በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ተመለስ

 ክፍል አራት

የበደለኝነት ስሜት—‘ከኃጢአቴ አንጻኝ’

የበደለኝነት ስሜት—‘ከኃጢአቴ አንጻኝ’

“አዲሱ ሥራዬ የቤተሰባችን ኑሮ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ቢያበረክትም አጠያያቂ በሆኑ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንድካፈል አደረገኝ። በዓላትን ማክበር፣ በፖለቲካዊ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ አልፎ ተርፎም ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክር ብባልም ለ40 ዓመት ያህል ከጉባኤ ርቄ ነበር። ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት እንደማልችል እየተሰማኝ መጣ። ራሴን ይቅር ማለት እንደማልችልም ማሰብ ጀመርኩ። ምክንያቱም በተሳሳተ ጎዳና ላይ መጓዝ ስጀምር እውነትን አውቅ ነበር።”—ማርታ

የበደለኝነት ስሜት፣ እንደሚያደቅ ሸክም ሊሆን ይችላል። ንጉሥ ዳዊት “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉና፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 38:4) አንዳንድ ክርስቲያኖች ይሖዋ ፈጽሞ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ስለሚሰማቸው ከመጠን ባለፈ ሐዘን ተውጠዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:7) እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ትክክል ነው? የፈጸምከው ኃጢአት ከባድ ቢሆንስ? ከይሖዋ በጣም ስለራቅክ ይቅር ሊልህ አይችልም ማለት ነው? አይደለም!

“በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ”

ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን አይተዋቸውም። እንዲያውም እንዲመለሱ ቅድሚያውን ወስዶ ሁኔታዎችን ያመቻችላቸዋል! ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ ይሖዋን ከአንድ አፍቃሪ አባት ጋር አመሳስሎታል፤ የዚህ ሰው ልጅ ቤተሰቡን ጥሎ በመሄድ ልቅ የሆነ ሕይወት ሲመራ ቆየ። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ። “ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” (ሉቃስ 15:11-20) አንተስ ወደ ይሖዋ መቅረብ ብትፈልግም በጣም “ሩቅ” እንዳለህ ይሰማሃል? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው አባት ሁሉ ይሖዋም ከአንጀቱ ይራራልሃል። ወደ እሱ ስትመለስ በደስታ ሊቀበልህ ይጓጓል።

ይሁን እንጂ ኃጢአትህ በጣም ከባድ ወይም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ይሖዋ ይቅር ሊልህ እንደማይችል ቢሰማህስ? በኢሳይያስ 1:18 ላይ ይሖዋ ያቀረበውን ግብዣ እንድታነብ እንጋብዝሃለን፦ “‘ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ’ ይላል ይሖዋ። ‘ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል።’” በደም ከመበላሸቱ የተነሳ ታጥቦ የሚጸዳ የማይመስልን ነጭ ጨርቅ ለማሰብ ሞክር፤ ኃጢአትህ እንደዚህ እንደሆነ ቢሰማህ እንኳ ይሖዋ ይቅር ሊልህ ይችላል።

ይሖዋ በበደለኝነት ስሜት እየተሠቃየህ እንድትኖር አይፈልግም። ታዲያ የአምላክን ይቅርታና ንጹሕ ሕሊና አግኝተህ እፎይ ማለት የምትችለው እንዴት ነው? ንጉሥ ዳዊት የወሰዳቸውን ሁለት እርምጃዎች እንመልከት። በመጀመሪያ፣ “የፈጸምኳቸውን በደሎች ለይሖዋ እናዘዛለሁ” ብሏል። (መዝሙር 32:5) ይሖዋ ወደ እሱ በጸሎት እንድትቀርብና ‘የተፈጠረውን ችግር ተወያይታችሁ እንድትፈቱ’ አስቀድሞ እንደጋበዘህ አስታውስ። ይህን ግብዣ ተቀበል። የሠራኸውን ኃጢአት ለይሖዋ ተናዘዝ፤ እንዲሁም ስሜትህን አውጥተህ ንገረው። ዳዊት ከግል ተሞክሮው በመነሳት ‘ከኃጢአቴ አንጻኝ’ ብሏል። አክሎም “አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም” በማለት በእርግጠኝነት ጸልዮአል።—መዝሙር 51:2, 17

