በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ አሥራ ሰባት

ወደ አምላክ የመጸለይ ውድ መብት

ወደ አምላክ የመጸለይ ውድ መብት

“ሰማይንና ምድርን የሠራው” አምላክ ጸሎታችንን መስማት ይፈልጋል።—መዝሙር 115:15

1, 2. ጸሎት ልዩ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት ምን እንደሚል ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ምድራችን ከጽንፈ ዓለሙ ጋር ስትወዳደር በጣም ትንሽ ናት። በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች በሙሉ በይሖዋ ዓይን ሲታዩ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ትንሽ ጠብታ ውኃ ናቸው። (መዝሙር 115:15፤ ኢሳይያስ 40:15) ከጽንፈ ዓለም አንጻር ስንታይ በጣም ትንሽ ብንሆንም እንኳ መዝሙር 145:18, 19 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። የሚፈሩትን ሰዎች ፍላጎት ያረካል፤ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል።” እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! ሁሉን ቻይ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ፣ ወደ እኛ መቅረብ እንዲሁም ጸሎታችንን መስማት ይፈልጋል። በእርግጥም ጸሎት ትልቅ መብት ነው፤ ይሖዋ ለእያንዳንዳችን የሰጠን ልዩ ስጦታ ነው።

2 ይሁንና ይሖዋ ጸሎታችንን የሚሰማው እሱ በሚፈልገው መንገድ ከጸለይን ብቻ ነው። በዚህ መንገድ መጸለይ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸሎት ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።

ወደ ይሖዋ የምንጸልየው ለምንድን ነው?

3. ወደ ይሖዋ መጸለይ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ወደ እሱ እንድንጸልይ ወይም እንድናነጋግረው ይፈልጋል። ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እባክህ ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ። እስቲ በዚህ ጥቅስ ላይ ስለቀረበልን ግብዣ ቆም ብለህ አስብ። የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ለአንተ በጣም የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ የሚሰማህን ስሜት እንዲሁም ያጋጠመህን ችግር እንድትነግረው ይፈልጋል።

4. ወደ ይሖዋ አዘውትረህ መጸለይህ ከእሱ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚረዳህ እንዴት ነው?

4 ጸሎት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ይረዳናል።  ሁለት ጓደኛሞች ሐሳባቸውን፣ የሚያስጨንቃቸውን ነገር እንዲሁም ስሜታቸውን አንዳቸው ለሌላው አዘውትረው የሚገልጹ ከሆነ ጓደኝነታቸው እየጠነከረ ይሄዳል። ከይሖዋ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት አመለካከቱን፣ ስሜቱን እንዲሁም ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ይገልጽልሃል። አንተም አዘውትረህ ወደ እሱ በመጸለይ የውስጥ ስሜትህን ጭምር ልትነግረው ትችላለህ። እንዲህ ስታደርግ ከይሖዋ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል።—ያዕቆብ 4:8

አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

5. ይሖዋ የማይሰማቸው ጸሎቶች እንዳሉ እንዴት እናውቃለን?

5 ይሖዋ ሁሉንም ጸሎቶች ይሰማል? በፍጹም፤ የማይሰማቸው ጸሎቶችም አሉ። በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ እስራኤላውያንን “ጸሎት ብታበዙም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 1:15) በመሆኑም ካልተጠነቀቅን ይሖዋ የሚጠላውን ነገር ልናደርግ እንችላለን፤ እንዲህ ካደረግን ደግሞ ይሖዋ ጸሎታችንን አይሰማም።

6. እምነት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እምነት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

 6 ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን በእሱ ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል። (ማርቆስ 11:24) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና።” (ዕብራውያን 11:6) ሆኖም እምነት እንዳለን መናገር ብቻውን በቂ አይደለም። በየዕለቱ ይሖዋን በመታዘዝ እምነት እንዳለን ማሳየት ያስፈልገናል።—ያዕቆብ 2:26ን አንብብ።

7. (ሀ) ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ትሕትናና አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የምናቀርበው ጸሎት ከልባችን እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

7 ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ትሕትናና አክብሮት ልናሳይ ይገባል። ለምን? አንድን ንጉሥ ወይም ፕሬዚዳንት ስናነጋግር አክብሮት እንደምናሳይ የታወቀ ነው። ታዲያ ሁሉን ቻይ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ከዚህ የበለጠ አክብሮትና ትሕትና ማሳየት አይኖርብንም? (ዘፍጥረት 17:1፤ መዝሙር 138:6) በተጨማሪም ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ተመሳሳይ ቃላት መደጋገም የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ የውስጥ ስሜታችንን አውጥተን በመግለጽ ከልብ መጸለይ ይኖርብናል።—ማቴዎስ 6:7, 8

8. አንድን ጉዳይ በተመለከተ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 ከዚህም ሌላ ስለ አንድ ነገር በምንጸልይበት ጊዜ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ የተቻለንን ያህል ጥረት ማድረግ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ነገር እንዲሰጠን ከጸለይን በኋላ ‘ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ ያሟላልኛል’ ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም። ከዚህ ይልቅ መሥራት የምንችልበት አቅም እስካለን ድረስ ማንኛውንም ሥራ ሳንመርጥ ጠንክረን ለመሥራት ፈቃደኞች መሆን አለብን። (ማቴዎስ 6:11፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10) ወይም ደግሞ መጥፎ ነገር መሥራታችንን እንድናቆም እንዲረዳን ወደ ይሖዋ ከጸለይን ለፈተና ሊያጋልጡን ከሚችሉ ሁኔታዎች በሙሉ መራቅ አለብን። (ቆላስይስ 3:5) ከዚህ በመቀጠል፣ ጸሎትን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን እስቲ እንመልከት።

 ጸሎትን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች

9. መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው? ዮሐንስ 14:6 ስለ ጸሎት ምን ያስተምረናል?

