በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 23

“እርሱ አስቀድሞ ወዶናል”

“እርሱ አስቀድሞ ወዶናል”

1-3. የኢየሱስን ሞት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ አንድ ሰው ባልሠራው ጥፋት ተወንጅሎ ከተፈረደበት በኋላ ተሠቃይቶ እንዲሞት ተደረገ። በሰው ዘር ታሪክ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊና ጭካኔ የተሞላበት ፍርድ ሲፈረድ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም። ሆኖም ይህን የሞት ቅጣት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ።

2 ይህ ሰው በከፍተኛ ሥቃይ እያጣጣረ በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በሰማይ ላይ የታየው ክስተት ራሱ በወቅቱ የተፈጸመው ሁኔታ ልዩ ትርጉም እንዳለው የሚጠቁም ነበር። ገና እኩለ ቀን የነበረ ቢሆንም ምድሪቱ በድንገት በጨለማ ተዋጠች። አንድ ታሪክ ጸሐፊ “ፀሐይም ጨለመ” ሲል ዘግቧል። (ሉቃስ 23:44, 45) ይህ ሰው እስትንፋሱ ሊያቆም ሲል “ተፈጸመ” በማለት የማይረሳ ቃል ተናግሯል። በእርግጥም ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት አንድ አስደናቂ ነገር ፈጽሟል። ይህ ሰው ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር በታሪክ ዘመናት ሁሉ የትኛውም ሰው ካሳየው ፍቅር የላቀ ነው።—ዮሐንስ 15:13፤ 19:30

3 ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚያ የመከራ ቀን (ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ብዙ ሥቃይ እንደደረሰበትና እንደሞተ የሚገልጸውን ታሪክ የማያውቅ የለም ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ብዙዎች ልብ የማይሉት አንድ ነገር አለ። ኢየሱስ ብዙ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም እንኳ ከእሱ ይበልጥ የተሠቃየ አንድ አካል አለ። እንዲያውም በዚያ ዕለት የበለጠ መሥዋዕት የከፈለውና አቻ የማይገኝለት ፍቅሩን ያሳየው እሱ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ፍቅር ያሳየ ማንም የለም። ይህን ፍቅሩን የገለጸው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ቀጥሎ ለምንመረምረው በጣም አስፈላጊ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ለይሖዋ ፍቅር ተስማሚ መግቢያ ነው።

 ከሁሉ የላቀው የፍቅር መግለጫ

4. አንድ ሮማዊ ወታደር ኢየሱስ ተራ ሰው አለመሆኑን የተገነዘበው እንዴት ነው? ምን ብሎስ ተናግሯል?

4 በኢየሱስ ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ ያስፈጸመው ሮማዊ መቶ አለቃ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ምድሪቱን በሸፈነው ጨለማም ሆነ ከሞተ በኋላ በተከሰተው ኃይለኛ የምድር ነውጥ በጣም ተደናግጦ ነበር። “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 27:54) ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። ይህ ወታደር የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ ያስገደለው የሉዓላዊውን አምላክ አንድያ ልጅ ነው። አምላክ ልጁን ምን ያህል ይወደው ነበር?

5. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር ለምን ያህል ጊዜ ኖሯል?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” ሲል ይጠራዋል። (ቆላስይስ 1:15) የይሖዋ ልጅ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንኳ ይኖር እንደነበረ ልብ በል። እንግዲያው ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የኖረው ለምን ያህል ጊዜ ነው? አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም የ13 ቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ይገምታሉ። ይህ ምን ያህል ረጅም ዘመን እንደሆነ መገመት ትችላለህ? ይህ ግምት ትክክል እንደሆነ አድርገን ብንቀበል እንኳ የይሖዋ ልጅ ዕድሜ ከዚህ እንደሚበልጥ ግልጽ ነው! ኢየሱስ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን ሲያከናውን ነበር?

6. (ሀ) የይሖዋ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ሲያከናውን ነበር? (ለ) ይሖዋና ልጁ ምን ዓይነት ወዳጅነት አላቸው?

6 “ዋና ሠራተኛ” በመሆን አባቱን በደስታ ሲያገለግል ነበር። (ምሳሌ 8:30) መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳች ስንኳ ያለ [ኢየሱስ] አልሆነም” ሲል ይገልጻል። (ዮሐንስ 1:3) በመሆኑም ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ወደ ሕልውና ያመጣው ከልጁ ጋር አብሮ በመሥራት ነው። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፈው ይሆን! በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ፍቅር እጅግ ጠንካራ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ፍቅር ደግሞ ‘በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስር’ ነው። (ቆላስይስ 3:14 አ.መ.ት) ይሖዋና ኢየሱስ ይህን ያህል ረጅም ዘመን አብረው ሲያሳልፉ በመካከላቸው ምን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተው እንደሚሆን መገመት የሚችል ይኖራል? በእርግጥም በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ያለው የጠበቀ ወዳጅነትና ፍቅር አቻ የለውም።

7. ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ይሖዋ ስለ ልጁ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?

