በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 30

“በፍቅር ተመላለሱ”

“በፍቅር ተመላለሱ”

1-3. ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ መኮረጃችን ምን ውጤት ያስገኛል?

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የሚከተለውን እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ:- ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መልሶ ይክሳል። ፍቅርን መቀበል ደስታ የሚያስገኝ ቢሆንም ፍቅርን ለሌሎች መስጠት ወይም ማሳየት የሚያስገኘው ደስታ ግን ከዚህ የላቀ ነው።

2 ይህን እውነታ በሰማይ ካለው አባታችን ይበልጥ የሚያውቅ የለም። በዚህ ክፍል ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ከሁሉ የላቀ የፍቅር ተምሳሌት ነው። ከይሖዋ በላቀ ደረጃ ፍቅርን ያሳየ ማንም የለም። ይህን ባሕርይ ለረጅም ዘመን በማንጸባረቅ ረገድም ቢሆን ተወዳዳሪ አይገኝለትም። ታዲያ ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ተብሎ መጠራቱ ሊያስደንቀን ይገባል?—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW

3 አፍቃሪ የሆነው አምላካችን በተለይ ፍቅርን በማሳየት ረገድ እሱን ለመምሰል እንድንጥር ይፈልጋል። ኤፌሶን 5:1, 2 “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ [“ምሰሉ፣” አ.መ.ት]፣ . . . በፍቅር ተመላለሱ” ይላል። ፍቅርን በማሳየት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ ከኮረጅን በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ መቅመስ እንችላለን። የአምላክ ቃል ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ’ የሚሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረጋችን ይሖዋን ያስደስተዋል፤ ይህ ደግሞ ትልቅ እርካታ ያስገኝልናል። (ሮሜ 13:8) ይሁን እንጂ ‘በፍቅር መመላለሳችን’ አስፈላጊ የሆነባቸው ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

4, 5. ለእምነት ባልንጀሮቻችን የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ፍቅር የእውነተኛ ክርስትና መለያ ባሕርይ ነው። ፍቅር ከሌለን ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አንችልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት አይኖረንም።  የአምላክ ቃል እነዚህን እውነታዎች እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚያሳይ ተመልከት።

5 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35) እኔ “እንደ ወደድኋችሁ” ሲል መናገሩን ልብ በል። አዎን፣ ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅር እንድናሳይ ታዝዘናል። በምዕራፍ 29 ላይ ኢየሱስ የሌሎችን ጥቅምና ፍላጎት ማስቀደም የሚጠይቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ የላቀ ምሳሌ እንደተወልን ተመልክተናል። እኛም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት ይጠበቅብናል። ይህን ፍቅራችንን ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ማስተዋል እንዲችሉ በግልጽ ማንጸባረቅ ይኖርብናል። በእርግጥም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው ይህ የወንድማማች ፍቅር የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳውቅ መለያ ምልክት ነው።

6, 7. (ሀ) የይሖዋ ቃል ለፍቅር የላቀ ግምት እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ጳውሎስ በ⁠1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የተናገረው ስለየትኛው ፍቅር ነው?

6 ፍቅር የሚጎድለን ቢሆንስ? ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) የሚንሽዋሽዋ ጸናጽል የሚረብሽ ድምፅ ያወጣል። የሚጮኽ ናስስ? ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ሐረግ “በጣም የሚጮኽ ደወል [የሙዚቃ መሣሪያ]” ወይም “የሚያስተጋባ ደወል” ሲሉ ተርጉመውታል። እንዴት ተስማሚ ምሳሌ ነው! ፍቅር የሌለው ሰው የሚረብሽና ለጆሮ የማይጥም ኃይለኛ ድምፅ ከሚያወጣ የሙዚቃ መሣሪያ ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል። እንዲህ ያለ ሰው ከሌሎች ጋር እንዴት ጥሩ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል? በተጨማሪም ጳውሎስ “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:2) እስቲ አስበው፣ አንድ ሰው የቱንም ያህል ትልቅ ነገር ማከናወን ቢችል እንኳ ፍቅር ከሌለው “ከንቱ” ነው! የይሖዋ ቃል ለፍቅር ምን ያህል የላቀ ግምት እንደሚሰጥ ከዚህ መረዳት አይቻልም?

