የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ዓለም አቀፍ የግንባታ ሥራዎች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ይደግፋሉ

1, 2. (ሀ) ከጥንትም ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ምን ማድረግ ያስደስታቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ነገር ምንድን ነው?

ከጥንትም ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ለአምላክ ስም ክብር የሚያመጡ የግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ያስደስታቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በማደሪያው ድንኳን ሥራ በቅንዓት የተካፈሉ ሲሆን ለግንባታው የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶችም በልግስና ሰጥተዋል።—ዘፀ. 35:30-35፤ 36:1, 4-7

2 ይሖዋ በዋነኝነት ለእሱ ክብር እንደሚያመጣ አድርጎ የሚመለከተው የግንባታ ቁሳቁሶቹን አይደለም፤ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውም ለእነዚህ ነገሮች አይደለም። (ማቴ. 23:16, 17) ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተውና እሱን ከምንም በላይ የሚያስከብረው ስጦታ፣ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡለት አምልኮ ነው፤ ይህም የሚያሳዩትን የፈቃደኝነት መንፈስና በቅንዓት የሚያከናውኑትን ሥራ ይጨምራል። (ዘፀ. 35:21፤ ማር. 12:41-44፤ 1 ጢሞ. 6:17-19) ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሐቅ ነው። ለምን? ምክንያቱም ሕንፃዎች ዛሬ ታይተው ነገ ሊጠፉ ይችላሉ። ለምሳሌ የማደሪያው ድንኳንና ቤተ መቅደሱ ዛሬ የሉም። እነዚህ የአምልኮ ቦታዎች አሁን ባይኖሩም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ግንባታውን ለመደገፍ ያሳዩትን ልግስና እንዲሁም በትጋት ያከናወኑትን ሥራ አይረሳም።—1 ቆሮንቶስ 15:58ን እና ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።

3. በዚህ ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 በዘመናችን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮችም የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት በትጋት ሲሠሩ ቆይተዋል። ደግሞም በንጉሣችን በኢየሱስ ክርስቶስ እየተመራን ያከናወንነው ሥራ እጅግ አስደናቂ ነው! ይሖዋ ጥረታችንን እንደባረከው ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 127:1) ካከናወንናቸው ሥራዎች አንዳንዶቹን እንዲሁም እነዚህ ሥራዎች ለይሖዋ ክብር ያመጡት እንዴት እንደሆነ በዚህ ምዕራፍ ላይ እንመረምራለን። በተጨማሪም በዚህ ሥራ የተካፈሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የሰጧቸውን አስተያየቶች እንመለከታለን።

የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት

4. (ሀ) ተጨማሪ የአምልኮ ቦታዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው? (ለ) የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንድ ላይ መጠቃለል ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? (“ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ—በለውጦች ምክንያት ማስተካከያ ማድረግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

4 በምዕራፍ 16 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ለአምልኮ እንድንሰበሰብ ይፈልጋል። (ዕብ. 10:25) ስብሰባዎቻችን እምነታችንን የሚያጠናክሩ ከመሆኑም ሌላ ለስብከቱ ሥራ ያለን ቅንዓት እንዲቀጣጠል ይረዱናል። ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ዘልቀን በገባንበት በዚህ ወቅት ይሖዋ ሥራውን እያፋጠነው ነው። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ድርጅቱ  እየጎረፉ ነው። (ኢሳ. 60:22) የመንግሥቱ ተገዢዎች ቁጥር በጨመረ መጠን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተሙባቸው ተጨማሪ ሕንፃዎችም ያስፈልጋሉ። ከዚህም ሌላ ተጨማሪ የአምልኮ ቦታዎች ያስፈልጉናል።

5. የመንግሥት አዳራሽ የሚለው መጠሪያ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? (“ የአዲስ ብርሃን ቤተ ክርስቲያን” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

