በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?

 ተጨማሪ ክፍል

የጌታ እራት—አምላክን የሚያስከብር በዓል

የጌታ እራት—አምላክን የሚያስከብር በዓል

ክርስቲያኖች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እንዲያከብሩ ታዘዋል። ይህ በዓል ‘የጌታ እራት’ ተብሎም ይጠራል። (1 ቆሮንቶስ 11:20) ይህን በዓል ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? መከበር ያለበትስ መቼና እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በዓል ያቋቋመው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የአይሁዶች የማለፍ በዓል ምሽት ነው። የማለፍ በዓል ይከበር የነበረው በዓመት አንድ ጊዜ ኒሳን ተብሎ በሚጠራው የአይሁዶች ወር 14ኛ ቀን ላይ ነው። አይሁዶች ይህ በዓል የሚውልበትን ቀን ለማስላት በጸደይ ወራት የቀኑም ሆነ የሌሊቱ ርዝማኔ በግምት እኩል 12 ሰዓት የሚሆንበትን ዕለት ይጠብቁ እንደነበር ካሉት መረጃዎች በግልጽ መገንዘብ ይቻላል። የኒሳን ወር የሚጀምረው ከዚህ ዕለት በኋላ ጨረቃ መታየት ከምትጀምርበት ቀን አንስቶ ነው። የማለፍ በዓል የሚከበረው በ14ኛው ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው።

ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ከሐዋርያቱ ጋር ካከበረና አስቆሮቱ ይሁዳ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ የጌታ እራትን አቋቋመ። ይህ እራት የአይሁዶችን የማለፍ በዓል የተካ በመሆኑ መከበር ያለበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

የማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ ‘እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው’ አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ ‘ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።”—ማቴዎስ 26:26-28

 አንዳንዶች ኢየሱስ ቂጣውን ቃል በቃል ወደ ሥጋው ወይኑን ደግሞ ወደ ደሙ እንደቀየረው አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቂጣውን በሰጣቸው ጊዜ በሥጋዊ አካሉ ላይ የተከሰተ ምንም ዓይነት ለውጥ አልነበረም። የኢየሱስ ሐዋርያት ቃል በቃል ሥጋውን በልተው እንዲሁም ደሙን ጠጥተው ነበር? በፍጹም፤ እንደዚያ አድርገው ቢሆን ኖሮ የአምላክን ሕግ የሚጻረር ዘግናኝ ድርጊት ይሆን ነበር። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:10) ሉቃስ 22:20 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው” ሲል ተናግሯል። ያ ጽዋ ቃል በቃል “አዲስ ኪዳን” ሆኖ ነበር ማለት ነው? ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ቃል ኪዳን አንድ ዓይነት ስምምነት እንጂ ሊጨበጥ የሚችል ግዑዝ ነገር አይደለም።

በመሆኑም ቂጣውም ሆነ ወይኑ ምሳሌዎች ናቸው። ቂጣው ፍጹም የሆነውን የክርስቶስ ሥጋ ይወክላል። ኢየሱስ የተጠቀመበት ቂጣ ከማለፍ በዓሉ የተረፈ ነው። ቂጣው ምንም ዓይነት እርሾ ሳይገባበት የተጋገረ ነው። (ዘፀአት 12:8) ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን ወይም ብክለትን ለማመልከት እርሾን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። ስለዚህ ቂጣው ኢየሱስ መሥዋዕት ያደረገውን ፍጹም ሥጋውን ያመለክታል። ሥጋው ከኃጢአት የጠራ ነው።—ማቴዎስ 16:11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 5:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 2:22፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

ቀዩ ወይን የኢየሱስን ደም ይወክላል። ይህ ደም አዲሱን ቃል ኪዳን ሕጋዊ ያደርገዋል። ኢየሱስ ደሙ የፈሰሰው ‘ለኀጢአት ይቅርታ’ እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም የሰው ልጆች በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነው ሊታዩና ይሖዋ በገባው አዲስ ቃል ኪዳን ሊታቀፉ ይችላሉ። (ዕብራውያን 9:14፤ 10:16, 17) ይህ ቃል ኪዳን ወይም ውል 144,000 ታማኝ ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ መሄድ የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች መላው የሰው ዘር በረከት ያገኝ ዘንድ በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ።—ዘፍጥረት 22:18፤ ኤርምያስ 31:31-33፤ 1 ጴጥሮስ 2:9፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-3

በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርቡትን ምሳሌያዊ የሆኑ ቂጣና ወይን ጠጅ መብላትና መጠጣት ያለባቸው እነማን ናቸው? በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት ማለትም ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ግልጽ ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እነዚህ ሰዎች በሰማይ ነገሥታት እንዲሆኑ የተመረጡ መሆናቸውን አምነው እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል። (ሮሜ 8:16) በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን ገብተዋል።—ሉቃስ 22:29 NW

 በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላላቸው ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በማክበር በጌታ እራት ላይ ይገኛሉ፤ ሆኖም በበዓሉ ላይ የሚገኙት አክብሮት በተሞላበት መንገድ የሥነ ሥርዓቱ ተካፋይ ለመሆን እንጂ ከቂጣውና ከወይኑ ለመካፈል አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች በዓመት አንድ ጊዜ ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የጌታ እራትን ያከብራሉ። በዓለም ዙሪያ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ እንዳላቸው የሚናገሩት በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ ቢሆኑም ይህ የመታሰቢያ በዓል በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። ይህ በዓል ሁሉም ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ስላሳዩት አቻ የማይገኝለት ፍቅር በጥሞና የሚያስቡበት ወቅት ነው።—ዮሐንስ 3:16