ሁለተኛ፣ ዳዊት አምላክ ከሾመው ከነቢዩ ናታን እርዳታ አግኝቷል። (2 ሳሙኤል 12:13) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ያዘጋጀ ሲሆን እነሱም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት እንዲያድሱ ለመርዳት የሚያስችል ሥልጠና አግኝተዋል። ወደ ሽማግሌዎች በምትቀርብበት ጊዜ እነሱ ልብህን ለማረጋጋት  እንዲሁም አሉታዊ ስሜትህ እንዲቀንስ ወይም እንዲጠፋ ለመርዳት ብሎም በመንፈሳዊ እንድትፈወስ ለማድረግ በቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቀማሉ፤ ከዚህም ሌላ ከልብ የመነጨ ጸሎት ያቀርባሉ።—ያዕቆብ 5:14-16

ይሖዋ ንጹሕ ሕሊና አግኝተህ እፎይ እንድትል ይፈልጋል

“በደሉ ይቅር የተባለለት . . . ሰው ደስተኛ ነው”

ኃጢአትህን ለይሖዋ አምላክ መናዘዝና ሽማግሌዎች እንዲረዱህ መጠየቅ በጣም ከባድ እንደሆነ ቢሰማህ አያስገርምም። ዳዊትም እንዲህ ዓይነት ስሜት የነበረው ይመስላል። ስለ ኃጢአቱ ከመናገር ይልቅ ለተወሰነ ጊዜ “ዝም” ብሎ ነበር። (መዝሙር 32:3) ውሎ አድሮ ግን ኃጢአቱን መናዘዝና አካሄዱን ማስተካከል ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቧል።

ዳዊት ያገኘው ዋነኛ ጥቅም ደስታው መመለሱ ነው። “በደሉ ይቅር የተባለለት፣ ኃጢአቱ የተተወለት ሰው ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 32:1 የግርጌ ማስታወሻ) በተጨማሪም ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፣ አፌ ምስጋናህን እንዲያውጅ ከንፈሮቼን ክፈት” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 51:15) ዳዊት ከበደለኝነት ስሜቱ ስለተላቀቀና አምላክ ይቅር ስላለው አመስጋኝ በመሆኑ ስለ ይሖዋ ለሌሎች ለመናገር ተነሳስቶ ነበር።

ይሖዋ አንተም ንጹሕ ሕሊና አግኝተህ እፎይ እንድትል ይፈልጋል። እንዲሁም ከበደለኝነት ስሜት ነፃ ሆነህ ብሎም ከልብ በመነጨ ጥልቅ ደስታ ተነሳስተህ ስለ እሱና ስለ ዓላማው ለሌሎች እንድትናገር ይፈልጋል። (መዝሙር 65:1-4) “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ . . . ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል” የሚለውን ግብዣ አስታውስ።—የሐዋርያት ሥራ 3:19

ማርታ ይህን ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ሁልጊዜ ይልክልኝ ነበር። ቀስ በቀስ ይሖዋን እንደገና እያወቅኩት መጣሁ። ስለ መመለስ ሳስብ በጣም የከበደኝ ነገር ለፈጸምኩት ኃጢአት ሁሉ ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ መጠየቅ ነበር። በመጨረሻ ግን በጸሎት ወደ አምላክ ቀርቤ ምሕረት እንዲያደርግልኝ ለመንኩት። ወደ ይሖዋ ለመመለስ 40 ዓመት የፈጀብኝ መሆኑን ማመን ይከብዳል። አንድ ሰው፣ ብዙ ዓመታት ቢያልፉም እንኳ እንደገና አምላክን ለማገልገልና ወደ ፍቅሩ ለመመለስ አጋጣሚ ሊያገኝ እንደሚችል እኔ ሕያው ማስረጃ ነኝ።”