5 ዘመናዊው የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ በጀመረበት ወቅት አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የራሳቸው መሰብሰቢያ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። መጀመሪያ ከተገነቡት የአምልኮ ቦታዎች አንዱ በ1890 በዌስት ቨርጂኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተሠራው ሳይሆን አይቀርም። በ1930ዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ሠርተው ወይም እንደገና አድሰው የሚጠቀሙባቸው በርካታ የመሰብሰቢያ ቦታዎች የነበሯቸው ቢሆንም እነዚህ አዳራሾች ለይቶ የሚያሳውቃቸው መጠሪያ ገና አልተሰጣቸውም ነበር። በ1935 ወንድም ራዘርፎርድ ሃዋይን በጎበኘበት ወቅት አዲስ ከሚገነባው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተሠራ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ ይህ ሕንፃ ምን ተብሎ ቢጠራ እንደሚሻል ሲጠየቅ “የምንሰብከው የመንግሥቱን ምሥራች ከመሆኑ አንጻር ‘የመንግሥት አዳራሽ’ ብለን ብንጠራው ተገቢ  አይመስላችሁም?” የሚል ምላሽ ሰጠ። (ማቴ. 24:14) ብዙም ሳይቆይ ይህ አዳራሽ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች የሚሰበሰቡባቸው አብዛኞቹ አዳራሾች በዚህ ተስማሚ መጠሪያ መጠቀም ጀመሩ።

6, 7. በፍጥነት የሚገነቡ የመንግሥት አዳራሾች ምን ውጤት አስገኝተዋል?

6 በ1970ዎቹ ዓመታት ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች በጣም ያስፈልጉ ጀመር። በመሆኑም በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ወንድሞች ማራኪና ተስማሚ የሆኑ አዳራሾችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመገንባት የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ አስተዋወቁ። በ1983 በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ እንዲህ ዓይነት 200 ያህል አዳራሾች ተገንብተው ነበር። ወንድሞች ይህን ሥራ ለማከናወን የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ማቋቋም ጀመሩ። ይህ ዘዴ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ በ1986 የበላይ አካሉ እውቅና የሰጠው ሲሆን በ1987 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 60 የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ነበሩ። * በ1992 በሜክሲኮ፣ በስፔን፣ በአርጀንቲና፣ በአውስትራሊያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጀርመን፣ በጃፓንና በፈረንሳይ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር። በመንግሥት አዳራሽና በትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ላይ በትጋት የሚሠሩት ወንድሞች የሚያከናውኑት ሥራ ቅዱስ አገልግሎት በመሆኑ ድጋፍ ልናደርግላቸው እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።

7 በፍጥነት የሚገነቡት እነዚህ የመንግሥት አዳራሾች በሚሠሩበት አካባቢ ላለው ማኅበረሰብ ግሩም ምሥክርነት ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በስፔን የሚታተም አንድ ጋዜጣ የፊት ሽፋኑ ላይ “እምነት ተራሮችን ያንቀሳቅሳል” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጋዜጣው በማርቶስ ከተማ ስለተከናወነው እንዲህ ያለ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ የዘገበ ሲሆን የሚከተለውን ጥያቄ አንስቷል፦ “ራስ ወዳድነት በነገሠበት በዚህ ዓለም ከተለያዩ [የስፔን] ግዛቶች የተሰባሰቡ  ፈቃደኛ ሠራተኞች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት አድርገው ወደ ማርቶስ በመምጣት በፍጥነት፣ በጥራትና በተደራጀ መንገድ በመሠራት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አዳራሽ ሊገነቡ የቻሉት እንዴት ነው?” ጋዜጣው ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠው በቦታው ከነበሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዱ የሆነ የይሖዋ ምሥክር የተናገረውን በመጥቀስ ነው፤ ወንድም “ይህ ሊከናወን የቻለው ከይሖዋ የተማርን ሕዝቦች በመሆናችን ነው” ብሎ ነበር።

የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ መገንባት

8. በ1999 የበላይ አካሉ የትኛውን አዲስ ፕሮግራም አጸደቀ? ለምንስ?

