በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 7

ምሥራቹ የሚሰበክባቸው ዘዴዎች—ምሥራቹን ለመስበክ በማንኛውም ዘዴ መጠቀም

ምሥራቹ የሚሰበክባቸው ዘዴዎች—ምሥራቹን ለመስበክ በማንኛውም ዘዴ መጠቀም

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

የአምላክ ሕዝቦች ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ሲሉ የተለያዩ የስብከት ዘዴዎችን ይጠቀማሉ

ኢየሱስ በአንድ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ሲሆን ሕዝቡ በዙሪያው ተሰብስበዋል፤ እሱ ግን ጀልባ ላይ በመውጣት ከሐይቁ ዳርቻ ትንሽ ፈቀቅ አለ። ኢየሱስ ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ውኃው ላይ መሆኑ ድምፁ ጎላ ብሎ እንዲሰማ እንደሚያደርግና ይህም የተሰበሰቡት በርካታ ሰዎች መልእክቱን ይበልጥ ጥርት ባለ መንገድ ለማዳመጥ እንደሚያስችላቸው ስለሚያውቅ ነው።—ማርቆስ 4:1, 2ን አንብብ።

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለብዙ ሰዎች ለመስበክ የትኛውን ዘዴ ተጠቅሟል? (ለ) ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የእሱን ምሳሌ የተከተሉት እንዴት ነው? ለምንስ?

2 መንግሥቱ በተወለደበት ጊዜ አካባቢ ባሉት አሥርተ ዓመታት የነበሩት ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ሲሉ የእሱን ፈለግ በመከተል አዳዲስ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ሁኔታዎች ሲለዋወጡና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ የአምላክ ሕዝቦችም በንጉሣቸው እየተመሩ አዳዲስ ዘዴዎችን መጠቀማቸውንና በሚጠቀሙባቸው መንገዶች ላይ ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የምንችለውን ያህል ለብዙ ሰዎች መስበክ እንፈልጋለን። (ማቴ. 24:14) ምሥራቹን በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ለማድረስ ስንጠቀምባቸው ከቆየናቸው ዘዴዎች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት። በተጨማሪም በቀድሞዎቹ ዓመታት ምሥራቹን ያስፋፉትን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምሳሌ መከተል የምትችልባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክር።

ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ማዳረስ

3 ጋዜጦች። ወንድም ራስልና አጋሮቹ፣ ከ1879 ጀምሮ መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በማተም የመንግሥቱ መልእክት ለብዙ ሰዎች እንዲደርስ አድርገዋል። ይሁንና ምሥራቹን ይበልጥ በስፋት መስበክ እንዲቻል ከ1914 በፊት ባለው አሥር ዓመት ውስጥ ክርስቶስ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ይመስላል። እነዚህ ሁኔታዎች መመቻቸት የጀመሩት በ1903 ነው። በፔንስልቬንያ ያሉ የፕሮቴስታንት አገልጋዮች ቃል አቀባይ የሆነው ዶክተር ኢፍሬም ልዌለን ኢተን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች ላይ ክርክር እንዲገጥመው ቻርልስ ቴዝ ራስልን የጋበዘው በዚህ ዓመት ነበር። ኢተን ለራስል በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኔና አንተ የማንስማማባቸውን . . . አንዳንድ ጥያቄዎች በተመለከተ በሕዝብ ፊት መወያየታችን የብዙኃኑን ትኩረት የሚስብ እንደሆነ ይሰማኛል።” ራስልና አጋሮቹም ይህ ውይይት የሕዝቡን ትኩረት እንደሚስብ ስለተሰማቸው ዘ ፒትስበርግ ጋዜት በተባለው ታዋቂ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ ዝግጅት አደረጉ። በጋዜጣው  ላይ የወጡት ርዕሶች ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈው ነበር፤ ከዚህም ሌላ ራስል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሰጠው ግልጽ ማብራሪያ በጣም አሳማኝ ነበር፤ በመሆኑም የጋዜጣው አታሚዎች የራስልን ንግግር በየሳምንቱ ለማተም ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹ። ይህ ሁኔታ የእውነትን ጠላቶች ምን ያህል አበሳጭቷቸው ይሆን!

