በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 7

‘መጠጊያችን የሆነው አምላክ’—ለመጠበቅ የሚጠቀምበት ኃይል

‘መጠጊያችን የሆነው አምላክ’—ለመጠበቅ የሚጠቀምበት ኃይል

1, 2. እስራኤላውያን በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ሲና ምድር ሲገቡ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸው ነበር? ይሖዋስ ያጽናናቸው እንዴት ነው?

እስራኤላውያን በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ሲና ምድር በገቡበት ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተደቅነውባቸው ነበር። ከፊታቸው በጣም አስፈሪ የሆነ ጉዞ ይጠብቃቸዋል። የሚጓዙበት ‘ጭልጥ ያለ አስፈሪ ምድረ በዳ፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ የሞላበት’ ነው። (ዘዳግም 8:15 አ.መ.ት) በተጨማሪም ከጠላት ብሔራት ሊሰነዘር የሚችለው ጥቃት ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ወዳሉበት ቦታ ያመጣቸው ይሖዋ ነው። ታዲያ አምላካቸው ከዚህ ሁሉ ችግር ይታደጋቸው ይሆን?

2 ይሖዋ “በግብፃውያን ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከምኋችሁ፣ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል” በማለት አጽናናቸው። (ዘጸአት 19:4) ይሖዋ ሕዝቦቹን በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ ንስር በክንፍ ተሸክሞ ከግብጻውያን እንዳዳናቸው መለስ ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ‘የንስር ክንፍ’ መለኮታዊ ጥበቃን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ነው እንድንል የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።

3. ‘የንስር ክንፍ’ መለኮታዊ ጥበቃን ለማመልከት ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 ንስር ረጅምና ጠንካራ የሆኑ ክንፎቹን የሚጠቀመው ከፍ ብሎ በሰማይ ላይ ለመንሳፈፍ ብቻ አይደለም። ቀትር ላይ ሙቀቱ ኃይለኛ በሚሆንበት ጊዜ እናቲቱ ንስር ከሁለት ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸውን ክንፎቿን በመዘርጋት ጫጩቶቿን ከፀሐይ ሐሩር ትጋርዳቸዋለች። በብርድ ጊዜ ደግሞ በክንፎቿ በማቀፍ ታሞቃቸዋለች። ንስር ጫጩቶቿን እንደምትንከባከብ ሁሉ ይሖዋም ገና ያልጠነከረውን የእስራኤል ብሔር ጠብቆታል እንዲሁም ተንከባክቦታል። በምድረ በዳ በሚጓዙበት ጊዜ ለእሱ  ታማኝ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ ኃያል በሆኑት ምሳሌያዊ ክንፎቹ ጥላ ሥር መሸሸግ ይችላሉ። (ዘዳግም 32:9-11፤ መዝሙር 36:7) ዛሬስ እኛ የአምላክን ጥበቃ እናገኛለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?

ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል

4, 5. አምላክ ሕዝቡን ለመጠበቅ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ አገልጋዮቹን መጠበቅ እንደማይሳነው የተረጋገጠ ነው። ‘ሁሉን የሚችል አምላክ’ የሚለው ስያሜ ይሖዋ ምንም ነገር ሊበግረው የማይችል ኃይል እንዳለው ያመለክታል። (ዘጸአት 6:3) ምንም ነገር ሊያቆመው እንደማይችል የባሕር ማዕበል የይሖዋንም ኃይል ሊገታ የሚችል ነገር አይኖርም። ይሖዋ የፈቀደውን ማድረግ የሚችል በመሆኑ ‘ኃይሉን ተጠቅሞ ሕዝቡን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነው?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

5 በአጭር አነጋገር መልሱ አዎን ነው! ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚጠብቅ ዋስትና ሰጥቶናል። መዝሙር 46:1 “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” ይላል። አምላክ “የማይዋሽ” በመሆኑ ሕዝቡን ለመጠበቅ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት እንችላለን። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ጥበቃና እንክብካቤ ለመግለጽ የተጠቀመባቸውን ግሩም ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት።

6, 7. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን የሚጠብቀው እንዴት ነበር? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በጎቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ያለውን ልባዊ ፍላጎት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የሚገልጸው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ እረኛችን ሲሆን ‘እኛ ደግሞ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።’ (መዝሙር 23:1፤ 100:3) እንደ በግ ምስኪን እንስሳ የለም ለማለት ይቻላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን ከአንበሳ፣ ከተኩላና ከድብ እንዲሁም ከሌባ ለመጠበቅ ደፋር መሆን ነበረበት። (1 ሳሙኤል 17:34, 35፤ ዮሐንስ 10:12, 13) ከዚህም ሌላ እረኛው በጎቹን በርኅራኄ መንከባከብ ይጠበቅበት ነበር። አንዲት በግ ምጥ ይዟት ከመንጋው በምትለይበት ጊዜ እረኛው አጠገቧ ሆኖ የሚጠብቃት  ከመሆኑም በላይ ከወለደች በኋላ ግልገሏን አቅፎ ወደ መንጋው ይወስዳታል።

“በዕቅፉም ይይዛቸዋል”

7 ይሖዋም ልክ እንደ አንድ እረኛ እንደሚጠብቀን ቃል ገብቶልናል። (ሕዝቅኤል 34:11-16) በዚህ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ የተብራራውን ኢሳይያስ 40:11ን መለስ ብለህ አስታውስ። ይህ ጥቅስ ይሖዋን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል [“በዕቅፉም ይይዛቸዋል፣” አ.መ.ት]።” ግልገሏ እረኛው ‘እንዲያቅፋት’ የምታደርገው እንዴት ነው? ወደ እረኛው ተጠግታ እግሩን ትታከከዋለች። ሆኖም ጎንበስ ብሎ በማንሳት እቅፍ የሚያደርጋት እረኛው ነው። ታላቁ እረኛ እኛን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!

8. (ሀ) አምላክ ጥበቃ የሚያደርገው ለእነማን ነው? ይህስ በምሳሌ 18:10 ላይ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ስም መሸሸጊያ እንዲሆንልን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

8 ሆኖም አምላክ የሚጠብቀው ወደ እሱ የሚቀርቡትን ብቻ ነው። ምሳሌ 18:10 [አ.መ.ት] “የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” በማለት ይገልጻል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በምድረ በዳ ለመሸሸጊያነት የሚያገለግሉ ግንቦች ይገነቡ ነበር። ሆኖም አስጊ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ወደዚህ ግንብ መሮጥ የግለሰቡ ፋንታ ነው። የአምላክም ስም መሸሸጊያ ሊሆነን የሚችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። የአምላክን ስም መጥራት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ስሙ በራሱ አንድ ዓይነት ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው አድርጎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዚህ ስም ባለቤት የሆነውን አምላክ ማወቅና በእሱ መታመን እንዲሁም ያወጣቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ መተርጎም ይኖርብናል። በእሱ ከታመንን ጥበቃ እንደሚያደርግልንና ከለላ እንደሚሆነን ቃል የገባልን መሆኑ ምን ያህል እንደሚያስብልን የሚያሳይ ነው።

“አምላካችን . . . ያድነን ዘንድ ይችላል”

9. ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ የገባውን ቃል በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ አገልጋዮቼን እጠብቃለሁ ብሎ ቃል በመግባት ብቻ አልተወሰነም።  በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ ሕዝቡን መጠበቅ እንደሚችል ተአምራዊ በሆነ መንገድ አሳይቷል። በጥንት እስራኤል ዘመን የይሖዋ ኃያል ‘እጅ’ የሕዝቡን ጠላቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት በቁጥጥር ስር አድርጓል። (ዘጸአት 7:4) ይሁን እንጂ ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ ለመጠበቅ ኃይሉን የተጠቀመባቸው ጊዜያትም አሉ።

10, 11. ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉ?

10 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን ወጣቶች ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል አንሰግድም ባሉ ጊዜ ንጉሡ በጣም ተባሳጭቶ በሚንቀለቀል የእቶን እሳት ውስጥ እንደሚጥላቸው ዛተባቸው። የዘመኑ ኃያል ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር “ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?” ሲል ተሳለቀ። (ዳንኤል 3:15) ሦስቱ ወጣቶች አምላካቸው እነሱን ለማዳን የሚያስችል ኃይል እንዳለው እርግጠኞች የነበሩ ቢሆንም በዚያ ወቅት ያድነናል ብለው ሙሉ በሙሉ አልጠበቁም ነበር። (ዳንኤል 3:17, 18) በእርግጥም እሳቱ ሰባት እጥፍ እንዲነድድ ቢደረግም እንኳ ምንም ለማይሳነው አምላካቸው ይህ ከባድ ነገር አልነበረም። ይሖዋ ወጣቶቹን ከእሳቱ ውስጥ በማዳኑ ንጉሡ “እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለም” ብሎ ለማመን ተገድዷል።—ዳንኤል 3:29

11 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የአንድያ ልጁን ሕይወት ወደ አይሁዳዊቷ ድንግል ማርያም ማህፀን ባዛወረ ጊዜ ኃይሉን በመጠቀም ጥበቃ ማድረግ እንደሚችል እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል። አንድ መልአክ ማርያምን “ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ” ብሏት ነበር። በተጨማሪም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል” ሲል ገልጾላታል። (ሉቃስ 1:31, 35) የአምላክ ልጅ ከምንጊዜውም ይበልጥ ሕይወቱ ለአደጋ ተጋልጦ ነበር ለማለት ይቻላል። የሰብዓዊ እናቱ ኃጢአትና አለፍጽምና ወደ ጽንሱ ይተላለፍ ይሆን? ሰይጣን ይህን ልጅ ገና ሳይወለድ ጉዳት ሊያደርስበት ወይም ሊገድለው ይችል ይሆን? በፍጹም! ይሖዋ ልጁ ከተጸነሰበት ጊዜ አንስቶ ኃጢአት እንዳይተላለፍበት እንዲሁም በሰው፣ በአጋንንትም ሆነ በሌላ በማንኛውም ኃይል ጉዳት እንዳይደርስበት ለማርያም ልዩ ጥበቃ አድርጎላት ነበር ለማለት ይቻላል። ኢየሱስ ከተወለደም በኋላ ቢሆን ይሖዋ  ጥበቃ አድርጎለታል። (ማቴዎስ 2:1-15) አምላክ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ውድ ልጁ ምንም ጉዳት አላገኘውም።

12. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ ለአንዳንድ ግለሰቦች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደረገው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ ለአንዳንድ ግለሰቦች እንዲህ ባለ ተአምራዊ ሁኔታ ጥበቃ ያደረገው ለምንድን ነው? ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ነው። ለምሳሌ ያህል አምላክ ለመላው የሰው ዘር ያወጣው ዓላማ እንዲፈጸም ሕፃን ለነበረው ለኢየሱስ ጥበቃ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። ‘በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ ለትምህርታችን’ የተጻፈው የአምላክ ቃል ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ለአገልጋዮቹ እንዴት ጥበቃ እንዳደረገ የሚገልጹ በርካታ ታሪኮችን ይዟል። (ሮሜ 15:4) አዎን፣ እነዚህ ታሪኮች ሁሉን ማድረግ በማይሳነው አምላካችን ላይ ያለንን እምነት ያጠነክሩልናል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ አምላክ ምን ዓይነት ጥበቃ ያደርግልናል ብለን መጠበቅ እንችላለን?

አምላክ ጥበቃ ያደርግልናል ሲባል ምን ማለት ነው?

13. ይሖዋ እኛን ከማንኛውም ዓይነት ችግር ለመታደግ ተአምር የመፈጸም ግዴታ አለበት? አብራራ።

13 ይሖዋ መለኮታዊ ጥበቃ ለማድረግ ቃል የገባ ቢሆንም እኛን ከማንኛውም ዓይነት ችግር ለመታደግ ተአምር የመፈጸም ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። አምላክ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ከችግር ነፃ ሆነን እንደምንኖር ዋስትና አልሰጠንም። ብዙ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ድህነትን፣ ጦርነትን፣ በሽታንና ሞትን ጨምሮ የተለያዩ መከራዎች ይደርሱባቸዋል። ኢየሱስ እስከ መጨረሻው መጽናት አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ የተናገረው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 24:9, 13) ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም አገልጋዮቹን ከማንኛውም ዓይነት ችግር የሚጠብቃቸው ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ይሖዋን ለመክሰስና ሰዎች ለአምላክ ባላቸው ታማኝነት ላይ ጥያቄ ለማንሳት ሰበብ ያገኝ ነበር።—ኢዮብ 1:9, 10

14. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በሙሉ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደርጋል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

14 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳ ቢሆን ይሖዋ አገልጋዮቹን በሙሉ  ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከሞት ይታደግ ነበር ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ያዕቆብ በ44 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሄሮድስ ተገድሏል። ይሁንና ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ጴጥሮስን “ከሄሮድስ እጅ” አድኖታል። (የሐዋርያት ሥራ 12:1-11) የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስ ደግሞ ከጴጥሮስም ሆነ ከያዕቆብ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ ኖሯል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ ለአገልጋዮቹ በሙሉ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ጥበቃ ያደርጋል ብለን መጠበቅ አንችልም። ከዚህም በተጨማሪ “ጊዜና አጋጣሚ” በሚፈጥረው ሁኔታ በሁላችንም ላይ ያልታሰበ ነገር ሊደርስ ይችላል። (መክብብ 9:11 NW) ታዲያ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

ይሖዋ ሰብዓዊ ጥበቃ ያደርግልናል

15, 16. (ሀ) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜም ሆነ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ለአገልጋዮቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

15 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ የሚያደርግልንን ሰብዓዊ ጥበቃ እንመልከት። የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን አምላክ በቡድን ደረጃ ጥበቃ ያደርግልናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። አለዚያ ለሰይጣን ጥቃት በእጅጉ የተጋለጥን እንሆናለን። “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ቢችል በጣም ደስ እንደሚለው መገመት አያዳግትም። (ዮሐንስ 12:31፤ ራእይ 12:17) አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት የስብከት ሥራችንን ከማገዳቸውም በላይ እኛን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች በአቋማቸው በመጽናት ያለማሰለስ መስበካቸውን ቀጥለዋል! ኃያላን ብሔራት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ መስለው የሚታዩትን የእነዚህን ክርስቲያኖች ሥራ ማስቆም ያልቻሉት ለምንድን ነው? ይሖዋ ኃያል በሆኑት ክንፎቹ ጥላ ስለጋረዳቸው ነው!—መዝሙር 17:7, 8

16 በቅርቡ በሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ ወቅት አምላክ ስለሚያደርግልን ጥበቃስ ምን ለማለት ይቻላል? አምላክ የሚወስደውን የቅጣት እርምጃ መፍራት አያስፈልገንም። ምክንያቱም “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።” (ራእይ 7:14፤ 2 ጴጥሮስ 2:9)  እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ስለ ሁለት ነገሮች እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ከምድር ገጽ እንዲጠፉ አይፈቅድም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እስከመጨረሻው በአቋማቸው የሚጸኑ አገልጋዮቹን ቢሞቱ እንኳ በትንሣኤ በማስነሳት ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ በዚህ ሥርዓት ለሚሞቱ የአምላክ አገልጋዮች ትልቅ ዋስትና ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29

17. ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

17 በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቢሆን ይሖዋ የሰዎችን የልብ ዝንባሌና ሕይወት የመለወጥ ኃይል ባለው ሕያው ‘ቃሉ’ አማካኝነት ይጠብቀናል። (ዕብራውያን 4:12) በቃሉ ውስጥ የሰፈሩትን መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎች በሥራ ላይ በማዋል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአካላችን ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ጉዳቶች ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። ኢሳይያስ 48:17 “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ . . . አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” ይላል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር መከተላችን የተሻለ ጤናና ረጅም ዕድሜ እንዲኖረን እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ከዝሙት እንድንርቅና ሰውነትን ከሚያረክስ ማንኛውም ነገር ራሳችንን እንድናነጻ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች በሚከተሏቸው መጥፎ ልማዶች ሳቢያ ከሚደርስባቸው ጉዳት ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) የአምላክ ቃል እንዲህ ያለ ጥበቃ ስለሚያደርግልን ከልብ አመስጋኞች ነን!

ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል

18. ይሖዋ ምን ዓይነት መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል?

