በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ወደ ይሖዋ ቅረብ

 ምዕራፍ 1

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”

1, 2. (ሀ) አምላክን መጠየቅ የምትፈልጋቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ሙሴ ለአምላክ ምን ጥያቄ አቅርቧል?

ከአምላክ ጋር ስለመነጋገር አስበህ ታውቃለህ? ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር ስለመነጋገር ማሰቡ ብቻ እንኳ ፍርሃት ሊያሳድርብህ ይችላል! አምላክ ወደ አንተ ቀርቦ ቢያነጋግርህ መጀመሪያ ላይ ፈርተህ ዝም ትል ይሆናል፤ በኋላ ግን እንደምንም መልስ መስጠትህ አይቀርም። በዚህ ጊዜ በጥሞና ያዳምጥሃል፣ መልስ ይሰጥሃል አልፎ ተርፎም ዘና ብለህ የፈለግኸውን መጠየቅ እንደምትችል እንዲሰማህ ያደርጋል። እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ብታገኝ ምን ጥያቄ ታቀርብ ነበር?

2 ከብዙ ዘመናት በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመው አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ሙሴ ይባላል። ይሁንና ለአምላክ ያቀረበው ጥያቄ ሊያስገርምህ ይችላል። ሙሴ የጠየቀው ስለ ራሱ፣ ስለ ወደፊት ዕጣው ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ስላለው መከራ ሳይሆን ስለ አምላክ ስም ነበር። የአምላክን የግል ስም ያውቅ ስለነበር ይህን ጥያቄ ማቅረቡ ግር ሊያሰኝህ ይችላል። እንግዲያው ሙሴ ያቀረበው ጥያቄ ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው መሆን አለበት። እንዲያውም ይህ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። የተሰጠው መልስ የሁላችንንም ሕይወት የሚነካ ነው። ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ እንድትወስድ ሊረዳህ ይችላል። እንዴት? በአምላክና በሙሴ መካከል የተካሄደውን ይህን አስደናቂ ውይይት እስቲ ጠለቅ ብለን እንመርምር።

3, 4. አምላክ ሙሴን ከማነጋገሩ በፊት ምን ነገር ተከሰተ? አምላክ ከሙሴ ጋር ያደረገው ውይይት ምንድን ነው?

3 በወቅቱ ሙሴ የ80 ዓመት ሰው ነበር። በግብጽ በባርነት ከሚኖሩት እስራኤላውያን ወገኖቹ ተለይቶ በስደት መኖር ከጀመረ አርባ ዓመት ገደማ አልፏል። አንድ ቀን የአማቱን በጎች እየጠበቀ ሳለ አንድ ትንግርት ተመለከተ። በአካባቢው የነበረ አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ተያያዘ። ይሁንና ቁጥቋጦው ከመንደድ ይልቅ እንደ ማሾ አካባቢውን ወገግ አደረገው። ሙሴ ሁኔታውን ቀረብ ብሎ ለመመልከት ወደ ቁጥቋጦው ተጠጋ። ከእሳቱ መካከል አንድ ድምፅ ሲያነጋግረው ምንኛ ደንግጦ ይሆን! አምላክ  አንድን መልአክ ቃል አቀባይ አድርጎ በመጠቀም ከሙሴ ጋር ረዘም ያለ ውይይት አደረገ። ከዚያም ሙሴ መጀመሪያ ላይ ቢያቅማማም ሰላማዊውን ኑሮ ትቶ ወደ ግብጽ እንዲመለስና እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ እንዲያወጣ የተሰጠውን ተልእኮ ተቀበለ።—ዘጸአት 3:1-12

4 በዚህ ጊዜ ሙሴ ለአምላክ የፈለገውን ጥያቄ ማቅረብ ይችል የነበረ ቢሆንም ምን ጥያቄ ማቅረብ እንደመረጠ ተመልከት፦ “እነሆ፣ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፦ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፣ ምን እላቸዋለሁ?”—ዘጸአት 3:13

5, 6. (ሀ) ሙሴ ያቀረበው ጥያቄ ምን ሐቅ ያስገነዝበናል? (ለ) በአምላክ የግል ስም ላይ ምን አሳዛኝ ድርጊት ተፈጽሟል? (ሐ) አምላክ ስሙን ለሰው ልጆች መግለጡ ምን ያሳያል?