 7 ይሁንና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ የሚገኙትን ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት እንመርምር። በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ የሚገልጸው አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር ወይም እኛ ለአምላክ ያለንን ፍቅር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ የተናገረው በመካከላችን ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር ነው። ፍቅር የሚያደርጋቸውንና የማያደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝሯል።

ፍቅር የሚያደርገው ነገር

8. ታጋሽ መሆናችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

8 “ፍቅር ይታገሣል።” መታገሥ ማለት ሌሎችን መቻል ማለት ነው። (ቆላስይስ 3:13 አ.መ.ት) እንዲህ ዓይነት ትዕግሥት ማሳየት አያስፈልገንም? ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር አብረን የምናገለግል ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አልፎ አልፎ አንዳችን ሌላውን ልናበሳጭ እንደምንችል የታወቀ ነው። ታጋሾችና ቻዮች መሆናችን ከሌሎች  ጋር ባለን ግንኙነት የሚፈጠሩትን ቀላል ግጭቶችና አለመግባባቶች መፍታት እንድንችል ይረዳናል። ይህም የጉባኤው ሰላም እንዳይደፈርስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

9. ለሌሎች ደግነት ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

9 “ፍቅር ደግ ነው።” [የ1980 ትርጉም] ደግነት ሌሎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን በማድረግና አሳቢነት የተሞላባቸውን ቃላት በመናገር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ፍቅር በተለይ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ደግነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ለምሳሌ ብቸኝነት የሚሰማቸውና ጠያቂ የሚያስፈልጋቸው አረጋዊ ወንድም ሊኖሩ ይችላሉ። ብቻዋን ሆና ልጆቿን የምታሳድግ ወይም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላት እህት ልትኖር ትችላለች። ወይም ደግሞ የሚያጽናናው ወዳጅ የሚፈልግ የታመመ ወይም ችግር ላይ የወደቀ ወንድም ሊኖር ይችላል። (ምሳሌ 12:25፤ 17:17) እንዲህ ባሉ መንገዶች ደግነት ለማሳየት የምንጥር ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን በግልጽ ይታያል።—2 ቆሮንቶስ 8:8

10. ሐቁን መቀበል አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ፍቅር ከእውነት ጎን እንድንቆምና እውነትን እንድንናገር የሚረዳን እንዴት ነው?

10 “ፍቅር . . . ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ፍቅር . . . በደስታ ከእውነት ጎን ይቆማል” ይላል። ፍቅር እውነትን እንድንደግፍና ‘እርስ በርሳችን እውነትን እንድንነጋገር’ ይገፋፋናል። (ዘካርያስ 8:16) ለምሳሌ ያህል አንድ የምንወደው ሰው ከባድ ኃጢአት ቢሠራ ለይሖዋ እንዲሁም ስህተቱን ለሠራው ሰው ያለን ፍቅር ኃጢአቱን ለመሸፋፈን፣ ለማቃለል ወይም ለመዋሸት ከመሞከር ይልቅ አምላክ ያወጣው መሥፈርት የሚጠይቀውን ነገር እንድናደርግ ኃይል ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ እውነታውን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ለዚህ ወዳጃችን ከልብ የምናስብ ከሆነ የአምላክን ፍቅራዊ ተግሣጽ እንዲያገኝና እንዲስተካከል እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ምሳሌ 3:11, 12) በፍቅር የምንመራ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሆነን መኖር” እንፈልጋለን።—ዕብራውያን 13:18 NW

11. ፍቅር ‘ሁሉን የሚታገሥ’ በመሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚሠሯቸውን ቀላል ስህተቶች በተመለከተ ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል?

11 “ፍቅር . . . ሁሉን ይታገሣል።” ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ፍቅር ሁሉን ይሸፍናል” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) አንደኛ ጴጥሮስ 4:8 “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” በማለት  ይገልጻል። አዎን፣ በፍቅር የሚመራ አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮቹን ድክመትና ገመና ሁሉ አይገልጥም። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችን የሚሠሯቸው ስህተቶች ቀላልና በፍቅር ሊታለፉ የሚችሉ ናቸው።—ምሳሌ 10:12፤ 17:9

ፍቅር በወንድሞቻችን ላይ እምነት እንዳለን እንድንገልጽላቸው ይገፋፋናል

12. ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልሞና ላይ እምነት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ከጳውሎስ ምን ልንማር እንችላለን?

