በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?

 ምዕራፍ አሥራ ስድስት

አምላክን በትክክለኛው መንገድ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ

አምላክን በትክክለኛው መንገድ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ

1, 2. ራስህን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብሃል? እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በርካታ ሰዎች አምላክን እንደሚያመልኩ ቢናገሩም የሚያስተምሩትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር አምላክን ደስ እንደማያሰኝ ተምረሃል። (2 ቆሮንቶስ 6:17) ይሖዋ ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ማለትም ከሐሰት ሃይማኖት እንድንወጣ ያዘዘን በዚህ ምክንያት ነው። (ራእይ 18:2, 4) ታዲያ ምን ለማድረግ አስበሃል? እያንዳንዳችን የግላችንን ውሳኔ ማድረግ እንችላለን፤ በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘አምላክን ማምለክ የምፈልገው እሱ በሚፈልገው መንገድ ነው? ወይስ እኔ በለመድኩት መንገድ?’

2 አስቀድመህ ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተህ ወይም ራስህን ከአባልነት አሰርዘህ ከሆነ ጥሩ እርምጃ ወስደሃል ማለት ነው። ይሁንና እስካሁን ያላስወገድካቸው ሥር የሰደዱና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር የተያያዙ ልማዶች ይኖሩህ ይሆናል። ከእነዚህ ልማዶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት፤ ከዚያም እነዚህን ልማዶች በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምና ወደ ሞቱ ሰዎች መጸለይ

3. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ምስሎችን ሳይጠቀሙ አምላክን ማምለክ ከባድ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን አስመልክቶ ምን ይላል?

3 አንዳንድ ሰዎች፣ በቤታቸው ውስጥ ለብዙ ዓመታት ለአምልኮ ሲጠቀሙባቸው የኖሩ ምስሎች ወይም የጸሎት ቦታዎች አሏቸው። አንተም እንዲህ ታደርግ ከነበረ ከለመድከው በተለየ መንገድ አምላክን ማምለክ ከባድ ሊሆንብህ ወይም ስህተት እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም እሱን እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ የሚያስተምረን ይሖዋ መሆኑን  አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይሖዋ ምስሎችን ተጠቅመን እንድናመልከው እንደማይፈልግ በግልጽ ይናገራል።—ዘፀአት 20:4, 5ን አንብብ፤ መዝሙር 115:4-8፤ ኢሳይያስ 42:8፤ 1 ዮሐንስ 5:21

4. (ሀ) ወደ ሞቱ ዘመዶቻችን መጸለይ የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሕዝቡን ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እንዳይሞክሩ ያዘዛቸው ለምንድን ነው?

4 አንዳንድ ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ያጠፋሉ። እንዲያውም የሞቱ ዘመዶቻቸውን እስከ ማምለክ ሊደርሱ ይችላሉ። ይሁንና የሞቱ ሰዎች ሊረዱንም ሆነ ሊጎዱን እንደማይችሉ ተመልክተናል። እነዚህ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሌላ ስፍራ እንደሚኖሩ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው። ከእነሱ ጋር ለመገናኘት መሞከር አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም ከሞቱ ዘመዶቻችን እንደመጣ አድርገን የምናስበው ማንኛውም መልእክት የሚመጣው ከአጋንንት ነው። በመሆኑም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እንዳይሞክሩ እንዲሁም ከማንኛውም አጋንንታዊ ድርጊት እንዲርቁ አዟቸው ነበር።—ዘዳግም 18:10-12ተጨማሪ ሐሳብ 26 እና 31⁠ን ተመልከት።

5. ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምህን ወይም ወደ ሞቱ ሰዎች መጸለይህን እንድታቆም ምን ሊረዳህ ይችላል?

5 ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምህን ወይም ወደ ሞቱ ሰዎች መጸለይህን እንድታቆም ምን ሊረዳህ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲሁም ይሖዋ ለእነዚህ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልግሃል። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ይሖዋ ‘ይጸየፋል’ ወይም ይጠላል። (ዘዳግም 27:15) ይሖዋ፣ የእሱ ዓይነት አመለካከት እንዲኖርህና እሱን በሚያስደስት መንገድ እንድታመልከው እንዲረዳህ በየዕለቱ ጸልይ። (ኢሳይያስ 55:9) ይሖዋ፣ ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገድ እንድትችል እንደሚረዳህ እርግጠኛ ሁን።

ገናን ማክበር ይኖርብናል?

