በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከአምላክ የተላከ ምሥራች!

 ትምህርት 9

ቤተሰብህ ደስተኛ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

ቤተሰብህ ደስተኛ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

1. በሕጋዊ መንገድ መጋባት ለቤተሰብ ደስታ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ምሥራቹ የተላከው ደስተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ሲሆን እሱም ቤተሰቦች ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ጋብቻን ያቋቋመው እሱ ነው። በሕጋዊ መንገድ መጋባት ልጆችን ማሳደግ የሚቻልበት አስተማማኝና ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ለቤተሰብ ደስታ ወሳኝ ነው። ክርስቲያኖች ጋብቻን ሕጋዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ በአካባቢያቸው ያለውን ሕግ ሊያከብሩ ይገባል።​—ሉቃስ 2:1, 4, 5ን አንብብ።

አምላክ ለጋብቻ ምን አመለካከት አለው? ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ይፈልጋል። ይሖዋ፣ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። (ዕብራውያን 13:4) ይሖዋ ፍቺን ይጠላል። (ሚልክያስ 2:16) ሆኖም አንደኛው የትዳር ጓደኛ ምንዝር ከፈጸመ ክርስቲያኖች መፋታትና በድጋሚ ማግባት እንደሚችሉ የአምላክ ቃል ይገልጻል።​—ማቴዎስ 19:3-6, 9ን አንብብ።

2. ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን እንዴት መያዝ ይኖርባቸዋል?

ይሖዋ ወንዶችንና ሴቶችን የፈጠረው በጋብቻ ውስጥ አንዳቸው የሌላውን ጉድለት እንዲያሟሉ አድርጎ ነው። (ዘፍጥረት 2:18) አንድ ባል የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብም ሆነ እነሱን ስለ አምላክ ለማስተማር ግንባር ቀደም መሆን አለበት። ለሚስቱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት ይኖርበታል። የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ መዋደድና መከባበር አለባቸው። ሁሉም ባልና ሚስት ፍጽምና ስለሚጎድላቸው ይቅር ባይ መሆናቸው ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።​—ኤፌሶን 4:31, 32ን፤ 5:22-25, 33ን እና 1 ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ።

3. በትዳራችሁ ደስተኛ ካልሆናችሁ መለያየት ይኖርባችኋል?

በትዳራችሁ ውስጥ ችግሮች ከተፈጠሩ አንዳችሁ ሌላውን በፍቅር ለመያዝ ጥረት አድርጉ። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) የአምላክ ቃል በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔው መለያየት እንደሆነ አይናገርም።​—1 ቆሮንቶስ 7:10-13ን አንብብ።

 4. ልጆች፣ አምላክ ምን እንድታገኙ ይፈልጋል?

ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል። የወጣትነት ዕድሜያችሁን በደስታ ለማሳለፍ እንድትችሉ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ ምክር ይሰጣችኋል። ወላጆቻችሁ ካካበቱት ጥበብና ካሳለፉት የሕይወት ተሞክሮ ጥቅም እንድታገኙ ይፈልጋል። (ቆላስይስ 3:20) ይሖዋ፣ የፈጣሪያችሁንና የልጁን ፈቃድ በማድረግ እንድትደሰቱም ይፈልጋል።​—መክብብ 11:9 እስከ 12:1ን፣ ማቴዎስ 19:13-15ን እና 21:15, 16ን አንብብ።

5. ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ደስተኞች እንዲሆኑ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ለልጆቻችሁ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ለማቅረብ በትጋት መሥራት ይኖርባችኋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሆኖም ልጆቻችሁ ደስተኞች እንዲሆኑ አምላክን እንዲወዱና እሱ የሚላቸውን ነገር እንዲሰሙ ማስተማርም ያስፈልጋችኋል። (ኤፌሶን 6:4) ለአምላክ ፍቅር እንዳላችሁ በተግባር የምታሳዩ ከሆነ ይህ ምሳሌነታችሁ የልጆቻችሁን ልብ በጥልቅ ሊነካ ይችላል። በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርታችሁ የምትሰጧቸው መመሪያዎች የልጆቻችሁን አስተሳሰብ በጥሩ መንገድ ሊቀርጹት ይችላሉ።​—ዘዳግም 6:4-7ን እና ምሳሌ 22:6ን አንብብ።

ልጆቻችሁ የእናንተን ምስጋና እና ማበረታቻ ማግኘታቸው ይጠቅማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እርማትና ተግሣጽም ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ደስታቸውን እንዲያጡ ከሚያደርግ አካሄድ እንዲርቁ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 22:15) ያም ቢሆን ልጆችን በኃይል ወይም በጭካኔ መቅጣት ተገቢ አይደለም።​—ቆላስይስ 3:21ን አንብብ።

የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆችንም ሆነ ልጆችን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ በርካታ መጻሕፍት አሳትመዋል። እነዚህ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የተዘጋጁ ናቸው።​—መዝሙር 19:7, 11ን አንብብ።