9 መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹን ‘በሰማያት ወደሚኖረው አባታችን’ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:6) በመሆኑም መጸለይ ያለብን ወደ ይሖዋ ብቻ ሲሆን ይህንንም የምናደርገው በኢየሱስ በኩል መሆን አለበት። በኢየሱስ በኩል መጸለይ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ ለኢየሱስ ለሰጠው ልዩ ቦታ አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል ማለት ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 5:12) ይሖዋ፣ ኢየሱስን ሊቀ ካህናትና ፈራጅ አድርጎም ሾሞታል።—ዮሐንስ 5:22፤ ዕብራውያን 6:20

በማንኛውም ጊዜ መጸለይ ትችላለህ

10. መጸለይ ያለብን እንዴት ሆነን ነው? አብራራ።

10 መጸለይ ያለብን እንዴት ሆነን ነው? ይሖዋ ተንበርክከን፣ ተቀምጠን ወይም ቆመን እንድንጸልይ የሚያዝ መመሪያ አልሰጠም። ለይሖዋ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ እስከሆነ ድረስ እንዴትም ሆነን ብንጸልይ ለውጥ እንደማያመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያሳያሉ። (1 ዜና መዋዕል 17:16፤ ነህምያ 8:6፤ ዳንኤል 6:10፤ ማርቆስ 11:25) በይሖዋ ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ተንበርክከን ወይም ቆመን መጸለያችን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በአክብሮትና ከልብ በመነጨ ስሜት መጸለያችን ነው። ቀንም ሆነ ሌሊት በማንኛውም ቦታና ሰዓት ጮክ ብለንም ሆነ ድምፅ ሳናሰማ መጸለይ እንችላለን። ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ሰው ባይሰማንም እንኳ ይሖዋ እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ነህምያ 2:1-6

11. ስለ ምን ነገሮች መጸለይ እንችላለን?

11 ስለ ምን ነገሮች መጸለይ እንችላለን? ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ስለ ማንኛውም ነገር መጸለይ እንችላለን።  መጽሐፍ ቅዱስ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:14) ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ እንችላለን? አዎ። ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ከቅርብ ጓደኛችን ጋር የምናወራ ያህል ሆኖ ሊሰማን ይገባል። በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ አውጥተን ለይሖዋ ልንነግረው እንችላለን። (መዝሙር 62:8) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንድንችል ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። (ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ የምንችልበት ጥበብ እንዲሁም ከባድ ሁኔታዎችን መቋቋም የምንችልበት ጥንካሬ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን። (ያዕቆብ 1:5) ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለንም መጸለይ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 1:3, 7) ከዚህም ሌላ ቤተሰቦቻችንን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጨምሮ ለሌሎች መጸለይ አለብን።—የሐዋርያት ሥራ 12:5፤ ቆላስይስ 4:12

12. በጸሎታችን ውስጥ ልንጠቅሳቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?

12 በጸሎታችን ውስጥ ልንጠቅሳቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? ከይሖዋና ከእሱ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። ስላደረገልን ነገሮች በሙሉ ይሖዋን ከልብ ልናመሰግነው ይገባል። (1 ዜና መዋዕል 29:10-13) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ጸሎት ይህን ግልጽ ያደርግልናል። (ማቴዎስ 6:9-13ን አንብብ።) ኢየሱስ በቅድሚያ የአምላክ ስም እንዲቀደስ መጸለይ እንዳለብን አስተምሯል። በመቀጠልም የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና የይሖዋ ፈቃድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲፈጸም መጸለይ እንዳለብን ተናግሯል። ኢየሱስ ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ ያለብን በጣም አስፈላጊ ስለሆኑት ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከጸለይን በኋላ መሆን እንዳለበት አስተምሯል። በጸሎታችን ውስጥ ለይሖዋና ከእሱ ፈቃድ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበን ይህ እንደሆነ እናሳያለን።

13. የጸሎታችን ርዝመት ምን ያህል መሆን አለበት?

