በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?

 ተጨማሪ ክፍል

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?

ሚካኤል የተባለው መንፈሳዊ ፍጡር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ በተጠቀሰባቸው ቦታዎች ላይ ያከናወናቸው ተግባሮችም ተገልጸዋል። በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ከክፉ መላእክት ጋር እንደታገለ፣ በይሁዳ መልእክት ላይ ከሰይጣን ጋር እንደተከራከረ እንዲሁም በራእይ መጽሐፍ ላይ ከዲያብሎስና ከአጋንንቱ ጋር እንደተዋጋ ተገልጿል። ሚካኤል የይሖዋን አገዛዝ በማስከበርና የአምላክን ጠላቶች በመዋጋት “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ከሚለው የስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ተግባር ፈጽሟል። ይሁንና ሚካኤል ማን ነው?

አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከአንድ በላይ በሆኑ ስሞች ይጠራሉ። ለምሳሌ ያህል የዕብራውያን አባት የሆነው ያዕቆብ እስራኤል ተብሎም ይጠራ የነበረ ሲሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ስሞዖን ተብሎም ይጠራ ነበር። (ዘፍጥረት 49:1, 2፤ ማቴዎስ 10:2) በተመሳሳይም ሚካኤል የሚለው ስም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ የሚጠራበት ሌላ መጠሪያው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። እንዲህ ብለን ለመደምደም የሚያስችሉንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

የመላእክት አለቃ። የአምላክ ቃል ሚካኤልን “የመላእክት አለቃ” ሲል ይጠራዋል። (ይሁዳ 9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የመላእክት አለቃ” የሚለው መጠሪያ በነጠላ ቁጥር እንጂ በብዙ ቁጥር ተጠቅሶ አይገኝም። ይህም የመላእክት አለቃ ተብሎ የሚጠራው አንድ መልአክ ብቻ እንደሆነ ይጠቁመናል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ከመላእክት አለቃነት ሥልጣን ጋር ተያይዞ ተገልጿል። 1 ተሰሎንቄ 4:16 ከሞት የተነሳውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን  አስመልክቶ ሲናገር “ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅ . . . ከሰማይ ይወርዳል” ይላል። ስለዚህ የኢየሱስ ድምፅ የመላእክት አለቃ ድምፅ እንደሆነ ተገልጿል። በመሆኑም ይህ ጥቅስ የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ኢየሱስ ራሱ እንደሆነ ያመለክታል።

የጦር ሠራዊት መሪ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶውና ከመላእክቱ ጋር እንደተዋጉ’ ይገልጻል። (ራእይ 12:7) ስለዚህ ሚካኤል ታማኝ የሆኑ መላእክት ሠራዊት መሪ ነው። የራእይ መጽሐፍ ኢየሱስም ታማኝ የሆኑ መላእክት ሠራዊት መሪ እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 19:14-16) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጌታ ኢየሱስን’ እና ‘ኀያላን መላእክቱን’ ለይቶ ጠቅሷል። (2 ተሰሎንቄ 1:7) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሚካኤልና “መላእክቱ” እንዲሁም ስለ ኢየሱስና ‘መላእክቱ’ ይናገራል። (ማቴዎስ 13:41፤ 16:27፤ 24:31፤ 1 ጴጥሮስ 3:22) የአምላክ ቃል በሰማይ ታማኝ መላእክትን ያቀፉ በሚካኤልና በኢየሱስ የሚመሩ ሁለት ሠራዊቶች እንዳሉ የሚናገር ባለመሆኑ ሚካኤል የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ የሚጫወተውን ሚና የሚያመለክት ስያሜ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። *

^ አን.1 ሚካኤል የሚለው ስም የአምላክን ልጅ እንደሚያመለክት የሚያሳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 393-394 እና ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 219 ላይ ይገኛል። ሁለቱም ጽሑፎች የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።