በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ከበላይ አካሉ የተላከ ደብዳቤ

ከበላይ አካሉ የተላከ ደብዳቤ

ውድ የእምነት አጋራችን፦

እንደምታውቀው መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው አብዛኞቹ ዘገባዎች የሰዎችን ሕይወት የሚዳስሱ ናቸው። በመጽሐፉ ላይ ከተጠቀሱት መካከል ብዙዎቹ፣ እኛ የሚደርሱብን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። እነዚህ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ነበራቸው። (ያዕቆብ 5:17) አንዳንዶቹ በችግርና በጭንቀት ተውጠው ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የቤተሰባቸው አባላት ወይም የእምነት አጋሮቻቸው ስሜታቸውን ጎድተውታል። እንዲሁም አንዳንዶች በሠሩት ጥፋት የተነሳ በበደለኝነት ስሜት ይሠቃዩ ነበር።

ይሁንና እነዚህ ግለሰቦች ከይሖዋ ጨርሶ ርቀው ነበር ማለት ነው? አይደለም። ብዙዎቹ “እንደጠፋ በግ ተቅበዘበዝኩ። አገልጋይህን ፈልገው፤ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና” በማለት እንደጸለየው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ነበራቸው። (መዝሙር 119:176) አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል?

ይሖዋ ከመንጋው መካከል የባዘኑ አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይረሳቸውም። እንዲያውም እነሱን ለመርዳት እርምጃ ይወስዳል፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርገው በእምነት አጋሮቻቸው በኩል ነው። ይሖዋ፣ ብዙ መከራ የደረሰበትን አገልጋዩን ኢዮብን የረዳበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኢዮብ ንብረቱ ወድሟል፣ የቤተሰቡን አባላት በሞት ተነጥቋል እንዲሁም ከባድ የጤና ችግር አጋጥሞታል። በተጨማሪም ሊያጽናኑት የሚገባቸው ሰዎች በንግግራቸው ጎድተውታል። ኢዮብ አስተሳሰቡ ለጊዜው ተዛብቶ ነበር፤ ያም ቢሆን ፈጽሞ ለይሖዋ ጀርባውን አልሰጠም። (ኢዮብ 1:22፤ 2:10) ታዲያ ይሖዋ፣ ኢዮብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነበር?

ይህን ያደረገበት አንዱ መንገድ ኤሊሁ በሚባል የኢዮብ የእምነት አጋር አማካኝነት ነው። ኢዮብ ያስጨነቀውን ነገር ሲገልጽ ኤሊሁ አዳመጠው፤ ከዚያ በኋላ ሐሳቡን ተናገረ። ታዲያ ምን ብሎት ይሆን? ነቅፎት አሊያም ኢዮብ የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ኀፍረት ተሰምቶት አመለካከቱን እንዲያስተካክል ለማድረግ ሞክሮ ይሆን? ከኢዮብ እንደሚበልጥ ተሰምቶትስ ነበር? በፍጹም! ኤሊሁ “በእውነተኛው አምላክ ፊት እኔም እንደ አንተው ነኝ፤ እኔም የተሠራሁት ከሸክላ ነው” በማለት በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ተናገረ። ከዚያም “እኔን ፈርተህ ልትሸበር አይገባም፤ የማሳድርብህ ጫናም ሊደቁስህ አይገባም” በማለት ኢዮብን አጽናንቶታል። (ኢዮብ 33:6, 7) ኤሊሁ በኢዮብ ላይ ተጨማሪ ሸክም ከመጫን ይልቅ ኢዮብ የሚያስፈልገውን ምክርና ማበረታቻ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ሰጥቶታል።

እኛም ይህን ብሮሹር ለማዘጋጀት የተነሳሳነው በዚሁ መንፈስ እንደሆነ ልንገልጽልህ እንፈልጋለን። ብሮሹሩን ማዘጋጀት ከመጀመራችን በፊት፣ ከእውነት ርቀው የነበሩ የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች የተናገሩትን ነገር አዳምጠናል፤ እንዲሁም የነበሩበትን ሁኔታና ስሜታቸውን ከግምት አስገብተናል። (ምሳሌ 18:13) ከዚያም ትኩረታችንን ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት አዞርን፤ ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እንዴት እንደረዳቸው የሚገልጹ ዘገባዎችን በጸሎት በመታገዝ መረመርን። በመጨረሻም እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎች ከዘመናዊ ተሞክሮዎች ጋር በማቀናጀት ይህን ብሮሹር አዘጋጀን። ይህን ጽሑፍ እንድታነበው ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። ከልብ እንወድሃለን።

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል