በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ አሥራ ሦስት

አምላክ ለሕይወት ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?

አምላክ ለሕይወት ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?
  • አምላክ ለሕይወት ምን አመለካከት አለው?

  • አምላክ ውርጃን በተመለከተስ ምን አመለካከት አለው?

  • ለሕይወት አክብሮት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?

1. ሕያዋን ነገሮችን በሙሉ የፈጠረው ማን ነው?

“እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው” ሲል ነቢዩ ኤርምያስ ተናግሯል። “እርሱ ሕያው አምላክ” ነው። (ኤርምያስ 10:10) ከዚህም በተጨማሪ የሕያዋን ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ነው። በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት “አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልም” ብለውታል። (ራእይ 4:11) ንጉሥ ዳዊት ለአምላክ ባቀረበው የውዳሴ መዝሙር ላይ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 36:9) እንግዲያው ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው።

2. አምላክ ለሕይወታችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ምን አድርጓል?

2 በተጨማሪም ይሖዋ ለሕይወታችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ይሰጠናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:28) የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውን ውኃ፣ የምንተነፍሰውን አየርና የምንኖርበትን መሬት ሰጥቶናል። (የሐዋርያት ሥራ 14:15-17) ይሖዋ ይህን ያከናወነው ሕይወትን አስደሳች በሚያደርግ መንገድ ነው። ሆኖም ሕይወትን በተሟላ ሁኔታ ማጣጣም እንድንችል የአምላክን ሕግጋት መማርና መታዘዝ ያስፈልገናል።—ኢሳይያስ 48:17, 18

ለሕይወት አክብሮት ማሳየት

3. አምላክ በአቤል ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንዴት ተመለከተው?

3 አምላክ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሕይወት አክብሮት እንድናሳይ ይፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ጥንት አዳምና ሔዋን ይኖሩ በነበረበት ዘመን ልጃቸው ቃየን በታናሽ ወንድሙ በአቤል ላይ በጣም ተቆጥቶ  ነበር። ይሖዋ ቁጣው ከባድ ኃጢአት እንዲፈጽም ሊገፋፋው እንደሚችል በመግለጽ ቃየንን አስጠነቀቀው። ቃየን የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት “ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም።” (ዘፍጥረት 4:3-8) ቃየን ወንድሙን በመግደሉ ይሖዋ ቀጣው።—ዘፍጥረት 4:9-11

4. አምላክ በሙሴ ሕግ አማካኝነት ለሕይወት ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

4 በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያገለግሉት ለመርዳት ሲል ሕጎች ሰጣቸው። እነዚህን ሕጎች የሰጣቸው በነቢዩ ሙሴ በኩል በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ የሙሴ ሕግ ተብለው ይጠራሉ። ከሙሴ ሕግ አንዱ “አትግደል” ይላል። (ዘዳግም 5:17) ይህም እስራኤላውያን፣ አምላክ ሰብዓዊ ሕይወትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትና ሰዎች የሌሎችን ሕይወት ከፍ አድርገው ሊመለከቱ እንደሚገባ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

5. ውርጃን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

5 በማኅፀን ውስጥ ስላለ ሕፃን ሕይወትስ ምን ለማለት ይቻላል? በሙሴ ሕግ መሠረት በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ያለን ሕፃን ለሞት መዳረግ የተወገዘ ነው። አዎን፣ ያልተወለደ ሕፃን ሕይወትም እንኳ በይሖዋ ፊት ውድ ነው። (ዘፀአት 21:22, 23፤ መዝሙር 127:3) ይህም ፅንስ ማስወረድ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልሆነ ያስገነዝበናል።

6. ሰውን መጥላት የሌለብን ለምንድን ነው?

6 ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ለሌሎች ሰዎች ትክክለኛ አመለካከት መያዝንም ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ” ይላል። (1 ዮሐንስ 3:15) የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ለሰው ያለንን ጥላቻ ከልባችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይኖርብናል። ምክንያቱም ለአብዛኞቹ የዓመጽ ድርጊቶች ዋነኛው መንስኤ ጥላቻ ነው። (1 ዮሐንስ 3:11, 12) እርስ በርስ መዋደድን መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው።

7. ለሕይወት አክብሮት እንደሌለን ሊያሳዩ የሚችሉት አንዳንድ ልማዶች ምንድን ናቸው?

