በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ተመለስ

 ክፍል አምስት

‘ወደ ነፍስህ እረኛና ጠባቂ ተመለስ’

‘ወደ ነፍስህ እረኛና ጠባቂ ተመለስ’

በዚህ ብሮሹር ላይ ከተገለጹት ፈተናዎች መካከል አንተን ያጋጠመህ አለ? ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰብህ አንተ ብቻ አይደለህም። ጥንትም ሆነ በዘመናችን የኖሩ በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ተመሳሳይ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። እንደዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሸነፍ ከይሖዋ እርዳታ እንዳገኙ ሁሉ አንተም የእሱን እርዳታ ማግኘት ትችላለህ።

ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስታስብ እሱ እጁን ዘርግቶ ይጠብቅሃል

 ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስታስብ እሱ እጁን ዘርግቶ እንደሚጠብቅህ እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ ጭንቀትን እንድትቋቋም፣ ስሜትህ ተጎድቶ ከነበረ ጠባሳው እንዲሽር እንዲሁም ከንጹሕ ሕሊና የሚገኘው የአእምሮና የልብ ሰላም እንዲኖርህ ይረዳሃል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ሆነህ እንደገና ይሖዋን ለማገልገል ሊያነሳሳህ ይችላል። ሁኔታህ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ከጻፈላቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጋር ይመሳሰላል፦ “እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።”—1 ጴጥሮስ 2:25

ወደ ይሖዋ መመለስ ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ እንደሆነ አትጠራጠር። ለምን? ምክንያቱም መመለስህ የይሖዋን ልብ ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ ስሜት ያለው አምላክ ነው፤ በመሆኑም የምናደርገው ነገር ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እንድንወደውና እንድናገለግለው አያስገድደንም። (ዘዳግም 30:19, 20) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልብ ከውጭ በኩል መክፈቻ የለውም። መከፈት ያለበት ከውስጥ ነው።” ይሖዋን በፍቅር በተሞላ ልብ ተገፋፍተን ስናመልክ የልባችንን በር ለመክፈት እንደመረጥን እናሳያለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋ ውድ ስጦታ እንሰጠዋለን፤ በሌላ አባባል ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ ልቡን በጣም እናስደስተዋለን። በእርግጥም ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ በመስጠት የምናገኘው ደስታ ከምንም ነገር ጋር አይወዳደርም።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ራእይ 4:11

ከዚህም በላይ በክርስቲያናዊ አምልኮ እንደገና መካፈል ስትጀምር መንፈሳዊ ፍላጎትህ ይሟላል። (ማቴዎስ 5:3) በምን መንገድ? በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ‘የተፈጠርነው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል። ስለ ሕይወት ዓላማ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጓጓሉ። የሰው ልጆች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች የምናነሳው ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ስለፈጠረን ነው። እሱን በማገልገል እርካታ ማግኘት እንድንችል ተደርገን ተፈጥረናል። ይሖዋን የምናመልከው በፍቅር ተነሳስተን እንደሆነ ከማወቅ የሚበልጥ አስደሳች ነገር ሊኖር አይችልም።—መዝሙር 63:1-5

ምንጊዜም ቢሆን አንድ ነገር አትርሳ፤ ይሖዋ ወደ እሱ እንድትመለስ በጣም ይፈልጋል። ይህን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይህን ብሮሹር ለማዘጋጀት ብዙ መጸለይ አስፈልጓል፤ እንዲሁም በጥሞና ታስቦበታል። ብሮሹሩ አንተ እጅ እንዲገባ ያደረገው ደግሞ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ወይም የእምነት አጋርህ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ብሮሹሩን ለማንበብና በውስጡ ያለውን ሐሳብ በሥራ ላይ ለማዋል ተነሳሳህ። ይህ ሁሉ፣ ይሖዋ እንዳልረሳህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። በደግነት ወደ ራሱ እየሳበህ ነው።—ዮሐንስ 6:44

ይሖዋ የጠፉ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይረሳ ማወቃችን ያጽናናናል። ዶና የምትባል አንዲት እህት ይህን ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከእውነት ቀስ በቀስ እየራቅኩ ብሄድም በመዝሙር 139:23, 24 ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስል ነበር፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ። መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ። በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።’ ዓለም ለእኔ እንደማይሆን ገብቶኝ ነበር፤ እዚያ ሆኜ ባይተዋርነት ይሰማኝ ነበር። በመሆኑም መኖር ያለብኝ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይሖዋ መቼም ቢሆን እንዳልተወኝ ማስተዋል ጀመርኩ፤ ከእኔ የሚጠበቀው ወደ እሱ መመለስ ነው። ደግሞም በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ!”

“ይሖዋ መቼም ቢሆን እንዳልተወኝ ማስተዋል ጀመርኩ፤ ከእኔ የሚጠበቀው ወደ እሱ መመለስ ነው”

አንተም ይሖዋ የሚሰጠውን ደስታ እንደገና እንድታጣጥም ልባዊ ጸሎታችን ነው። (ነህምያ 8:10) ወደ ይሖዋ በመመለስህ ፈጽሞ አትቆጭም።