 13 የጸሎታችን ርዝመት ምን ያህል መሆን አለበት? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ አይናገርም። ጸሎታችን እንደ ሁኔታው አጭር ወይም ረጅም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ከመመገባችን በፊት አጠር ያለ ጸሎት እናቀርብ ይሆናል፤ ይሖዋን ስናመሰግን ወይም ያስጨነቀንን ነገር ለእሱ ስንነግረው ደግሞ ጸሎታችንን ረዘም ልናደርገው እንችላለን። (1 ሳሙኤል 1:12, 15) በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት አንዳንድ ሰዎች፣ ሌሎች እንዲያደንቁን ብለን ብቻ ረጃጅም  ጸሎቶችን ማቅረብ የለብንም። (ሉቃስ 20:46, 47) እንዲህ ያሉ ጸሎቶች ይሖዋን አያስደስቱትም። ይሖዋን የሚያስደስተው ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን ነው።

14. መጸለይ ያለብን ምን ያህል ጊዜ ነው? ይህስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

14 መጸለይ ያለብን ምን ያህል ጊዜ ነው? ይሖዋ፣ አዘውትረን እንድናነጋግረው ግብዣ አቅርቦልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሳታሰልሱ ጸልዩ፣’ “ሳትታክቱ ጸልዩ” እንዲሁም “ዘወትር ጸልዩ” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ማቴዎስ 26:41፤ ሮም 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ ምንጊዜም ጸሎታችንን ለመስማት ዝግጁ ነው። ላሳየን ፍቅርና ደግነት በየቀኑ ልናመሰግነው እንችላለን። መመሪያ፣ ጥንካሬና ማጽናኛ እንዲሰጠንም ልንጠይቀው እንችላለን። ወደ ይሖዋ የመጸለይ መብታችንን ከፍ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እሱን እናነጋግረዋለን።

15. ስንጸልይ መጨረሻ ላይ “አሜን” ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

 15 ስንጸልይ መጨረሻ ላይ “አሜን” ማለት ያለብን ለምንድን ነው? “አሜን” የሚለው ቃል “ይሁን” የሚል ትርጉም አለው። “አሜን” ስንል በጸሎቱ ውስጥ የተጠቀሰውን ሐሳብ እንደምናምንበት ማለትም የጸለይነው ከልባችን እንደሆነ መግለጻችን ነው። (መዝሙር 41:13) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው፣ ሌላም ሰው ጸሎት ሲያቀርብ መጨረሻ ላይ ጮክ ብለንም ሆነ ድምፃችንን ሳናሰማ “አሜን” ማለታችን በጸሎቱ መስማማታችንን ያሳያል።—1 ዜና መዋዕል 16:36፤ 1 ቆሮንቶስ 14:16

አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?

16. ይሖዋ በእርግጥ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል? አብራራ።

16 ይሖዋ በእርግጥ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል? አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጸሎት የሚሰማ ከመሆኑም ሌላ ለጸሎታቸው መልስ ይሰጣል፤ መልስ የሚሰጠው ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ነው።

17. ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት መላእክትን ወይም ምድር ላይ የሚኖሩ አገልጋዮቹን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

17 ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት በመላእክትና ምድር ላይ ባሉ አገልጋዮቹ ይጠቀማል። (ዕብራውያን 1:13, 14) ይህን የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፤ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንዲችሉ አምላክ እንዲረዳቸው ከጸለዩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው አነጋግረዋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ያጋጠማቸው ሁኔታ፣ መላእክት ‘ምሥራቹ’ በመላው ዓለም እንዲሰበክ የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ እንዳለ ያሳያል። (ራእይ 14:6ን አንብብ።) በተጨማሪም ብዙዎቻችን አንድን ችግር ወይም የሚያስፈልገንን ነገር በተመለከተ ከጸለይን በኋላ ይሖዋ በአንድ ክርስቲያን ወንድም ወይም እህት ተጠቅሞ የሚያስፈልገንን እርዳታ እንድናገኝ ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ።—ምሳሌ 12:25፤ ያዕቆብ 2:16

ይሖዋ ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲረዱን በማድረግ ለጸሎታችን መልስ ሊሰጥ ይችላል

18. ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት ቅዱስ መንፈሱንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

 18 ከዚህም ሌላ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል። አንድን ችግር ለመቋቋም እንዲረዳን ወደ ይሖዋ ስንጸልይ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት መመሪያና ጥንካሬ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎች እንድናደርግ ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀማል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ጠቃሚ ጥቅሶችን ልናገኝ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ አንድ ሰው በጉባኤ ላይ እኛን የሚጠቅም ሐሳብ እንዲሰጥ ሊያነሳሳው ይችላል፤ ወይም አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥሩ ምክር እንዲሰጠን ሊያደርግ ይችላል።—ገላትያ 6:1

19. አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ እንዳልሰጠን የሚሰማን ለምን ሊሆን ይችላል?

19 ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ‘ይሖዋ እስካሁን ድረስ ለጸሎቴ መልስ ያልሰጠኝ ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጥበትን ትክክለኛ ጊዜና መንገድ እንደሚያውቅ አስታውስ። እሱ ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ሆኖም እኛ አንድን ነገር በጣም እንደምንፈልገው እንዲሁም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለን ለማሳየት በተደጋጋሚ መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። (ሉቃስ 11:5-10) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን ባልጠበቅነው መንገድ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንጸልይ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ መቋቋም የምንችልበት ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።

20. ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለያችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

20 በእርግጥም ጸሎት ትልቅ መብት ነው! ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 145:18) አዘውትረን ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ደግሞ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየጠነከረ ይሄዳል።