7 ለራሳችን ሕይወት አክብሮት ስለማሳየትስ ምን ሊባል ይችላል? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መሞት የማይፈልጉ ቢሆንም እንኳ አንዳንዶች ደስታ ለማግኘት በሚል ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች  ትምባሆ ያጨሳሉ፣ ጫት ይቅማሉ ወይም ደግሞ ለመዝናናት ብለው አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ይወስዳሉ። እንዲህ ያሉ ነገሮች ሰውነትን የሚጎዱ ከመሆናቸውም በላይ ብዙውን ጊዜ ተጠቃሚዎቹን ለሞት ይዳርጋሉ። እነዚህን ነገሮች የመጠቀም ልማድ ያለው ሰው ሕይወትን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ አይመለከትም። እነዚህ ልማዶች በአምላክ ፊት ርኩስ ናቸው። (ሮሜ 6:19፤ 12:1፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገል እንድንችል እንዲህ ያሉትን ልማዶች እርግፍ አድርገን መተው ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጉ በጣም ከባድ ሊሆን ቢችልም እንኳ ይሖዋ አስፈላጊውን እርዳታ ሊሰጠን ይችላል። በተጨማሪም ሕይወታችንን ከእሱ እንደተገኘ ውድ ስጦታ አድርገን ለመያዝ የምናደርገውን ጥረት ያደንቃል።

8. ምንጊዜም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ደኅንነት ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

8 ለሕይወት አክብሮት ካለን ምንጊዜም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ደኅንነት እንጠነቀቃለን። ግድየለሾች አንሆንም ወይም ደስታ ለማግኘት ብቻ ብለን ሕይወታችንን ለአደጋ አናጋልጥም። ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ መኪና አናሽከረክርም እንዲሁም አደገኛ ከሆኑ ወይም ዓመጽ ከሚንጸባረቅባቸው ስፖርቶች እንርቃለን። (መዝሙር 11:5) አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል:- “አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፣ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፣ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።” (ዘዳግም 22:8) በዚህ ሕግ ውስጥ ከተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ ሰው ተደናቅፎ እንዳይወድቅና ጉዳት እንዳይደርስበት በቤትህ ያሉ እንደ ደረጃ ያሉ ነገሮች ለአደጋ የሚያጋልጡ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ አድርግ። መኪና ካለህ የመኪናህ ደኅንነት የተሟላ መሆኑን አረጋግጥ። ቤትህም ሆነ መኪናህ የአንተንም ይሁን የሌሎችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆን አይኖርበትም።

9. ለሕይወት አክብሮት ካለን በእንስሳት ላይ ምን ዓይነት ድርጊት ከመፈጸም እንቆጠባለን?

9 ስለ እንስሳ ሕይወትስ ምን ማለት ይቻላል? የእንስሳ ሕይወትም በፈጣሪ ፊት ቅዱስ ነው። ምግብና ልብስ ለማግኘት ወይም ሰዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ እንስሳትን መግደል የአምላክን ፈቃድ አይጻረርም። (ዘፍጥረት 3:21፤ 9:3፤ ዘፀአት 21:28) ይሁን እንጂ በእንስሳት ላይ የጭካኔ  ድርጊት መፈጸም ወይም ለመዝናናት ብሎ ብቻ እንስሳትን መግደል ስህተት ከመሆኑም በላይ ለሕይወት ቅድስና አክብሮት ማጣት ነው።—ምሳሌ 12:10

ለደም አክብሮት ማሳየት

10. አምላክ ሕይወትና ደም እርስ በርስ የተሳሰሩ ነገሮች እንደሆኑ ያመለከተው እንዴት ነው?

10 ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ ይሖዋ ቃየንን “የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” ብሎታል። (ዘፍጥረት 4:10) አምላክ ስለ አቤል ደም ሲናገር ስለ አቤል ሕይወት መናገሩ ነበር። ቃየን የአቤልን ሕይወት በማጥፋቱ መቀጣት ያስፈልገው ነበር። የአቤል ደም ወይም ሕይወት ፍትሕ ለማግኘት ወደ ይሖዋ የጮኸ ያህል ነበር። በሕይወትና በደም መካከል ያለው ዝምድና ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ እንደገና በግልጽ ታይቷል። ከጥፋት ውኃው በፊት ሰዎች ይበሉ የነበረው ፍራፍሬና አትክልት እንዲሁም የተለያዩ እህሎችንና ጥራጥሬዎችን ነበር። ከጥፋት ውኃው በኋላ ይሖዋ ኖኅንና ልጆቹን “ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ” አላቸው። ይሁን እንጂ አምላክ “ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ” የሚል እገዳ ጥሏል። (ዘፍጥረት 1:29፤ 9:3, 4) ይሖዋ የአንድን ፍጡር ሕይወትና ደም አጣምሮ እንደሚመለከት በግልጽ መረዳት ይቻላል።

11. አምላክ ከኖኅ ዘመን አንስቶ ሰዎች ደምን ለምን ዓላማ እንዳይጠቀሙበት አዟል?