7 ይሁንና ይሖዋ፣ ልጁ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ወደ ምድር ላከው። ይህን  ለማድረግ ሲል የሚወደውን ልጁን ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ከአጠገቡ ማጣት ግድ ሆኖበታል። ከሰማይ ሆኖ የኢየሱስን አስተዳደግ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በትኩረት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው ተጠመቀ። ይሖዋ ለኢየሱስ ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው ግልጽ ነው። “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስ አስቀድሞ ስለ እሱ የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ በታማኝነት በመፈጸም ከእሱ የሚጠበቀውን ሁሉ እንዳከናወነ ሲመለከት አባቱ እጅግ እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም!—ዮሐንስ 5:36፤ 17:4

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ምን ደረሰበት? አባቱስ ይህን ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? (ለ) ይሖዋ ልጁ ይህ ሁሉ ሥቃይ እንዲደርስበትና እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ ይሖዋ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተፈጸመውን ሁኔታ ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? በዚያ ቀን ሌሊት ይሁዳ አሳልፎ ሲሰጠውና ሰዎች ተሰብስበው መጥተው ሲይዙት፣ ወዳጆቹ ትተውት ሲሄዱና አላግባብ ለፍርድ ሲቀርብ፣ ጠላቶቹ ሲያፌዙበት፣ ሲተፉበትና ሲጎስሙት፣ ጀርባው እስኪተለተል ሲገርፉት፣ እጅና እግሩ በእንጨት ላይ በምስማር ሲቸነከርና ተሰቅሎ እያለ አላፊ አግዳሚው ሲሰድበው፣ የሚወደው ልጁ በጭንቅ እያጣጣረ ወደ እሱ ሲጮኽ እንዲሁም የመጨረሻዋን እስትንፋስ ተንፍሶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞትን ጽዋ ሲጎነጭና ከሕልውና ውጪ ሲሆን ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን?—ማቴዎስ 26:14-16, 46, 47, 56, 59, 67፤ 27:38-44, 46፤ ዮሐንስ 19:1

‘እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጥቷል’

9 ይህን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል። ይሖዋ ስሜት ያለው እንደመሆኑ መጠን ልጁ ሲሞት የተሰማው ሥቃይ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው። ልንገልጸው የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንዲፈቅድ የገፋፋው ምን እንደሆነ ብቻ ነው። አብ እንዲህ ያለው ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ በ⁠ዮሐንስ 3:16 ላይ አንድ አስደናቂ ሐሳብ ገልጾልናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትልቅ ትርጉም ያለው መልእክት ያዘለ በመሆኑ የወንጌል ፍሬ ሐሳብ ተብሎ ይጠራል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።” ስለዚህ ይሖዋ ይህን እንዲፈቅድ ግድ ያለው  ፍቅር ነው። ይሖዋ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት በማድረግ ያሳየን ፍቅር ከዚህ ቀደም ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው።

የመለኮታዊ ፍቅር ትርጉም

10. ሰዎች ምን ማግኘት ይሻሉ? “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉምስ ምን እየሆነ መጥቷል?

10 “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? የሰው ልጆች ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ፍቅር ነው። ሰዎች ከልደት እስከ ሕልፈት ፍቅርን ይሻሉ፣ ፍቅርን ሲያገኙ ሕይወታቸው ያብባል፣ ፍቅርን ሲያጡ ደግሞ ይኮሰምናሉ አልፎ ተርፎም ይሞታሉ። ያም ሆኖ ፍቅርን እንዲህ ነው ብሎ መግለጽ በጣም ያስቸግራል። እርግጥ ነው፣ ስለ ፍቅር ብዙ ተብሏል። ስለ ፍቅር ብዙ ተጽፏል፣ ብዙ ተዘፍኗል እንዲሁም ብዙ ተገጥሟል። ይሁንና ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ፍቅርን በትክክል የሚገልጹ ሆነው አልተገኙም። እንዲያውም ስለ ፍቅር ብዙ ከመባሉ የተነሳ ትክክለኛ ትርጉሙ ግራ እያጋባ መጥቷል።

11, 12. (ሀ) ስለ ፍቅር ብዙ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከየት ነው? ለምንስ? (ለ) በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ የተጠቀሱት የፍቅር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው የትኛው “የፍቅር” ዓይነት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ሐ) አጋፔ ምንድን ነው?