12 “ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል።” የሞፋት ትርጉም ፍቅር “ምንጊዜም መልካም የሆነውን ጎን ያምናል” ይላል። የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ነገር በጥርጣሬ ዓይን አንመለከትም። ፍቅር የወንድሞቻችንን ‘መልካም ጎን እንድናምን’ እና እንዳንጠረጥራቸው ይረዳናል። * ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ፊልሞና ትቶት ሄዶ የነበረውንና ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን የሆነውን አገልጋዩን አናሲሞስን በቀና መንፈስ እንዲቀበለው ለማበረታታት ነው። ጳውሎስ ፊልሞናን ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ በፍቅር ተማጽኖታል። “ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ” በማለት ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ያለውን እምነት ገልጿል። (ቁጥር 21) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እምነት እንድንጥልባቸው የሚገፋፋን ከሆነ እነሱም መልካም ነገር ለማድረግ ሊነሳሱ ይችላሉ።

13. ለወንድሞቻችን መልካም እንደምንመኝ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 “ፍቅር . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል።” ፍቅር ሁሉን ማመን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ተስፋ ያደርጋል። ወንድሞቻችንን ስለምንወድ መልካም የሆነውን ነገር እንመኝላቸዋለን። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም ‘አንድ በደል ቢሠራ’ የሚሰጠውን ፍቅራዊ እርዳታ ተቀብሎ አዎንታዊ እርምጃ በመውሰድ ይስተካከላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (ገላትያ 6:1) እምነታቸው የተዳከመባቸው ወንድሞቻችንም ቢሆኑ ዳግመኛ በመንፈሳዊ እንደሚበረቱ ተስፋ እናደርጋለን። እምነታቸው እንዲጠነክር ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ ጥረት በማድረግ በትዕግሥት እንይዛቸዋለን። (ሮሜ 15:1፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) አንድ የምንወደው ሰው ከእውነት መንገድ ቢወጣ ኢየሱስ በተናገረው  ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው አባካኝ ልጅ አንድ ቀን ልብ እንደሚገዛና ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርጋለን።—ሉቃስ 15:17, 18

14. በጉባኤ ውስጥ ጽናታችንን የሚፈታተን ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ፍቅር ሊረዳን የሚችለውስ እንዴት ነው?

14 “ፍቅር . . . በሁሉ ይጸናል።” ጽናት የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ወይም ችግር ሲያጋጥመን ተስፋ ቆርጠን ወደ ኋላ እንዳንል ይረዳናል። ጽናታችንን የሚፈታተን ነገር የሚያጋጥመን ከጉባኤ ውጭ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎችም ፈተና ሊሆኑብን ይችላሉ። ወንድሞቻችን ፍጹማን ባለመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኙን ይሆናል። አሳቢነት የጎደለው አነጋገር ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 12:18) ወይም አንድ የጉባኤ ጉዳይ እኛ ባሰብነው መንገድ እልባት አላገኘ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የጎለመሰ ክርስቲያን ነው ብለን የምናስበው አንድ ወንድም የሚያደርገው ነገር ሊያበሳጨንና ‘አንድ ክርስቲያን እንዴት እንዲህ ያደርጋል?’ በሚል ስሜት ቅሬታ ሊያድርብን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ራሳችንን ከጉባኤ በማግለል ይሖዋን ማገልገላችንን እናቆማለን? ፍቅር ካለን እንዲህ እንደማናደርግ የታወቀ ነው! አዎን፣ ፍቅር ካለን አንድ ወንድም ያለበት ድክመት አመለካከታችንን ሁሉ ሊያጨልምብንና ይህ ወንድምም ሆነ መላው ጉባኤ ያለውን መልካም ጎን እንዳናይ ሊያደርገን አይችልም። እንዲህ ያለው ፍቅር ፍጽምና የጎደለው አንድ ሰው የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር ምንም ይሁን ምን ለአምላክ ታማኝ እንድንሆንና ከጉባኤው ጎን እንድንቆም ይረዳናል።—መዝሙር 119:165

ፍቅር የማያደርገው ነገር

15. ተገቢ ያልሆነ ቅናት ምንድን ነው? ፍቅር ይህን ጎጂ ስሜት እንድናስወግድ የሚረዳንስ እንዴት ነው?