5 በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ጥያቄ አምላክ ራሱ ስም እንዳለው ያስገነዝበናል። ይህ ደግሞ ወሳኝ ነገር ነው። ብዙዎች ግን አቅልለው ይመለከቱታል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን የግል ስም በማውጣት “ጌታ” እና “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። ይህ በሃይማኖት ስም ከተፈጸሙት እጅግ አሳዛኝ ድርጊቶች አንዱ ነው። ከአንድ ሰው ጋር በምትተዋወቅበት ጊዜ መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? ስሙን እንደምትጠይቅ የታወቀ ነው። ከአምላክ ጋር ለመተዋወቅም ልናደርግ የሚገባው ነገር ይኸው ነው። አምላክ ልናውቀውና ልንቀርበው የማንችል ስም የለሽ አካል እንደሆነ አድርገን ልናስብ አይገባንም። የማይታይ ቢሆንም እንኳ የራሱ የሆነ ሕልውና ያለው ከመሆኑም በላይ ስም አለው። ስሙም ይሖዋ ነው።

6 ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የግል ስሙን መግለጡ እርሱን በቅርብ እንድናውቀው ልዩና አስደሳች ግብዣ እያቀረበልን እንዳለ የሚያሳይ ነው። ወደ እሱ በመቅረብ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የተሻለውን የጥበብ እርምጃ እንድንወስድ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስሙን ብቻ ሳይሆን ስሙ የሚወክለውን አካል ማንነትም ገልጾልናል።

የአምላክ ስም ትርጉም

7. (ሀ) የአምላክ የግል ስም ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ሙሴ የአምላክን ስም በጠየቀበት ጊዜ ማወቅ የፈለገው ነገር ምን ነበር?

7 ብዙዎች፣ “ይሖዋ” የሚለው ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። ይሖዋ ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና እንዲመጡ  ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ዓላማው በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ስለሚያደርግ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ነው። ይህ ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል። ይሁን እንጂ የስሙ መሠረታዊ ትርጉም የአምላክን ፈጣሪነት ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ሙሴ ከዚህ የበለጠ ሊያውቀው የፈለገው ነገር እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሖዋ፣ ፈጣሪ እንደሆነ እንዲሁም ስሙ ማን እንደሆነ ሙሴ ያውቅ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ መለኮታዊው ስም ለሰዎች አዲስ አልነበረም። ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ሙሴ የአምላክን ስም ሲጠይቅ ስሙ ስለሚወክለው አካል መጠየቁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። በሌላ አነጋገር ሙሴ ‘እስራኤላውያን ሕዝቦችህ በአንተ እንዲታመኑና ነፃ እንደምታወጣቸው እርግጠኛ እንዲሆኑ ስለ አንተ ምን ልነግራቸው እችላለሁ?’ ብሎ የጠየቀ ያህል ነበር።

8, 9. (ሀ) ይሖዋ ለሙሴ ምን መልስ ሰጠው? የሰጠው መልስ ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጎመውስ እንዴት ነው? (ለ) “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” የሚለው አገላለጽ ምን ማለት ነው?

8 ይሖዋ፣ ስለ ማንነቱ አስገራሚ የሆነ ነገር በመግለጽ መልስ ሰጥቶታል፤ የተናገረው ነገር ከስሙ ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው። ሙሴን “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” አለው። (ዘጸአት 3:14 NW) የ1954ቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “ያለና የሚኖር እኔ ነኝ” ሲሉ ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ትክክለኛው አተረጓጎም እንደሚያሳየው አምላክ ይህን ሲናገር ስለ ሕልውናው በአጽንኦት መግለጹ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ስሙ ምን ትርጉም እንደሚያስተላልፍ ለሙሴ ብሎም ለሁላችንም መናገሩ ነበር። ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ‘መሆን የሚፈልገውን’ ሁሉ ይሆናል። የጄ ቢ ሮዘርሃም ትርጉም “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት ይህን ጥቅስ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሑር የሆኑ አንድ ሰው ይህን ሐረግ “ሁኔታው ወይም የተፈለገው ነገር ምንም ይሁን ምን . . . አምላክ ለተፈለገው ነገር መፍትሔ ‘ሆኖ ይገኛል’” ሲሉ ገልጸውታል።