8 ሃያኛው መቶ ዘመን እየተገባደደ ሲመጣ፣ የወንድሞች የገንዘብ አቅም ውስን በሆነባቸው አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት ጎርፈዋል። በእነዚህ አገሮች ያሉት ጉባኤዎች የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ያደርጉ ነበር። ያም ቢሆን በአንዳንድ አገሮች ያሉ ወንድሞች የመንግሥት አዳራሻቸው ከሌሎች ሃይማኖቶች የአምልኮ ቦታዎች አንጻር እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ሰዎች ያሾፉባቸው እንዲሁም ያጥላሏቸው ነበር። ከ1999 ወዲህ ግን የበላይ አካሉ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ እንዲፋጠን የሚረዳ ፕሮግራም አጸደቀ። የተሻለ አቅም ካላቸው አገሮች የተሰበሰበውን መዋጮ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ያሉ ወንድሞች እንዲጠቀሙበት መደረጉ ‘ሸክሙን እኩል ለመጋራት’ አስችሏል። (2 ቆሮንቶስ 8:13-15ን አንብብ።) እንዲሁም በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞችና እህቶች የግንባታ ሥራውን ለማገዝ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል።

9. የማይቻል ይመስል የነበረው የትኛው ሥራ ነው? ይሁንና ምን ተከናውኗል?

9 መጀመሪያ ላይ ሥራው የማይቻል ይመስል ነበር። በ2001 የቀረበ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው በ88 ታዳጊ አገሮች ውስጥ ከ18,300 በላይ  የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጉ ነበር። ይሁንና የአምላክ መንፈስና የንጉሣችን የኢየሱስ ክርስቶስ ድጋፍ እስካልተለየን ድረስ የማይቻል ሥራ አይኖርም። (ማቴ. 19:26) ከ1999 እስከ 2013 ባሉት ወደ 15 የሚጠጉ ዓመታት በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የአምላክ ሕዝቦች 26,849 የመንግሥት አዳራሾችን ገንብተዋል። * ይሖዋ የስብከቱን ሥራ መባረኩን ቀጥሏል፤ በመሆኑም 2013 ላይ በእነዚህ አገሮች ውስጥ 6,500 የሚያህሉ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጉ የነበረ ሲሆን አሁንም ቢሆን በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ።

የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ያስከትላል

10-12. የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣው እንዴት ነው?

10 የእነዚህ አዳዲስ መንግሥት አዳራሾች መገንባት ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣው እንዴት ነው? የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ የላከው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “አዲስ የመንግሥት አዳራሽ በሠራን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተሰብሳቢዎች ቁጥር በአብዛኛው በእጥፍ ይጨምራል።” በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች፣ ተስማሚ የአምልኮ ቦታ ከሌለን ከእኛ ጋር ለመሰብሰብ እምብዛም ፍላጎት አይኖራቸውም። የመንግሥት አዳራሽ ሲሠራ ግን ወዲያውኑ ግጥም ስለሚል ሌላ አዳራሽ መሥራት አስፈላጊ ይሆናል። ይሁንና ሰዎችን ወደ ይሖዋ የሚስባቸው የሕንፃዎቹ ውበት ብቻ አይደለም። ሰዎች ለአምላክ ድርጅት ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ የሚያመጣው አዳራሾቹን የሚገነቡት ወንድሞች የሚያሳዩት እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅርም ጭምር ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

11 ኢንዶኔዥያ። የመንግሥት አዳራሽ ሲሠራ ይመለከት የነበረ አንድ ሰው ሁሉም ሠራተኞች ሳይከፈላቸው እንደሚሠሩ ሲገነዘብ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም የምታስደንቁ ሰዎች ናችሁ! ምንም ገንዘብ የማይከፈላችሁ ቢሆንም ሁላችሁም ከልባችሁና በደስታ እንደምትሠሩ አስተውያለሁ። እንደ እናንተ ያለ ሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት የሚኖር አይመስለኝም!”

12 ዩክሬን። የመንግሥት አዳራሽ በሚሠራበት ቦታ በየቀኑ ታልፍ የነበረች አንዲት ሴት ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆን እንዳለባቸውና የሚገነቡትም የመንግሥት አዳራሽ እንደሚሆን ደመደመች። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው እህቴ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰምቻለሁ። ይህን ግንባታ ስመለከት እኔም የዚህ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል መሆን አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። በዚህ ቦታ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ አይቻለሁ።” ይህች ሴት መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ሲሆን በ2010 ተጠምቃለች።

13, 14. (ሀ) አንድ ባልና ሚስት፣ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ አይተው ከወሰዱት እርምጃ ምን ትምህርት አግኝተሃል? (ለ) የምትሰበሰብበት የአምልኮ ቦታ ለይሖዋ ስም ክብር እንዲያመጣ ለማድረግ ምን አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለህ?

13 አርጀንቲና። አንድ ባልና ሚስት፣ የመንግሥት አዳራሽ በሚሠራበት ቦታ ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠረውን ወንድም ቀርበው አነጋገሩት። ባልየው እንዲህ አለ፦ “የምታከናውኑትን የግንባታ ሥራ በትኩረት ስንከታተል ቆይተናል፤ . . . በዚህ ቦታ ስለ አምላክ ለመማር ወስነናል።” አክሎም “በዚህ ቦታ ለመሰብሰብ ምን ብቃት ማሟላት ይጠበቅብናል?” በማለት ጠየቀ። ባልና ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ቢቀበሉም ይህን የሚያደርጉት ቤተሰባቸው በሙሉ ማጥናት የሚፈቀድለት ከሆነ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ። ወንድሞችም ደስ እያላቸው በዚህ ተስማሙ።

14 የምትሰበሰብበት የመንግሥት አዳራሽ ሲሠራ የማገዝ አጋጣሚ አላገኘህ  ይሆናል፤ ያም ቢሆን ይህ የአምልኮ ቦታ ለይሖዋ ስም ክብር እንዲያመጣ ለማድረግ ልታበረክተው የምትችለው አስተዋጽኦ አለ። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችህ፣ ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸው ሰዎችና ሌሎች በዚህ የመንግሥት አዳራሽ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ ልታቀርብላቸው ትችላለህ። በተጨማሪም ይህን የአምልኮ ቦታ በማጽዳትና በመንከባከቡ ሥራ እገዛ የማድረግ አጋጣሚ አለህ። አስቀድመህ እቅድ በማውጣት፣ ለምትሰበሰብበት አዳራሽ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ወይም በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሚሠሩ የአምልኮ ቦታዎች የሚውል የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 16:2ን አንብብ።) ይህ ሁሉ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል።