11 ደምን ባለመብላት ለደም አክብሮት እንዳለን ልናሳይ እንችላለን። ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ እንዲህ ሲል አዟል:- ‘እንዲበላ የተፈቀደውን ማንኛውንም እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ የያዘ ደሙን ከውስጡ ያፍስስ፤ ዐፈርም ያልብሰው፤ እስራኤላውያንን “የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ” አልኋቸው።’ (ዘሌዋውያን 17:13, 14) ወደ 800 የሚጠጉ ዓመታት አስቀድሞ አምላክ የሰው ልጆች የእንስሳን ደም መብላት እንደሌለባቸው በመግለጽ በመጀመሪያ ለኖኅ የሰጠው ትእዛዝ በዚያም ወቅት ይሠራ ነበር። የይሖዋ አመለካከት ግልጽ ነበር:- አገልጋዮቹ የእንስሳን ሥጋ እንጂ ደሙን መብላት አይችሉም። ደሙን ወደ መሬት ማፍሰስ ነበረባቸው፤ ይህም የዚያን ፍጡር ሕይወት ወደ አምላክ እንደመመለስ ይቆጠራል።

12. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደምን በተመለከተ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሰጠውና ዛሬም የሚሠራው ትእዛዝ ምንድን ነው?

 12 ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ የሆነ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያትና ለኢየሱስ ተከታዮች አመራር ይሰጡ የነበሩ ሌሎች ወንዶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ የትኞቹን ትእዛዛት ሊያከብሩ እንደሚገባ ለመወሰን ተሰብስበው ነበር። የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፈዋል:- “ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስም ለእኛም መልካም መስሎ ታይቶናል፤ ይኸውም:- ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ [ደሙ ከውስጡ ያልፈሰሰ] እንዲሁም ከዝሙት ርኵሰት እንድትርቁ ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ 21:25) ስለዚህ ‘ከደም መራቅ’ አለብን። ይህን ማድረጋችን በአምላክ ፊት ከጣዖት አምልኮና ከጾታ ብልግና የመራቅን ያህል አስፈላጊ ነው።

ሐኪምህ ከአልኮል መጠጥ እንድትታቀብ ቢነግርህ በደም ሥርህ በኩል ትወስዳለህ?

13. ከደም እንድንርቅ የተሰጠን ትእዛዝ ደምን በደም ሥር ከመውሰድ መታቀብን የሚያጠቃልለው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

13 ከደም እንድንርቅ የተሰጠን ትእዛዝ ደምን በደም ሥር ከመውሰድ መታቀብን ይጨምራል? አዎን። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ ዶክተር የአልኮል መጠጦች እንዳትወስድ ነገረህ እንበል። ይህ ማለት የአልኮል መጠጥ እስካልጠጣህ ድረስ በደም ሥርህ ብትወስድ ችግር አይኖረውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት እንዳልሆነ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ከደም መራቅ ማለት በምንም ዓይነት መንገድ ወደ ሰውነታችን አለማስገባት ማለት ነው። ስለዚህ ከደም እንድንርቅ የተሰጠንን ትእዛዝ ለማክበር ስንል ማንም ሰው ደም በደም ሥራችን እንዲሰጠን አንፈቅድም።

14, 15. አንድ ክርስቲያን ሐኪሞች ደም መውሰድ አለብህ ቢሉት ምን ምላሽ ይሰጣል? ለምንስ?

14 አንድ ክርስቲያን ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ወይም ከፍተኛ የሆነ ቀዶ ሕክምና ቢያስፈልገውስ? ሐኪሞቹ ደም ካልወሰደ በስተቀር ሕይወቱ ሊተርፍ አይችልም አሉ እንበል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ የወደቀው ክርስቲያን መሞት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። የአምላክ ውድ ስጦታ የሆነውን ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ያለ ደም የሚሰጡ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን ይቀበላል። በመሆኑም በተቻለ መጠን እንዲህ ያለ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት የሚጥር ከመሆኑም በላይ በደም ምትክ የሚሰጡ ነገሮችን ለመውሰድ ፈቃደኛ ነው።

 15 አንድ ክርስቲያን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ዕድሜውን ትንሽ ለማራዘም ብሎ የአምላክን ሕግ ይጥሳል? ኢየሱስ “ነፍሱን [ወይም ሕይወቱን] ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነገር ግን ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ያድናታል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:25) መሞት አንፈልግም። ሆኖም የአምላክን ሕግ በመጣስ የአሁኑን ሕይወታችንን ለማዳን ብንሞክር የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን ልናጣ እንችላለን። እንግዲያው በማንኛውም ምክንያት ብንሞት ሕይወት ሰጪያችን በትንሣኤ እንደሚያስበንና ውድ የሆነውን የሕይወት ስጦታ መልሶ እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ በመተማመን በአምላክ ሕግ ትክክለኛነት ላይ መታመናችን የተገባ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ዕብራውያን 11:6

16. የአምላክ አገልጋዮች ደምን በተመለከተ ምን ቁርጥ አቋም አላቸው?