በ1914 ከ2,000 በላይ ጋዜጦች የራስልን ስብከቶች ያትሙ ነበር

4, 5. ወንድም ራስል የትኛውን ባሕርይ አሳይቷል? በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ወንድሞች የእሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ጋዜጦችም የራስልን ንግግሮች ማተም ፈለጉ። መጠበቂያ ግንብ በ1908 እንደገለጸው በወቅቱ የራስል ስብከቶች “በአሥራ አንድ ጋዜጦች ላይ በቋሚነት” ይወጡ ነበር። ያም ቢሆን ግን፣ ራስል የማኅበሩን ቢሮ ከፒትስበርግ ወደ ሌላ ታዋቂ ከተማ ቢያዛውረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የሚዘጋጁት ዓምዶች በብዙ ጋዜጦች ላይ ሊወጡ እንደሚችሉ ስለ ጋዜጣ ሥራ የሚያውቁ ወንድሞች ሐሳብ አቀረቡ። ወንድም ራስል ይህን ሐሳብና ሌሎች ነገሮችን ግምት ውስጥ ካስገባ በኋላ በ1909 የማኅበሩ ቢሮ ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ እንዲዛወር አደረገ። ውጤቱ ምን ሆነ? ይህ በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥ 400 የሚያህሉ ጋዜጦች የራስልን ንግግሮች ማተም ጀመሩ፤ ይህን የሚያደርጉት ጋዜጦች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይሄድ ነበር። የአምላክ መንግሥት በ1914 በተቋቋመበት ወቅት የራስል ስብከቶችና የሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች በአራት ቋንቋዎች ከ2,000 በሚበልጡ ጋዜጦች ላይ ይታተሙ ነበር።

5 ይህ ሁኔታ ምን ያስተምረናል? በዛሬው ጊዜ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ያላቸው ክርስቲያኖች በትሕትና ረገድ የወንድም ራስልን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል። እንዴት? ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ሲያደርጉ የሌሎችን ምክር ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።—ምሳሌ 15:22ን አንብብ።

6. በጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩት እውነቶች የአንዲት ሴትን ሕይወት የለወጡት እንዴት ነው?

6 በእነዚያ ጋዜጦች ላይ የሚወጡት ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ እውነቶች በሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥተዋል። (ዕብ. 4:12) ለምሳሌ ያህል፣ በ1917 የተጠመቀችው ኦራ ሄትሴል በጋዜጦች ላይ በሚወጡት ርዕሶች አማካኝነት እውነትን ከሰሙ ሰዎች አንዷ ናት። ኦራ እንዲህ ብላለች፦ “ካገባሁ በኋላ በሮቸስተር፣ ሚኒሶታ የምትኖረውን እናቴን ልጠይቅ ሄድኩ። እናቴ ጋ ስደርስ ጋዜጣ ላይ የወጡ ርዕሶችን እየቆረጠች ስታወጣ አገኘኋት። እነዚህ ርዕሶች የራስል ስብከቶች ነበሩ። እናቴ ከእነዚህ ስብከቶች ያገኘችውን ትምህርት አብራራችልኝ።” ኦራ የተማረችውን እውነት የተቀበለች ሲሆን ስልሳ ለሚያህሉ ዓመታት ስለ አምላክ መንግሥት በታማኝነት ስትሰብክ ኖራለች።

7. ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ወንድሞች በጋዜጦች የመጠቀሙን ዘዴ መለስ ብለው መገምገም ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

7 ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ወንድሞች በጋዜጦች ተጠቅሞ ምሥራቹን የማሰራጨቱን ዘዴ በ1916 መለስ ብለው ገመገሙት፤ ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሷቸው ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። አንደኛ፣ በወቅቱ እየተካሄደ የነበረው ታላቁ ጦርነት ለሕትመት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎ ነበር። በብሪታንያ የነበረው የጋዜጣ ክፍላችን የሁኔታውን አስቸጋሪነት ሲገልጽ በ1916 የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቦ ነበር፦ “በአሁኑ ጊዜ [የራስል] ስብከቶች የሚታተሙት 30 በሚያህሉ ጋዜጦች ላይ ብቻ ነው። ወረቀት በጣም እየተወደደ በመሆኑ ይህ ቁጥር ብዙም ሳይቆይ መቀነሱ አይቀርም።” ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ወንድም ራስል ጥቅምት 31, 1916 መሞቱ ነው። የታኅሣሥ 15, 1916 መጠበቂያ ግንብ “ወንድም ራስል ስለሞተ [በጋዜጦች ላይ የሚወጡት] ስብከቶች ሙሉ በሙሉ ይቋረጣሉ” የሚል ማስታወቂያ ይዞ ነበር። ይሄኛው የስብከት ዘዴ ቢቋረጥም “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” እንደ ተባለው  ፊልም የመሳሰሉት ሌሎች ዘዴዎች ውጤታማ መሆናቸውን ቀጥለው ነበር።

