በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ተመለስ

 ክፍል አንድ

“የጠፋውን እፈልጋለሁ”

“የጠፋውን እፈልጋለሁ”

በጓ ግራ ተጋብታለች። ሜዳው ላይ ሣር እየጋጠች ሳለ ሳይታወቃት ከሌሎቹ በጎች ተነጥላ ቀረች። አሁን መንጋውም ሆነ እረኛው አይታዩአትም። ቀኑ ደግሞ እየመሸ ነው። ይህች በግ ያለችው አራዊት በሚፈነጩበት ገደላማ አካባቢ በመሆኑ ከአደጋ የሚያስጥላት የለም። በኋላ ላይ ግን የምታውቀው ድምፅ ሰማች፤ እረኛው እየጠራት ነው፤ ከዚያም እየሮጠ ወደ እሷ በመሄድ እቅፍ አድርጎ ጉያው ውስጥ ካስገባት በኋላ ተሸክሞ ወደ ቤቱ ወሰዳት።

ይሖዋ እንዲህ ካለ እረኛ ጋር ራሱን ብዙ ጊዜ አመሳስሏል። “እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ ደግሞም እንከባከባቸዋለሁ” የሚል ማረጋገጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰጥቶናል።—ሕዝቅኤል 34:11, 12

“የምንከባከባችሁ በጎች”

የይሖዋ በጎች እነማን ናቸው? በአጭሩ፣ የይሖዋ በጎች እሱን የሚወዱትና የሚያመልኩት ሰዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኑ፣ እናምልክ፤ እንስገድም፤ ሠሪያችን በሆነው በይሖዋ ፊት እንንበርከክ። እሱ አምላካችን ነውና፤ እኛ ደግሞ በመስኩ የተሰማራን ሕዝቦች፣ በእሱ እንክብካቤ ሥር ያለን በጎች ነን።” (መዝሙር 95:6, 7) እረኛቸውን እንደሚከተሉ በጎች ሁሉ የይሖዋ አምላኪዎችም እረኛቸውን ለመከተል ዝግጁ ናቸው። ይሁንና በጎቹ ምንም አያጠፉም ማለት ነው? አይደለም። የአምላክ አገልጋዮች ‘እንደተበተኑ በጎች፣’ ‘እንደጠፉ በጎች’ እና “እንደባዘኑ በጎች” የሆኑበት ጊዜ አለ። (ሕዝቅኤል 34:12፤ ማቴዎስ 15:24፤ 1 ጴጥሮስ 2:25) ያም ቢሆን አንድ ሰው ከንጹሕ አምልኮ ሲርቅ ይሖዋ፣ ምንም ተስፋ እንደሌለው ቆጥሮ ከናካቴው አይተወውም።

አንተስ ይሖዋ አሁንም እረኛህ እንደሆነ ይሰማሃል? ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እረኛ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት፦

በመንፈሳዊ ይመግበናል። ይሖዋ ስለ በጎቹ ሲናገር “ጥሩ በሆነ መስክ ላይ አሰማራቸዋለሁ” ብሏል። አክሎም “በዚያም ጥሩ በሆነ የግጦሽ መሬት ላይ ያርፋሉ፤ . . . በለመለመ መስክ ይሰማራሉ” በማለት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 34:14) ይሖዋ ወቅታዊ የሆኑና መንፈስን የሚያድሱ የተለያዩ መንፈሳዊ ምግቦችን ሳይሰጠን የቀረበት ጊዜ የለም። እርዳታ ለማግኘት ላቀረብከው ጸሎት በአንድ ጽሑፍ፣ ንግግር ወይም ቪዲዮ አማካኝነት መልስ ይሖዋ የሰጠበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ታዲያ ይህን ማድረጉ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ እንድትሆን አላደረገህም?

ጥበቃና ድጋፍ ያደርግልናል። ይሖዋ “የባዘነውን መልሼ አመጣለሁ፤ የተጎዳውን በጨርቅ አስራለሁ፤ የደከመውን አበረታለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሕዝቅኤል 34:16) የደከሙትን ወይም በጭንቀት የተዋጡትን ይሖዋ ያበረታቸዋል። እንዲሁም በእምነት ባልንጀሮቻቸው አሊያም በሌላ ምክንያት በጎቹ ሲጎዱ በጨርቅ በማሰር እንዲድኑ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም የባዘኑና ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር የሚታገሉ በጎቹን መልሶ ያመጣቸዋል።

ሊንከባከበን እንደሚገባ ይሰማዋል። ይሖዋ “ከተበተኑባቸው ቦታዎች ሁሉ እታደጋቸዋለሁ። የጠፋውን እፈልጋለሁ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 34:12, 16) ይሖዋ፣ የጠፋን በግ ጨርሶ ሊመለስ እንደማይችል አድርጎ አይመለከተውም። አንድ በግ ሲጠፋ ያስተውላል፤ በጉን ይፈልገዋል፤ ሲያገኘውም በጣም ይደሰታል። (ማቴዎስ 18:12-14) ደግሞም እውነተኛ አምላኪዎቹን “በጎቼ፣ የምንከባከባችሁ በጎች” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ሕዝቅኤል 34:31) አንተም ከእነዚህ በጎች አንዱ ነህ።

ይሖዋ፣ የጠፋን በግ ጨርሶ ሊመለስ እንደማይችል አድርጎ አይመለከተውም። በጉን ሲያገኘው በጣም ይደሰታል

“ዘመናችንን እንደቀድሞው አድስልን”

ይሖዋ የሚፈልግህና ወደ እሱ እንድትመለስ የሚጋብዝህ ለምንድን ነው? ደስተኛ እንድትሆን ስለሚሻ ነው። ለበጎቹ ‘በረከት እንደ ዝናብ እንደሚወርድላቸው’ ቃል ገብቷል። (ሕዝቅኤል 34:26) ይህ ባዶ ተስፋ አይደለም። እውነት እንደሆነ አንተ ራስህ በሕይወትህ ተመልክተኸዋል።

ስለ ይሖዋ ስትማር የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ይሖዋ ስምና ለሰዎች ስላለው ዓላማ የሚገልጹትን አስደሳች እውነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ስታውቅ ምን ተሰምቶህ ነበር? ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገናኘት ምን ያህል መንፈስን የሚያድስ እንደነበረ ታስታውሳለህ? ለአንድ ሰው ምሥራቹን ነግረኸው በደስታ የተቀበለህ ጊዜስ ትዝ ይልሃል? በዚያ ወቅት ወደ ቤትህ የተመለስከው ደስ እያለህና ጥልቅ እርካታ ተሰምቶህ አልነበረም?

አሁንም እንደዚያ ዓይነት ደስታ ማግኘት ትችላለህ። የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች “ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም በፈቃደኝነት እንመለሳለን። ዘመናችንን እንደቀድሞው አድስልን” በማለት ጸልየው ነበር። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 5:21) ይሖዋ ለዚህ ጸሎት መልስ የሰጠ ሲሆን ሕዝቦቹም ደስታቸው ታድሶላቸው እሱን ለማገልገል ተመልሰዋል። (ነህምያ 8:17) ይሖዋ ለአንተም እንደዚሁ ያደርጋል።

ያም ቢሆን ወደ ይሖዋ መመለስ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። ወደ ይሖዋ መመለስ አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና እነዚህን ነገሮች እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል እስቲ እንመልከት።