15 “ፍቅር አይቀናም።” ተገቢ ያልሆነ ቅናት በሌሎች ንብረት፣ መብት ወይም ችሎታ እንድንመቀኝ ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ቅናት ከራስ ወዳድነት የመነጨ ጎጂ ስሜት ሲሆን ይህን ስሜት ማስወገድ ካልተቻለ የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችላል። ‘የቅናት መንፈስ’ እንዳያድርብን ምን ሊረዳን ይችላል? (ያዕቆብ 4:5) በአጭር አነጋገር ፍቅር ነው። ይህ ውድ ባሕርይ ሌሎች ከእኛ የተሻለ ነገር ቢያገኙ ወይም ቢኖራቸው ከመቅናት ይልቅ እንድንደሰት ያደርገናል። (ሮሜ 12:15) በተጨማሪም  ፍቅር አንድ ሰው ባለው ልዩ ችሎታ ወይም ባከናወነው ላቅ ያለ ነገር ቢመሰገን ቅር እንዳንሰኝ ይረዳናል።

16. ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወድ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት እያከናወን ስላለው ነገር ጉራ ከመንዛት የምንታቀበው ለምንድን ነው?

16 “ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም።” ፍቅር ስለ ችሎታችን ወይም ስላከናወንነው ነገር ጉራ ከመንዛት እንድንቆጠብ ያደርገናል። ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ ነጋ ጠባ በአገልግሎት ስላገኘነው ስኬት ወይም በጉባኤ ውስጥ ስላገኘናቸው መብቶች በጉራ አንናገርም። እንዲህ ያለው ጉራ የሌሎችን ቅስም ሊሰብርና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ ሊያደርግ ይችላል። ፍቅር አምላክ በሰጠን የአገልግሎት መብት ከመኩራራት እንድንታቀብ ያደርገናል። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9) በተጨማሪም ፍቅር “አይታበይም” ወይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚለው “ራሱን ከልክ በላይ ከፍ አድርጎ አይመለከትም።” ፍቅር ስለ ራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዳያድርብን ይረዳናል።—ሮሜ 12:3

17. ፍቅር ለሌሎች እንዴት ያለ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል? ምን ዓይነት ጠባይ ከማሳየትስ እንድንቆጠብ ያደርገናል?

17 “ፍቅር . . . የማይገባውን አያደርግም።” የማይገባውን የሚያደርግ ሰው ከሥርዓት ውጭ የሆነ ወይም ሌሎችን የሚያስቀይም ነገር ያደርጋል። እንዲህ ያለው ምግባር ለሌሎች ስሜትና ደኅንነት ደንታ ቢስ መሆንን የሚያሳይ ስለሆነ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው። በአንጻሩ ግን ፍቅር ሥርዓታማ እንድንሆንና ለሌሎች ስሜትና ደኅንነት እንድናስብ ይገፋፋናል። ፍቅር ጨዋዎች እንድንሆን፣ ጥሩ ምግባር እንዲኖረንና ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት እንድናሳይ ያደርገናል። በመሆኑም ፍቅር “የሚያሳፍር ነገር” እንዳናደርግ ማለትም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን የሚያሸማቅቅ ወይም ቅር የሚያሰኝ ጠባይ ከማሳየት እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ኤፌሶን 5:3, 4

18. አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁሉ ነገር እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ ብሎ ድርቅ የማይለው ለምንድን ነው?

18 “ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ ይህን አገላለጽ “ፍቅር እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ አይልም” ሲል ተርጉሞታል። አፍቃሪ የሆነ ሰው ሁልጊዜ የእሱ ሐሳብ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስል ሁሉም ነገር እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ ብሎ ድርቅ አይልም። ከእሱ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች በማግባባትና በማሳመን  የእሱን አመለካከት እንዲደግፉ ለማድረግ አይሞክርም። እንዲህ ያለው ግትር ሰው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኩራት ያለበት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” ይላል። (ምሳሌ 16:18) ወንድሞቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ አመለካከታቸውን የምናከብር ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእኛን አመለካከት ለመለወጥ ፈቃደኞች እንሆናለን። ይህም ጳውሎስ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” ሲል ከሰጠው ምክር ጋር ይስማማል።—1 ቆሮንቶስ 10:24

19. ፍቅር ካለን ሌሎች ሲያስቀይሙን ምን እናደርጋለን?

