በመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ መዝሙር 83:18 የተተረጎመው እንዴት ነው? የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ይህን ጥቅስ “ሰዎች ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው” ሲል ተርጉሞታል። በርከት ያሉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይሖዋ የሚለውን ስም “ጌታ” ወይም “ዘላለማዊ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። እዚህ ጥቅስ ላይ ሊገባ የሚገባው የትኛው ነው? የማዕረግ ስም ወይስ ይሖዋ የሚለው ስም?

የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ፊደላት

ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ስም ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ እዚህ ጥቅስ ላይ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የግል ስም ሠፍሮ ይገኛል። ይህ ስም በዕብራይስጥ ፊደላት יהוה (የሐወሐ) ተብሎ ተጽፏል። በአማርኛ የተለመደው የዚህ ስም አጠራር “ይሖዋ” ነው። ይህ ስም የሚገኘው በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው? አይደለም። መጀመሪያ በተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል!

የአምላክ ስም ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበውን የናሙና ጸሎት ተመልከት። ጸሎቱ የሚጀምረው “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” በሚሉት ቃላት ነው። (ማቴዎስ 6:9) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ “አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። አምላክም “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” ሲል ከሰማይ መልስ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 12:28) የአምላክ ስም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ታዲያ አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ በማውጣት በማዕረግ ስሞች የተኩት ለምንድን ነው?

ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ይመስላል። አንደኛው ምክንያት ብዙዎች ስሙ መጀመሪያ ይጠራበት የነበረው መንገድ ዛሬ ስለማይታወቅ ልንጠቀምበት አይገባም የሚል አቋም ያላቸው መሆኑ ነው። የጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጻፈው ያለአናባቢ ነበር። ስለሆነም ዛሬ የሐወሐ የሚሉት ፊደላት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንዴት ይነበቡ እንደነበር በእርግጠኝነት የሚያውቅ የለም። ይሁን እንጂ ይህ የአምላክን ስም እንዳንጠቀም ሊያግደን ይገባል? በመጽሐፍ ቅዱስ  ዘመን ኢየሱስ የሚለው ስም ይጠራ የነበረው የሹዋ ወይም የሆሹዋ ተብሎ ሊሆን ይችላል፤ በአሁኑ ጊዜ ይህን በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም። ሆኖም ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች በቋንቋቸው የተለመደውን አጠራር በመጠቀም ኢየሱስ የሚለውን ስም በተለያየ መንገድ ይጠሩታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን አጠራር ስለማያውቁ ብቻ በዚህ ስም ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም። በተመሳሳይም ወደ ውጭ አገር ብትሄድ የራስህ ስም በሌላ ቋንቋ ለየት ባለ መንገድ እንደሚጠራ ትረዳ ይሆናል። ስለዚህ የአምላክ ስም ጥንት ይጠራበት የነበረውን መንገድ በእርግጠኝነት አለማወቃችን በስሙ እንዳንጠቀም ምክንያት ሊሆነን አይችልም።

የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነ ተደርጎ የሚጠቀሰው ሁለተኛው ነገር ለረጅም ዘመን ከኖረ የአይሁዳውያን ወግ ጋር የተያያዘ ነው። ብዙዎቹ አይሁዳውያን የአምላክ ስም ፈጽሞ መጠራት የለበትም የሚል እምነት አላቸው። ይህ እምነት የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በተሳሳተ መንገድ ከመተርጎም የመነጨ እንደሆነ ካለው ሁኔታ መረዳት ይቻላል:- “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] የአምላክህን ስም ያለ አግባብ አታንሣ፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና።”—ዘፀአት 20:7

