በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 11

“መንገዱ ሁሉ ፍትሕ ነው”

“መንገዱ ሁሉ ፍትሕ ነው”

1, 2. (ሀ) ዮሴፍ በተለያዩ ጊዜያት ምን ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል? (ለ) ይሖዋ ኢፍትሐዊ የሆነውን ድርጊት ለማስተካከል ምን እርምጃ ወስዷል?

አንድ መልከ መልካም ወጣት፣ አስገድደህ ለመድፈር ሞክረሃል በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ባልሠራው ጥፋት ወኅኒ ተጥሏል። ሆኖም በደል ሲፈጸምበት ይህ የመጀመሪያው አልነበረም። ዮሴፍ የተባለው ይህ ወጣት ከተወሰኑ ዓመታት በፊትም ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ወንድሞቹ ስለጠሉት ሊገድሉት አስበው ነበር። በኋላ ግን ሐሳባቸውን በመለወጥ ባሪያ እንዲሆን ለባዕድ አገር ሰዎች ሸጡት። በባርነት በሚያገለግልበት ቤት የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ ልታባብለው ብትሞክርም ያቀረበችለትን ግብዣ ሳይቀበል ቀረ። በዚህ የተናደደችው ይህች ሴት በሐሰት ወንጅላ አሳሰረችው። የሚያሳዝነው ደግሞ ዮሴፍ አስታዋሽ አልነበረውም።

ዮሴፍ “በግዞት” አላግባብ ተንገላቷል

2 ይሁን እንጂ ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወደው’ አምላክ ዮሴፍ የደረሰበትን ነገር ሁሉ ይመለከት ነበር። (መዝሙር 33:5) ይሖዋ፣ ዮሴፍ ከወኅኒ የሚወጣበትን ሁኔታ በማመቻቸት ኢፍትሐዊ የሆነውን ድርጊት ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ “በግዞት” የነበረውን ዮሴፍን ከማስፈታቱም በተጨማሪ ከፍተኛ ሥልጣንና ክብር እንዲያገኝ አድርጓል። (ዘፍጥረት 40:15፤ 41:41-43፤ መዝሙር 105:17, 18) በመጨረሻም ዮሴፍ ከተወነጀለበት ክስ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ያገኘውንም ከፍተኛ ሥልጣን የአምላክን ዓላማ ለማስፈጸም ተጠቅሞበታል።—ዘፍጥረት 45:5-8

3. ሁላችንም ፍትሕን የምንሻ መሆናችን ሊያስገርም የማይገባው ለምንድን ነው?

3 እንዲህ ያለው ታሪክ ልብ የሚነካ አይደለም? ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸም ያላየ ወይም በራሱ ላይ ያልደረሰበት ማን አለ? አዎን፣ ሁላችንም አድሏዊነት ተወግዶ ፍትሕ እንዲሰፍን እንፈልጋለን። ይሖዋ የእሱን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ አድርጎ ስለፈጠረን ይህ ፍላጎት ያለን መሆኑ ሊያስገርም አይገባም። ከይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ደግሞ ፍትሕ  ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይሖዋን በሚገባ ለማወቅ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት መረዳት ያስፈልገናል። ይህን ካደረግን አስደናቂ የሆኑትን መንገዶቹን ይበልጥ ልናደንቅና ከምንጊዜውም በበለጠ ወደ እሱ ለመቅረብ ልንገፋፋ እንችላለን።

ፍትሕ ምንድን ነው?

4. ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን የሚረዱት እንዴት ነው?

4 ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን የሚረዱት ሕግን በአግባቡ ከማስፈጸም አንጻር ነው። ራይት ኤንድ ሪዝን—ኤቲክስ ኢን ቲዮሪ ኤንድ ፕራክቲስ የተባለው መጽሐፍ “ፍትሕ ከሕግ፣ ከግዴታ፣ ከመብትና ከኃላፊነት ጋር የተያያዘ ሲሆን አድልዎ የሌለበት ወይም ተገቢ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ይጠይቃል” ይላል። የይሖዋ ፍትሕ ግን እንዲሁ ድርቅ ባለ መንገድ ሕግን ለማስፈጸም ብቻ የቆመ አይደለም።

