1-3. ሁላችንም የምን እስረኞች ነን? ይሖዋስ እኛን ከዚህ እስራት ነፃ ለማውጣት ምን ያደርጋል?

አንተ ባልፈጸምከው ወንጀል ተከሰህ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደብህ እንበል። ከእስር ልትለቀቅ የምትችልበት ምንም መንገድ የለም። ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ ምንም ነገር ልታደርግ አትችልም። በጣም ተስፋ ቆርጠህ ሳለ ከእስር ቤት ሊያስወጣህ የሚችል ሰው እንዳለ ሰማህ፤ ሰውየውም እንደሚረዳህ ቃል ገባልህ! በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል?

2 ሁላችንም የሞት እስረኞች ነን ሊባል ይችላል። ምንም ነገር ብናደርግ ከሞት ማምለጥ አንችልም። ይሖዋ ግን እኛን ከሞት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ኃይል አለው። ደግሞም ይሖዋ “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል” በማለት ቃል ገብቶልናል።—1 ቆሮንቶስ 15:26

3 ወደፊት ስለ ሞት የማንጨነቅበት ዘመን ይመጣል፤ ያ ጊዜ ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ይሖዋ ሞትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የሞቱ ሰዎችም እንደገና በሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህ እንደሚያጽናናህ ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ፣ “በሞት የተረቱት” ዳግመኛ በሕይወት እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 26:19) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትንሣኤ በማለት ይጠራዋል።

የምንወደው ሰው ሲሞት

4. (ሀ) የቤተሰባችን አባል ወይም ጓደኛችን ሲሞት መጽናኛ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው? (ለ) ከኢየሱስ የቅርብ ጓደኞች መካከል እነማን ይገኙበታል?

4 የቤተሰባችን አባል ወይም የቅርብ ጓደኛችን ሲሞት በጣም እናዝናለን፤ ስሜታችን በጣም ይጎዳል። ምንም አቅም እንደሌለን  ይሰማናል። በሞት ያጣነው ሰው ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖር ማድረግ አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ያጽናናናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) ይሖዋና ኢየሱስ፣ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ከሞት ማስነሳት ይፈልጋሉ፤ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም የተባሉ የቅርብ ጓደኞች ነበሩት። ኢየሱስ አዘውትሮ ወደ እነሱ ቤት ይሄድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር” ይላል።—ዮሐንስ 11:3-5

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ፣ የአልዓዛር ቤተሰቦችና ወዳጆች ሲያለቅሱ ሲያይ ምን ተሰማው? (ለ) ኢየሱስ ሞትን በተመለከተ ያለውን ስሜት ማወቃችን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል?

5 አንድ ቀን አልዓዛር ሞተ። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ማርታንና ማርያምን ሊያጽናና ሄደ። ማርታ፣ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ልትቀበለው ወጣች። ኢየሱስን በማግኘቷ የተደሰተች ቢሆንም “አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። ማርታ፣ ኢየሱስ የደረሰው ዘግይቶ ስለነበር ምንም ማድረግ እንደማይችል ተሰምቷት ነበር። ኢየሱስ፣ የማርታ እህት ማርያምና አብረዋት የነበሩት ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ ስሜቱ ስለተረበሸ አለቀሰ። (ዮሐንስ 11:21, 33, 35) እኛ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ በጣም እንደምናዝን ሁሉ ኢየሱስም ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶታል።

6 ኢየሱስ ሞትን በተመለከተ እኛ የሚሰማን ዓይነት ስሜት እንዳለው ማወቃችን በጣም ያጽናናናል። ኢየሱስ ደግሞ የአባቱ ዓይነት ባሕርይና ስሜት ያለው በመሆኑ ይሖዋም ስሜታችንን እንደሚረዳ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 14:9) ይሖዋ ሞትን ለዘላለም ማስወገድ ይችላል፤ ደግሞም በቅርቡ ይህን ያደርጋል።

“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”

7, 8. ማርታ ድንጋዩ እንዲነሳ ያልፈለገችው ለምን ነበር? ሆኖም ኢየሱስ ምን አደረገ?

