በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 12

“በአምላክ ዘንድ ግፍ አለን?”

“በአምላክ ዘንድ ግፍ አለን?”

1. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል?

አንዲት አረጋዊት መበለት ያጠራቀሟትን ገንዘብ ሰው አጭበርብሮ ወሰደባቸው። አንድ አራስ ልጅ አውላላ ሜዳ ላይ ተጥሎ ተገኘ። አንድ ሰው ባልሠራው ወንጀል ተከሶ ለእስር ተዳረገ። እንዲህ ስለመሳሰሉት ድርጊቶች ምን ይሰማሃል? እነዚህ ነገሮች አእምሮህን እንደሚረብሹት የታወቀ ነው፤ ደግሞም አያስገርምም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ነገር የመለየትና የማመዛዘን ችሎታ ተሰጥቶታል። በመሆኑም ግፍ ሲፈጸም ስናይ ያናድደናል። ግፍ የተፈጸመበት ሰው እንዲካስና በዳዩ ትክክለኛውን ቅጣት እንዲያገኝ እንፈልጋለን። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ‘ለመሆኑ አምላክ ይህን ግፍ ያያል? የሚያይ ከሆነስ ለምን እርምጃ አይወስድም?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

2. ዕንባቆም ሲፈጸም ስላየው ግፍ ምን ተሰምቶት ነበር? ይሖዋስ ያልገሠጸው ለምንድን ነው?

2 ከጥንት ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በተለያዩ ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አንስተዋል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ዕንባቆም “በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዕንባቆም 1:3) ዕንባቆም በቅንነት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በማቅረቡ ይሖዋ አልገሠጸውም። ምክንያቱም ሰዎች የፍትሕ ባሕርይ እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው እሱ ራሱ ነው። አዎን፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የእሱን ፍጹም ፍትሕ እንድናንጸባርቅ አድርጎ ፈጥሮናል።

ይሖዋ ግፍን ይጠላል

3. ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ  ክፉ እንደ ሆነ አየ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:5) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። ብዙውን ጊዜ ስለ ፍትሕ መጓደል ያለን ግንዛቤ በሰማናቸው ወይም ባየናቸው አንዳንድ ክስተቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በጣም ውስን ነው። በአንጻሩ ግን ይሖዋ በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል! ከዚህም በላይ የሰዎችን የልብ ዝንባሌ ማለትም ከሚፈጽሟቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በስተጀርባ ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ መረዳት ይችላል።—ኤርምያስ 17:10

4, 5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ሰዎች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በራሱ በይሖዋ ላይስ በደል የተፈጸመው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከማየት ባሻገር በዚህ ሳቢያ ለሚሰቃዩት ሰዎች ያስባል። ይሖዋ ጠላት የሆኑ መንግሥታት ሕዝቦቹን “ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበር።” (መሳፍንት 2:18) አንዳንድ ሰዎች የፍትሕ መጓደል የዕለት ተዕለት ክስተት ሲሆንባቸው ሁኔታውን እየተላመዱት ስለሚሄዱ በደል እየተፈጸመባቸው ላሉ ሰዎች ያላቸው አዘኔታ እንደሚቀንስ አስተውለህ ይሆናል። ይሖዋ ግን እንዲህ አይደለም! በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለ6,000 ዓመታት ሲመለከት የቆየ ቢሆንም እንዲህ ላለው ድርጊት ያለው ጥላቻ አልቀነሰም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ” እና “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” በይሖዋ ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ይገልጽልናል።—ምሳሌ 6:16-19