11 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጣል። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “ፍቅርን ማወቅ የሚቻለው በሚያከናውነው ተግባር ብቻ ነው” በማለት ይገልጻል። ይሖዋ ስላከናወናቸው ነገሮች የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ለፍጥረታቱ ስላለው የጠለቀ ፍቅር ብዙ ያስተምረናል። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ፍቅሩን በተግባር ከገለጸበት የቤዛ ዝግጅት ይበልጥ ይህን ባሕርይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምን ነገር ይኖራል? በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር የገለጸባቸውን ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት የገቡትን ቃላት በመመርመር ግንዛቤያችንን ማስፋት እንችላለን። በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት  የሚያገለግሉ አራት ቃላት ነበሩ። * ከእነዚህ መካከል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው አጋፔ የሚለው ቃል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ፍቅርን ለመግለጽ የሚያስችል ከዚህ የተሻለ ቃል የለም” ሲል ዘግቧል። ለምን?

12 አጋፔ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር ነው። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ፍቅር በተደረገልን ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚገለጽ ፍቅር አይደለም። ይህ ፍቅር ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን ቆም ብሎ ማሰብን የሚጠይቅ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ አጋፔ ፈጽሞ ከራስ ወዳድነት መንፈስ ነፃ በሆነ መንገድ የሚገለጽ ፍቅር ነው። እስቲ ዮሐንስ 3:16ን በድጋሚ ተመልከት። አምላክ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ የወደደው የትኛውን ‘ዓለም’ ነው? ከኃጢአት ሊቤዥ የሚችለውን የሰው ዘር ዓለም ነው። ይህም በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሱ ያሉ ብዙ ሰዎችን ይጨምራል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዩ እንደነበረው እንደ አብርሃም እያንዳንዱን ሰው ወዳጁ አድርጎ ይመለከተዋል ማለት ነው? (ያዕቆብ 2:23) እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም እንኳ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም ሰው ደግነት አሳይቷል። ሁሉም ንስሐ እንዲገቡና አኗኗራቸውን እንዲለውጡ ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ደግሞም ብዙዎች ይህን አድርገዋል። እነዚህን ሰዎች ወዳጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል።

13, 14. አጋፔ በአብዛኛው የጠበቀ የመውደድ ስሜትን እንደሚያካትት የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 ይሁንና አንዳንዶች ስለ አጋፔ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። ምንም ዓይነት ስሜት የማይንጸባረቅበት፣ እንዲሁ በደንብና በሥርዓት ብቻ የሚመራ ፍቅር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። አጋፔ ብዙውን ጊዜ የጠበቀ የመውደድ ስሜትን የሚያካትት ነው። ለምሳሌ ያህል ዮሐንስ “አባት ልጅን ይወዳል” ሲል በጻፈ ጊዜ የተጠቀመው አጋፔ የተባለውን ቃል ነው። ይህ ፍቅር በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ ብቻ የተመሠረተና ውስጣዊ ስሜት የሚጎድለው ነው ሊባል ይችላል?  በፍጹም፤ ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 5:20 ላይ ይህንኑ ሐሳብ ለመግለጽ ፊሌኦ የተባለውን የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ ይህ ፍቅር የጠበቀ የመውደድ ስሜት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 3:35) ይሖዋ የጠበቀ የመውደድ ስሜት አለው። እንዲህ ሲባል ግን እንዲሁ በስሜት ይመራል ማለት አይደለም። ምንጊዜም ፍቅሩን የሚገልጸው ጥበብና ፍትሕ በሚንጸባረቅባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ በመመራት ነው።

14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሁሉም የይሖዋ ባሕርያት እጅግ የላቁ፣ ምንም እንከን የማይወጣላቸውና ማራኪ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ማራኪ የሆነው ግን ፍቅር ነው። የፍቅርን ያህል ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ነገር የለም። የሚያስደስተው ደግሞ ከይሖዋ ባሕርያት ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ፍቅር ነው። ይህን ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”

15. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ በተመለከተ ምን ይላል? ይህን አገላለጽ ለየት የሚያደርገውስ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

15 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎቹ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት በተለየ መልኩ ስለ ፍቅር የሚናገረው አንድ ነገር አለ። ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ኃይል ነው ወይም አምላክ ፍትሕ ነው ወይም ደግሞ አምላክ ጥበብ ነው አይሉም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት አሉት። የእነዚህ ባሕርያት ዋነኛ ምንጭ እሱ ከመሆኑም በላይ በጥበብ፣ በፍትሕም ሆነ በኃይል ረገድ አቻ የለውም። አራተኛውን ባሕርይ በተመለከተ ግን “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚል ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው አነጋገር ተጠቅሶ እናገኛለን። * (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ምን ማለት ነው?