19 “ፍቅር . . . አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም።” ፍቅር ሌሎች በሚናገሩትም ሆነ በሚያደርጉት ነገር በቀላሉ አይበሳጭም። እርግጥ ነው፣ ሌሎች ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲፈጽሙብን እንደምንበሳጭ የታወቀ ነው። ሆኖም እንድንቆጣ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ቢኖረንም እንኳ ፍቅር ካለን ቁጣችን ቶሎ ይበርዳል። (ኤፌሶን 4:26, 27) ቅር ያሰኘንን አነጋገር ወይም ድርጊት በመዝገብ ጽፈን የመያዝ ያህል ሁልጊዜ በውስጣችን ይዘን አንኖርም። ከዚህ ይልቅ ፍቅር ካለን አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ለመኮረጅ እንገፋፋለን። በምዕራፍ 26 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ይቅር ይላል። አንዴ ይቅር ካለ ደግሞ የሠራነውን በደል ዳግመኛ አያስበውም፤ ወይም ያንኑ ጥፋት መልሶ መላልሶ እየጠቀሰ አይወነጅለንም። ይሖዋ በደልን የማይቆጥር አምላክ በመሆኑ አመስጋኞች መሆን አይገባንም?

20. አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ሊሰማን አይገባም?

20 “ፍቅር . . . ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም።” ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ፍቅር . . . ሌሎች ሰዎች በኃጢአት ሲወድቁ በማየት አይደሰትም” ይላል። የሞፋት ትርጉም ደግሞ “ፍቅር በሌሎች ስህተት አይደሰትም” ይላል። ፍቅር በዓመጽ የማይደሰት በመሆኑ ማንኛውንም የሥነ ምግባር ብልግና አቅልለን አንመለከትም። አንድ የእምነት ባልንጀራችን በኃጢአት ወጥመድ ቢወድቅና መጥፎ ነገር ቢደርስበት ምን ይሰማናል? ፍቅር ካለን ‘ጎሽ፣ ዋጋውን አገኘ!’ አንልም። (ምሳሌ 17:5) ከዚህ ይልቅ ኃጢአት የሠራ አንድ ወንድም አዎንታዊ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ከደረሰበት መንፈሳዊ ውድቀት ሲያገግም ስንመለከት ደስ ይለናል።

 “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ”

21-23. (ሀ) ጳውሎስ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ለ) በዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

21 “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ለጥንት ክርስቲያኖች ተሰጥቶ ስለነበረው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ አምላክ በወቅቱ ለተቋቋመው አዲስ ጉባኤ ሞገስ ማሳየቱን የሚያመለክት ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች መፈወስ፣ መተንበይ ወይም በልሳን መናገር ይችሉ ነበር ማለት አይደለም። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ልዩ ስጦታዎች ለሁልጊዜ የሚቀጥሉ አልነበሩም። ይሁንና እያንዳንዱ ክርስቲያን ሊያዳብረው የሚገባ ለዘላለም የሚቀጥል አንድ ነገር አለ። ይህ ነገር ከየትኛውም ተአምራዊ ስጦታ የላቀና ለዘላለም የሚጸና ነው። እንዲያውም ጳውሎስ “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” ሲል  ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 12:31) ይህ “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ” ምንድን ነው? የፍቅር መንገድ ነው።

የይሖዋ ሕዝቦች መለያ ምልክት እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር ነው

22 በእርግጥም ጳውሎስ የገለጸው ክርስቲያናዊ ፍቅር “ለዘወትር አይወድቅም፤” በሌላ አነጋገር የሚያከትምበት ጊዜ አይኖርም። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቀው ይህ የወንድማማች ፍቅር እስከዛሬም ድረስ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መለያ ምልክት ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚታየው ይህ ፍቅር አይደለም? ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት አገልጋዮቹ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጥ ቃል የገባ በመሆኑ ይህ ፍቅር ዘላለማዊ ነው። (መዝሙር 37:9-11, 29) እንግዲያው ‘በፍቅር ለመመላለስ’ የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን በመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣም እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ አፍቃሪ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በመምሰል ለዘላለም ፍቅርን እያንጸባረቅን መኖር እንችላለን።

23 ስለ ፍቅር የሚያብራራው ክፍል መደምደሚያ በሆነው በዚህ ምዕራፍ ላይ አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። ይሁንና ከይሖዋ ፍቅር፣ ብሎም ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ በእጅጉ የምንጠቀም ከመሆኑ አንጻር ‘ይሖዋን ከልብ እንደምወደው ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ይህ ጥያቄ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

^ አን.12 እርግጥ ክርስቲያናዊ ፍቅር ሁሉን ያምናል ሲባል በቀላሉ ይታለላል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ” ሲል ያሳስበናል።—ሮሜ 16:17