9 ይህ ለእስራኤላውያን ምን ዋስትና ይሰጣቸዋል? ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥማቸው ወይም ደግሞ የሚገጥማቸው ሁኔታ ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ይሖዋ ከባርነት ነፃ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር  ለማስገባት መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። በእርግጥም ስሙ በአምላክ እንዲታመኑ የሚያደርግ ነበር። ይህ ስም በዛሬውም ጊዜ በአምላክ እንድንታመን ሊያደርገን ይችላል። (መዝሙር 9:10) ለምን?

10, 11. የይሖዋ ስም፣ አምላክ ሁኔታው የሚጠይቅበትን ሁሉ መሆን የሚችል ከሁሉ የተሻለ ጥሩ አባት እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው የሚገፋፋን እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

10 ለምሳሌ ያህል ወላጆች ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ሁለገብ መሆን እንደሚጠይቅ ያውቃሉ። አንድ ወላጅ በአንድ ቀን ውስጥ አስታማሚ፣ የወጥ ቤት ሠራተኛ፣ አስተማሪ፣ ሥርዓት አስከባሪ እንዲሁም ፈራጅ ሆኖ መገኘትና ሌሎችንም ድርሻዎች መወጣት ሊያስፈልገው ይችላል። ብዙዎቹ ወላጆች ሊወጧቸው የሚገቡት በርካታ የሥራ ድርሻዎች ከአቅማቸው በላይ ይሆኑባቸዋል። ሕፃናት በወላጆቻቸው ላይ በጣም ስለሚተማመኑ ቢያማቸው ሕመማቸውን የሚያስታግስ ነገር እንደሚያደርጉላቸው፣ ቢጣሉ እንደሚያስታርቋቸው፣ መጫወቻቸው ቢሰበር እንደሚጠግኑላቸውና ለሚያነሱት ማንኛውም ጥያቄ መልስ እንደሚሰጧቸው እርግጠኞች ናቸው። አንዳንድ ወላጆች እንዲህ ያለ እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ ዓይነት ሰዎች እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ ባለባቸው የአቅም ገደብ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ሲበሳጩ ይታያል። ከእነዚህ ኃላፊነቶች መካከል ብዙዎቹን መወጣት ባለመቻላቸው በጣም ያዝናሉ።

11 ይሖዋም አፍቃሪ የሆነ አባት ነው። ሆኖም ፍጹም የሆኑትን ደንቦቹን ሳይጥስ በምድር ያሉትን ልጆቹን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመንከባከብ ሁሉን መሆን ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ የተባለው ስሙ ከሁሉ የተሻለ ጥሩ አባት እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው ይገፋፋናል። (ያዕቆብ 1:17) ብዙም ሳይቆይ ሙሴም ሆነ ታማኝ የሆኑት እስራኤላውያን በሙሉ ይሖዋ ልክ እንደ ስሙ መሆኑን በተግባር አይተዋል። ይሖዋ በማንም የማይበገር የጦር አበጋዝ፣ የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ አዛዥ፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሕግ ሰጪ፣ ፈራጅና ንድፍ አውጪ ሲሆን በመመልከታቸው ታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት አድሮባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ምግብና ውኃ በማቅረብ እንዲሁም ልብሳቸውና ጫማቸው እንዳያልቅ በማድረግ ሌሎች ድርሻዎችንም ተወጥቷል።

12. ፈርዖን ለይሖዋ የነበረው አመለካከት ሙሴ ከነበረው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