16-18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለው ለምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጅ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ሲባል “እግዚአብሔር ማለት ፍቅር ነው፤ ፍቅር ማለት እግዚአብሔር ነው” እንደማለት ያህል እንደሆነ አድርገን  ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋን እንደ አንድ ረቂቅ የሆነ ባሕርይ አድርገን ልንወስደው አይገባም። ከፍቅር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስሜቶችና ባሕርያት ያሉት አምላክ ነው። ይሁንና ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅር ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ ሲናገር “ፍቅር የአምላክ ዋነኛ መለያ ባሕርይ ነው” ብሏል። ነጥቡን በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል:- የይሖዋ ኃይል ማንኛውንም ነገር ማከናወን ያስችለዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ፍትሑንና ጥበቡን ይጠቀማል። ማንኛውንም ነገር ለማከናወን የሚያነሳሳው ግን ፍቅር ነው። በተጨማሪም ሌሎቹን ባሕርያቱን የሚጠቀምባቸው ፍቅሩን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው።

17 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። በመሆኑም አጋፔ ስለተባለው የፍቅር ዓይነት ማወቅ ከፈለግን ስለ ይሖዋ መማር ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ሰዎችም ይህን ግሩም ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ልጁን “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የማፍቀር ችሎታ ያላቸውና በዚህ ረገድ አምላካቸውን መምሰል የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያቱን ለመግለጽ የተለያዩ ፍጥረታትን ምሳሌ አድርጎ እንደተጠቀመ አስታውስ። ይሁንና ጎላ ብሎ የሚታየውን ባሕርይውን ማለትም ፍቅሩን ለመግለጽ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመው በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን የሰውን ልጅ ነው።—ሕዝቅኤል 1:10

18 በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የምናሳይ ከሆነ ከሁሉ የላቀውን የይሖዋ ባሕርይ እያንጸባረቅን ነው ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:19) ይሁን እንጂ ይሖዋ አስቀድሞ የወደደን እንዴት ነው?

ቀድሞ የወደደን ይሖዋ ነው

19. በይሖዋ የፍጥረት ሥራ ውስጥ ፍቅር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

19 ፍቅር ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረ የይሖዋ ባሕርይ ነው። ለመሆኑ ይሖዋ ለመፍጠር እንዲነሳሳ የገፋፋው ምንድን ነው? ብቸኝነት ተሰምቶት ወይም አብሮት የሚሆን ፈልጎ አይደለም። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር  ስለሌለ ከሌላ የሚፈልገው አንዳች ነገር የለም። የሕይወትን ስጦታ የሚያደንቁ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን በመፍጠር የሕይወትን ጣዕም እንዲቀምሱ ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። ‘እግዚአብሔር መጀመሪያ የፈጠረው’ አንድያ ልጁን ነው። (ራእይ 3:14) ከዚያም ይሖዋ አንድያ ልጁን ዋና ሠራተኛ አድርጎ በመጠቀም ከመላእክት አንስቶ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና አምጥቷል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ቆላስይስ 1:16) እነዚህ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራን ነፃነት፣ የማሰብ ችሎታና የተለያዩ ስሜቶች ያሏቸው በመሆኑ እርስ በርሳቸው በተለይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ አግኝተዋል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) በመሆኑም ይሖዋ አስቀድሞ ስለወደዳቸው እነሱም ይወዱታል።

20, 21. አዳምና ሔዋን ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ምን ነገሮችን ተመልክተዋል? ሆኖም ይሖዋ ላሳያቸው ፍቅር ምን ምላሽ ሰጡ?

