1, 2. (ሀ) አንድን ስጦታ በጣም እንድትወደው የሚያደርግህ ምንድን ነው? (ለ) ቤዛው አምላክ ከሰጠን ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

እስከ ዛሬ ከተሰጡህ ስጦታዎች መካከል ከሁሉ አስበልጠህ የምትወደው የትኛውን ነው? አንድን ስጦታ በጣም እንድትወደው የሚያደርግህ ብዙ ገንዘብ የወጣበት መሆኑ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው በጣም የምትፈልገውን ነገር በስጦታ መልክ ቢሰጥህ እጅግ እንደምትደሰትና ስጦታውን ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተው ጥርጥር የለውም።

2 አምላክ ከሰጠን ስጦታዎች መካከል ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ አንድ ስጦታ አለ። ይህ ስጦታ አምላክ ለሰዎች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር እንደላከው እንማራለን። (ማቴዎስ 20:28ን አንብብ።) ይሖዋ ኢየሱስን ቤዛ እንዲሆን ወደ ምድር መላኩ በጣም እንደሚወደን ያሳያል።

ቤዛው ምንድን ነው?

3. ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?

3 ቤዛው፣ ይሖዋ ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ያደረገው ዝግጅት ነው። (ኤፌሶን 1:7) ቤዛው ያስፈለገበትን ምክንያት ለመረዳት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት የተከናወነውን ነገር ማወቅ ያስፈልገናል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሠሩ። በዚህም የተነሳ ሞቱ። እኛም ከአዳምና ከሔዋን ኃጢአት ስለወረስን እንሞታለን።—ተጨማሪ ሐሳብ 9⁠ን ተመልከት።

4. አዳም ማን ነው? ይሖዋ ምን ነገሮችን ሰጥቶት ነበር?

 4 ይሖዋ በመጀመሪያ የፈጠረው ሰው አዳም ሲሆን በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ሰጥቶት ነበር። አዳም ፍጹም ሕይወት ነበረው። ፍጹም አእምሮና ፍጹም አካል ነበረው። አይታመምም፣ አያረጅም እንዲሁም አይሞትም ነበር። ይሖዋ አዳምን ስለፈጠረው ለእሱ ልክ እንደ አባቱ ነው። (ሉቃስ 3:38) ይሖዋ አዳምን ሁልጊዜ ያነጋግረው ነበር። አምላክ፣ ለአዳም ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን ነገር በግልጽ የነገረው ከመሆኑም ሌላ አስደሳች ሥራ ሰጥቶት ነበር።—ዘፍጥረት 1:28-30፤ 2:16, 17

5. መጽሐፍ ቅዱስ አዳም “በአምላክ መልክ” እንደተፈጠረ ሲናገር ምን ማለቱ ነው?

5 አዳም የተፈጠረው “በአምላክ መልክ” ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይሖዋ እንደ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ኃይል ያሉ ባሕርያት አሉት፤ አዳምን ሲፈጥረውም እነዚህን ባሕርያት ስለሰጠው በእሱ መልክ ፈጥሮታል ሊባል ይችላል። በተጨማሪም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶታል። አዳም ሮቦት ወይም ማሽን አልነበረም። አምላክ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር መምረጥ እንዲችል አድርጎ ፈጥሮታል። አዳም አምላክን ለመታዘዝ ቢመርጥ ኖሮ በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖር ነበር።

6. አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ምን ነገሮችን አጥቷል? ይህስ በእኛ ላይ ምን አስከትሏል?

6 አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ምክንያት ሞት በተፈረደበት ጊዜ በጣም ውድ የሆኑ ነገሮችን አጥቷል። ከይሖዋ ጋር የነበረውን ወዳጅነት፣ ፍጹም ሕይወቱን እንዲሁም በገነት የመኖር መብቱን አጥቷል። (ዘፍጥረት 3:17-19) አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ሆን ብለው ስለጣሱ ምንም ተስፋ የላቸውም። በአዳም ምክንያት “ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ራሱንም ሆነ እኛን ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ‘ሸጧል።’ (ሮም 7:14) ታዲያ ምንም ተስፋ የለንም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም።

7, 8. ቤዛ ምንድን ነው?

 7 ቤዛ ምንድን ነው? ቤዛ የሚለው ቃል በዋነኝነት ሁለት ነገሮችን ያመለክታል። አንደኛ፣ አንድን ሰው ለማስለቀቅ ወይም አንድን ነገር መልሶ ለመግዛት የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። ሁለተኛ ደግሞ አንድን ጉዳት ለማካካስ የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል።

8 አዳም፣ ኃጢአት በመሥራትና ሞትን በሰዎች ላይ በማምጣት ላደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ካሳ ሊከፍል የሚችል ሰው የለም። ይሁንና ይሖዋ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ዝግጅት አድርጓል። ቤዛው ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚያወጣን እንዴት እንደሆነና ከቤዛው ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

9. ምን ዓይነት ቤዛ ያስፈልግ ነበር?