5, 6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍትሕን” ለማመልከት የገቡት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? (ለ) አምላክ ፍትሐዊ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ፍትሕን ለማመልከት የገቡትን ቃላት ጠለቅ ብሎ በመመርመር የይሖዋ ፍትሕ ያለውን ስፋትና ጥልቀት በሚገባ መረዳት ይቻላል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ፍትሕን ለማመልከት የተሠራባቸው ሦስት መሠረታዊ ቃላት አሉ። በብዙ ቦታዎች ላይ “ፍትሕ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ትክክል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ዘፍጥረት 18:25 የ1980 ትርጉም) ሌሎቹ ሁለት ቃላት ደግሞ በብዙ ቦታዎች ላይ “ጽድቅ” ተብለው ተተርጉመዋል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ጽድቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ትክክለኛ ወይም ፍትሐዊ መሆን” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ጽድቅና ፍትሕ የሚሉት ቃላት ብዙም ልዩነት የላቸውም።—አሞጽ 5:24 አ.መ.ት

6 በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ፍትሐዊ ነው ሲል ምንጊዜም አድልዎ የሌለበት ትክክለኛ ነገር ያደርጋል ማለቱ ነው። (ሮሜ 2:11) አምላክ ያዳላል ወይም አግባብ ያልሆነ ነገር ይፈጽማል ማለት ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነው። ታማኙ ኤሊሁ “ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 34:12)  በእርግጥም ይሖዋ ‘ፍርድን ሊያጣምም’ አይችልም። ለምን? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንመልከት።

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር ማድረግ የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን የሚገፋፋው ምንድን ነው?

7 በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ቅዱስ ነው። ምዕራፍ 3 ላይ እንዳየነው ይሖዋ በንጽሕናውና በጽድቅ አቋሙ ወደር አይገኝለትም። ስለሆነም ጠማማ ወይም ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር ሊያደርግ አይችልም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ሰማያዊ አባታችን ቅዱስ በመሆኑ በልጆቹ ላይ ፈጽሞ በደል እንደማይፈጽም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ኢየሱስ በአባቱ ላይ እንዲህ ዓይነት እምነት ነበረው። በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ሌሊት “ቅዱስ አባት ሆይ፣ እነዚህን [ደቀ መዛሙርት] . . . በስምህ ጠብቃቸው” ሲል ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:11) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ቅዱስ አባት” የሚለው መጠሪያ የተሰጠው ለይሖዋ ብቻ ነው። በቅድስና ከይሖዋ ጋር ሊተካከል የሚችል ሰብዓዊ አባት ስለማይኖር ይህ መጠሪያ ለእሱ ብቻ መሰጠቱ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ንጹሕ በሆነውና ምንም ዓይነት ኃጢአት በሌለበት አባቱ ጥበቃ ሥር እስከሆኑ ድረስ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ሙሉ እምነት ነበረው።—ማቴዎስ 23:9

8 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የተላበሰ አምላክ ነው። ይህ ፍቅር ማንኛውንም ነገር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን ይገፋፋዋል። ዘረኝነትን፣ ወገናዊነትንና አድሏዊነትን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ብዙውን ጊዜ ከፍቅር ሳይሆን ከስግብግብነትና ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ሲናገር “እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፣ ጽድቅንም ይወድዳል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 11:7) ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር ‘ፍትሕን እወዳለሁ’ ብሏል። (ኢሳይያስ 61:8) አምላካችን ይሖዋ ትክክል ወይም ፍትሕ  የሆነ ነገር ማድረግ እንደሚያስደስተው ማወቅ አያጽናናም?—ኤርምያስ 9:24

ምሕረትና ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ

9-11. (ሀ) የይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ምን ዝምድና አላቸው? (ለ) ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ፍትሕና ምሕረት ያሳየው እንዴት ነው?