7 ኢየሱስ አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ሲደርስ መቃብሩ በትልቅ  ድንጋይ ተዘግቶ ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱት” አለ። ማርታ ግን ድንጋዩን እንዲያነሱት አልፈለገችም። ምክንያቱም አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። (ዮሐንስ 11:39) ማርታ፣ ኢየሱስ ቀጥሎ ምን ለማድረግ እንዳሰበ የምታውቀው ነገር አልነበረም።

አልዓዛር ከሞት ሲነሳ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! —ዮሐንስ 11:38-44

8 ከዚያም ኢየሱስ አልዓዛርን “ና ውጣ!” አለው። በዚህ ጊዜ ማርታና ማርያም ያዩት ነገር በጣም የሚያስገርም ነበር። “የሞተው ሰው እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ” ወይም በጨርቅ እንደተጠቀለሉ ወጣ። (ዮሐንስ 11:43, 44) አልዓዛር እንደገና በሕይወት መኖር ጀመረ! ከቤተሰቡና ከወዳጆቹ ጋር ዳግመኛ ተገናኘ። እነዚህ ሰዎች አልዓዛርን ሊጨብጡት፣ ሊያቅፉትና ሊያናግሩት ይችሉ ነበር። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ማስነሳቱ በጣም የሚያስደንቅ ተአምር ነው!

“አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!”

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ያገኘው ከማን ነው? (ለ) ስለ ትንሣኤ የሚናገሩት ታሪኮች ጠቃሚ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

9 ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን ያስነሳው በራሱ ኃይል ነው? አይደለም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል፤ ይሖዋም አልዓዛርን ማስነሳት እንዲችል ኃይል ሰጥቶታል። (ዮሐንስ 11:41, 42ን አንብብ።) ከሞት የተነሳው አልዓዛር ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ በጣም ታማ እንደነበረ ይገልጻል። ኢያኢሮስ የተባለው የልጅቷ አባት በጣም ስለተጨነቀ ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው። ይህ ሰው ከእሷ በስተቀር ሌላ ልጅ አልነበረውም። ኢያኢሮስ ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የተወሰኑ ሰዎች መጥተው “ልጅህ ሞታለች! ከዚህ በኋላ መምህሩን ለምን ታስቸግረዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ኢያኢሮስን “አትፍራ፤ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” አለው። ከዚያም አብረው ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሄዱ። እዚያ ሲደርሱ የሚያለቅሱ ሰዎች ነበሩ።  ኢየሱስም የሚያለቅሱትን ሰዎች “በቃ አታልቅሱ፤ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። የልጅቷ አባትና እናት ኢየሱስ እንዲህ ማለቱ ግራ ሳያጋባቸው አይቀርም። ኢየሱስ ቤት ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ ካስወጣ በኋላ ከልጅቷ አባትና እናት ጋር ሆኖ ትንሿ ልጅ ተኝታ ወደነበረችበት ክፍል ገባ። ከዚያም እጇን በመያዝ “አንቺ ልጅ፣ ተነሽ!” አላት። ልጅቷ ወዲያውኑ ተነስታ መራመድ ስትጀምር ወላጆቿ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ኢየሱስ ልጃቸውን ከሞት አስነሳላቸው። (ማርቆስ 5:22-24, 35-42፤ ሉቃስ 8:49-56) ከዚያ ቀን ጀምሮ ልጃቸውን ባዩ ቁጥር ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ያደረገላቸውን ታላቅ ነገር እንደሚያስታውሱ ጥርጥር የለውም። *

10 ኢየሱስ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ ሞተዋል። ይሁንና የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ማንበባችን ጠቃሚ ነው፤ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ይረዳናል። ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ከሞት ማስነሳት ይፈልጋል፤ ደግሞም ያስነሳቸዋል።

ስለ ትንሣኤ ከሚናገሩት ታሪኮች ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሐዋርያው ጴጥሮስ ዶርቃ የተባለችን ክርስቲያን ከሞት አስነስቷል። —የሐዋርያት ሥራ 9:36-42

ኤልያስ የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት አስነስቷል።—1 ነገሥት 17:17-24

11. መክብብ 9:5 ከሚገልጸው ሐሳብ አንጻር አልዓዛር ስለነበረበት ሁኔታ ምን ማለት እንችላለን?