6. ታኅሣሥ 25 የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ቀን እንዲሆን የተመረጠው ለምንድን ነው?

6 በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ በጣም ተወዳጅ የሆኑ በዓላት መካከል አንዱ የገና በዓል ሲሆን በርካታ ሰዎች ይህ በዓል የክርስቶስ ልደት  የሚከበርበት ቀን እንደሆነ ያስባሉ። ይሁን እንጂ ገና ከሐሰት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው በዓል ነው። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ሮማውያን ጣዖት አምላኪዎች ታኅሣሥ 25 ላይ የፀሐይን ልደት ያከብሩ እንደነበር ይገልጻል። የሃይማኖት መሪዎች፣ ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 እንዳልሆነ ቢያውቁም በርካታ ጣዖት አምላኪዎች ክርስትናን እንዲቀበሉ ለማድረግ ሲሉ የኢየሱስን ልደት በዚያ ዕለት ለማክበር ወሰኑ። * (ሉቃስ 2:8-12) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የገና በዓልን አያከብሩም ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ በነበሩት 200 ዓመታት ኢየሱስ “መቼ እንደተወለደ የሚያውቅ ሰው አልነበረም፤ ይህን ለማወቅ ይፈልጉ የነበሩ ሰዎችም እምብዛም አልነበሩም” በማለት ይናገራል። (ሴክረድ ኦሪጅንስ ኦቭ ፕሮፋውንድ ቲንግስ) ሰዎች የገና በዓልን ማክበር የጀመሩት ኢየሱስ ከተወለደ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ ነው።

7. እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

7 ብዙ ሰዎች የገና በዓል እንዲሁም እንደመገባበዝና ስጦታ እንደመለዋወጥ ያሉ ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ልማዶች ከጣዖት አምልኮ ሥርዓቶች የተወሰዱ እንደሆኑ ያውቃሉ። ለምሳሌ በእንግሊዝና በአሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የገና በዓል ከጣዖት አምልኮ የመጣ እንደሆነ ስለታመነ በአንድ ወቅት ይህን በዓል ማክበር ተከልክሎ ነበር። የገና በዓልን የሚያከብር ሰው ይቀጣ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሰዎች በድጋሚ ገናን ማክበር ጀመሩ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው? የሚያደርጉት ነገር ሁሉ አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን ስለሚፈልጉ ነው።

ልደት ማክበር ይኖርብናል?

8, 9. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ልደት የማያከብሩት ለምን ነበር?

8 በርካታ ሰዎች የሚያከብሩት ሌላው በዓል ደግሞ ልደት ነው። ክርስቲያኖች ልደት ሊያከብሩ ይገባል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልደታቸውን እንዳከበሩ የተነገረላቸው ሰዎች ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች  ናቸው። (ዘፍጥረት 40:20፤ ማርቆስ 6:21) የልደት በዓላት ይከበሩ የነበረው የሐሰት አማልክትን ከፍ ከፍ ለማድረግ ነው። በመሆኑም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “የማንኛውንም ሰው የልደት በዓል ማክበር የአረማውያን ልማድ እንደሆነ ያምኑ ነበር።”—ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ

9 የጥንቶቹ ሮማውያንና ግሪካውያን፣ አንድ ሰው የሚወለድበት ቀን ከአንድ አምላክ የልደት ቀን ጋር እንደሚገጣጠም ያምኑ ነበር። ‘ግለሰቡ ሲወለድ ከዚህ አምላክ ጋር ግንኙነት ያላት መንፈስ’ በቦታው ትገኛለች ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ‘ይህች መንፈስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለግለሰቡ ጥበቃ እንድታደርግለት’ ልደቱን ማክበር አለበት የሚል አመለካከት ነበራቸው።—ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ

10. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ልደት የማያከብሩት ለምንድን ነው?

10 ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያላቸው በዓላት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያላቸው ይመስልሃል? በፍጹም! (ኢሳይያስ 65:11, 12) በመሆኑም ልደትን ጨምሮ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውም በዓል አናከብርም

የበዓላት አመጣጥ ሊያሳስበን ይገባል?