9 ማናችንም ብንሆን አዳም ላጣው ፍጹም ሕይወት ቤዛ መክፈል አንችልም። ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም ፍጹም አይደለንም። (መዝሙር 49:7, 8) ቤዛ ሆኖ መከፈል ያለበት ሌላ ፍጹም ሕይወት ነው። “ተመጣጣኝ ቤዛ” የተባለውም ለዚህ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) ቤዛው አዳም ካጣው ሕይወት ጋር እኩል ዋጋ ሊኖረው ይገባል።

10. ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው? በጣም የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር በመላክ ነው። ይህ ልጅ ማለትም ኢየሱስ የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት ነው። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ኢየሱስ አባቱንና በሰማይ ያለውን መኖሪያውን ትቶ ለመምጣት ፈቃደኛ ሆኗል። (ፊልጵስዩስ 2:7) ይሖዋ፣ የኢየሱስ ሕይወት ከሰማይ ወደ ምድር እንዲዛወር አደረገ፤ በመሆኑም ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ።—ሉቃስ 1:35

ይሖዋ በጣም የሚወደውን ልጁን ለእኛ ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል

11. አንድ ሰው ለሁሉም ሰው ቤዛ ሊከፍል የቻለው እንዴት ነው?

11 የመጀመሪያው ሰው አዳም አምላክን ባለመታዘዙ የሰው ልጆች  በሙሉ ፍጹም የሆነ ሕይወት አጥተዋል። ታዲያ የአዳምን ልጆች በሙሉ ከሞት ባርነት ነፃ ሊያወጣ የሚችል ሌላ ሰው አለ? አዎ አለ። (ሮም 5:19ን አንብብ።) ኃጢአት ሠርቶ የማያውቀው ኢየሱስ፣ ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ይህን ቤዛ በመክፈል የአዳም ልጆች በሙሉ ከሞት ባርነት ነፃ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ከፍቷል።—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22

12. ኢየሱስ ይህ ሁሉ ሥቃይ የደረሰበት ለምንድን ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከባድ ሥቃይ እንደደረሰበት ይገልጻል። ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተገርፏል፤ ከዚያም በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሠቃይ ከቆየ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። (ዮሐንስ 19:1, 16-18, 30) ኢየሱስ ይህ ሁሉ ሥቃይ የደረሰበት ለምንድን ነው? ሰይጣን፣ ማንም ሰው ከባድ ፈተና ቢደርስበት ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆን ስለተናገረ ነው። ኢየሱስ፣ አንድ ፍጹም ሰው ከባድ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ ለአምላክ ታማኝ ሊሆን እንደሚችል በሚገባ አሳይቷል። ኢየሱስ በታማኝነት መጽናቱ ይሖዋን ምን ያህል አስደስቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ!—ምሳሌ 27:11ተጨማሪ ሐሳብ 15⁠ን ተመልከት።

13. ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው?

13 ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት በ33 ዓ.ም. ኒሳን 14 ቀን፣ ኢየሱስ በጠላቶቹ እንዲገደል ፈቀደ። (ዕብራውያን 10:10) ከሦስት ቀን በኋላ ይሖዋ ኢየሱስን ሰው ሆኖ ሳይሆን፣ መንፈስ ሆኖ ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖር አደረገ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመለስ ለአዳም ዘሮች ቤዛ አድርጎ የሰጠውን የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ በአምላክ ፊት አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:24) በዚህ ሁኔታ ቤዛው በመከፈሉ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የምንሆንበት መንገድ ተከፍቶልናል።—ሮም 3:23, 24ን አንብብ።

 ከቤዛው ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

14, 15. ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 ከሁሉ የላቀው የአምላክ ስጦታ ማለትም ቤዛው አሁንም ቢሆን እየጠቀመን ነው። በዛሬው ጊዜም ሆነ ወደፊት ከቤዛው ምን ጥቅም እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

15 ኃጢአታችን ይቅር ይባልልናል። ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ቀላል አይደለም። ሁላችንም ስህተት እንሠራለን፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር የምንናገርበትና የምናደርግበት ጊዜ አለ። (ቆላስይስ 1:13, 14) ታዲያ ኃጢአታችን ይቅር ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ስህተት ስንሠራ ከልብ ማዘን እንዲሁም ይሖዋ ይቅር እንዲለን በትሕትና መጠየቅ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ዮሐንስ 1:8, 9