12 በዚህ መንገድ አምላክ የግል ስሙ እንዲታወቅ አድርጓል፣ በዚህ  ስም ስለሚጠራው አካል አስገራሚ ነገሮችን ገልጿል፤ አልፎ ተርፎም ስለ ራሱ የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑን በተግባር አሳይቷል። አምላክ እንድናውቀው እንደሚፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ እኛ ምን ምላሽ እንሰጣለን? ሙሴ አምላክን ለማወቅ ፍላጎት ነበረው። ይህ ከፍተኛ ፍላጎት የሙሴን የሕይወት ጎዳና የለወጠው ከመሆኑም በተጨማሪ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር በጣም እንዲቀራረብ አድርጎታል። (ዘኍልቁ 12:6-8፤ ዕብራውያን 11:27) የሚያሳዝነው ግን በሙሴ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አልነበራቸውም። ሙሴ በፈርዖን ፊት የይሖዋን ስም በጠቀሰበት ጊዜ ዕብሪተኛው የግብጽ ንጉሥ “ይሖዋ ማን ነው?” ሲል ተናግሯል። (ዘጸአት 5:2 NW) ፈርዖን እንዲህ ሲል የተናገረው ስለ ይሖዋ የማወቅ ፍላጎት ኖሮት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘ይሖዋ ደግሞ ማን ነው’ በማለት በንቀት መናገሩ ነበር። ዛሬም ብዙዎች ለአምላክ እምብዛም ትኩረት አይሰጡም። ይህ ደግሞ ሰዎች ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ እንደሆነ የሚገልጸውን እውነት እንዳያስተውሉ ያደርጋቸዋል።

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ

13, 14. (ሀ) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ የማዕረግ ስሞች የተሰጡት ለምንድን ነው? ከእነዚህስ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ( ገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ‘ሉዓላዊ ጌታ’ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ይሖዋ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ሁኔታው የሚጠይቀውን ሁሉ መሆን የሚችል አምላክ ነው። ከዚህ አንጻር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተለያዩ የማዕረግ ስሞች መጠራቱ የተገባ ነው። ይሁንና እነዚህ የማዕረግ ስሞች የአምላክን የግል ስም ሊተኩ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ ስሙ የሚወክለውን ነገር በተመለከተ ያለን ግንዛቤ እንዲሰፋ የሚያደርጉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ልዑል እግዚአብሔር” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ሳሙኤል 7:22 አ.መ.ት) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሶ የሚገኘው ይህ ከፍ ያለ የማዕረግ ስም ይሖዋ ያለውን ቦታ በግልጽ የሚያሳይ ነው። መላውን ጽንፈ ዓለም የመግዛት መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። ይህ የሆነበትን ምክንያት ቀጥሎ ተመልከት።

14 ይሖዋ ብቸኛ ፈጣሪ ነው። ራእይ 4:11 እንዲህ ይላል፦ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና  ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” ከይሖዋ በቀር እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሌላ ማንም የለም። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው እሱ ነው! ሁሉን የፈጠረ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ክብር፣ ውዳሴና ኃይል ሊቀበል እንደሚገባው ምንም አያጠያይቅም።

15. ይሖዋ ‘የዘመናት ንጉሥ’ የተባለው ለምንድን ነው?

15 ሌላው ለይሖዋ ብቻ የተሰጠ የማዕረግ ስም ‘የዘመናት ንጉሥ’ የሚለው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 15:3 አ.መ.ት) ይህ ምን ማለት ነው? ሁኔታው ከእኛ የመረዳት አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ጥንትም ሆነ ወደፊት ዘላለማዊ አምላክ ነው። መዝሙር 90:2 “ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” ይላል። በመሆኑም ይሖዋ መጀመሪያም መጨረሻም የለውም። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት የነበረ በመሆኑ “በዘመናት የሸመገለ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው! (ዳንኤል 7:9, 13, 22) ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ ሊሆን አይገባውም ብሎ ሊከራከር የሚችል ይኖራል?