‘ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው’ የሚያቀርቡ ሠራተኞች

15-17. (ሀ) አብዛኛውን የግንባታ ሥራ የሚያከናውኑት እነማን ናቸው? (ለ) በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ የሚካፈሉ ባለትዳሮች ከሰጡት ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 ከመንግሥት አዳራሾች፣ ከትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችና ከቅርንጫፍ ቢሮዎች ግንባታ ጋር በተያያዘ አብዛኛውን ሥራ የሚያከናውኑት በአካባቢው ያሉት ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ብዙውን ጊዜ ግን ከሌሎች አገሮች የመጡ በግንባታ ሥራ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶችም ይረዷቸዋል። ከእነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዳንዶቹ በሌሎች አገሮች በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ለተወሰኑ ሳምንታት ለመካፈል እንዲችሉ ፕሮግራማቸውን ያመቻቻሉ። ሌሎች ደግሞ በተለያዩ ምድቦች ላይ ለዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ቲሞ እና ሊን ላፓላይነን (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16 በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ መካፈል የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም ሥራው በእጅጉ የሚያረካ ነው። ለምሳሌ ቲሞ እና ሊን በአውሮፓ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ወደሚገኙ የተለያዩ አገሮች በመጓዝ በመንግሥት አዳራሾች፣ በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችና በቅርንጫፍ ቢሮዎች ግንባታ ተካፍለዋል። ቲሞ “ላለፉት 30 ዓመታት በአማካይ በየሁለት ዓመቱ ምድቤ ይቀየር ነበር” ብሏል። ከ25 ዓመታት በፊት ቲሞን ያገባችው ሊን  ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከቲሞ ጋር በአሥር አገሮች አገልግያለሁ። አዲስ ምግቦችን፣ የአየር ጠባዮችን፣ ቋንቋዎችንና የአገልግሎት ክልሎችን መልመድ እንዲሁም አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ከፍተኛ ጥረትና ጊዜ ይጠይቃል።” * ታዲያ ይህ ጥረት የሚክስ ነበር? ሊን እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የተትረፈረፈ በረከት አግኝተናል፤ የወንድሞችን ክርስቲያናዊ ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነት እንዲሁም የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ አይተናል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ በማርቆስ 10:29, 30 ላይ ለደቀ መዛሙርቱ የገባው ቃል ሲፈጸም ተመልክተናል። መንፈሳዊ ወንድሞችን፣ እህቶችንና እናቶችን መቶ እጥፍ አግኝተናል።” ቲሞ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ያሉንን ችሎታዎች ከሁሉ ለላቀው ዓላማ ማዋላችን ይኸውም የንጉሡን ንብረት በማስፋፋቱ ሥራ መካፈላችን ጥልቅ እርካታ አምጥቶልናል።”

17 በመካከለኛው አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በደቡብ አሜሪካና በደቡብ ፓስፊክ በተካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተካፈሉት ዳረን እና ሴራ እነሱ ከሰጡት ይበልጥ እንዳገኙ ይሰማቸዋል። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ዳረን እንዲህ ብሏል፦ “በተለያየ የዓለም ክፍል ካሉ ወንድሞች ጋር መሥራት ታላቅ መብት ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር በዓለም ዙሪያ ያለነውን ክርስቲያኖች እንደሚያስተሳስር ገመድ እንደሆነ ተመልክቻለሁ።” ሴራም እንዲህ ብላለች፦ “የተለያየ ባሕል ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ! ይሖዋን ለማገልገል ምን ያህል መሥዋዕት እንደሚከፍሉ ማየቴ እኔም ምንጊዜም ለይሖዋ ምርጤን እንድሰጥ አነሳስቶኛል።”

18. በመዝሙር 110:1-3 ላይ የሚገኘው ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?

18 ንጉሥ ዳዊት፣ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም መንግሥቱን ለመደገፍ ‘ራሳቸውን በገዛ ፈቃዳቸው’ እንደሚያቀርቡ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (መዝሙር 110:1-3ን አንብብ።) መንግሥቱን በሚደግፍ ሥራ የሚካፈሉ ሁሉ ይህን ትንቢት እየፈጸሙ ነው። (1 ቆሮ. 3:9) በዓለም ዙሪያ የተሠሩት በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ብሎም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ እየገዛ እንዳለ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው። ይሖዋ፣ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ በሚያደርግ ሥራ በመካፈል ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን ማገልገል መቻል ምንኛ ታላቅ መብት ነው!

^ አን.6 በ2013 በዩናይትድ ስቴትስ በነበሩት 132 የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ሥር ከ230,000 በላይ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸው ነበር። በዚያ አገር እነዚህ ኮሚቴዎች በየዓመቱ 75 ያህል አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን ግንባታ እንዲሁም 900 ያህል አዳራሾችን የማስተካከል ወይም የማደስ ሥራ አስተባብረዋል።

^ አን.9 ይህ አኃዝ በዚህ ፕሮግራም ባልተካተቱ አገሮች የተገነቡትን በርካታ የመንግሥት አዳራሾች አይጨምርም።

^ አን.16 ዓለም አቀፍ አገልጋዮች እና ፈቃደኛ ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በግንባታው ሥራ ላይ ቢሆንም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ወይም ምሽት ላይ በስብከቱ ሥራ በመሳተፍ በአካባቢው ያሉ ጉባኤዎችን ይረዳሉ።