5 በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ጨቋኝ ገዥዎች አጥብቆ እንዳወገዘ ልብ በል። “ፍርድን [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን?” ሲል በነቢዩ አማካኝነት ጠይቋቸዋል። ሥልጣናቸውን ምን ያህል አላግባብ እየተጠቀሙበት እንዳሉ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ከገለጸላቸው በኋላ እነዚህ ብልሹ መሪዎች ምን እንደሚጠብቃቸው እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፣ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።” (ሚክያስ 3:1-4) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ምን ያህል እንደሚጠላ የሚያሳይ ነው! እንዲህ ያለው በደል በራሱም ላይ  ደርሷል! ሰይጣን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋን ሲሳደብ ኖሯል። (ምሳሌ 27:11) ከዚህም በተጨማሪ ‘ምንም ኃጢአት ያልሠራው’ ልጁ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በተገደለበት ጊዜ የተፈጸመው ከሁሉ የከፋ ግፍ ይሖዋን በእጅጉ አሳዝኖታል። (1 ጴጥሮስ 2:22፤ ኢሳይያስ 53:9) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ግፍ በሚፈጸምባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ይህ ሁኔታ በጣም ያሳስበዋል።

6. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል? ለምንስ?

6 ይሁንና ግፍ ሲፈጸም ስናይ ወይም በራሳችን ላይ በደል ሲደርስብን መበሳጨታችን ወይም ማዘናችን ያለ ነገር ነው። የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ሲሆን ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ደግሞ ከይሖዋ ባሕርይ ጋር ጨርሶ አይሄድም። (ዘፍጥረት 1:27) ታዲያ ይሖዋ ፍትሕ ሲጓደል እያየ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?

በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ

7. የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ ጥያቄ የተነሳው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

7 የዚህ ጥያቄ መልስ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ከተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው ፈጣሪ ምድርንም ሆነ በእርስዋ የሚኖሩትን ሁሉ የመግዛት መብት አለው። (መዝሙር 24:1፤ ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ አንድ ጥያቄ ተነሳ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው ሰው አዳም መኖሪያው በሆነችው በገነት ውስጥ ከነበረ አንድ ዛፍ እንዳይበላ አምላክ አዝዞት ነበር። ይህን ትእዛዝ ጥሶ ፍሬውን ቢበላስ? አምላክ “ሞትን ትሞታለህ” ሲል አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አምላክ ለአዳምም ሆነ ለሚስቱ ለሔዋን የሰጠው ትእዛዝ ከባድ አልነበረም። ሆኖም ሰይጣን፣ አምላክ ፍሬውን እንዳይበሉ የከለከላቸው አላግባብ እንደሆነ በመግለጽ ሔዋንን አሳመናት። ከፍሬው ብትበላ ውጤቱ ምን ይሆናል? ሰይጣን እንዲህ አላት:- ‘ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።’—ዘፍጥረት 3:1-5

8. (ሀ) ሰይጣን ለሔዋን የነገራት ነገር ምን መልእክት ያዘለ ነው? (ለ) ሰይጣን የአምላክን ሉዓላዊነት በተመለከተ ያነሳው ጥያቄ ምንድን ነው?

 8 ሰይጣን እንዲህ ብሎ ሲናገር ይሖዋ ሔዋንን የደበቃት ትልቅ ቁም ነገር እንዳለ ብቻ ሳይሆን እንደዋሻትም መናገሩ ነበር። ሰይጣን በቀጥታ አምላክ ሉዓላዊ ገዥ አይደለም ብሎ አልተከራከረም። ከዚህ ይልቅ ያነሳው ጥያቄ ‘አምላክ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑ ተገቢ ነው?’ የሚል ነው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥነቱን በአግባቡ ወይም ለተገዥዎቹ በሚበጅ መንገድ አልተጠቀመበትም ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።

9. (ሀ) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመጻቸው ምን አስከተለባቸው? ሰይጣን የተናገረው ውሸት ምን ወሳኝ ጥያቄዎች አስነስቷል? (ለ) ይሖዋ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

9 አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ በመብላት በአምላክ ላይ ዓመጹ። በዚህም ምክንያት አምላክ አስቀድሞ በደነገገው መሠረት ሞት ተበየነባቸው። ሰይጣን የተናገረው ውሸት መልስ የሚያሻቸው ወሳኝ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ይሖዋ የሰውን ልጅ የመግዛት መብት አለው ወይስ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው? ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥነቱን የሚጠቀመው ለሌሎች በሚበጅ መንገድ ነው? ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚያስችለውን ኃይሉን ተጠቅሞ እነዚህን ዓመጸኞች ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ሆኖም ጥያቄ የተነሳው የአምላክን ኃይል ሳይሆን አገዛዙን በሚመለከት ነው። ስለዚህ አዳምን፣ ሔዋንንና ሰይጣንን ወዲያውኑ ማጥፋት የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ አይሆንም። እንዲያውም እንዲህ ያለው እርምጃ የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት ይበልጥ አጠያያቂ ሊያደርግ ይችል ነበር። የሰው ልጆች ያለ አምላክ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት የግድ ጊዜ መስጠት ያስፈልግ ነበር።

10. ታሪክ የሰውን ልጅ አገዛዝ በተመለከተ ምን ሐቅ አረጋግጧል?

10 ታዲያ ያለፈው የሰው ልጅ ታሪክ ምን ሐቅ አረጋግጧል? ባለፉት ሺህ ዓመታት ሰዎች አምባገነናዊም ሆኑ ዲሞክራሲያዊ አገዛዞችን እንዲሁም የሶሻሊዝምና የኮሚኒዝም ሥርዓትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት መስተዳድሮችን ሞክረዋል። “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ለመግዛት  ያደረገው ሙከራ ያስከተለውን ውጤት ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። (መክብብ 8:9) ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል መናገሩ ትክክል ነው።—ኤርምያስ 10:23

11. ይሖዋ የሰው ዘር መከራ እንዲደርስበት የፈቀደው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ብዙ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል መጀመሪያውኑም ያውቅ ነበር። ታዲያ ይህ እንደሚሆን እያወቀ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ ኢፍትሐዊ አይሆንም? በፍጹም! ለምሳሌ ያህል ልጅህ በጣም በመታመሙ ሕይወቱ እንዲተርፍ የግድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልገዋል እንበል። ቀዶ ሕክምናው ልጅህን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደሚያሰቃየው ስለምታውቅ ሁኔታው በጣም እንደሚያስጨንቅህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሕክምናው ልጅህን ከበሽታው እንደሚገላግለውና በቀሪው ሕይወቱ ጤናማ ሆኖ እንዲኖር እንደሚረዳው ታውቃለህ። በተመሳሳይም አምላክ ሰብዓዊ አገዛዝ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል ያውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:16-19) ሆኖም ዘላቂና አስተማማኝ እፎይታ እንዲገኝ ከተፈለገ የሰው ልጆች በሙሉ ዓመጽ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት እንዲመለከቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያውቅ ነበር። በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ ለዘለቄታው ወይም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ሊያገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው።

የሰውን ልጅ ታማኝነት በተመለከተ የተነሳ ጥያቄ

12. በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው ሰይጣን የሰው ልጆችን ምን ብሎ ከሷል?

12 ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳ አንድ ሌላ ጥያቄም አለ። ሰይጣን የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛና ጻድቅ ስለመሆኑ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት የይሖዋን ስም ከማጥፋቱም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች ለፈጣሪያቸው ያላቸው ታማኝነት አጠያያቂ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ የእነሱንም ስም አጥፍቷል። ለምሳሌ ያህል ሰይጣን ጻድቁን ሰው ኢዮብን አስመልክቶ ለይሖዋ ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ በል:- “እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን  ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፣ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።”—ኢዮብ 1:10, 11

13. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያቀረበው ክስ ምን መልእክት ያዘለ ነው? ይህ ክስ ሁሉንም የሰው ዘር የሚመለከት ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