16, 17. (ሀ) ይሖዋን ልናየው የማንችለው ለምንድን ነው? ይህስ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ልናየው ወይም ልንዳስሰው ከምንችለው ከማንኛውም ነገር በላቀ ደረጃ እውን ነው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

16 ይሁንና አንዳንዶች እንደ ፈርዖን የይሖዋን ሉዓላዊነት መቀበል ያዳግታቸዋል። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች በአብዛኛው አምነው የሚቀበሉት በዓይናቸው የሚያዩትን ነገር ነው። ሉዓላዊውን ጌታ ልናየው አንችልም። መንፈስ በመሆኑ በሰብዓዊ ዓይን አይታይም። (ዮሐንስ 4:24) ከዚህም በተጨማሪ ሰው ቃል በቃል በአምላክ ፊት ቢቆም በሕይወት ሊቀጥል አይችልም። ይሖዋ ራሱ ሙሴን “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” ብሎታል።—ዘጸአት 33:20፤ ዮሐንስ 1:18

17 ይህ ሊያስገርመን አይገባም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሙሴ የአምላክ ወኪል በሆነ አንድ መልአክ አማካኝነት የይሖዋን ክብር በትንሹ ተመልክቷል። ውጤቱስ ምን ነበር? ይህ ከሆነ በኋላ እስራኤላውያን የሙሴን ፊት ማየት እስኪያስፈራቸው ድረስ ፊቱ ለተወሰነ ጊዜ ‘ያንጸባርቅ’ ነበር። (ዘጸአት 33:21-23፤ 34:5-7, 29, 30) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የሉዓላዊውን ጌታ ክብር ሙሉ በሙሉ ሊያይ የሚችል ሰው የለም! እንዲህ ሲባል ታዲያ ይሖዋ እንደሚታይ ወይም እንደሚዳሰስ  ነገር እውን ሊሆንልን አይችልም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ለምሳሌ እንደ ነፋስ፣ የራዲዮ ሞገድና ሐሳብ ያሉ በርካታ ነገሮች ባናያቸውም እንዳሉ አምነን እንቀበላለን። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዓመታት ቢያልፉ እንኳ በጊዜ ሂደት የማይለወጥና ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር አምላክ ነው! ከዚህ አንጻር ሲታይ በዓይን የሚታየው ነገር ሊያረጅና ሊጠፋ የሚችል በመሆኑ ይሖዋ ከምናየው ወይም ከምንዳስሰው ነገር በላቀ ደረጃ እውን ነው ሊባል ይችላል። (ማቴዎስ 6:19) ይሁን እንጂ አምላክ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል ወይም የራሱ የሆነ ምንም ዓይነት ባሕርይ የሌለው አንድ ኃይል እንደሆነ አድርገን ልናስብ ይገባል? እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።

የራሱ ባሕርያት ያሉት አምላክ

18. ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ምንድን ነው? በይሖዋ ዙሪያ የታዩት “ሕያዋን ፍጡራን” ያላቸው አራት ፊትስ ምን ያመለክታል?

18 አምላክን ልናየው ባንችልም እንኳ በሰማይ ያለውን ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቁሙ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። የሕዝቅኤል መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለዚህ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። ሕዝቅኤል በሰማይ የሚገኘውንና በአንድ ግዙፍ ሰማያዊ ሰረገላ የተመሰለውን የይሖዋ ድርጅት በራእይ ተመልክቷል። በተለይ ደግሞ በይሖዋ ዙሪያ ያሉትን ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ በጣም አስደናቂ ነው። (ሕዝቅኤል 1:4-10) እነዚህ “ሕያዋን ፍጡራን” [አ.መ.ት] ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን መልካቸው አምላክን በተመለከተ በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። እያንዳንዳቸው አራት ፊት ማለትም የበሬ፣ የአንበሳ፣ የንስርና የሰው ፊት አላቸው። እነዚህም ጎላ ብለው የሚታዩትን አራቱን የይሖዋ ባሕርያት እንደሚያመለክቱ መገመት ይቻላል።—ራእይ 4:6-8, 10

19. (ሀ) በበሬ (ለ) በአንበሳ (ሐ) በንስር (መ) በሰው ፊት የተወከለው ባሕርይ ምንድን ነው?

