በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?

 ምዕራፍ ሁለት

መጽሐፍ ቅዱስ—ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ

መጽሐፍ ቅዱስ—ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰጠን ልዩ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ጓደኛህ አንድ ስጦታ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? ስጦታውን ለመክፈት አትጓጓም? ለአንተ ያለውን አሳቢነት የሚያሳይ ስለሆነ ትደሰታለህ። ጓደኛህን እንደምታመሰግነው የታወቀ ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰጠን ልዩ ስጦታ ነው። ከየትም ልናገኘው የማንችለውን እውቀት ይሰጠናል። ለምሳሌ አምላክ ሰማይንና ምድርን እንዲሁም የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት እንደፈጠረ ይነግረናል። ለችግሮቻችን መፍትሔ የሚሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይሰጠናል። አምላክ ወደፊት ምድርን ገነት የማድረግ ዓላማ አለው፤ ይህን ዓላማውን እንዴት እንደሚፈጽም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ስጦታ ነው!

3. ማጥናትህን ስትቀጥል ምን ትገነዘባለህ?

3 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን ስትቀጥል አምላክ ወዳጁ እንድትሆን እንደሚፈልግ ትገነዘባለህ። ስለ እሱ ይበልጥ ስታውቅ ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት እየተጠናከረ ይሄዳል።

4. መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚያስገርምህ ነገር ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በቢሊዮን በሚቆጠሩ ቅጂዎች ታትሟል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ ይችላሉ። በየሳምንቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ይሰራጫሉ! በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው።

5. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው የምንለው ለምንድን ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ’ ነው።  (2 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ።) ሆኖም አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ከሆኑ እንዴት የአምላክ ቃል ነው ሊባል ይችላል?’ ይሉ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው [ወይም ተመርተው] ተናገሩ” በማለት መልስ ይሰጣል። (2 ጴጥሮስ 1:21) ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ የአንድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆነ አንድ ሰው ጸሐፊውን ደብዳቤ እንድትጽፍ ነገራት እንበል። የደብዳቤው ሐሳብ የማን ነው? የጸሐፊዋ ሳይሆን የኃላፊው ነው። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አምላክ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ የተጠቀመባቸው ሰዎች አይደሉም። አምላክ የራሱን ሐሳብ እንዲጽፉ እነዚህን ሰዎች ተጠቅሞባቸዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ቃል ነው።”—1 ተሰሎንቄ 2:13ተጨማሪ ሐሳብ 2⁠ን ተመልከት።

አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በብዙ ቋንቋዎች ይገኛል

 መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ ትክክል ነው

6, 7. መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይስማማል የምንለው ለምንድን ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ነው። ጸሐፊዎቹ በተለያዩ ዘመናት የኖሩ ናቸው። አንዳንዶቹ የተማሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አልተማሩም። ለምሳሌ ከጸሐፊዎቹ መካከል አንዱ ሐኪም ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ገበሬዎች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ እረኞች፣ ነቢያት፣ መሳፍንትና ነገሥታት ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት የተለያዩ ሰዎች ቢሆኑም የያዘው ሐሳብ እርስ በርሱ ይስማማል። በአንድ ምዕራፍ ላይ የተገለጸው ሐሳብ በሌላ ምዕራፍ ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር አይጋጭም። *

7 የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች፣ በዓለም ላይ ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ የቻሉት ለምን እንደሆነ ይገልጻሉ፤ የመጨረሻዎቹ ምዕራፎች ደግሞ አምላክ ምድርን ገነት በማድረግ እነዚህን ችግሮች እንዴት እንደሚያስወግድ ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ ታሪኮችን የያዘ ከመሆኑም ሌላ አምላክ ምንጊዜም ዓላማውን እንደሚፈጽም ያሳያል።

8. መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክል እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

8 መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንስ ለማስተማር ተብሎ የተዘጋጀ መጽሐፍ ባይሆንም ሳይንሳዊ ስለሆኑ ጉዳዮች የሚናገራቸው ነገሮች በሙሉ ትክክል ናቸው። ደግሞም ይህ ከአምላክ ቃል የሚጠበቅ ነገር ነው። ለምሳሌ የዘሌዋውያን መጽሐፍ፣ በጥንት እስራኤላውያን ዘመን በሽታ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ ይገልጻል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው፣ ባክቴሪያና ቫይረስ በሽታ እንደሚያመጡ ከመታወቁ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር በባዶ ስፍራ ላይ እንደተንጠለጠለች በመግለጽ በትክክል ያስተምራል። (ኢዮብ 26:7) ከዚህም  ሌላ ሰዎች፣ ምድር ጠፍጣፋ እንደሆነች ያስቡ በነበረበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ክብ እንደሆነች ተናግሯል።—ኢሳይያስ 40:22

9. የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት መጻፋቸው ምን ያሳያል?

