህ የዛፉ ዕድሜ ምን ያህል እንደሚሆን ምናልባትም ቅድመ አያቶችህ ከመወለዳቸው በፊት የነበረ መሆኑን ስታስብ በአግራሞት መዋጥህ አይቀርም። መቼም ቢሆን ከአለፍጽምና የማትላቀቅ ቢሆን እንዲህ ያለው ዛፍ አንተ ሞተህ ከተረሳህም በኋላ ምንም ሳይሆን ለረጅም ዘመናት እንደሚኖር የታወቀ ነው። ይሖዋ፣ ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ እኛም ለረጅም ዘመን በሰላም እንደምንኖር ቃል መግባቱ ደግነቱን የሚያሳይ ነው! (መዝ. 37:11, 29) እኛ ለዘላለም ስለምንኖር፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዛፍ እንኳ ዛሬ ታይቶ ነገ እንደሚጠፋ ሣር ሆኖ የሚታየን ጊዜ ይመጣል!

20. ታማኝ የመንግሥቱ ተገዢዎች ፍጹም ጤንነት የሚያገኙት እንዴት ነው?

20 ፍጹም ጤንነት። በዛሬው ጊዜ በሽታና ሞት ቤቱን ያላንኳኩበት ሰው የለም። ሁላችንም ኃጢአት በሚባል ገዳይ በሽታ የተያዝን ያህል ነው። ከዚህ በሽታ ሊያድነን የሚችለው ብቸኛው መድኃኒት የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። (ሮም 3:23፤ 6:23) ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ሰዎች ከዚህ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ በማድረግ፣ ኃጢአት ታማኝ በሆኑ የሰው ልጆች ላይ ያስከተላቸውን ችግሮች ሁሉ ቀስ በቀስ ያስወግዳሉ። “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም። በምድሪቱ ላይ የሚቀመጡ በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት በተሟላ መንገድ ፍጻሜውን ያገኛል። (ኢሳ. 33:24) ዓይነ ስውር፣ መስማት የተሳነው ወይም የአካል ጉዳተኛ የማይኖርበት ጊዜ ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ኢሳይያስ 35:5, 6ን አንብብ።) ኢየሱስ ሊፈውሰው የማይችል አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ወይም ስሜታዊ ሕመም አይኖርም። ታማኝ የመንግሥቱ ተገዢዎች ፍጹም ጤንነት ይኖራቸዋል!

21. ሞት ምን ይሆናል? ይህ ተስፋ የሚያጽናናህስ ለምንድን ነው?

21 ይሁንና ብዙውን ጊዜ በሽታን ተከትሎ የሚመጣውና የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞትስ? ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሙሉ ይዋል ይደር እንጂ ኃያል ባላጋራ ለሆነው ለዚህ “የመጨረሻው ጠላት” መሸነፋቸው አይቀርም። (1 ቆሮ. 15:26) ሆኖም ሞት ከይሖዋ አቅም በላይ የሆነ ጠላት ነው? “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” የሚለውን የኢሳይያስ ትንቢት ተመልከት። (ኢሳ. 25:8) ያንን ጊዜ በአእምሮህ መሳል ትችላለህ? የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ የመቃብር ቦታ ወይም በሐዘን ምክንያት የሚፈስ እንባ አይኖርም! ከዚህ በተቃራኒ፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ የገባው አስደሳች ቃል ሲፈጸም ሰዎች የደስታ እንባ ያነባሉ! (ኢሳይያስ 26:19ን አንብብ።) በመጨረሻም ሞት ያስከተላቸው ጠባሳዎች ሁሉ ይሽራሉ።

22 በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ለማድረግ የሚያከናውነው ሥራ ያበቃል፤ እንዲሁም ክርስቶስ ሥልጣኑን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮ. 15:25-28) ፍጽምና የተላበሱት የሰው ልጆች ሰይጣን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ከማያደርግበት ከጥልቁ ሲወጣ የመጨረሻ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ከዚህ ፈተና በኋላ ክርስቶስ ያንን ክፉ እባብና ግብረ አበሮቹን በሙሉ ይጨፈልቃቸዋል። (ዘፍ. 3:15፤  ራእይ 20:3, 7-10) ይሖዋን የሚወዱ ታማኝ አገልጋዮቹ ሁሉ ግን ከፊታቸው ብሩህ ተስፋ ይጠብቃቸዋል። ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” እንደሚኖራቸው ከሚናገረው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ተስፋ ይበልጥ ይህን ጊዜ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ሐሳብ የለም።—ሮም 8:21

የይሖዋ ሕዝቦች በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ወደፊት በሚኖረው ገነት ውስጥ በደስታ ሲኖሩ

23, 24. (ሀ) አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

23 እነዚህ ተስፋዎች እንዲሁ ቅዠት፣ ምኞት ወይም የሕልም እንጀራ አይደሉም። ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች ነን! ለምን? በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የተመለከትነውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አስታውስ። ተከታዮቹ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለው ወደ ይሖዋ እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴ. 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ምናብ የፈጠረው ነገር አይደለም። እውን መስተዳድር ነው! በአሁኑ ጊዜም በሰማይ እየገዛ ነው። ለመቶ ዓመታት ያህል ይህ መንግሥት፣ ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በግልጽ ልናየው በምንችለው መንገድ ሲፈጽም ቆይቷል። በመሆኑም የአምላክ መንግሥት ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ምድር በሚያደርግበት ጊዜ፣ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች አንድም ሳይቀር እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

24 የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣ እርግጠኞች ነን። ይሖዋ የገባው እያንዳንዱ ቃል እንደሚፈጸም አንጠራጠርም። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠይቀው የሚገባው ጥያቄ ‘እኔስ ለአምላክ መንግሥት እየተገዛሁ ነው?’ የሚለው ነው። ፍጹምና ፍትሐዊ በሆነው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ወደፊት ለዘላለም መኖር እንድንችል አሁን ታማኝ የመንግሥቱ ተገዢዎች ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ!