በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 15

ኢየሱስ ‘በምድር ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል’

ኢየሱስ ‘በምድር ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል’

1, 2. ኢየሱስ የተቆጣው መቼ ነው? ለምንስ?

ኢየሱስ በጣም ተቆጥቷል፤ ደግሞም ሊቆጣ ይገባዋል። ይሁንና ኢየሱስ የዋህ ሰው ስለሆነ እንዲህ መቆጣቱ ሊያስገርምህ ይችላል። (ማቴዎስ 21:4, 5) በእርግጥ ቁጣው የጽድቅ ቁጣ ስለነበር ስሜቱ ከቁጥጥር ውጪ አልሆነም። * ይሁን እንጂ ይህ ሰላማዊ ሰው እንዲህ የተቆጣው ለምንድን ነው? አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም በማየቱ ነው።

2 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለነበረው ቤተ መቅደስ ልዩ አክብሮት ነበረው። በምድር ላይ ሰማያዊ አባቱ የሚመለክበት ብቸኛው ቅዱስ ሥፍራ ይህ ነበር። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ አይሁዳውያን ረጅም መንገድ ተጉዘው ለአምልኮ ወደዚህ ሥፍራ ይመጡ ነበር። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አሕዛብ እንኳ ሳይቀሩ ለእነሱ ወደተመደበው ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ይመጡ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደጀመረ አካባቢ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ አንድ እጅግ አሳዛኝ ነገር ተመለከተ። ሥፍራው የገበያ እንጂ የአምልኮ ቦታ አይመስልም ነበር! በነጋዴዎችና በገንዘብ ለዋጮች ተጨናንቋል። ታዲያ አግባብ ያልሆነው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቤተ መቅደስ ይጠቀሙበት የነበረው ሕዝቡን ለመበዝበዝ አልፎ ተርፎም ለመዝረፍ ነበር። እንዴት?—ዮሐንስ 2:14

3, 4. በይሖዋ ቤት ውስጥ ምን ብዝበዛ ይካሄድ ነበር? ኢየሱስስ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ምን እርምጃ ወሰደ?

3 የሃይማኖት መሪዎቹ ለቤተ መቅደሱ ግብር የሚከፍል ማንኛውም ሰው አንድ የተወሰነ ዓይነት ሳንቲም ብቻ እንዲጠቀም የሚያዝ ሕግ አውጥተው ነበር። ግብር ከፋዮቹ እንዲህ ዓይነቱን ሳንቲም ለማግኘት ገንዘባቸውን ለመመንዘር ይገደዱ ነበር። ስለዚህ ገንዘብ ለዋጮች በቤተ መቅደሱ ውስጥ ጠረጴዛ ዘርግተው እያተረፉ ገንዘብ ይመነዝሩ ነበር። እንስሳትን  መሸጥም ሌላው ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ ነበር። መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡ ሰዎች በከተማው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ነጋዴ እንስሳ መግዛት ይችሉ የነበረ ቢሆንም ያመጡት እንስሳ በቤተ መቅደሱ ኃላፊዎች ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። ከዚያው ከቤተ መቅደሱ የሚገዙት እንስሳት ግን ተቀባይነት እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነበር። ነጋዴዎቹ እነዚህ ሰዎች አማራጭ እንደሌላቸው ስለሚያውቁ አንዳንድ ጊዜ ውድ ዋጋ ያስከፍሏቸው ነበር። * ይህ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ነበር!

“ይህን ከዚህ ውሰዱ”

4 ኢየሱስ በአባቱ ቤት እንዲህ ያለ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጸም በዝምታ ሊመለከት አይችልም! ጅራፍ አበጅቶ ከብቶቹንና በጎቹን ከቤተ መቅደሱ አስወጣቸው። ከዚያም ወደ ገንዘብ ለዋጮቹ በመሄድ ጠረጴዛቸውን ገለበጠ። ጠረጴዛው ላይ ተቆልሎ የነበረው ሳንቲም ወለሉ ላይ ሲበተን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ርግብ ሻጮቹን “ይህን ከዚህ ውሰዱ” ሲል በቁጣ ተናገራቸው። (ዮሐንስ 2:15, 16) ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ብሎ ሊቃወመው የደፈረ አልነበረም።

“ልክ እንደ አባቱ”

5-7. (ሀ) ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ያሳለፈው ሕይወት ፍትሕን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል? የእሱን ሕይወት በመመርመርስ ምን ልንማር እንችላለን? (ለ) ክርስቶስ በይሖዋ ሉዓላዊነትና ስም ላይ የተነሳውን አግባብ ያልሆነ ክስ ውድቅ ያደረገው እንዴት ነው?

5 እርግጥ ነው፣ ነጋዴዎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ተመልሰው በመምጣት ንግዳቸውን ቀጥለው ነበር። ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ይህንኑ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ ስላገኛቸው ቤቱን “የሌቦች ዋሻ” ያደረጉትን ሰዎች በመቃወም በአንድ ወቅት ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት በመጥቀስ አወገዛቸው። (ማቴዎስ 21:13፤ ኤርምያስ 7:11) አዎን፣ ኢየሱስ ሕዝቡን ሲበዘብዙና የአምላክን ቤተ መቅደስ ሲያረክሱ በመመልከቱ አባቱ የተሰማው ዓይነት ስሜት ተሰምቶታል። ይህ ደግሞ ምንም አያስገርምም! ኢየሱስ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ከአባቱ ብዙ ተምሯል።  በዚህም የተነሳ የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ ተላብሷል። በመሆኑም ኢየሱስ “ልክ እንደ አባቱ ነው” ቢባል ተገቢ ነው። ስለዚህ ስለ ይሖዋ የፍትሕ ባሕርይ በሚገባ ለማወቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ከመመርመር የተሻለ ዘዴ የለም።—ዮሐንስ 14:9, 10

6 ሰይጣን ይሖዋ አምላክን ውሸታም ብሎ አላግባብ ሲወነጅልና በይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥር ክስ ሲሰነዝር የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሁኔታውን በቅርብ ይከታተል ነበር። ይህ የይሖዋን ስም በእጅጉ የሚያጎድፍ መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነበር! በተጨማሪም ኢየሱስ ለጥቅም ካልሆነ በስተቀር ማንም ፍጡር በፍቅር ተገፋፍቶ ይሖዋን አያገለግልም ሲል ሰይጣን ያነሳውን ክርክር ሰምቷል። ኢየሱስ በእነዚህ የሐሰት ክሶች እጅግ እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። ይህ ውንጀላ መሠረተ ቢስ መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሲያውቅ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት! (2 ቆሮንቶስ 1:20) ይህን የሚያከናውነው እንዴት ነው?

7 ምዕራፍ 14 ላይ እንደተመለከትነው የይሖዋ ፍጥረታት ለአምላካቸው ታማኞች አይሆኑም ሲል ሰይጣን ላነሳው ክርክር ኢየሱስ የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የይሖዋ ሉዓላዊነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲረጋገጥና ስሙ እንዲቀደስ ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ጥሏል። ኢየሱስ የይሖዋ ዋና ወኪል በመሆኑ በመላው ጽንፈ ዓለም መለኮታዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 5:31) በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወትም መለኮታዊ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር። ይሖዋ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፣ ፍርድንም [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ለአሕዛብ ያወራል” ብሏል። (ማቴዎስ 12:18) ኢየሱስ ይህ ቃል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ‘ፍትሕ ምን እንደሆነ’ ግልጽ አደረገ

8-10. (ሀ) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ያወጧቸው ወጎች ሕዝቡ ለሴቶችና አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ንቀት እንዲያድርበት ይገፋፉ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የአይሁዳውያን የቃል ሕግ ይሖዋ ያወጣውን የሰንበት ሕግ ያወሳሰበው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ የይሖዋን ሕግ ይወድና ያከብር ነበር። ይሁን እንጂ በዘመኑ  የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሕጉን ከማጣመማቸውም በላይ አላግባብ ይጠቀሙበት ነበር። ኢየሱስ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ . . . ፍርድንና [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር” ትተዋላችሁ ሲል ተናግሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:23) እነዚህ የአምላክ ሕግ አስተማሪዎች መለኮታዊ ‘ፍትሕ ምን እንደሆነ’ ግልጽ ከማድረግ ይልቅ እንዲድበሰበስና እንዲሰወር አድርገዋል። እንዴት? እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

9 ይሖዋ ሕዝቦቹ በአካባቢያቸው ከሚኖሩት አረማዊ ብሔራት ጋር እንዳይወዳጁ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (1 ነገሥት 11:1, 2) ይሁን እንጂ አንዳንድ አክራሪ የሃይማኖት መሪዎች ሕዝቡ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን ሁሉ በንቀት እንዲመለከቱ ይገፋፉ ነበር። ሌላው ቀርቶ የአይሁዳውያን የሕግ መጽሐፍ በሆነው በሚሽና ላይ “አሕዛብ ከእንስሳት ጋር የጾታ ግንኙነት የማድረግ ልማድ እንዳላቸው ስለሚታመን አንድ አይሁዳዊ ከብቱን በእነሱ ማረፊያ ማሳደር የለበትም” የሚል ደንብ ሰፍሮ ይገኛል። እንዲህ ያለው ጭፍን ጥላቻ አግባብ ካለመሆኑም በላይ ከሙሴ ሕግ መንፈስ ጋር የሚቃረን ነበር። (ዘሌዋውያን 19:34) ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ ሕጎችንም አውጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሚስት ከባሏ ጎን ሳይሆን ከኋላ ኋላ እየተከተለች እንድትሄድ የሚያዝ የቃል ሕግ ነበራቸው። አንድ ወንድ ሚስቱን ጨምሮ ከማንኛዋም ሴት ጋር በአደባባይ ቆሞ ማውራት አይችልም ነበር። ልክ እንደ ባሮች ሴቶችም ፍርድ ቤት ቆመው መመሥከር አይፈቀድላቸውም ነበር። ሌላው ቀርቶ ወንዶች ሴት ሆነው ባለመፈጠራቸው አምላክን የሚያመሰግኑበት የተለመደ ጸሎት ነበራቸው።

10 የአምላክ ሕግ የሃይማኖት መሪዎቹ ባወጧቸው ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎችና ደንቦች ተውጦ ነበር። ለምሳሌ ያህል የሰንበት ሕግ አይሁዳውያን ሥራ ከመሥራት ታቅበው የአምልኮ ሥርዓት እንዲያከናውኑና እንዲያርፉ ያዛል። ፈሪሳውያን ግን ይህን ሕግ ውስብስብና አስቸጋሪ አድርገውት ነበር። “ሥራ” ሲባል ምን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት የሚገልጽ የራሳቸውን ዝርዝር ደንብ አውጥተዋል። እንደ ማጨድና ማደን ያሉ 39 የተለያዩ የሥራ ዓይነቶችን በዝርዝር ይጠቅሱ ነበር። ይህ ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። አንድ ሰው በሰንበት ቁንጫ ቢገድል እንዳደነ ይቆጠራል? በመንገድ ሲያልፍ እሸት ቀጥፎ ቢበላ እንዳጨደ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል? የታመመን ሰው ቢፈውስ ሥራ ሠርቷል ሊባል ይችላል? እንዲህ  ያሉትን ጉዳዮች የሚመለከቱ የማያፈናፍኑ ዝርዝር ደንቦች ወጥተው ነበር።

11, 12. ኢየሱስ በአምላክ ቃል ውስጥ የማይገኙትን የፈሪሳውያን ወጎች እንደሚቃወም ያሳየው እንዴት ነው?

11 እንዲህ ያለ ወግና ሥርዓት ተንሰራፍቶ እያለ ኢየሱስ ሰዎች መለኮታዊ ፍትሕ ምን እንደሆነ በትክክል እንዲገነዘቡ የረዳቸው እንዴት ነው? ትምህርቱም ሆነ አኗኗሩ የእነዚህን ሃይማኖታዊ መሪዎች አቋም የሚያወግዝ ነበር። ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት። “ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ” በማለት ያወጧቸውን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ወጎች አውግዟል።—ማርቆስ 7:13

12 ኢየሱስ ፈሪሳውያን የሰንበትን ሕግ በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ እንደሆነና የሕጉን ዓላማ እንደሳቱ በግልጽ አስተምሯል። መሲሑ “የሰንበት ጌታ” እንደሆነ በመግለጽ በሰንበት ሰዎችን የመፈወስ ሥልጣን እንዳለው ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:8) ይህንንም ጎላ አድርጎ ለማሳየት በሰንበት ቀን በይፋ ፈውሷል። (ሉቃስ 6:7-10) እንዲህ ያሉት ፈውሶች በሺው ዓመት ግዛት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከናውናቸውን ተአምራት ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናሙናዎች ናቸው። ይህ የሺህ ዓመት ግዛት ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ ለብዙ መቶ ዘመናት ተጭኗቸው ከኖረው ከኃጢአትና ከሞት ቀንበር የሚገላገሉበት ታላቅ ሰንበት ይሆናል።

13. ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ምን ሕግ ተቋቁሟል? ይህስ ከሙሴ ሕግ የሚለየው እንዴት ነው?

13 በተጨማሪም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ በተቋቋመው አዲስ ሕግ ማለትም ‘በክርስቶስ ሕግ’ አማካኝነት ፍትሕ ምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ አድርጓል። (ገላትያ 6:2) ይህ ሕግ ቀደም ሲል እንደነበረው የሙሴ ሕግ በአብዛኛው የያዘው በዝርዝር የሰፈሩ ትእዛዛትን ሳይሆን መሠረታዊ ሥርዓቶችን ነው። ይሁንና አንዳንድ ቀጥተኛ የሆኑ ትእዛዛትንም ይዟል። ከእነዚህ ትእዛዛት አንዱን ኢየሱስ “አዲስ ትእዛዝ” ሲል ጠርቶታል። ተከታዮቹ እርሱ እንደወደዳቸው እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) አዎን፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ‘በክርስቶስ ሕግ’ የሚመሩ ሰዎች ሁሉ መለያ ምልክት ነው።

 ሕያው የሆነ የፍትሕ ምሳሌ

14, 15. ኢየሱስ የተሰጠው ሥልጣን ገደብ ያለው መሆኑን እንደተገነዘበ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ በእሱ ላይ ምን እምነት እንዲያድርብን ያደርገናል?

14 ኢየሱስ ፍቅርን በቃል በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። ‘በክርስቶስ ሕግ’ ይመራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህን ሕግ በመላ አኗኗሩ አንጸባርቋል። ኢየሱስ ፍትሕን ያንጸባረቀባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

15 በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት እንዳይፈጽም ይጠነቀቅ ነበር። ብዙውን ጊዜ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በመታበይና አለቦታቸው በመግባት ኢፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶችን እንደሚፈጽሙ አስተውለህ ይሆናል። ኢየሱስ ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አልነበረም። በአንድ ወቅት አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “መምህር ሆይ፣ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው” አለው። ሆኖም ኢየሱስ “አንተ ሰው፣ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ እንድሆን ማን ሾመኝ?” ሲል መለሰለት። (ሉቃስ 12:13, 14) ኢየሱስ እንዲህ ያለ መልስ መስጠቱ አያስገርምም? የኢየሱስ እውቀትና የማመዛዘን ችሎታ አልፎ ተርፎም አምላክ የሰጠው ሥልጣን በምድር ላይ ካለ ከማንም ሰው የላቀ እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች የመፍረድ ሥልጣን ስላልተሰጠው በጉዳዩ እጁን ጣልቃ ማስገባት አልፈለገም። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ በኖረባቸው ብዙ ሺህ ዓመታትም እንኳ ሳይቀር እንዲህ ያለውን የትሕትና ባሕርይ አሳይቷል። (ይሁዳ 9) ራሱን ዝቅ በማድረግ ትክክለኛውን ፍርድ ለይሖዋ መተዉ የሚደነቁ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት የሚያሳይ ነው።

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲሰብክ ፍትሕን ያንጸባረቀው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ የፍትሕ ባሕርይ ምሕረት የተንጸባረቀበት እንዴት ነው?

16 በሁለተኛ ደረጃ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሰበከበት መንገድ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር። ምንም ዓይነት አድልዎ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመስበክ ጥረት አድርጓል። በአንጻሩ ግን ፈሪሳውያን ድሃና ተራ የሆኑትን ሰዎች ይንቁ የነበረ ሲሆን አምሃሬትስ ወይም “የመሬት ሰዎች” በማለት ይጠሯቸው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ያለውን መድልዎ እንደማይደግፍ በግልጽ አሳይቷል። ምሥራቹን ለሰዎች ሲሰብክ አልፎ ተርፎም ከሰዎች ጋር ሲበላ፣ ሲመግባቸው፣ ሲፈውሳቸውም ሆነ ከሞት ሲያስነሳቸው “ሰዎች  ሁሉ” እውነትን እንዲያውቁ የሚፈልገው አባቱ ያለውን የፍትሕ ባሕርይ አንጸባርቋል። *1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

