በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 14

ይሖዋ “ለብዙዎች ቤዛ” አዘጋጀ

ይሖዋ “ለብዙዎች ቤዛ” አዘጋጀ

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? ብቸኛው መፍትሔስ ምንድን ነው?

“ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ” ይኖራል። (ሮሜ 8:22) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጆች የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ በዚህ መንገድ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ሥቃይ፣ ኃጢአትና ሞት ምንም ዓይነት መፍትሔ የሌላቸው ነገሮች ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ሰዎች አቅሙ ውስን አይደለም። (ዘኍልቍ 23:19) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከሥቃይና ከመከራ ለመገላገል የሚያስችለንን ቤዛ አዘጋጅቶልናል።

2 ቤዛው ይሖዋ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው። ከኃጢአትና ከሞት ባርነት መላቀቅ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ኤፌሶን 1:7) በሰማይም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው በቤዛው ዝግጅት ላይ ነው። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 1:4) ለመሆኑ ቤዛው ምንድን ነው? ወደር የለሽ ስለሆነው የይሖዋ ፍትሕስ ምን ያስተምረናል?

ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

3. (ሀ) ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ ማቅለል የማይችለው ለምንድን ነው?

3 ቤዛ ያስፈለገው አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነው። አዳም በአምላክ ላይ በማመጹ ለዘሮቹ በሽታን፣ ሐዘንን፣ ሥቃይንና ሞትን አውርሷል። (ዘፍጥረት 2:17፤ ሮሜ 8:20) አምላክ እንዲሁ በማዘን የሞት ፍርዱን ሊያቀልል አይችልም። እንዲህ ቢያደርግ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” የሚለውን ራሱ ያወጣውን ሕግ ችላ እንዳለ ያስቆጥርበታል። (ሮሜ 6:23) በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ መንገድ ፍትሐዊ ሕጎቹን የሚሽር ቢሆን ኖሮ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሥርዓት አልበኝነትና ሕገ ወጥነት ይነግሥ ነበር!

4, 5. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ስም ያጠፋው እንዴት ነው? ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት የተሰማውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች በተመለከተ ምን ክስ አቅርቧል?

4 ምዕራፍ 12 ላይ እንደተመለከትነው በኤደን የተፈጸመው ዓመጽ ትልልቅ  ጥያቄዎችንም አስነስቷል። ሰይጣን የአምላክን መልካም ስም አጉድፏል። ይሖዋ ውሸታም እንደሆነና ፍጥረታቱን ነፃነት የሚነፍግ ጨካኝና አምባገነን ገዥ እንደሆነ አድርጎ ከሶታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) በተጨማሪም ሰይጣን፣ ይሖዋ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት ያለውን ዓላማ በማሰናከል ይሖዋ ያሰበውን ማሳካት የማይችል አምላክ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። (ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ባይፈቅድ ኖሮ የማሰብ ችሎታ ያላቸው አብዛኞቹ ፍጥረታቱ በእሱ አገዛዝ ላይ ያላቸውን አመኔታ ሊያጡ ይችሉ ነበር።

5 ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነና ችግር ቢደርስባቸው አምላክን እንደሚክዱ በመግለጽ ስማቸውን አጥፍቷል። (ኢዮብ 1:9-11) አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው እነዚህ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ሲል ነው። ይሖዋ፣ ሰይጣን ያቀረባቸው የሐሰት ክሶች መልስ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት ተሰምቶታል። ይሁን እንጂ አምላክ እነዚሁ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና የሰው ልጆች እንዲድኑ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

ቤዛ ምንድን ነው?

6. አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ያደረገው ዝግጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን የተለያዩ መንገዶች ተገልጿል?

6 ይሖዋ ያቀረበው መፍትሔ ታላቅ ምሕረትና ፍጹም የሆነ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነው። ሰዎች መቼም ቢሆን እንዲህ ያለ መፍትሔ ሊያመጡ አይችሉም። ይሁንና ይሖዋ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ በቀላሉ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ የተጠቀመበት ዝግጅት በጣም የሚያስደንቅ ነው። ይህ ዝግጅት መዋጀት፣ ማስታረቅና ማስተሰረይ ተብሎ በተለያየ መንገድ ተገልጿል። (መዝሙር 49:8፤ ዳንኤል 9:24፤ ገላትያ 3:13፤ ቆላስይስ 1:19, 20፤ ዕብራውያን 2:17) ይሁን እንጂ ይህን ዝግጅት በተሻለ መንገድ የሚገልጸው ኢየሱስ ራሱ የተጠቀመበት ቃል ነው። “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ [በግሪክኛ ሊትሮን] ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 20:28

7, 8. (ሀ) “ቤዛ” የሚለው ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ቤዛ የሚለው ቃል ተመጣጣኝ የሆነን ነገር የሚያመለክተው በምን መንገድ ነው?