13 እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ኢዮብ ለአምላክ ያደረ ሰው ሊሆን የቻለው ይሖዋ ጥበቃ ስላደረገለትና ስለተንከባከበው ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ የሆነው በፍቅር ተነሳስቶ ሳይሆን በጥቅም ተደልሎ ነው። በመሆኑም ሰይጣን፣ አምላክ በረከቱን ቢነፍገው ኢዮብ ፈጣሪውን ይሰድባል ሲል ተከራክሯል። ሰይጣን፣ ኢዮብ “ፍጹምና [“ነቀፋ የሌለበት፣” አ.መ.ት] ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው” እንደነበረና በዚህ ረገድ ጎልቶ የሚታይ ግሩም ምሳሌ እንደሆነ ያውቅ ነበር። * ስለሆነም ኢዮብ አምላክን እንዲክድ ማድረግ ቻለ ማለት የተቀረውን የሰው ዘር በተመለከተም ምን ትርጉም ሊያስተላልፍ እንደሚችል አስብ። በመሆኑም ሰይጣን ያነሳው ጥያቄ ሁሉንም የአምላክ አገልጋዮች የሚመለከት ነው። እንዲያውም ‘ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል’ በማለት ጥያቄው ኢዮብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰው ዘሮችንም የሚመለከት እንደሆነ ጠቁሟል።—ኢዮብ 1:8፤ 2:4

14. ሰይጣን በሰዎች ላይ የሰነዘረውን ክስ በተመለከተ ታሪክ ምን ይመሠክራል?

14 እንደ ኢዮብ ያሉ ብዙ ሰዎች መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንደተገኙ ታሪክ ይመሠክራል። ይህ ደግሞ የሰይጣንን አባባል ውድቅ ያደርገዋል። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሲሆን ይህ አቋማቸው ሰይጣን የሰው ልጆች መከራ ከደረሰባቸው አምላክን ከማገልገል ወደ ኋላ ይላሉ ሲል ላነሳው ክርክር አጥጋቢ መልስ አስገኝቷል። (ዕብራውያን 11:4-38) አዎን፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን ለመተው ፈቃደኞች አልሆኑም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው እንኳ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው በመተማመን ይበልጥ ወደ እሱ ተጠግተዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-10

15. አምላክ ቀደም ሲል የወሰዳቸውንና ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች አስመልክቶ ምን ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?

 15 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍትሕ የተገለጠው ሉዓላዊነቱንና ሰዎች ለእሱ ያላቸውን ታማኝነት በተመለከተ ከተነሱት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ይሖዋ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራት ላይ የበየነውን ፍርድ የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። በተጨማሪም ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች የሚገልጹ ትንቢቶች አሉ። ይሖዋ ቀደም ሲል የወሰዳቸውም ሆኑ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ትክክለኛ ናቸው ብለን ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

የአምላክ ፍትሕ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ‘ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር አያጠፋም’

16, 17. ሰዎች ከእውነተኛ ፍትሕ ጋር በተያያዘ ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

16 ይሖዋ “መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሐዊ፣” NW] ነው” መባሉ የተገባ ነው። (ዘዳግም 32:4) ማንኛችንም ብንሆን ስለ ራሳችን እንዲህ ብለን መናገር አንችልም። ስለ ማንኛውም ነገር ያለን ግንዛቤ ውስን በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር መለየት ሊሳነን ይችላል። አብርሃምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሰዶም በክፋት ድርጊቶች ተሞልታ የነበረ ቢሆንም እንኳ አብርሃም ይሖዋ ከተማዋን እንዳያጠፋት ተማጽኖት ነበር። “በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን?” ሲል ይሖዋን ጠይቋል። (ዘፍጥረት 18:23-33) ይሖዋ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር አያጠፋም። በሰዶም ላይ ‘እሳትና ዲን ያዘነበው’ ጻድቁ ሎጥና ልጆቹ ሸሽተው ወደ ዞዓር ከተማ ከገቡ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 19:22-24) በአንጻሩ ደግሞ ዮናስ አምላክ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት በማድረጉ ‘ተቆጥቶ ነበር።’ ዮናስ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚጠፉ ተናግሮ ስለነበር ከልብ ንስሐ ቢገቡም እንኳ መጥፋት አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ነበር።—ዮናስ 3:10–4:1