17 በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የኢየሱስ የፍትሕ ባሕርይ ምሕረት የተንጸባረቀበት ነበር። ኃጢአተኞችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ማቴዎስ 9:11-13) ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ከመርዳት ወደ ኋላ አይልም ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በዘመኑ እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሰዎች አሕዛብ የሆኑትን ሁሉ በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከቱ አላደረገም። ምንም እንኳ ኢየሱስ በዋነኝነት የተላከው ለአይሁዳውያን ቢሆንም በምሕረት ተገፋፍቶ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎችን የረዳበትና ያስተማረበት ጊዜ አለ። በአንድ ወቅት “በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም” ብሎ በመናገር የአንድን ሮማዊ መቶ አለቃ ልጅ ፈውሷል።—ማቴዎስ 8:5-13

18, 19. (ሀ) ኢየሱስ ለሴቶች አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የተወው ምሳሌ በድፍረትና በፍትሕ መካከል ያለውን ዝምድና እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው?

18 በተጨማሪም ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ብዙዎቹ አይሁዳውያን ለሴቶች የነበራቸውን አመለካከት አልደገፈም። ከዚህ ይልቅ ቆራጥ አቋም በመውሰድ ትክክለኛ የሆነውን ነገር አድርጓል። እንደ አሕዛብ ሁሉ ሳምራውያን ሴቶችም እንደ ርኩስ ይታዩ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት ከመስበክ ወደ ኋላ አላለም። እንዲያውም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ የተናገረው ለዚች ሴት ነው። (ዮሐንስ 4:6, 25, 26) ፈሪሳውያን፣ ሴቶች የአምላክን ሕግ መማር የለባቸውም የሚል አቋም የነበራቸው ቢሆንም ኢየሱስ ጊዜና ጉልበቱን ሳይቆጥብ ሴቶችን አስተምሯል። (ሉቃስ 10:38-42) በአይሁዶች ወግ መሠረት ሴቶች ለምሥክርነት አይበቁም የሚል አስተሳሰብ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው ለሴቶች ነው። አልፎ ተርፎም ይህን አስደናቂ ዜና ሄደው ለወንዶቹ ደቀ መዛሙርት እንዲያበስሩ ልኳቸዋል!—ማቴዎስ 28:1-10

 19 አዎን፣ ኢየሱስ ሰዎች ፍትሕ ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ እንዲገነዘቡ አድርጓል። ይህን ለማድረግም ሕይወቱን ለአደጋ እስከማጋለጥ ደርሷል። ይህ የኢየሱስ ምሳሌ ለእውነተኛ ፍትሕ መቆም ድፍረት እንደሚጠይቅ ያስገነዝበናል። “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” መባሉ የተገባ ነው። (ራእይ 5:5) አንበሳ ድፍረት የሚጠይቀውን የፍትሕ ባሕርይ እንደሚወክል አስታውስ። ይሁንና በቅርቡ ኢየሱስ የላቀ የፍትሕ እርምጃ ይወስዳል። ‘በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ፍትሕ’ እንዲሰፍን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 42:4 አ.መ.ት

መሲሐዊው ንጉሥ ‘በምድር ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል’

20, 21. በዘመናችን መሲሐዊው ንጉሥ በመላው ምድርና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍትሕ እንዲስፋፋ ያደረገው እንዴት ነው?

20 ኢየሱስ በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በምድር ላይ ፍትሕ እንዲስፋፋ ሲያደርግ ቆይቷል። እንዴት? በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ላይ ነው። በምድር ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ተከታዮች ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ለሰዎች ሁሉ በማስተማር ላይ ናቸው። ልክ እንደ ኢየሱስ ያላንዳች አድልዎ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመስበክ ወጣት አረጋዊ፣ ሀብታም ድሀ፣ ወንድ ሴት ሳይሉ ሁሉም ሰው የፍትሕ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ መማር የሚችልበትን አጋጣሚ እንዲያገኝ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

21 በተጨማሪም ኢየሱስ በእሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ነው። አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ወንዶችን ማለትም ጉባኤውን የሚመሩ ታማኝ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን “ስጦታ” አድርጎ ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8-12) እነዚህ ወንዶች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ውድ የሆነውን የአምላክ መንጋ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይጠብቃሉ። ሽማግሌዎች የመንጋው አባላት ያሉበት የኑሮ ደረጃ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ሁሉም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዙ እንደሚፈልግ ይገነዘባሉ።

22. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ስለተንሠራፋው የፍትሕ መጓደል ምን ይሰማዋል? ልጁንስ ምን እንዲያደርግ ሾሞታል?