16. ጥሩ ሕሊና እንዲኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ጥሩ ሕሊና ይኖረናል። ሕሊናችን ስህተት እንደሠራን በሚነግረን ጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን እንዲሁም ተስፋ ልንቆርጥና ምንም ዋጋ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከለመንን፣ ጸሎታችንን እንደሚሰማና ኃጢአታችንን ይቅር እንደሚል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዕብራውያን 9:13, 14) ይሖዋ፣ የሚያጋጥመንን ችግር ሁሉ እንዲሁም ያለብንን ድክመት እንድንነግረው ይፈልጋል። (ዕብራውያን 4:14-16) እንዲህ ማድረጋችን በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና እንዲኖረን ያስችለናል።

17. ኢየሱስ ለእኛ ሲል መሞቱ ምን በረከት ያስገኝልናል?

17 ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን። “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮም 6:23) ኢየሱስ ለእኛ ሲል ስለ ሞተ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለን፤ እንዲሁም የተሟላ ጤንነት  ይኖረናል። (ራእይ 21:3, 4) ይሁንና ይህን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ለቤዛው አድናቆት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

18. ይሖዋ እንደሚወደን ያሳየው እንዴት ነው?

18 አንድ ሰው በጣም የምትወደውን ነገር ስጦታ አድርጎ ቢሰጥህ ምን ያህል እንደምትደሰት እስቲ አስበው! ቤዛው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው፤ በመሆኑም ይሖዋን ከልብ ልናመሰግነው ይገባል። ዮሐንስ 3:16 “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል” ይላል። አዎ፣ ይሖዋ እኛን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ውድ ልጁን ሰጥቶናል። ኢየሱስም ቢሆን ለእኛ ሲል ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ እንደሚወደን ያሳያል። (ዮሐንስ 15:13) ቤዛው ይሖዋና ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚወዱህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ገላትያ 2:20

ስለ ይሖዋ መማራችንን ስንቀጥል የእሱ ወዳጆች እንሆናለን፤ እንዲሁም እሱን ይበልጥ እንወደዋለን

19, 20. (ሀ) የይሖዋ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ለኢየሱስ ቤዛ አድናቆት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

19 አምላክ ለአንተ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አይተናል፤ ታዲያ የእሱ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? የማታውቀውን ሰው ልትወደው አትችልም። ዮሐንስ 17:3 ስለ ይሖዋ ማወቅ እንደምንችል ይናገራል። እንዲህ ስታደርግ እሱን ይበልጥ እየወደድከው ትሄዳለህ፤ እንዲሁም እሱን ማስደሰት ትፈልጋለህ፤ ይህም የእሱ ወዳጅ እንድትሆን ያስችልሃል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ ይሖዋ መማርህን ቀጥል።—1 ዮሐንስ 5:3

20 ኢየሱስ ለከፈለው ቤዛ አድናቆት እንዳለህ አሳይ። መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” በማለት ይናገራል። (ዮሐንስ 3:36) በወልድ ማመን ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ያስተማረውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው። (ዮሐንስ 13:15) በኢየሱስ አምናለሁ ማለት ብቻውን በቂ አይደለም። ለቤዛው አድናቆት እንዳለን ማሳየት ከፈለግን እንዲሁ ከማመን ያለፈ  ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ያዕቆብ 2:26 ‘እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው’ ይላል።

21, 22. (ሀ) በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ በየዓመቱ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በምዕራፍ 6 እና 7 ላይ ምን እንማራለን?

21 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝ። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የሞቱን መታሰቢያ እንድናከብር አሳስቦናል። ይህን በዓል በየዓመቱ የምናከብር ሲሆን የመታሰቢያው በዓል ወይም “የጌታ ራት” በመባል ይታወቃል። (1 ቆሮንቶስ 11:20፤ ማቴዎስ 26:26-28) ኢየሱስ ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠን ዘወትር እንድናስታውስ ይፈልጋል። “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19ን አንብብ።) በመታሰቢያው በዓል ላይ ስትገኝ ለቤዛው እንዲሁም ይሖዋና ኢየሱስ ላሳዩን ጥልቅ ፍቅር አድናቆት እንዳለህ ታሳያለህ።—ተጨማሪ ሐሳብ 16⁠ን ተመልከት።

22 ቤዛው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:14, 15) ይህ ውድ ስጦታ፣ በሞት ላንቀላፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም እንኳ ጥቅም ያስገኛል። ቤዛው ለሞቱ ሰዎች ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምዕራፍ 6 እና 7 ላይ እንማራለን።