 7 ቤዛ ምንድን ነው? ቤዛን ለመግለጽ የገባው የግሪክኛ ግስ “መፍታት፣ መልቀቅ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል የጦር እስረኞችን ለማስለቀቅ የሚከፈልን ገንዘብ ያመለክታል። እንግዲያው ቤዛ አንድን ነገር መልሶ ለማግኘት የሚከፈል ዋጋ እንደሆነ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ቤዛ” (ኮፌር) የሚለው ቃል “መሸፈን” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የመጣ ነው። ለምሳሌ ያህል አምላክ ኖኅን የሠራትን መርከብ በቅጥራን ‘እንዲለቀልቃት [ወይም እንዲሸፍናት]’ አዞት ነበር። (ዘፍጥረት 6:14) ይህም መቤዠት የሚለው ቃል ኃጢአትን መሸፈን የሚል ትርጉም እንዳለውም እንድንገነዘብ ይረዳናል።—መዝሙር 65:3 NW

8 ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ቃል (ኮፌር) “ምንጊዜም ተመጣጣኝ የሆነን ነገር እንደሚያመለክት” ይገልጻል። በመሆኑም የቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ወይም ሽፋን ከታቦቱ ጋር የሚመጣጠን ነበር። በተመሳሳይም ኃጢአትን ለመቤዠት ወይም ለመሸፈን የሚከፈለው ዋጋ በኃጢአቱ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ የሚያካክስ ወይም የሚሸፍን መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ “ነፍስ በነፍስ፣ ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር፣ ይመለሳል” ሲል ይገልጻል።—ዘዳግም 19:21

9. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የእንስሳት መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው? ይሖዋስ ለእነዚህ መሥዋዕቶች ምን አመለካከት ነበረው?

9 ከአቤል አንስቶ በምድር ላይ የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ይህን ማድረጋቸው ኃጢአት እንዳለባቸውና መቤዠት እንደሚያስፈልጋቸው እንደተገነዘቡ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ አምላክ ‘በዘሩ’ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያመለክት ነው። (ዘፍጥረት 3:15፤ 4:1-4፤ ዘሌዋውያን 17:11፤ ዕብራውያን 11:4) ይሖዋ  እንዲህ ያሉትን መሥዋዕቶች የተቀበለ ሲሆን ለእነዚህ አገልጋዮቹ ሞገሱን አሳይቷቸዋል። ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች ያቀርቧቸው የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ ያህል ብቻ የሚያገለግሉ ነበሩ። እንስሳት ከሰዎች ያነሱ በመሆናቸው የሰውን ኃጢአት ሊሸፍኑ አይችሉም። (መዝሙር 8:4-8) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነው” ይላል። (ዕብራውያን 10:1-4) እንዲህ ያሉት መሥዋዕቶች ለእውነተኛው ቤዛዊ መሥዋዕት እንደ ምሳሌ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ።

“ተመጣጣኝ ቤዛ”

10. (ሀ) ቤዛው ከማን ጋር የሚመጣጠን መሆን አለበት? ለምንስ? (ለ) አንድ ሰው ብቻ መሥዋዕት መሆኑ በቂ የሚሆነው ለምንድን ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሁሉ በአዳም ይሞታሉ’ ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) በመሆኑም ቤዛው እንዲከፈል ከአዳም ጋር የሚመጣጠን ፍጹም ሰው መሞት ነበረበት። (ሮሜ 5:14) ይህን የፍትሕ መሥፈርት ሊያሟላ የሚችል ሌላ ምንም ፍጡር ሊኖር አይችልም። አዳም ላጠፋው ፍጹም ሕይወት “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊሆን የሚችለው በአዳም ላይ ከተበየነው የሞት ፍርድ ነፃ የሆነ ፍጹም ሰው ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6 NW) ለእያንዳንዱ የአዳም ዘር ተመጣጣኝ የሆነ ቤዛ ለመክፈል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሥዋዕት መሆን አያስፈልጋቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት’ ሲል ገልጿል። (ሮሜ 5:12) ‘ሞት በአንድ ሰው በኩል ስለ መጣ’ አምላክ ‘በአንድ ሰው’ አማካኝነት የሰውን ዘር ለመቤዠት ዝግጅት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 15:21) እንዴት?