9 አቻ እንደማይገኝላቸው እንደ ሌሎቹ የይሖዋ ባሕርያት ሁሉ ፍትሑም ፍጹምና እንከን የማይገኝበት ነው። ሙሴ ይሖዋን እንዲህ ሲል አወድሷል:- “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሕ፣” NW] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።” (ዘዳግም 32:3, 4) ይሖዋ ፍትሑን የሚገልጽበት መንገድ ሁሉ እንከን የማይወጣለት ነው፤ በጣም ልዝብ ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ አይደለም።

10 የይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ተዛማጅ ነገሮች ናቸው። መዝሙር 116:5 “እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ [“ፍትሐዊ፣” ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል] ነው፣ አምላካችንም ይቅር ባይ ነው” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ፍትሐዊና መሐሪ አምላክ ነው። ሁለቱ ባሕርያት እርስ በርስ አይቃረኑም። ይሖዋ ፍትሑ ከልክ በላይ ጥብቅ የሆነ ይመስል ምሕረት የሚያሳየው ፍርዱን ለማለዘብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ባሕርያት እርስ በርስ የሚደጋገፉ በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ ይሖዋ አንድ ላይ ሲጠቀምባቸው ይታያል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

11 የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአትን የወረሱ በመሆናቸው በኃጢአት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት ማለትም ሞት ይገባቸዋል። (ሮሜ 5:12) ሆኖም ኃጢአተኞች መሞታቸው ለይሖዋ የሚሰጠው ምንም ደስታ የለም። “ይቅር ባይ፣ ቸርና መሐሪ አምላክ” ነው። (ነህምያ 9:17) ይሁንና ቅዱስ አምላክ በመሆኑ ክፋትን በቸልታ ሊያልፍ አይችልም። ታዲያ ኃጢአትን ለወረሱ የሰው ልጆች ምሕረት ሊያሳይ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሰው ዘርን ለማዳን ቤዛ እንዳዘጋጀ የሚገልጸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ውድ እውነት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። በምዕራፍ 14 ላይ ስለዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት በዝርዝር እንመለከታለን። ይህ ዝግጅት አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍትሕም ምሕረትም  የተንጸባረቀበት ነው። ይሖዋ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ፍጹም የሆነውን ፍትሑን ሳያዛባ ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ምሕረት ሊያሳይ ይችላል።—ሮሜ 3:21-26

የይሖዋ ፍትሕ ማራኪ ነው

12, 13. (ሀ) የይሖዋ ፍትሕ ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚጋብዘን ለምንድን ነው? (ለ) ዳዊት የይሖዋን ፍትሕ በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? ይህስ ሊያጽናናን የሚችለው እንዴት ነው?

12 የይሖዋ ፍትሕ ርኅራኄ የጎደለውና ከእሱ እንድንርቅ የሚያደርግ ሳይሆን እንድንወደውና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ፍትሕ ወይም ጽድቅ ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ይገልጻል። ይሖዋ ፍትሑን የሚገልጥባቸውን አንዳንድ ማራኪ ገጽታዎች እንመልከት።

13 ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ ለአገልጋዮቹ ታማኝ እንዲሆን ይገፋፋዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ይህን በራሱ ሕይወት ማየት ችሏል። ዳዊት ከራሱ የሕይወት ተሞክሮም ሆነ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ካደረገው ምርምር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ ደርሷል? “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 37:28 አ.መ.ት) ይህ እንዴት የሚያጽናና ዋስትና ነው! አምላካችን ለእሱ ታማኝ የሆኑትን መቼም ቢሆን አይተዋቸውም። በመሆኑም ይሖዋ እንደማይከዳንና ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልን ልንተማመን እንችላለን። ፍትሑ ለዚህ ዋስትና ነው!—ምሳሌ 2:7, 8

14. ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለድሆች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 የአምላክ ፍትሕ የተቸገሩ ሰዎችን ስሜትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ለድሆች እንደሚያስብ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል ሕጉ ወላጅ የሌላቸው ልጆችና መበለቶች ተገቢውን እንክብካቤ ሊያገኙ የሚችሉበትን ዝግጅት ያካተተ ነው። (ዘዳግም 24:17-21) ይሖዋ እንዲህ ያሉ ቤተሰቦች፣ ኑሮ ምን ያህል ሊከብድባቸው እንደሚችል ስለሚያውቅ አባታዊ እንክብካቤ  የሚያደርግላቸው ከመሆኑም በላይ “ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል።” (ዘዳግም 10:18፤ መዝሙር 68:5) እስራኤላውያን ረዳት የሌላቸውን ሴቶችና ልጆች የሚበድሉ ከሆነ ይሖዋ የእነዚህን ሰዎች ጩኸት እንደሚሰማና እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። “ቁጣዬም ይጸናባችኋል” ሲል ተናግሯል። (ዘጸአት 22:22-24) ቁጣ ከይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት አንዱ ባይሆንም እንኳ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ኢፍትሐዊ ድርጊት በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉና ረዳት በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግፍ የጽድቅ ቁጣ እንዲቆጣ ያነሳሳዋል።—መዝሙር 103:6

15, 16. ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳየው ግሩም ማስረጃ ምንድን ነው?

15 በተጨማሪም ይሖዋ “በፍርድ የማያደላ፣ መማለጃም የማይቀበል” መሆኑን ገልጿል። (ዘዳግም 10:17) ይሖዋ በሥልጣን ላይ እንዳሉ ብዙ ሰዎች በቁሳዊ ሀብት ወይም ከውጭ በሚታይ ነገር አይደለልም። ምንም ዓይነት የወገናዊነትና የአድሏዊነት ስሜት አይታይበትም። ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳይ አንድ ግሩም ማስረጃ እንመልከት። የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች በመሆን የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ የተዘረጋላቸው በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ “በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ” ነው። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ይህ አስደናቂ ተስፋ የተዘረጋው በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ የትኛውም ዓይነት የቆዳ ቀለም ላላቸው ወይም በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ነው። ከዚህ የላቀ እውነተኛ ፍትሕ ሊኖር ይችላል?

16 ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ በጥንቃቄ ልንመረምረው የሚገባ ሌላ ገጽታም አለው። ይህም የጽድቅ ሥርዓቱን በሚጥሱ ሰዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ የሚመለከት ነው።

ሳይቀጣ አያልፍም

17. በዚህ ዓለም ውስጥ የሚታዩት አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች የይሖዋን ፍትሕ አጠያያቂ ሊያደርጉ የማይችሉት ለምን እንደሆነ አብራራ።

17 አንዳንዶች ‘ይሖዋ ዓመጽን በቸልታ የማያልፍ ከሆነ በዛሬው ጊዜ ግፍና ምግባረ ብልሹነት ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው?’ ብለው ሊጠይቁ  ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች መስፋፋት የይሖዋን ፍትሕ አጠያያቂ ሊያደርግ አይችልም። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ የሚታዩት አብዛኞቹ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ሰዎች ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ምክንያት የመጡ ናቸው። ራሳቸው በመረጡት የኃጢአት ጎዳና የሚመላለሱ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች መስፋፋታቸው አያስገርምም። ሆኖም ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አይቀጥልም።—ዘዳግም 32:5

18, 19. ይሖዋ የጽድቅ ሕግጋቱን ሆን ብለው የሚጥሱ ሰዎችን ለዘላለም እንደማይታገሥ የሚያሳየው ምንድን ነው?

18 ይሖዋ በቅን ልቦና ተነሳስተው ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ታላቅ ምሕረት የሚያሳይ ቢሆንም ቅዱስ በሆነው ስሙ ላይ ነቀፋ የሚያስከትል ሁኔታን ለዘላለም አይታገሥም። (መዝሙር 74:10, 22, 23) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ አይዘበትበትም፤ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ያደርጋል። ይሖዋ ‘ርኅሩኅ፣ ቸር፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ የማይተው’ አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6, 7 አ.መ.ት) በመሆኑም ይሖዋ ሆን ብለው የጽድቅ ሕግጋቱን የሚጥሱ ሰዎችን የቀጣባቸው ጊዜያት አሉ።

19 ለምሳሌ ያህል አምላክ ከጥንት እስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበረ እንመልከት። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ እንኳ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ ዓምጸዋል። ምንም እንኳ መጥፎ ድርጊታቸው ‘ቢያሳዝነውም’ ወዲያው እርግፍ አድርጎ አልተዋቸውም። (መዝሙር 78:38-41) ከዚህ ይልቅ በተደጋጋሚ ጊዜያት ምሕረት በማሳየት ከመጥፎ መንገዳቸው መመለስ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። “ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፣ . . . የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?” ሲል ተማጽኗቸዋል። (ሕዝቅኤል 33:11) ይሖዋ ሕይወትን እንደ ውድ ነገር ስለሚመለከት በተደጋጋሚ ጊዜያት ነቢያቱን በመላክ እስራኤላውያን ከመጥፎ መንገዳቸው  እንዲመለሱ ለማድረግ ሞክሯል። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ልበ ደንዳና የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋን ለመስማትና ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ብለዋል። በመጨረሻም ይሖዋ ቅዱስ የሆነው ስሙ እንዳይነቀፍ ሲል ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጣቸው።—ነህምያ 9:26-30