8. “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም የተሠራው እንዴት ነው?

8 ተንቀሳቃሽ ምስል። ራስልና አጋሮቹ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለማዘጋጀት ሦስት ዓመት ያህል የፈጀባቸው ሲሆን ይህ ፊልም በ1914 ወጣ። (ምሳሌ 21:5) “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ የተቀዱ ድምፆችንና በባለ ቀለም መስታወት የተሠሩ ስላይዶችን አንድ ላይ በማቀናጀት የተዘጋጀ አዲስ ዓይነት ፊልም ነበር። በዚህ ፊልም ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ የሚሠሩ ሲሆን እንስሳትም እንኳ ተካትተው ነበር። በ1913 የወጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ብሏል፦ “የኖኅ ታሪክ በተሠራበት የፊልሙ ክፍል ላይ በአንድ ትልቅ መካነ አራዊት ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ እንስሳት የተሳተፉ ሲሆን ፊልሙ ድምፅም ታክሎበት ነበር።” በፎቶ ድራማው ላይ የሚታዩት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመስታወት ስላይዶች ደግሞ በለንደን፣ በኒው ዮርክ፣ በፊላደልፊያና በፓሪስ በሚገኙ ሠዓሊዎች አንድ በአንድ በእጅ የተሳሉ ናቸው።

9. “ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለማዘጋጀት ይህን ያህል ጊዜና ገንዘብ መሥዋዕት የተደረገው ለምንድን ነው?

 9 “ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ለማዘጋጀት ይህን ያህል ጊዜና ገንዘብ መሥዋዕት የተደረገው ለምንድን ነው? በ1913 በተደረጉ ተከታታይ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የወጣው የአቋም መግለጫ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “የአሜሪካ ጋዜጦች፣ በዜና እንዲሁም በሌሎች ዓምዶች ላይ በሚጠቀሙባቸው ምስሎችና የካርቱን ሥዕሎች አማካኝነት የሕዝቡን አመለካከት በመቅረጽ ረገድ ይህ ነው የማይባል ስኬት አግኝተዋል፤ ይህ ስኬት፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከፍተኛ ተወዳጅነት ከማትረፋቸውና እንደ አስፈላጊነቱ መለዋወጥ የሚችሉ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ [ምስሎች] ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው በግልጽ አሳይቷል፤ እኛም፣ በየጊዜው ለውጥ እያደረግን የምንሄድ ሰባኪዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች እንደመሆናችን ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ስላይዶች ለወንጌላውያንና ለአስተማሪዎች ውጤታማ ብሎም ጠቃሚ ዘዴዎች እንደሆኑ በመቀበል ይህን ዘዴ ሙሉ በሙሉ መደገፋችን ተገቢ እንደሆነ እናምናለን።”