9 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አንጻር የሚናገረው ሐሳብ ትክክለኛ ነው። በርካታ የታሪክ መጻሕፍት ግን ጸሐፊዎቻቸው ሐቀኛ ስላልሆኑ አንዳንድ ጊዜ የሚናገሩት ነገር ትክክለኛ አይደለም። ለምሳሌ አገራቸው በጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት የሚደብቁበት ጊዜ አለ። ከእነዚህ ሰዎች በተቃራኒ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በእስራኤል ላይ የደረሰውን ሽንፈት በሐቀኝነት ጽፈዋል። የራሳቸውንም ስህተት ቢሆን ጽፈዋል። ለምሳሌ በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ሙሴ ከባድ ስህተት እንደሠራና በዚህም ምክንያት አምላክ ተግሣጽ እንደሰጠው ጽፏል። (ዘኁልቁ 20:2-12) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት መጻፋቸው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ መተማመን እንችላለን።

ጠቃሚ ምክር የያዘ መጽሐፍ

10. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር በዛሬው ጊዜም ጠቃሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ’ ሲሆን “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ” ይጠቅማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛም ጠቃሚ ነው። ይሖዋ አፈጣጠራችንን ስለሚያውቅ አስተሳሰባችንንም ሆነ ስሜታችንን ይረዳል። ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል፤ ደስተኞች እንድንሆንም ይፈልጋል። ለእኛ ጠቃሚ የሆነውንና ጎጂ የሆነውን ነገር ያውቃል።

11, 12. (ሀ) ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ኢየሱስ ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኞቹን ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶች እናገኛለን?

11 ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ፣ ኢየሱስ ደስተኞች መሆንና ከሌሎች ጋር ተስማምተን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ፣ መጸለይ ያለብን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ለገንዘብ ምን አመለካከት ሊኖረን  እንደሚገባ የሚገልጽ ምክር ሰጥቷል። ይህን ምክር የሰጠው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ቢሆንም ምክሩ ዛሬም በጣም ጠቃሚ ነው።

12 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ፣ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረን፣ ታታሪ ሠራተኞች እንድንሆንና ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ናቸው፤ የትም ቦታ ብንኖር ወይም ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንጊዜም ይረዱናል።—ኢሳይያስ 48:17ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 3⁠ን ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መተማመን ትችላለህ

ነቢዩ ኢሳይያስ ባቢሎን ድል እንደምትደረግ ትንቢት ተናግሯል

13. ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር?

13 በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ለምሳሌ ኢሳይያስ፣ ባቢሎን እንደምትጠፋ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 13:19) ከተማዋ ድል የምትደረገው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ተናግሮ ነበር። የባቢሎን ከተማ ትላልቅ በሮች የነበሯት ሲሆን በወንዝ የተከበበች ነበረች። ሆኖም ኢሳይያስ ወንዙ እንደሚደርቅና በሮቿ ሳይዘጉ እንደሚቀሩ ትንቢት ተናገረ። በተጨማሪም ወራሪዎች ያለምንም ውጊያ ከተማዋን እንደሚይዟት እንዲሁም ቂሮስ የሚባል ሰው ባቢሎንን ድል እንደሚያደርጋት ገልጾ ነበር።—ኢሳይያስ 44:27–45:2ን አንብብ፤ ተጨማሪ ሐሳብ 4⁠ን ተመልከት።

14, 15. ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

14 ይህ ትንቢት ከተጻፈ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ አንድ ሠራዊት በባቢሎን ላይ ዘመተ። ሠራዊቱን የሚመራው ማን ነበር? በትንቢት በተነገረው መሠረት የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ነበር። ታዲያ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት የቂሮስ ሠራዊት ባቢሎንን ያላንዳች ውጊያ ይይዝ ይሆን?

15 የዚያን ቀን ሌሊት ባቢሎናውያን ታላቅ ግብዣ አድርገው ነበር። ትላልቅ በሆኑት ግንቦቻቸውና በከተማቸው ዙሪያ በሚፈሰው ወንዝ  ተማምነው ነበር። ቂሮስና ሠራዊቱ ከከተማዋ ውጭ ቦይ በመቆፈር ወንዙ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲፈስና እንዲቀንስ አደረጉ። የውኃው መጠን በጣም ስለጎደለ የፋርስ ወታደሮች ወንዙን በእግር መሻገር ቻሉ። ሆኖም ወታደሮቹ የባቢሎንን ግንብ እንዴት ማለፍ ይችላሉ? በትንቢት በተነገረው መሠረት የከተማዋ በሮች ክፍት ሆነው ስለነበር ወታደሮቹ ያለምንም ውጊያ ከተማዋን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ።

16. (ሀ) ኢሳይያስ፣ ባቢሎን ከጊዜ በኋላ ምን እንደምትሆን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት እንደተፈጸመ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

 16 ኢሳይያስ ከጊዜ በኋላ ባቢሎን ዳግመኛ የሰው መኖሪያ እንደማትሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር። “ከዚያ በኋላ የሚቀመጥባት አይኖርም፤ እንዲሁም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ የመኖሪያ ቦታ አትሆንም” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 13:20) ይህስ ትንቢት ተፈጽሟል? የኢራቅ ከተማ ከሆነችው ከባግዳድ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው የቀድሞዋ ባቢሎን አሁን የፍርስራሽ ክምር ሆናለች። እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ የሚኖር ሰው የለም። ይሖዋ ባቢሎንን “በጥፋት መጥረጊያ” ጠርጓታል ወይም አጥፍቷታል።—ኢሳይያስ 14:22, 23 *

ባቢሎን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ

17. አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

17 በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለወደፊቱ ጊዜ የሚናገራቸው ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው እንደማይቀር እንድንተማመን ያስችለናል። ይሖዋ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዘኁልቁ 23:19ን አንብብ።) ‘ሊዋሽ የማይችለው  አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት የሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ አለን።—ቲቶ 1:2 *

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትህን ሊለውጠው ይችላል?

18. ጳውሎስ ስለ ‘አምላክ ቃል’ ምን ብሏል?

18 መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ እንደሆነ ተመልክተናል። እርስ በርሱ የሚስማማ ከመሆኑም ሌላ ከሳይንስና ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምክር ይዟል፤ በውስጡ የሚገኙ በርካታ ትንቢቶችም ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሆኖም ‘መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ ነው’ የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” በማለት ጽፏል። ይህ ምን ማለት ነው?—ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።

19, 20. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ማንነትህን በትክክል እንድታውቅ የሚረዳህ እንዴት ነው? (ለ) አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠህ አመስጋኝ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

19 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወትህን ሊለውጠው ይችላል። ማንነትህን በትክክል እንድታውቅ ይረዳሃል። በውስጥህ ያለውን ሐሳብና ስሜት እንድትረዳ ያስችልሃል። ለምሳሌ አምላክን እንደምንወደው ይሰማን ይሆናል። ሆኖም እውነተኛ ፍቅር በስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚገለጽ ነገር ነው። አምላክን የምንወደው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል።

20 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስጦታ ነው። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ውድ ስጦታ በመመልከት እንድታነበውና እንድታጠናው ይፈልጋል። የአምላክን ቃል በሚገባ በማጥናት ለዚህ ስጦታ አመስጋኝ መሆንህን አሳይ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ትገነዘባለህ። የሚቀጥለው ምዕራፍ ስለ አምላክ ዓላማ ያብራራል።

^ አን.6 አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ እንደማይስማማ ይናገራሉ፤ ሆኖም ይህ እውነት አይደለም። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።

^ አን.16 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 27-29 ተመልከት።

^ አን.17 ስለ ባቢሎን ጥፋት ከተነገረው ትንቢት በተጨማሪ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አሉ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶችን፣ ተጨማሪ ሐሳብ 5 ላይ ማግኘት ትችላለህ።