11. አንዳንድ ሰዎች በዓል የሚያከብሩት ለምንድን ነው? ከሁሉ በላይ ሊያሳስብህ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

11 አንዳንድ ሰዎች ገናን ጨምሮ ሌሎች በርካታ በዓላት የመጡት ከጣዖት አምልኮ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሆኖም እነዚህን በዓላት ማክበራቸውን አላቆሙም። የበዓል ወቅት፣ ከቤተሰባቸው ጋር አብረው ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተም እንደዚህ ይሰማሃል? ከቤተሰብህ ጋር አብረህ ጊዜ ለማሳለፍ መፈለግህ ስህተት አይደለም። ይሖዋ፣ የቤተሰብ መሥራች እንደመሆኑ መጠን ከቤተሰባችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ይፈልጋል። (ኤፌሶን 3:14, 15) ይሁንና ከቤተሰባችን ጋር የሐሰት ሃይማኖት በዓላትን በማክበር እነሱን ከማስደሰት ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም “በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ” የሚል ምክር የሰጠው ለዚህ ነው።—ኤፌሶን 5:10

12. የትኞቹ በዓላት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት የላቸውም?

 12 በርካታ ሰዎች የአንድ በዓል አመጣጥ ሊያሳስበን እንደማይገባ ይሰማቸዋል፤ ይሖዋ ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት አለው። ከሐሰት አምልኮ የመጡ በዓላት አሊያም ሰዎችን ወይም ብሔራዊ አርማዎችን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ክብረ በዓላት በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ ግብፃውያን ለሐሰት አማልክታቸው ክብር ሲሉ የሚያከብሯቸው በርካታ በዓላት ነበሯቸው። እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ግብፃውያን የሚያከብሩትን አንድ በዓል በመኮረጅ ያከበሩ ሲሆን በዓሉንም “ለይሖዋ የሚከበር በዓል” ብለው ጠርተውት ነበር። ይሖዋ ይህን በማድረጋቸው እስራኤላውያንን ቀጥቷቸዋል። (ዘፀአት 32:2-10) እኛም ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ‘ማንኛውንም ርኩስ ነገር መንካት’ የለብንም።—ኢሳይያስ 52:11ን አንብብ።

የምታምንበትን ነገር ለሌሎች በአክብሮት አስረዳ

13. በዓላትን ማክበርህን ለማቆም ስትወስን የትኞቹ ጥያቄዎች ወደ አእምሮህ ሊመጡ ይችላሉ?

13 በዓላትን ማክበርህን ለማቆም ስትወስን ብዙ ጥያቄዎች ወደ አእምሮህ ሊመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል እንዲህ እያልክ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል፦ የሥራ ባልደረቦቼ ገናን አብሬአቸው የማላከብረው ለምን እንደሆነ ቢጠይቁኝ ምን ብዬ እመልስላቸዋለሁ? አንድ ሰው የገና ስጦታ ቢሰጠኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? የትዳር ጓደኛዬ አብሬያት በዓል እንዳከብር ብትፈልግ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? ልጆቼ ልደት ወይም በዓል ባለማክበራቸው የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንዳይሰማቸው ምን ማድረግ እችላለሁ?

14, 15. ሰዎች “እንኳን አደረሰህ” ቢሉህ ወይም ስጦታ ቢሰጡህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

14 የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቅመህ መልስ መስጠትህ ወይም እርምጃ መውሰድህ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ሰዎች “እንኳን አደረሰህ” ቢሉህ ችላ ብለሃቸው ከማለፍ ይልቅ “አመሰግናለሁ” ልትላቸው ትችላለህ። በዓሉን የማታከብርበትን ምክንያት ማወቅ ከፈለጉ ግን ልታስረዳቸው ትችላለህ። ይሁንና የምታምንበትን  ነገር የምታስረዳው በትሕትና፣ በዘዴና በአክብሮት ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን” ይላል። (ቆላስይስ 4:6) ከሌሎች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍና ስጦታ መስጠት እንደሚያስደስትህ ልትገልጽላቸው ትችላለህ፤ ሆኖም ከበዓላት ጋር በተያያዘ እንዲህ ማድረግ እንደማትፈልግ ልትነግራቸው ትችላለህ።