ከላይ፦ “የፎቶ ድራማ” ማሳያ መሣሪያ፤ ከታች፦ “የፎቶ ድራማ” የመስታወት ስላይዶች

10 በ1914 “ፎቶ ድራማ” በ80 ከተሞች ውስጥ በየቀኑ ይታይ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ የሚኖሩ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ፊልሙን ተመልክተውታል። “ፎቶ ድራማ” በዚያው ዓመት በስዊዘርላንድ፣ በስዊድን፣ በብሪታንያ፣ በኒው ዚላንድ፣ በኖርዌይ፣ በአውስትራሊያ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመንና በፊንላንድ ታይቷል። ይህ ፊልም፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሳይካተቱበት አጠር ባለ መልኩም የተዘጋጀ ሲሆን በትናንሽ ከተሞች ውስጥ ይታይ ነበር። “ዩሬካ ድራማ” ተብሎ የተጠራው ይሄኛው ፊልም፣ ለማዘጋጀት ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ከመሆኑም ሌላ ለማጓጓዝ ቀላል ነበር። “ፎቶ ድራማ” አሊያም “ዩሬካ ድራማ” በ1916 በስዊድን ቋንቋ፣ በስፓንኛ፣ በአርሜንያ ቋንቋ፣ በዴኖ ኖርዌጂያን፣ በጀርመንኛ፣ በግሪክኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በፈረንሳይኛና በፖላንድ ቋንቋ ተተርጉመው ነበር።

በ1914 “ፎቶ ድራማ” በሕዝብ በተጨናነቁ አዳራሾች ውስጥ ይታይ ነበር

11, 12. “ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም በአንድ ወጣት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ይህ ወጣት ምን ምሳሌ ትቶልናል?

11 ሻርለ ሮኔር የተባለ የ18 ዓመት ወጣት በፈረንሳይኛ የተተረጎመውን “ፎቶ ድራማ” ፊልም መመልከቱ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ሻርለ እንዲህ ብሏል፦ “ፊልሙ በኮልማህ፣ አልሳስ፣ ፈረንሳይ ውስጥ የታየ ሲሆን እኔም የምኖረው በዚህ ከተማ ነበር። ገና ከመጀመሪያው የማረከኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ግልጽ በሆነ መንገድ መቅረቡ ነበር።”

12 ሻርለ የተመለከተው ነገር ልቡን ስለነካው ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ፤ ከዚያም በ1922 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። መጀመሪያ ላይ ከተሰጡት የሥራ ምድቦች አንዱ “ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም ፈረንሳይ ውስጥ ለሰዎች በማሳየቱ ሥራ መካፈል ነው። ሻርለ የተሰጠውን ሥራ አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የተለያዩ ሥራዎችን እንዳከናውን ይኸውም ቫዮሊን እንድጫወት እንዲሁም የሒሳብና የሥነ ጽሑፍ አገልጋይ ሆኜ እንድሠራ ተመድቤ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ ሊጀምር ሲል ተመልካቹን ጸጥ የማሰኘት ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር። በእረፍት ሰዓት ላይ ጽሑፎችን እናበረክታለን። ወንድሞች ወይም እህቶች በሙሉ በአዳራሹ ውስጥ የተወሰነ አካባቢ ላይ እንዲሠሩ እንመድባለን። ሁሉም በርከት ያሉ ጽሑፎችን ይዘው በተመደቡበት ቦታ በመዘዋወር እያንዳንዱን ሰው ያነጋግራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአዳራሹ መግቢያ ላይ ጽሑፎች የያዙ ጠረጴዛዎችን እናስቀምጥ ነበር።” በ1925 ሻርለ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል እንዲያገለግል ተጋበዘ። በዚያም ደብልዩ ቢ ቢ አር በተባለው  አዲስ የተቋቋመ የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ኦርኬስትራውን እንዲመራ ተመደበ። እኛም የዚህን ወንድም ተሞክሮ ስናነብ ‘የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨቱ ሥራ የሚሰጠኝን ማንኛውንም ምድብ ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?’ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።—ኢሳይያስ 6:8ን አንብብ።

13, 14. ምሥራቹን ለማሰራጨት ሬዲዮ ጥቅም ላይ የዋለው እንዴት ነው? (“ በደብልዩ ቢ ቢ አር ይተላለፉ የነበሩ ፕሮግራሞች” እና “ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ስብስባ” የሚሉትን ሣጥኖችም ተመልከት።)

13 ሬዲዮ። “ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም የማሳየቱ ሥራ በ1920ዎቹ ዓመታት እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ሬዲዮ የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት ጀመረ። ሚያዝያ 16, 1922 ወንድም ራዘርፎርድ በፊላደልፊያ፣ ፔንስልቬንያ ከሚገኘው ሜትሮፖሊታን ኦፔራ ሃውስ የመጀመሪያውን በሬዲዮ የሚተላለፍ ንግግር አቀረበ። “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” በሚል ርዕስ የቀረበውን ይህን ንግግር 50,000 ያህል ሰዎች እንዳዳመጡት ይገመታል። ከዚያም በ1923 የአንድ ትልቅ ስብሰባ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ በሬዲዮ ተላለፈ። ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ወንድሞች፣ በሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ከመጠቀም በተጨማሪ የራሳችንን ጣቢያ ማቋቋሙ ጠቃሚ እንደሆነ አመኑበት። ጣቢያው የተቋቋመው በስታትን ደሴት፣ ኒው ዮርክ ሲሆን ደብልዩ ቢ ቢ አር በሚል ስም ተመዘገበ። የካቲት 24, 1924 የመጀመሪያው ስርጭት ተላለፈ።

በ1922 ወደ 50,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር በሬዲዮ አዳምጠዋል

14 የታኅሣሥ 1, 1924 መጠበቂያ ግንብ ደብልዩ ቢ ቢ አር ሬዲዮ ጣቢያ የተቋቋመበትን ዓላማ ሲገልጽ “የእውነትን መልእክት ለማሰራጨት እስከ ዛሬ ከተጠቀምንባቸው ዘዴዎች ሁሉ፣ ብዙ ወጪ የማይጠይቀውና ውጤታማ የሆነው ዘዴ ሬዲዮ እንደሆነ እናምናለን” ብሏል። መጽሔቱ አክሎም “ጌታ እውነትን ለማሰራጨት ሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎችን ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ከተሰማው በራሱ መንገድ ገንዘቡን እንድናገኝ ያደርጋል” ብሏል። (መዝ. 127:1) በ1926 የይሖዋ ሕዝቦች ስድስት የሬዲዮ ጣቢያዎች ነበሯቸው። ሁለቱ የሚገኙት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይኸውም ደብልዩ ቢ ቢ አር በኒው ዮርክ ከተማ፣ ደብልዩ ኦ አር ዲ የተባለው ጣቢያ ደግሞ በቺካጎ አቅራቢያ ነበር። ሌሎቹ አራቱ ካናዳ ውስጥ በሳስካችዋን፣ በብሪትሽ ኮሎምቢያ፣ በአልበርታና በኦንታሪዮ ይገኙ ነበር።

15, 16. (ሀ) በካናዳ ያሉ ቀሳውስት በሬዲዮ ከምናስተላልፈው መልእክት ጋር በተያያዘ ምን አደረጉ? (ለ) በሬዲዮ የሚቀርቡት ንግግሮችና ከቤት ወደ ቤት የምናከናውነው የስብከት ሥራ እርስ በርስ ይደጋገፉ የነበረው እንዴት ነው?

15 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በዚህ መንገድ መሰራጨቱ ከሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት እይታ አላመለጠም። በሳስካችዋን፣ ካናዳ በሚገኘው የሬዲዮ ጣቢያ የሚከናወነውን ሥራ በደንብ የሚያውቀው አልበርት ሆፍማን እንዲህ ብሏል፦ “ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች [በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው] ማወቅ ቻሉ። እስከ 1928 ድረስ በሬዲዮ ግሩም ምሥክርነት ተሰጥቶ ነበር፤ በዚያ ዓመት ግን ቀሳውስቱ በባለሥልጣናቱ ላይ ጫና በማሳደራቸው በካናዳ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚተዳደሩ የሬዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ ፈቃዳቸው ተነጠቀ።”

16 በካናዳ የነበሩት የሬዲዮ ጣቢያዎቻችን ቢዘጉም የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች ሌሎች ባቋቋሟቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች ይተላለፉ ነበር። (ማቴ. 10:23) እነዚህ ስርጭቶች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚተላለፍባቸው ሌሎች ጣቢያዎች ስም መጠበቂያ ግንብ እና ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ! ይባላል) ላይ ይወጣ ነበር፤ በመሆኑም አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ፣ የቤቱ ባለቤቶች በአካባቢያቸው ባለው የሬዲዮ  ጣቢያ የሚቀርቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች እንዲያዳምጡ ያበረታቱ ነበር። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ? የጥር 1931 ቡለቲን እንዲህ ብሏል፦ “የሬዲዮ ስርጭቱ፣ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት በመስበኩ ሥራ ይበልጥ እንዲካፈሉ አበረታትቷቸዋል። ሰዎች፣ የሬዲዮ ጣቢያዎቹን እንዳዳመጡና ወንድም ራዘርፎርድ የሰጣቸውን ንግግሮች በመስማታቸው የተነሳ፣ የሚበረከቱላቸውን መጽሐፎች ለመውሰድ ፈቃደኛ እንደሆኑ የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶች ወደ ቢሮው ይመጡ ነበር።” የሬዲዮ ስርጭቱና ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው ስብከት “የጌታ ድርጅት የሚጠቀምባቸው ሁለቱ ታላላቅ የስብከት ዘዴዎች” እንደሆኑ ቡለቲን ገልጿል።

17, 18. ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ሬዲዮ ምሥራቹን በማሰራጨት ረገድ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

17 በሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ተጠቅመን በመስበካችን ምክንያት የሚሰነዘርብን ተቃውሞ በ1930ዎቹ ዓመታት እየጨመረ መጣ። በመሆኑም በ1937 መገባደጃ አካባቢ የይሖዋ ሕዝቦች የሁኔታዎችን መለዋወጥ ግምት ውስጥ በማስገባት ለውጥ አደረጉ። በሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ተጠቅመው ምሥራቹን ማሠራጨታቸውን በማቆም ከቤት ወደ ቤት በሚከናወነው አገልግሎት ላይ ይበልጥ ትኩረት አደረጉ። * ያም ቢሆን ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ወይም በፖለቲካው ሁኔታ ምክንያት ምሥራቹን በቀላሉ ማድረስ በማይቻልባቸው የዓለም ክፍሎች የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨት ረገድ ሬዲዮ ጠቃሚ ሚና መጫወቱን ቀጥሎ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ምሥራቅ ጀርመን ይባል በነበረው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት መስማት እንዲችሉ ሲባል ከ1951 እስከ 1991 ባለው ጊዜ ውስጥ በምዕራብ በርሊን፣ ጀርመን የሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን በቋሚነት ያሰራጭ ነበር። በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በሱሪናም ደግሞ ከ1961 ጀምሮ ከሦስት አሥርተ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የአገሪቱ ብሔራዊ የሬዲዮ ጣቢያ በየሳምንቱ ለ15 ደቂቃ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያስተላልፍ ነበር። ከ1969 እስከ 1977 ባሉት ዓመታት ውስጥ የይሖዋ ድርጅት “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ ይጠቅማሉ” በሚል ርዕስ ከ350 በላይ ተከታታይ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቷል። በዩናይትድ ስቴትስ በ48 ግዛቶች ውስጥ 291 የሬዲዮ ጣቢያዎች ይህንን ፕሮግራም ያስተላልፉ ነበር። በ1996 ደግሞ በደቡብ ፓስፊክ ባለችው በሳሞኣ ዋና ከተማ፣ በአፒያ የሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ “ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎቻችሁ የተሰጡ መልሶች” የሚል ርዕስ ያለው ሳምንታዊ ፕሮግራም ያስተላልፍ ነበር።

18 ሃያኛው መቶ ዘመን እየተገባደደ ሲሄድ ሬዲዮ ምሥራቹን በማሰራጨት ረገድ ዋነኛ ሚና መጫወቱ እየቀረ መጣ። ይሁንና ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ የሚያስችል ሌላ ቴክኖሎጂ ብቅ አለ።

19, 20. የይሖዋ ሕዝቦች jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ያዘጋጁት ለምንድን ነው? ይህ ድረ ገጽ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል? (“ JW.ORG” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

19 ኢንተርኔት። በ2013 ከ2.7 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ማለትም ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው። አንዳንድ ግምታዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሁለት ቢሊዮን የሚያህሉት ሰዎች ኢንተርኔት የሚጠቀሙት እንደ ስማርትፎን እና ታብሌት ኮምፒውተር ባሉ ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎች ነው። ይህ ቁጥር በዓለም ዙሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሄዱን ቀጥሏል፤ ተንቀሳቃሽ በሆኑ መሣሪያዎች አማካኝነት ኢንተርኔት መጠቀም በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው አፍሪካ ውስጥ ሲሆን በዚህች አህጉር በአሁኑ ወቅት ከ90 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዚህ መንገድ ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ኢንተርኔት  መስፋፋቱ በርካታ ሰዎች መረጃ በሚያገኙበት መንገድ ላይ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል።

20 ከ1997 ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ ሰዎችን ማግኘት በሚቻልበት በዚህ ዘዴ መጠቀም ጀመሩ። በ2013 jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ወደ 300 በሚጠጉ ቋንቋዎች ማግኘት የተቻለ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ከ520 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማውረድ ይቻላል። ድረ ገጹ በየቀኑ ከ750,000 በላይ ጎብኚዎች አሉት። በየወሩ ደግሞ ሰዎች፣ ቪዲዮ ከመመልከት በተጨማሪ ከ3 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን፣ 4 ሚሊዮን መጽሔቶችን እና 22 ሚሊዮን በድምፅ የተቀዱ ነገሮችን ከድረ ገጻችን ላይ ያወርዳሉ።

21 ይህ ድረ ገጽ የስብከቱ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ጭምር የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማዳረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ቴክኖሎጂ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በ2013 መጀመሪያ አካባቢ፣ ሲና የተባለ አንድ ሰው jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ከተመለከተ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት በመደወል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠው ጠየቀ። ይህ ሰው መደወሉ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? ሲና የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን የሚኖረው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በጥብቅ በታገደበት አገር ርቃ በምትገኝ መንደር ውስጥ ነው። ሲና፣ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት በመደወሉ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በሳምንት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት ተደርጎለታል። ጥናቱን የሚያካሂዱት በኢንተርኔት አማካኝነት በቪዲዮ እየተያዩ ነበር።

በግለሰብ ደረጃ ማስተማር

22, 23. (ሀ) ብዛት ላላቸው ሰዎች ለመስበክ የተጠቀምንባቸው ዘዴዎች ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነውን አገልግሎት ተክተዋል? (ለ) ንጉሡ ጥረታችንን የባረከው እንዴት ነው?

22 ብዛት ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ከተጠቀምንባቸው እንደ ጋዜጦች፣ “ፎቶ ድራማ፣” የሬዲዮ ፕሮግራም እና ኢንተርኔት ያሉ ዘዴዎች መካከል የትኛውም  ቢሆን የተዘጋጀበት ዓላማ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገልን እንዲተካ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋ ሕዝቦች ኢየሱስ የተወዉን ምሳሌ ይከተላሉ። ኢየሱስ አንድ ላይ ለተሰበሰቡ በርካታ ሰዎች በመስበክ ብቻ ሳይወሰን በግለሰብ ደረጃ ለሰዎች ትኩረት ሰጥቶ ይረዳቸው ነበር። (ሉቃስ 19:1-5) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ይህን እንዲያደርጉ ያሠለጠናቸው ሲሆን የሚሰብኩትን መልእክትም ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 10:1, 8-11ን አንብብ።) በምዕራፍ 6 ላይ እንደተመለከትነው ኃላፊነት ወስደው ሥራውን የሚመሩት ወንድሞች፣ እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ሰዎችን በአካል አግኝቶ እንዲያነጋግር ሲያበረታቱ ቆይተዋል።—ሥራ 5:42፤ 20:20

23 በአሁኑ ጊዜ ይኸውም መንግሥቱ ከተወለደ ከመቶ ዓመታት በኋላ፣ ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ አስፋፊዎች ስለ አምላክ ዓላማዎች ለሌሎች በማስተማሩ ሥራ በቅንዓት እየተካፈሉ ነው። ንጉሡ፣ በተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅመን መንግሥቱን ለማስታወቅ ያደረግነውን ጥረት እንደባረከው ምንም ጥያቄ የለውም። የሚቀጥለው ምዕራፍ እንደሚያሳየው ንጉሡ ምሥራቹን ለሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች ለመስበክ የሚያስችሉንን መሣሪያዎችም ሰጥቶናል።—ራእይ 14:6

^ አን.17 ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ ከነበሩን የሬዲዮ ጣቢያዎች የመጨረሻውን ማለትም ደብልዩ ቢ ቢ አር የተባለውን በኒው ዮርክ የሚገኝ ጣቢያ በ1957 ለመዝጋት ወሰኑ።