11 መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” በማለት በግልጽ ይናገራል። አልዓዛር የነበረበት ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። (መክብብ 9:5) ኢየሱስ እንደተናገረው አልዓዛር የተኛ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 11:11) አልዓዛር መቃብር ውስጥ በነበረበት ጊዜ ‘ምንም አያውቅም’ ነበር።

12. አልዓዛር ከሞት እንደተነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 12 ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ብዙ ሰዎች ተመልክተዋል። የኢየሱስ ጠላቶችም እንኳ ይህን ተአምር እንደፈጸመ ያውቁ ነበር። አልዓዛር ዳግመኛ በሕይወት መኖሩ ለዚህ ማስረጃ ነው። (ዮሐንስ 11:47) በተጨማሪም ብዙ ሰዎች አልዓዛርን ለማየት የሄዱ ሲሆን በዚህም የተነሳ ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ እንደሆነ አምነዋል። የኢየሱስ ጠላቶች በዚህ ስላልተደሰቱ ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል አስበው ነበር።—ዮሐንስ 11:53፤ 12:9-11

13. ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

13 ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” ከሞት እንደሚነሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28) በመሆኑም ይሖዋ ከሞት የሚያስነሳቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው። ሆኖም ይሖዋ አንድን ሰው ከሞት ለማስነሳት ስለዚያ ሰው ሁሉንም ነገር ማስታወስ ይኖርበታል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ማድረግ ይችላል? እስቲ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስለሚገኙት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት አስብ። ይሖዋ የእያንዳንዱን ኮከብ ስም እንደሚያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:26ን አንብብ።) ይሖዋ የእያንዳንዱን ኮከብ ስም ማስታወስ ከቻለ፣ ከሞት የሚያስነሳቸውን ሰዎች የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን ማስታወስ እንደማይከብደው ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ይሖዋ በመሆኑ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

14, 15. ኢዮብ የተናገረው ሐሳብ ምን ያስገነዝበናል?

14 ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ በትንሣኤ ያምን ነበር። “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም ይሖዋን “አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ” ብሎታል። አዎ፣ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቀ እንዳለ ኢዮብ ተገንዝቦ ነበር።—ኢዮብ 14:13-15

 15 ስለ ትንሣኤ ተስፋ ስታውቅ ምን ተሰማህ? ‘በሞት የተለዩኝ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼስ ይነሱ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት እንደሚጓጓ ማወቃችን ያጽናናናል። ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እስቲ እንመልከት።

‘ድምፁን ሰምተው ይወጣሉ’

16. ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራቸዋል?

16 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ከሞት የተነሱ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ዳግመኛ የኖሩት እዚሁ ምድር ላይ ነው። ወደፊትም ከሞት የሚነሱት ሰዎች እዚሁ ምድር ላይ ይኖራሉ፤ በዚያን ጊዜ ግን በምድር ላይ የሚኖረው ሁኔታ በጣም የተሻለ ይሆናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከሞት የሚነሱት ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይችላሉ። በተጨማሪም ያን ጊዜ የሚኖረው ዓለም አሁን ከምንኖርበት ዓለም በጣም የተለየ ነው። ጦርነት፣ ወንጀልና ሕመም አይኖርም።

17. ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?

17 ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን ሰምተው ይወጣሉ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ራእይ 20:13 “ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና መቃብርም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ” ይላል። አዎ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዳግመኛ በሕይወት ይኖራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?

የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በገነት ውስጥ ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ዳግመኛ አብረው ይኖራሉ

18. ከሞት የሚነሱት “ጻድቃን” እነማን ናቸው?

18 “ጻድቃን” ከተባሉት መካከል ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይገኙበታል። እንደ  ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩትና አስቴር ያሉ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ተጠቅሰዋል። ይሁንና በዘመናችን ስለሞቱት የአምላክ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱም ቢሆኑ “ጻድቃን” ስለሆኑ ከሞት ይነሳሉ።

19. “ዓመፀኞች” የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋስ ምን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል?

 19 “ዓመፀኞች” የተባሉት ስለ ይሖዋ የመማር አጋጣሚ ያላገኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ ይሖዋ አይረሳቸውም። ከሞት ያስነሳቸዋል፤ በመሆኑም ስለ እሱ የመማርና እሱን የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ።

20. ትንሣኤ የሚያገኙት ሁሉም አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?