22 ይሁን እንጂ ኢየሱስ በቅርቡ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በመላው ምድር ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ ብልሹ ዓለም  በግፍ ተሞልቷል። ብዙ ሕፃናት በረሃብ እየረገፉ ሳለ የጦር መሣሪያ ለማምረትና ተድላን የሚያሳድዱ ራስ ወዳድ ሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ይህ ነው የማይባል ጊዜና ገንዘብ የሚጠፋ መሆኑ ይቅር የማይባል ግፍ ነው። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት መትረፍ ሲችሉ ለሞት መዳረጋቸው በዓለም ላይ የፍትሕ መጓደል ምን ያህል እንደተንሠራፋ ከሚያሳዩት በርካታ ማስረጃዎች አንዱ ሲሆን እንዲህ ያሉት ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የይሖዋን የጽድቅ ቁጣ ይቀሰቅሳሉ። በምድር ላይ ያለውን የፍትሕ መጓደል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የጽድቅ ጦርነት እንዲያካሂድ ልጁን ሾሞታል።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-15

23. ክርስቶስ ከአርማጌዶን በኋላ ፍትሕ ለዘላለም እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?

23 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍትሕ ክፉዎችን በማጥፋት ብቻ አይወሰንም። ይሖዋ ልጁን “የሰላም ልዑል” አድርጎም ሾሞታል። ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ የኢየሱስ መንግሥት በምድር ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ “በፍትሕ” ይገዛል። (ኢሳይያስ 9:6, 7 አ.መ.ት) ከዚያም ኢየሱስ በዓለም ላይ ብዙ ሥቃይና መከራ ያስከተለውን የፍትሕ መጓደል ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። ፍጹም ከሆነው የይሖዋ ፍትሕ ጎን ለዘላለም በታማኝነት ይቆማል። እንግዲያው ዛሬ የይሖዋን ፍትሕ ለመኮረጅ ጥረት ማድረጋችን ወሳኝ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

^ አን.1 ኢየሱስ የጽድቅ ቁጣ በመቆጣት ረገድ በክፋት ሁሉ ላይ ‘መዓቱን’ እንደሚያወርደው እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ነው። (ናሆም 1:2) ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ዓመጸኛ የሆኑት ሕዝቦቹ ቤቱን “የሌቦች ዋሻ” እንዳደረጉት ከገለጸ በኋላ “ቁጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ . . . ይፈስሳል” ሲል ተናግሯል።—ኤርምያስ 7:11, 20

^ አን.3 ሚሽና እንደሚገልጸው ከሆነ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡት ርግቦች ዋጋ እየተወደደ መምጣቱ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር። ወዲያውኑ የርግቦቹ ዋጋ 99 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል! በዚህ አትራፊ ንግድ ይበልጥ ይጠቀሙ የነበሩት እነማን ናቸው? አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በቤተ መቅደሱ የሚካሄደውን ንግድ በአብዛኛው የተቆጣጠሩት የሊቀ ካህናቱ የሐና ቤተሰቦች እንደነበሩና ይህም ለቤተሰቡ ከፍተኛ ሀብት እንዳስገኘ ይናገራሉ።—ዮሐንስ 18:13

^ አን.16 ፈሪሳውያን ሕግን ያልተማረው ተራው ሕዝብ ‘የተረገመ’ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። (ዮሐንስ 7:49) ማንም ሰው እንዲህ ያሉትን ሰዎች ማስተማር ወይም ከእነዚህ ሰዎች ጋር መነገድ፣ መብላት ወይም መጸለይ የለበትም ይሉ ነበር። አንድ ሰው ሴት ልጁን እንዲህ ላለ ሰው ቢድር ለአውሬ እንደሰጣት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ፈሪሳውያን እነዚህ ተራ ሰዎች ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ እንኳ የላቸውም የሚል እምነት ነበራቸው።