15 አንድ ሰው ስጦታ ቢሰጥህስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ሁኔታ ዝርዝር መመሪያ ባይሰጥም ጥሩ ሕሊና ሊኖረን እንደሚገባ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19) ምናልባት ስጦታውን የሰጠህ ሰው በዓል እንደማታከብር አያውቅ ይሆናል። ወይም ደግሞ “በዓሉን እንደማታከብር አውቃለሁ፤ እንዲሁ ስጦታ ልሰጥህ ስለፈለግኩ ነው” ሊልህ ይችላል። በሁለቱም ሁኔታዎች፣ ስጦታውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ልትወስን ትችላለህ። ያም ሆነ ይህ የምታደርገው ውሳኔ ሕሊናህ እንዲወቅስህ የሚያደርግ ሊሆን አይገባም። ማናችንም ብንሆን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም።

ቤተሰቦችህን በተመለከተስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው

16. ቤተሰቦችህ በዓል ማክበር የሚፈልጉ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

16 ቤተሰቦችህ በዓል ማክበር ቢፈልጉ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ከእነሱ ጋር መጣላት አይኖርብህም። ቤተሰቦችህ ማድረግ የሚፈልጉትን ነገር የመምረጥ መብት እንዳላቸው አስታውስ። አሳቢነት ልታሳያቸው ይገባል፤ ቤተሰቦችህ ውሳኔህን እንዲያከብሩልህ እንደምትፈልግ ሁሉ አንተም የእነሱን ውሳኔ አክብርላቸው። (ማቴዎስ 7:12ን አንብብ።) ይሁንና ቤተሰቦችህ በበዓሉ ወቅት አብረሃቸው ጊዜ እንድታሳልፍ ቢፈልጉስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ምን ማድረግ እንዳለብህ ከመወሰንህ በፊት ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ስለ ሁኔታው አስቀድመህ ለማሰብ እንዲሁም ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርግ። ምንጊዜም ቢሆን ፍላጎትህ ይሖዋን ማስደሰት ሊሆን ይገባል።

17. ልጆችህ በዓል የሚያከብሩ ሰዎችን ሲያዩ የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንዳይሰማቸው ምን ማድረግ ትችላለህ?

 17 ልጆችህ፣ በዓል የሚያከብሩ ሰዎችን ሲያዩ የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንዳይሰማቸው መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? አልፎ አልፎ ለየት ያለ ነገር ልታደርግላቸው ወይም ስጦታ ልትሰጣቸው ትችላለህ። ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍህና ፍቅርህን መግለጽህ ግን ከሁሉ የላቀ ስጦታ እንደሆነ አትርሳ።

እውነተኛውን ሃይማኖት ተከተል

18. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

18 ይሖዋን ደስ ለማሰኘት የሐሰት ሃይማኖትን እንዲሁም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ያላቸውን ልማዶችና በዓላት መተው ይኖርብናል። ይህ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፤ እውነተኛውን ሃይማኖት መከተልም ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ናቸው። (መዝሙር 22:22፤ 122:1) ከሌሎች ጋር አብረን በመሰብሰብ አንዳችን ሌላውን ማበረታታት እንችላለን።—ሮም 1:12

19. ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርካቸውን እውነቶች ለሌሎች መንገርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 እውነተኛውን አምልኮ እንደመረጥክ የምታሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከውን ለሌሎች መናገር ነው። በርካታ ሰዎች በዓለም ላይ የሚፈጸሙት መጥፎ ነገሮች ያስጨንቋቸዋል። አንተም እንዲህ የሚሰማቸው ሰዎች ታውቅ ይሆናል። አምላክ የሰጠንን አስደሳች ተስፋ ለእነዚህ ሰዎች ልትነግራቸው ትችላለህ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለሌሎች ስትናገር የሐሰት ሃይማኖትንና ልማዶቹን የመከተል ፍላጎትህ እየጠፋ ይሄዳል። ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ለማምለክ መምረጥህ ደስታና የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝልህ እርግጠኛ ሁን።—ሚልክያስ 3:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አንዳንድ አገሮች የገና በዓል የሚከበረው ጥር 7 (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ነው።