20 እንዲህ ሲባል ታዲያ የሞቱ ሰዎች ሁሉ ትንሣኤ ያገኛሉ ማለት ነው? በፍጹም። ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች ከሞት እንደማይነሱ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:5) አንድ ሰው ከሞት ይነሳል ወይስ አይነሳም የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው ማን ነው? የመጨረሻው ፈራጅ ይሖዋ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስን “በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ” ሾሞታል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42) ክፉ ተብሎ የተፈረደበትና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው ከሞት አይነሳም።—ተጨማሪ ሐሳብ 19⁠ን ተመልከት።

ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?

21, 22. (ሀ) ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ምን ዓይነት አካል ይኖራቸዋል? (ለ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ የሄደው ማን ነው?

21 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉም ይናገራል። ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ የሚሄድ ሰው ከሞት የሚነሳው የሰው አካል ይዞ አይደለም። ወደ ሰማይ የሚሄደው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ነው።

22 ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ያለውን ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 3:13) ኢየሱስ ከተገደለ ከሦስት ቀን በኋላ ይሖዋ ከሞት አስነስቶታል። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 13:34, 35) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው የሰው አካል ይዞ አልነበረም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ “ሥጋዊ አካል ለብሶ እያለ ተገደለ፤ ሆኖም መንፈሳዊ አካል ይዞ ሕያው ሆነ” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ነው!  (1 ቆሮንቶስ 15:3-6) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ትንሣኤ የሚያገኙ ሌሎች ሰዎችም እንዳሉ ይናገራል።

23, 24. ኢየሱስ “ትንሽ መንጋ” በማለት የጠራቸው እነማንን ነው? ቁጥራቸውስ ምን ያህል ነው?

23 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት፣ ታማኝ ለሆኑት ደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2) ስለዚህ ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል አንዳንዶቹ ትንሣኤ አግኝተው ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ይኖራሉ ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች “ትንሽ መንጋ” በማለት መጥራቱ ቁጥራቸው ጥቂት እንደሆነ ያመለክታል። (ሉቃስ 12:32) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስን በጽዮን ተራራ (በሰማይ) ላይ ቆሞ ባየው ጊዜ “ከእሱም ጋር . . . 144,000 ነበሩ” በማለት ቁጥራቸውን በቀጥታ ለይቶ ጠቅሷል።—ራእይ 14:1

24 ታዲያ 144,000ዎቹ ክርስቲያኖች ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? ይህ የሚሆነው ክርስቶስ በሰማይ መግዛት ከጀመረ በኋላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:23) በዛሬው ጊዜ የምንኖረው ክርስቶስ እየገዛ ባለበት ወቅት ላይ ሲሆን ከ144,000ዎቹ መካከል አብዛኞቹ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ሄደዋል። አሁን በምድር ላይ የሚገኙት ደግሞ ሲሞቱ ወዲያውኑ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ይሁን እንጂ በሞት ያንቀላፉ አብዛኞቹ ሰዎች ያላቸው ተስፋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ነው።

25. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንማራለን?

25 በቅርቡ ይሖዋ የሰው ልጆችን በሙሉ ከሞት እስራት ነፃ የሚያወጣቸው ከመሆኑም ሌላ ሞትን ለዘላለም ያስወግዳል! (ኢሳይያስ 25:8ን አንብብ።) ይሁንና ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች እዚያ ምን ያከናውናሉ? መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በተቋቋመው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር እንደሚገዙ ይናገራል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለዚህ መንግሥት እንማራለን።

^ አን.9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ታሪኮች ላይ ወጣቶችና አረጋውያን፣ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም እስራኤላውያንና የሌላ አገር ሰዎች ከሞት እንደተነሱ እናነባለን። እነዚህ ዘገባዎች በ1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:32-37፤ 13:20, 21፤ ማቴዎስ 28:5-7፤ ሉቃስ 7:11-17፤ 8:40-56፤ የሐዋርያት ሥራ 9:36-42፤ 20:7-12 ላይ ይገኛሉ።