20. (ሀ) ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ስለ እሱ ምን ያስተምረናል? (ለ) አንበሳ የይሖዋን ፍትሕ የሚወክል ተስማሚ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የነበረው ግንኙነት ስለ እሱ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ። ሁሉን ማየት የሚችሉት ዓይኖቹ የሚፈጸመውን ዓመጽ ሁሉ እንደሚመለከቱና ይህም እሱን እንደሚያሳዝነው ያስገነዝበናል። (ምሳሌ 15:3) በተጨማሪም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል ሁኔታ ካለ ምሕረት ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ማወቃችን የሚያጽናና ነው። ከዚህም ሌላ ይሖዋ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ አይቸኩልም። ይሖዋ ለረጅም ጊዜ ስለሚታገሥ ብዙ ሰዎች አምላክ በክፉዎች ላይ እርምጃ አይወስድም ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ይደርሳሉ። ሆኖም አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት መለኮታዊ ትዕግሥት ገደብ እንዳለው ስለሚያሳይ እንዲህ ያለው የሰዎች አመለካከት ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። ይሖዋ ለጽድቅ የቆመ አምላክ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ፍትሕን ለማስከበር ቆራጥ አቋም መውሰድ ሲሳናቸው ይታያል። ይሖዋ ግን ትክክል ለሆነው ነገር ምንጊዜም ቆራጥ አቋም አለው። አንበሳ ድፍረት የሚጠይቀውን የፍትሕ ባሕርይ የሚወክል  እንደመሆኑ መጠን ከአምላክና ከዙፋኑ ጋር ተያይዞ መገለጹ የተገባ ነው። * (ሕዝቅኤል 1:10፤ ራእይ 4:7) በመሆኑም ይሖዋ ግፍን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ለማስወገድ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው የይሖዋን ፍትሕ በሚከተለው መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል:- አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ እርምጃ ይወስዳል፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ምሕረት ያደርጋል።—2 ጴጥሮስ 3:9

የፍትሕ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረብ

21. ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ ስለሚወስድበት መንገድ ስናሰላስል ስለ እሱ ምን አመለካከት ሊያድርብን ይገባል? ለምንስ?

21 ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ ስለሚወስድበት መንገድ ስናሰላስል ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ብቻ የቆመ ርኅራኄ የሌለው ጨካኝ ፈራጅ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይገባንም። ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ ለልጆቹ መልካም ነገር እንደሚያስብ አፍቃሪ ሆኖም ጥብቅ አቋም ያለው አባት አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ይሖዋ ፍትሐዊ ወይም ጻድቅ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅ አቋም ያለው ቢሆንም የእሱን እርዳታና ምሕረት ለሚሹት ምድራዊ ልጆቹ ርኅራኄ ያሳያል።—መዝሙር 103:10, 13

22. ይሖዋ ፍትሑን መሠረት በማድረግ ምን ተስፋ ዘርግቶልናል? ይህን ያደረገልንስ ለምንድን ነው?

22 የአምላክ ፍትሕ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት ብቻ የቆመ እንዳልሆነ ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ ፍትሑን መሠረት በማድረግ አስደሳች ተስፋ ማለትም ‘ጽድቅ በሚኖርበት’ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላካችን ይህን ያደረገው ፍትሑ በተቻለ መጠን ሰዎችን ለማዳን እንጂ ለማጥፋት የቆመ ስላልሆነ ነው። በእርግጥም ስለ ይሖዋ ፍትሕ ያለን ግንዛቤ እየጨመረ በሄደ መጠን ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ እንገፋፋለን። ይሖዋ ይህን ድንቅ ባሕርይ ያንጸባረቀባቸውን መንገዶች በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ በጥልቀት እንመረምራለን።

^ አን.20 ይሖዋ ከሃዲ በሆነችው እስራኤል ላይ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድ ሲገልጽ ራሱን በአንበሳ መስሏል።—ኤርምያስ 25:38፤ ሆሴዕ 5:14