18 ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋምና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና አጠንክረን ለመያዝ የሚያስችለንን ትጥቅ በመስጠት መንፈሳዊ ጉዳት እንዳያገኘን ይጠብቀናል። ይሖዋ እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያደርግልን ለአሁኑ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን ለዘላለማዊ ደኅንነታችን ሲል ነው። አምላክ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ሲል ያደረጋቸውን አንዳንድ ዝግጅቶች እንመልከት።

19. የይሖዋ መንፈስ የሚያጋጥመንን ችግር ሁሉ መቋቋም እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?

 19 ይሖዋ ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ ነው። (መዝሙር 65:2) በሕይወታችን ውስጥ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ በመንገር ትልቅ እፎይታ ልናገኝ እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ያለብንን ችግር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባያስወግድልንም እንኳ ለእሱ ያቀረብነውን ልባዊ ጸሎት በመስማት ችግሩን ለመቋቋም ወይም ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5, 6) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሚለምኑት ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:13) ይህ መንፈስ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና ወይም ችግር እንድንቋቋም የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ችግር እስኪያስወግድልን ድረስ ጸንተን እንድንኖር የሚያስችለንን ‘ታላቅ ኃይል’ ይሰጠናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7

20. ይሖዋ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በመጠቀም ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

20 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ጥበቃ የሚያደርግልን በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ሕዝቡ በአንድ ዓለም አቀፋዊ “የወንድማማች ማኅበር” ሥር እንዲሰባሰቡ አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW፤ ዮሐንስ 6:44) በዚህ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለው ፍቅር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሰዎች ላይ ምን  ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይህ መንፈስ እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ቸርነት ያሉ ማራኪና ውድ ባሕርያትን እንድናፈራ ያስችለናል። (ገላትያ 5:22, 23) በመሆኑም ተጨንቀን ባለንበት ጊዜ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ወደ እኛ ቀርቦ ጠቃሚ ምክር ቢሰጠን ወይም ቢያበረታታን ይሖዋ ይህን ሰው በመጠቀም ላደረገልን እርዳታ ልናመሰግነው ይገባናል።

21. (ሀ) ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል ምን ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል? (ለ) ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ባደረጋቸው ዝግጅቶች አንተ በግልህ የተጠቀምከው እንዴት ነው?

21 ከዚህም ሌላ ይሖዋ እኛን ለመጠበቅ ሲል በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ይሰጠናል። በቃሉ አማካኝነት ብርታት እንድናገኝ ሲል ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርብ ሾሞታል። ይህ ታማኝ ባሪያ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ጨምሮ በርካታ ጽሑፎችን በማተምና የተለያዩ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የሚያስፈልገንን ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ ያቀርብልናል። (ማቴዎስ 24:45) በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር ወይም ሐሳብ አለዚያም ደግሞ ጸሎት አበረታቶህና አጽናንቶህ ያውቃል? ወይም ደግሞ በመጽሔቶቻችን ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ልብህን በጣም ነክቶት ያውቃል? ይህ ሁሉ ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ያደረገው ዝግጅት መሆኑን መዘንጋት የለብህም።

22. ይሖዋ ምንጊዜም ኃይሉን የሚጠቀመው ምን ለማድረግ ነው? እንዲህ የሚያደርገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

22 ይሖዋ በእርግጥም “በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።” (መዝሙር 18:30) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ምንም ዓይነት መከራ እንዳይደርስብን ይጋርደናል ብለን መጠበቅ እንደሌለብን እናውቃለን። ይሁን እንጂ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ምንጊዜም ኃይሉን በመጠቀም አገልጋዮቹን እንደሚጠብቅ የታወቀ ነው። ይህን የሚያደርገውም ለሕዝቡ ዘላቂ ጥቅም ሲል ነው። ወደ እሱ ከቀረብንና ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት እስከ መጨረሻው ጠብቀን ከዘለቅን ዘላለማዊ የሆነ ፍጹም ሕይወት ይሰጠናል። በመሆኑም በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ ‘ጊዜያዊና ቀላል’ እንደሆነ እንገነዘባለን።—2 ቆሮንቶስ 4:17