ይህ ሕግ የአምላክን ስም ያለ አግባብ መጠቀምን ያወግዛል። ይሁን እንጂ ስሙን አክብሮት በተሞላበት መንገድ እንዳንጠቀምበት ይከለክላል? በፍጹም። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን (“ብሉይ ኪዳንን”) የጻፉት ጸሐፊዎች በሙሉ አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ይመሩ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ናቸው። ሆኖም የአምላክን ስም በተደጋጋሚ ጊዜያት ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል በብዙ አምላኪዎች ፊት በታላቅ ድምፅ ይዘመሩ በነበሩ ብዙ መዝሙራት ውስጥ የአምላክን ስም ጠቅሰዋል። እንዲያውም ይሖዋ አምላክ አምላኪዎቹ ስሙን እንዲጠሩ ያዘዛቸው ሲሆን ታማኝ አገልጋዮቹም ይህን ትእዛዝ አክብረዋል። (ኢዩኤል 2:32 NW፤ የሐዋርያት ሥራ 2:21 NW) ስለዚህ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንዳደረገው የአምላክን ስም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም።—ዮሐንስ 17:26

የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን ስም በማዕረግ ስሞች በመተካታቸው ትልቅ ስህተት ሠርተዋል። አምላክ ሊቀረብም ሆነ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል እንደሆነ አድርገው አቅርበውታል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰዎች ከይሖዋ ጋር ‘ወዳጅነት’ እንዲመሠርቱ አጥብቆ ይመክራል። (መዝሙር 25:14) እስቲ በጣም ስለምትቀርበው ጓደኛህ አስብ። የጓደኛህን ስም ባታውቅ ኖሮ ምን ያህል ትቀርበው ነበር? በተመሳሳይም ሰዎች ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም እንዳያውቁ ከተደረጉ እንዴት ወደ አምላክ ሊቀርቡ ይችላሉ? ከዚህም ሌላ ሰዎች  የአምላክን ስም የማይጠቀሙ ከሆነ በጣም አስደናቂ የሆነውን የስሙን ትርጉም ሳይገነዘቡ ይቀራሉ። መለኮታዊው ስም ትርጉሙ ምንድን ነው?

ይሖዋ ራሱ የስሙን ትርጉም ታማኝ ለሆነው አገልጋዩ ለሙሴ ገልጾለታል። ሙሴ ስለ አምላክ ስም በጠየቀ ጊዜ ይሖዋ “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት መልስ ሰጥቶታል። (ዘፀአት 3:14 NW) የሮዘርሃም ትርጉም እነዚህን ቃላት “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” ሲል ተርጉሟቸዋል። ስለዚህ ይሖዋ ዓላማዎቹን ዳር ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል።

መሆን የምትፈልገውን ሁሉ መሆን ትችላለህ እንበል። ለጓደኞችህ ምን ታደርግላቸው ነበር? ከጓደኞችህ መካከል አንዱ በጣም ቢታመም የተዋጣለት ዶክተር በመሆን ልትፈውሰው ትችላለህ። ሌላው ጓደኛህ የገንዘብ ኪሳራ ቢደርስበት ወዲያውኑ ባለጸጋ ሰው ሆነህ ገንዘብ በመለገስ ከደረሰበት ኪሳራ ልትታደገው ትችላለህ። ዳሩ ምን ያደርጋል ይህን ሁሉ ለመሆን አቅምህ አይፈቅድም። ሁላችንም ብንሆን ያለን አቅም ውስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዴት መሆን እንደሚችል ስታውቅ በጣም ትገረማለህ። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ኃይሉን እሱን ለሚወዱት ሰዎች ጥቅም ማዋል በጣም ያስደስተዋል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ስሙን የማያውቁ ሰዎች እነዚህን አስደሳች የሆኑ የይሖዋ ባሕርያት ገጽታዎች ሳይረዱ ይቀራሉ።

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ የሚለው ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊወጣ አይገባውም። የስሙን ትርጉም ማወቃችንና ስሙን በአምልኳችን ውስጥ በሚገባ መጠቀማችን ሰማያዊ አባታችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ በእጅጉ ይረዳናል። *

^ አን.3 የአምላክን ስም፣ የስሙን ትርጉምና ስሙን በአምልኳችን ውስጥ መጠቀማችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።