20 የሰው ልጆችንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አዳምና ሔዋን በተፈጠሩበት ጊዜ በዙሪያቸው ያለው ነገር ሁሉ ፍቅርን የተላበሰ ነበር ማለት ይቻላል። መኖሪያቸው በነበረችው ኤደን ገነት ውስጥ የሚያዩት ነገር ሁሉ ፈጣሪያቸው ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው” ይላል። (ዘፍጥረት 2:8) ውብ የሆነ የአትክልት ሥፍራ ወይም መናፈሻ አይተህ ታውቃለህ? በጣም የማረከህ ነገር ምንድን ነው? በዛፎች መካከል አልፎ የሚመጣው የፀሐይ ብርሃን፣ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የሚያማምሩ አበቦች፣ እየተንሿሿ የሚወርደው ጅረት፣ የአእዋፍ ዝማሬ ወይስ የተለያዩ ነፍሳት የሚያሰሙት በጣም የሚመስጥ ድምፅ? የዛፎቹ፣ የፍራፍሬዎቹና የአበቦቹ መዓዛስ? ያም ሆነ ይህ በዛሬው ጊዜ፣ በኤደን የነበረውን የአትክልት ሥፍራ የሚወዳደር መናፈሻ ሊኖር አይችልም። ለምን?

21 ያንን የአትክልት ሥፍራ ያዘጋጀው ይሖዋ ራሱ ነው! በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ እጅግ ውብ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዓይን የሚማርኩ ዛፎችና ግሩም ጣዕም ያላቸው ፍሬዎች የሞሉበት ነበር። ይህ ሰፊ የአትክልት ሥፍራ በቂ ውኃ ያገኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ በጣም አስደናቂ የሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት እንስሳት ይርመሰመሱበት ነበር። አዳምና ሔዋን እርካታ የሚያስገኝ ሥራንና ፍጹም የሆነ ወዳጅነትን ጨምሮ በሕይወታቸው እንዲደሰቱ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውላቸው ነበር። ይሖዋ አስቀድሞ የወደዳቸው በመሆኑ እነሱም በአጸፋው  ሊወድዱት ይገባ ነበር። ይሁንና ይህን ሳያደርጉ ቀሩ። የሰማይ አባታቸውን በፍቅር ተነሳስተው ሊታዘዙት ሲገባ ራስ ወዳድ በመሆን ዓመጹበት።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 2

22. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን ባመጹ ጊዜ የወሰደው እርምጃ ፍቅሩ ዘላለማዊ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

22 ይህ ይሖዋን እጅግ እንዳሳዘነው ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁን እንጂ ይህ ዓመጽ ልቡ እንዲጨክን አድርጎታል? በፍጹም! “ምሕረቱ [ወይም ጽኑ ፍቅሩ] ለዘላለም ነው።” (መዝሙር 136:1) በመሆኑም የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን የአዳምና የሔዋን ዘሮች ለመዋጀት የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሚያደርግ ወዲያውኑ አስታወቀ። ቀደም ሲል እንዳየነው ይህ ዝግጅት የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆበታል።—1 ዮሐንስ 4:10

23. ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ለየትኛው ጥያቄ መልስ ይሰጣል?

23 አዎን፣ ይሖዋ ከመጀመሪያ አንስቶ ቀዳሚ በመሆን ለሰው ልጆች ፍቅሩን አሳይቷል። ይሖዋ ‘አስቀድሞ እንደወደደን’ የሚያሳዩ በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ፍቅር ባለበት ሰላምና ደስታ ስለሚኖር ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ተብሎ መገለጹ ምንም አያስደንቅም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ይሁን እንጂ እዚህ ላይ አንድ መልስ ማግኘት የሚያሻው ጥያቄ ይነሳል። በእርግጥ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ይወደናል? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

^ አን.11 “መውደድ (እንደ ቅርብ ወዳጅ ወይም ወንድም አድርጎ መመልከት)” የሚል ትርጉም ያለው ፊሌኦ የተባለው ግስ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተሠርቶበታል። የጠበቀ ቤተሰባዊ ፍቅርን የሚያመለክተው ስቶርጊ የተባለው ቃል በ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:3 ላይ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ያለው ፍቅር እንደሚጠፋ ለመግለጽ ተሠርቶበታል። ኤሮስ ወይም በተቃራኒ ጾታዎች መካከል በሚኖረው መሳሳብ የሚፈጠረው ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢጠቀስም እንኳ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አይገኝም።—ምሳሌ 5:15-20

^ አን.15 ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አገላለጽ ያላቸው ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል “እግዚአብሔር ብርሃን ነው” እና “አምላካችን . . . የሚያጠፋ እሳት ነው” የሚሉ ጥቅሶች እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 1:5፤ ዕብራውያን 12:29) ይሁን እንጂ እነዚህ አገላለጾች ይሖዋን ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የሚያነጻጽሩት በመሆኑ ዘይቤያዊ አነጋገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ይሖዋ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ በብርሃን ሊመሰል ይችላል። “ጨለማ” ወይም ርኩሰት በእርሱ ዘንድ የለም። ኃይሉን በመጠቀም ማጥፋት የሚችል በመሆኑም ከእሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።