19 በሬ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው እንስሳ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአብዛኛው ኃይልን ለማመልከት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል። አንበሳ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ፍትሕን ያመለክታል። እውነተኛ ፍትሕ ድፍረት የሚጠይቅ ሲሆን አንበሳም በዚህ ባሕርይው ይታወቃል። ንስር ከፍተኛ የሆነ የማየት ችሎታ ያለው በመሆኑ ከብዙ መቶ ሜትር ርቀት ላይ እንኳ ሆኖ  ትናንሽ ነገሮችን ማየት ይችላል። ስለዚህ የንስሩ ፊት አምላክ አርቆ በማስተዋል ረገድ ያለውን ጥበብ በሚገባ ይወክላል። በራእዩ ላይ የታየው የሰው ፊትስ ምን ያመለክታል? ሰው በአምላክ መልክ የተፈጠረ ስለሆነ ከሁሉ የላቀውን የአምላክ ባሕርይ ማለትም ፍቅርን የማንጸባረቅ ችሎታ ተሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 1:26) እነዚህ የይሖዋ ባሕርያት ማለትም ኃይል፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጎላ ብለው የተገለጹ በመሆናቸው የአምላክ ዋነኛ ባሕርያት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።

20. የይሖዋ ባሕርይ ተለውጦ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? እንደዚህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

20 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚሰጠው መግለጫ ከተጻፈ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፉ በመሆኑ በእነዚህ ጊዜያት አምላክ ተለውጦ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? በፍጹም፤ የአምላክ ባሕርይ አይለወጥም። ይሖዋ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል። (ሚልክያስ 3:6) ይሖዋ እንዲሁ በስሜት ተገፋፍቶ ሐሳቡን አይለውጥም። ከዚህ ይልቅ ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሚወስደው እርምጃ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አባት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ባሕርያቱን እንደ አስፈላጊነቱ ይጠቀምባቸዋል። ከአራቱ ባሕርያት መካከል ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ፍቅር ነው። አምላክ በሚያከናውነው በማንኛውም ነገር ላይ ፍቅሩ ይንጸባረቃል። ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን የሚያንጸባርቀው  በፍቅር ላይ ተመርኩዞ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ይህን ባሕርይ ለየት ባለ መንገድ ይገልጸዋል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ፍቅር አለው ወይም አምላክ አፍቃሪ ነው እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ፍቅር ነው ይላል። አምላክ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ዋነኛ ባሕርይው በሆነው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው።

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”

21. ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ ምን ስሜት ያድርብናል?

21 አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን ለጓደኞቹ እያሳየ ከልብ በመነጨ የደስታና የኩራት ስሜት “አባቴን አያችሁት” ሲል ሰምተህ ታውቃለህ? የአምላክ አገልጋዮችም ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ እንዲሰማቸው የሚያደርግ በቂ ምክንያት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው” ብለው በደስታ ስሜት የሚናገሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 25:8, 9) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ባወቅህ መጠን ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ጥሩ አባት እንደሆነ እየተሰማህ ይሄዳል።

22, 23. መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ስላለው አባታችን ምን መግለጫ ይሰጣል? ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?

22 እንዲህ ያለው አባት አንዳንድ የባሕታዊ ኑሮ የሚኖሩ ሃይማኖተኞችና ፈላስፎች እንደሚያስቡት ፍቅር የሌለው ወይም ሊቀረብ የማይችል አይደለም። ፍቅር የሌለውን አምላክ መቅረብ እንደሚከብደን የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን በሰማይ ስላለው አባታችን የሚሰጠው መግለጫ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። እንዲያውም “ደስተኛ አምላክ” ሲል ይጠራዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ይሖዋ ሊያዝንም ሊደሰትም የሚችል አምላክ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ ለእነሱ ደኅንነት ሲል ያወጣቸውን ደንቦች ሲጥሱ ‘እጅግ ያዝናል።’ (ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:41) ይሁን እንጂ ቃሉ የሚለውን ስናደርግ ‘ልቡን ደስ እናሰኘዋለን።’—ምሳሌ 27:11

23 አባታችን ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ቃሉ አምላክን ‘እየመረመርን እንድናገኘው’ የሚያበረታታን ከመሆኑም በላይ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” አለመሆኑን ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) ይሁንና ተራ የሆኑ ሰዎች የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ እንዴት ሊቀርቡት ይችላሉ?