17 ይሖዋ ፍትሑ ክፉዎችን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጻድቃንንም ለማዳን የቆመ እንደሆነ ለአብርሃም አረጋግጦለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ዮናስ ይሖዋ መሐሪ አምላክ መሆኑን መገንዘብ አስፈልጎት ነበር። ይሖዋ ክፉ  ሰዎች አካሄዳቸውን ካስተካከሉ ‘ይቅር ለማለት’ ዝግጁ ነው። (መዝሙር 86:5) ይሖዋ ለሥልጣናቸው እንደሚሰጉ ሰብዓዊ ገዦች ኃይሉን በማሳየት ሌሎችን ለማስፈራራት ሲል ብቻ የቅጣት እርምጃ አይወስድም ወይም እንደ ደካማ ሊያስቆጥረኝ ይችላል በሚል ስሜት ርኅራኄ ከማሳየት ወደ ኋላ አይልም። ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።—ኢሳይያስ 55:7፤ ሕዝቅኤል 18:23

18. ይሖዋ በስሜት ብቻ ተገፋፍቶ እንደማይፈርድ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።

18 ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ ተዘፍቀው በነበረበት ጊዜ ይሖዋ “እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፣ ጉስቁልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ” ሲል ጥብቅ አቋሙን ገልጿል። (ሕዝቅኤል 7:3, 4) በመሆኑም ሰዎች ከመጥፎ ድርጊታቸው አልታረም ሲሉ ይሖዋ ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ፍርድ የሚሰጠው በቂ በሆነ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ነው። ስለሆነም ይሖዋ ‘የሰዶምና የገሞራን ጩኸት’ በሰማ ጊዜ “እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ይሖዋ ተጨባጭ ማስረጃ ሳያገኙ ለመፍረድ እንደሚቸኩሉ ሰዎች ባለመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በእርግጥም ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ፍትሕ የማያጓድል የታመነ አምላክ” ነው።—ዘዳግም 32:4 NW

በይሖዋ ፍትሕ ላይ እምነት ይኑርህ

19. ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ የሚወስድበትን መንገድ በተመለከተ አእምሯችን ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን?

19 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ቀደም ባሉት ዘመናት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ይሰጣል ብለን ልንጠብቅ አንችልም። በተጨማሪም ይሖዋ ወደፊት በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ በሰዎች ላይ ስለሚወስደው እርምጃ ዝርዝር መረጃ አናገኝም። እንዲህ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወይም ትንቢቶች ግልጽ በማይሆኑልን ጊዜ “አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ” ሲል እንደጻፈው  እንደ ነቢዩ ሚክያስ ዓይነት ታማኝነት ልናሳይ እንችላለን።—ሚክያስ 7:7

20, 21. ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛ እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን እንችላለን። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚፈጸሙ አንዳንድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ችላ የተባሉ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ” በማለት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። (ሮሜ 12:19) ይሖዋን በትዕግሥት የምንጠባበቅ ከሆነ “በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ [“ግፍ፣” NW] አለ ወይ? አይደለም” ሲል እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ጠንካራ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ሮሜ 9:14

21 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የምንኖርበት ‘ዘመን አስጨናቂ’ እንደሚሆን የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙ ሰዎች በሚደርስባቸው “ግፍ” እና ጭቆና እየተሰቃዩ ነው። (መክብብ 4:1) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን ግፍን የሚጠላ ሲሆን በዚህ ምክንያት እየተሰቃዩ ላሉ ሰዎች ከልብ ያዝናል። ይሖዋንና ሉዓላዊነቱን በታማኝነት ከደገፍን በመንግሥቱ አማካኝነት ግፍንና ጭቆናን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

^ አን.13 ይሖዋ ኢዮብን አስመልክቶ ሲናገር ‘በምድር ላይ እንደ እርሱ ያለ ሰው የለም’ ብሏል። (ኢዮብ 1:8) ስለሆነም ኢዮብ የኖረው ዮሴፍ በሞተበትና ሙሴ የእስራኤል መሪ ሆኖ በተሾመበት ዘመን መካከል እንደሆነ መገመት ይቻላል። ስለዚህ በወቅቱ እንደ ኢዮብ ያለ ለአምላክ ታማኝ የሆነ ሰው አልነበረም ሊባል ይችላል።