“ለሁሉም የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛ”

11. (ሀ) ቤዛውን የሚከፍለው ሰው ‘ስለ ሁሉ ሞትን የሚቀምሰው’ እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይችሉት ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

11 ይሖዋ አንድ ፍጹም ሰው በፈቃደኝነት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ዝግጅት አደረገ። ሮሜ 6:23 እንደሚገልጸው “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።” ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ሰው ‘ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምሳል።’ በሌላ አነጋገር ለአዳም ኃጢአት ደመወዝ ይከፍላል። (ዕብራውያን 2:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:21፤ 1 ጴጥሮስ  2:24) ይህ ከሕግ አንጻር ትልቅ ትርጉም አለው። ቤዛው ታዛዥ በሆኑ የአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ በመሻር የኃጢአትን መዘዝ ከሥሩ ነቅሎ ያስወግዳል። *ሮሜ 5:16

12. አንድ ዕዳ መከፈሉ ለብዙ ሰዎች ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በምሳሌ አስረዳ።

12 ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በምትኖርበት ከተማ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ነዋሪዎች በአንድ ትልቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው እንበል። አንተም ሆንክ ጎረቤቶችህ ይህ ፋብሪካ በሚከፍላችሁ ደመወዝ ጥሩ ኑሮ ትኖራላችሁ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ፋብሪካ ሊዘጋ ነው። ለምን? የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ በሙስና በመዘፈቁና ድርጅቱን ለኪሳራ በመዳረጉ ነው። አንተም ሆንክ አብረውህ የሚሠሩት ሰዎች በድንገት ከሥራ በመውጣታችሁ የተለያዩ ወጪዎቻችሁን የምትሸፍኑበት ገንዘብ በማጣት ችግር ላይ ወደቃችሁ። አንድ ሰው በፈጸመው ሙስና ሳቢያ የትዳር ጓደኞቻችሁ፣ ልጆቻችሁና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሳይቀሩ ለችግር ተዳርገዋል። ይህ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን! አንድ ባለጸጋ ሰው የፋብሪካውን ጥቅም በመገንዘብና ችግር ላይ ለወደቁት ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በማዘን ፋብሪካውን ከደረሰበት ኪሳራ ለመታደግ እርምጃ ይወስዳል። የፋብሪካውን ዕዳ በሙሉ በመክፈል እንደገና ተከፍቶ ሥራ እንዲጀምር ያደርጋል። ይህ ዕዳ መከፈሉ በዚያ ተቀጥረው ይሠሩ ለነበሩ በርካታ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ትልቅ እፎይታ ያስገኛል። በተመሳሳይም አዳም ያመጣው ዕዳ መከፈሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ትልቅ በረከት ያስገኛል።

ቤዛውን ሊያቀርብ የሚችለው ማን ነው?

13, 14. (ሀ) ይሖዋ ለሰው ዘር ቤዛ ያቀረበው እንዴት ነው? (ለ) ቤዛው የተከፈለው ለማን ነው? ቤዛው በዚህ መንገድ መከፈሉስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ‘የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደውን በግ’ ሊያቀርብ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:29) ይሁን እንጂ አምላክ የሰውን ዘር  ለማዳን እንዲሁ አንድ መልአክ አልላከም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ላቀረበው ክስ የማያዳግም ምላሽ መስጠት የሚችለውን መልአክ መርጦ ልኳል። አዎን፣ ይሖዋ ‘ደስ የሚያሰኘውን’ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ተወዳዳሪ የሌለው መሥዋዕት ከፍሏል። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጅ በሰማይ የነበረውን ሕይወት በፈቃደኝነት በመተው “ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵስዩስ 2:7) ይሖዋ የበኩር ልጁን ሕይወትና ሁለንተናዊ ባሕርይ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ማርያም ወደምትባል አይሁዳዊት ድንግል ማህፀን አዛወረው። (ሉቃስ 1:27, 35) ይህ የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ተብሎ ቢጠራም ከአዳም ጋር ፍጹም ተመጣጣኝ ስለሆነ ከሕግ አንጻር ሁለተኛው አዳም ተብሎ ሊጠራ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም ኢየሱስ ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ራሱን ቤዛ አድርጎ ማቅረብ ይችላል።