16 በአሁኑ ጊዜ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ደምን በተመለከተ የሰጣቸውን መመሪያ ለመከተል ቁርጥ አቋም አላቸው። ደምን በምንም መንገድ አይበሉም። በተጨማሪም ለሕክምና ብለው ደም አይወስዱም። * ደምን የፈጠረው አምላክ ለእነሱ የሚበጀውን ነገር እንደሚያውቅ እርግጠኞች ናቸው። አንተስ በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት አለህ?

ደምን በአግባቡ መጠቀም የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ

17. በጥንቷ እስራኤል ደምን በይሖዋ አምላክ ፊት ተቀባይነት ባለው ሁኔታ መጠቀም የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ምን ነበር?

17 የሙሴ ሕግ ደምን በአግባቡ መጠቀም የሚቻልበትን ብቸኛ መንገድ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይሖዋ ከጥንት እስራኤላውያን የሚፈለገውን አምልኮ  በተመለከተ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር:- “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው።” (ዘሌዋውያን 17:11) እስራኤላውያን ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ በመገናኛው ድንኳን፣ የአምላክ ቤተ መቅደስ ከተገነባ በኋላ ደግሞ በቤተ መቅደሱ የእንስሳ መሥዋዕት በማቅረብና በመሠዊያው ላይ ጥቂት ደም እንዲረጭ በማድረግ ምሕረት ማግኘት ይችሉ ነበር። ደም አግባብ ባለው መንገድ ጥቅም ላይ የሚውለው በእነዚህ መሥዋዕቶች ላይ ብቻ ነበር።

18. የኢየሱስ ደም መፍሰሱ ምን ጥቅሞችና በረከቶች ሊያስገኝልን ይችላል?

18 እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም፤ ስለሆነም የእንስሳት መሥዋዕት አያቀርቡም እንዲሁም የእንስሳት ደም በመሠዊያ ላይ እንዲረጭ አያደርጉም። (ዕብራውያን 10:1) ይሁን እንጂ በጥንት እስራኤላውያን ዘመን በመሠዊያው ላይ ደም መረጨቱ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከፍለውን ውድ የሆነ መሥዋዕት የሚያመለክት ነበር። በዚህ መጽሐፍ አምስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው ኢየሱስ  ደሙ መሥዋዕት ሆኖ እንዲፈስ በመፍቀድ ሰብዓዊ ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል። ከዚያም ወደ ሰማይ በማረግ የፈሰሰውን ደሙን ዋጋ ለአንዴና ለመጨረሻ በአምላክ ፊት አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:11, 12) ይህ ለኃጢአቶቻችን ይቅርታ ማግኘት የምንችልበትን መሠረት የጣለ ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን በር ከፍቶልናል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ደሙ ለዚህ ዓላማ መዋሉ ታላቅ ጥቅም አስገኝቷል! (1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ድነት ልናገኝ የምንችለው የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ባለው ዋጋ የምናምን ከሆነ ብቻ ነው።

ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

19. “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ” ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ይሖዋ አምላክ ሕይወትን የመሰለ ፍቅራዊ ስጦታ ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባል! ይህ ስጦታ በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ለሌሎች እንድንነግር ሊያነሳሳን አይገባም? ልክ እንደ ይሖዋ እኛም ለሰዎች ሕይወት የምናስብ ከሆነ በከፍተኛ ጉጉትና በቅንዓት ስሜት ይህን ለሌሎች ለመናገር እንገፋፋለን። (ሕዝቅኤል 3:17-21) ይህን ኃላፊነት በትጋት ከተወጣን ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ . . . [ነኝ]፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽ የተቈጠብሁበት ጊዜ የለምና” ብለን መናገር እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 20:26, 27) ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች መናገር ለሕይወትና ለደም የላቀ ግምት እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችልበት ግሩም መንገድ ነው።

^ አን.16 በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 13-17 ተመልከት።