14 ይህ ቤዛ የተከፈለው ለማን ነው? መዝሙር 49:7 ይህ ቤዛ የተከፈለው “ለእግዚአብሔር” እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ቤዛውን ያዘጋጀው ራሱ ይሖዋ አይደለምን? አዎን፣ እሱ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን ቤዛው ገንዘብን ከአንድ ኪስ አውጥቶ ወደ ሌላ ኪስ የመክተት ያህል ትርጉም የለሽ ነገር እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ቤዛው የተከፈለው ፍትሕ የሚጠይቀውን መሥፈርት ለማሟላት እንጂ እንዲሁ አንድን ነገር በሌላ ለመተካት ብቻ ተብሎ አይደለም። ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም እንኳ ቤዛውን በመክፈል ፍጹም ለሆነው ፍትሑ ያለውን የጸና አቋም አሳይቷል።—ዘፍጥረት 22:7, 8, 11-13፤ ዕብራውያን 11:17፤ ያዕቆብ 1:17

15. ኢየሱስ መከራ መቀበሉና መሞቱ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

15 በ33፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛውን ለመክፈል ሲል ራሱን በፈቃደኝነት ለመከራ አሳልፎ ሰጠ። በሐሰት ክሶች ተወንጅሎ ተያዘ፣ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት፣ በመጨረሻም በእንጨት ላይ በምስማር ተቸነከረ። ኢየሱስ ይህን ያህል መከራ መቀበሉ አስፈላጊ ነበር? አዎን፣ ምክንያቱም የአምላክ አገልጋዮችን የታማኝነት አቋም በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረበት። አምላክ፣ ሄሮድስ ሕፃን የነበረውን ኢየሱስን ለመግደል ያደረገውን ሙከራ አክሽፏል። (ማቴዎስ 2:13-18) ኢየሱስ ካደገ በኋላ ግን የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች በሚገባ ስለሚገነዘብ  ሰይጣን የሚሰነዝርበትን ጥቃት በጽናት መቋቋም ይችል ነበር። * ይህ ነው የማይባል ግፍ ቢደርስበትም እንኳ “ቅዱስና ያለ ተንኰል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ” ሆኖ እስከ መጨረሻው ድረስ በመጽናት ይሖዋ መከራ እየደረሰባቸውም ቢሆን በታማኝነት ጸንተው የሚቆሙ አገልጋዮች እንዳሉት በማያሻማ ሁኔታ አስመስክሯል። (ዕብራውያን 7:26) ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት “ተፈጸመ” ብሎ በድል አድራጊነት ስሜት መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ዮሐንስ 19:30

የመቤዠት ተልእኮውን መፈጸም

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ማከናወኑን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ” መቅረቡ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

16 ይሁንና ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ገና አልፈጸመም ነበር። ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ከሞት አስነሳው። (የሐዋርያት ሥራ 3:15፤ 10:40) ይሖዋ ይህን በማድረግ ልጁ ላከናወነው የታማኝነት አገልግሎት ወሮታ ከመክፈሉም በላይ የአምላክ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሰጠውን የመቤዠት ተልእኮ መፈጸም የሚችልበትን አጋጣሚም ከፍቶለታል። (ሮሜ 1:4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-8) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ክርስቶስ . . . ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ . . . የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች፣ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።”—ዕብራውያን 9:11, 12, 24

17 ክርስቶስ ቃል በቃል ደሙን ወደ ሰማይ ይዞ ሊሄድ አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ ይዞ የሄደው ደሙ የሚወክለውን ነገር ማለትም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ፍጹም ሰብዓዊ  ሕይወት ዋጋ ነው። ከዚያም የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ በአምላክ ፊት አቀረበ። ይሖዋ ይህን መሥዋዕት ተቀብሎታል? አዎን፣ ተቀብሎታል። በ33፣ በጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ለዚህ ማስረጃ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚያን ጊዜ የተከናወነው ነገር እጅግ የሚያስደስት ቢሆንም ቤዛው የሚያስገኘው አስደናቂ ጥቅም በዚህ ብቻ የሚወሰን አልነበረም።

ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

18, 19. (ሀ) በክርስቶስ ደም አማካኝነት ከአምላክ ጋር የመታረቅ አጋጣሚ የተከፈተላቸው ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? (ለ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” አሁንም ሆነ ወደፊት በቤዛው አማካኝነት የሚያገኟቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

18 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ፣ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር በክርስቶስ ሁሉን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እንደወደደ ገልጿል። በተጨማሪም ጳውሎስ ይህ እርቅ ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን ማለትም ‘በሰማይ ያሉትን ነገሮች’ እና ‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ እንደሚያጠቃልል አብራርቷል። (ቆላስይስ 1:19, 20፤ ኤፌሶን 1:10) የመጀመሪያው ቡድን በሰማይ ካህናት ሆኖ የማገልገልና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው በምድር ላይ የመግዛት ተስፋ ያላቸውን 144,000 ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:4፤ 14:1-3) እነዚህ ነገሥታትና ካህናት በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ቀስ በቀስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች እንዲዳረስ ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ራእይ 20:6፤ 21:3, 4

19 ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች ናቸው። ራእይ 7:9-17 እነዚህ ሰዎች በቅርቡ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የሚተርፉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሆኑ ይገልጻል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከቤዛው ለመጠቀም የሺው ዓመት ግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ አለባቸው ማለት አይደለም። ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል።’ በቤዛው ስለሚያምኑ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ከዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት  መንፈሳዊ ጥቅሞችን በማግኘት ላይ ናቸው። የአምላክ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን ተቆጥረዋል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለከፈለ ‘ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ’ ይችላሉ። (ዕብራውያን 4:14-16) ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም አምላክ በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ይላቸዋል። (ኤፌሶን 1:7) ምንም እንኳ ፍጹም ባይሆኑም ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። (ዕብራውያን 9:9፤ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) በመሆኑም ዛሬ ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ በመፍጠር ላይ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 5:19, 20) በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ደግሞ ቀስ በቀስ ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥተው ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት ይደርሳሉ።’—ሮሜ 8:21

20. በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰልህ ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል?

20 የቤዛውን ዝግጅት ስላደረገልን “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” (ሮሜ 7:25) የቤዛው ዝግጅት እንዲሁ ሲታይ ቀላል ሊመስል ቢችልም ከምናስበው በላይ አስገራሚ ነው። (ሮሜ 11:33) በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልተን በዚህ የቤዛ ዝግጅት ላይ ካሰላሰልን ልባችን በጥልቅ ሊነካና የፍትሕ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልንገፋፋ እንችላለን። በተጨማሪም “እርሱ ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” ብለን እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን ለማወደስ እንገፋፋለን።—መዝሙር 33:5 አ.መ.ት

^ አን.11 አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም። የሙሴ ሕግ ሆን ብሎ ነፍስ የሚያጠፋን ሰው በተመለከተ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስቀምጧል:- “ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ።” (ዘኍልቍ 35:31) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ያመጹት ሆን ብለው ስለሆነ ሞት ይገባቸዋል። በዚህም ምክንያት ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጥተዋል።

^ አን.15 ኢየሱስ ለአዳም ኃጢአት ተመጣጣኝ ቤዛ ሊሆን የሚችለው ሕፃን ሆኖ ሳይሆን ሙሉ ሰው ከሆነ በኋላ ሲሞት ነው። አዳም ኃጢአት የሠራው ድርጊቱ የሚያስከትልበትን መዘዝ እያወቀ ሆን ብሎ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ኢየሱስም “ኋለኛው አዳም” ለመሆንና የአዳምን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን በራሱ ምርጫና ውሳኔ ከይሖዋ ጎን መቆሙን ማስመስከር ነበረበት። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም መሥዋዕታዊ ሞቱን ጨምሮ ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት ሰዎችን ለማዳን የሚያስችል ‘አንድ የጽድቅ ሥራ’ ሆኖ አገልግሏል።—ሮሜ 5:18, 19