ጭፍን ጥላቻ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ጭፍን ጥላቻ ማለት አንድን ሰው የተለየ መልክ ስላለው ወይም የተለየ ቋንቋ ስለሚናገር ብቻ መጥላት ማለት ነው። ስለዚህ ጭፍን ጥላቻ ካለብህ አንድን ሰው ገና ሳታውቀው ስለ እሱ መጥፎ ስሜት ወይም መጥፎ አስተሳሰብ ያድርብሃል ማለት ነው።

አንድን ሰው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ሳታውቅ ወይም ከአንተ የተለየ ስለሆነ ብቻ መጥላት ተገቢ ይመስልሃል?— ጭፍን ጥላቻ ተገቢ ያልሆነና ደግነት የጎደለው ድርጊት ነው። አንድ ሰው ከእኛ የተለየ ስለሆነ ብቻ ልንጠላው ወይም ክፉ ልንሆንበት አይገባም።

ከአንተ የተለየ የቆዳ ቀለም ያለው ወይም አንተ የማታውቀውን ቋንቋ የሚናገር ሰው ታውቃለህ?— በአደጋ ወይም በበሽታ ምክንያት የተለየ መልክ ያላቸው ሰዎች ታውቅ ይሆናል። ከአንተ የተለየ መልክና ቋንቋ ላላቸው ሰዎች ደግና አፍቃሪ ነህ?—

ከእኛ የተለዩ ሰዎችን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

ታላቅ አስተማሪ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናዳምጥ ከሆነ ለሰው ሁሉ ደግ እንሆናለን። አንድ ሰው ከየትኛውም አገር ቢመጣ ወይም ምንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ቢኖረው፣ እኛ ለእሱ ሊኖረን በሚገባው አመለካከት ላይ ምንም ለውጥ ማምጣት የለበትም። ከየትኛውም አገር ቢመጣ ወይም ምንም ዓይነት የቆዳ ቀለም ቢኖረው ደግነት ልናሳየው ይገባል። በዚህ አስተሳሰብ የማይስማሙ ሰዎች ቢኖሩም ኢየሱስ ግን ያስተማረው ይህንኑ ነው። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ እንነጋገር።

በሌሎች ላይ ጭፍን ጥላቻ ያለው አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ ‘የዘላለም ሕይወት እንዳገኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብሎ ጠየቀው። ይህ ሰው ይህን ጥያቄ ያነሳው ‘ደግነት ማሳየት ያለብን የራሳችን ዘር ለሆኑ ሰዎች ወይም ለአገራችን ዜጎች ብቻ መሆን አለበት’ ብሎ እንዲመልስለት ፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ኢየሱስ አውቋል። ስለዚህ ኢየሱስ ጥያቄውን በቀጥታ  ከመመለስ ይልቅ ሰውየውን ‘የአምላክ ሕግ የሚነግረን ምን እንድናደርግ ነው?’ ብሎ ጠየቀው።

ሰውየውም ሕጉ ‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ ውደድ፤ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ’ ይላል ብሎ መለሰለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ‘በትክክል መልሰሃል። ዘወትር ይህን አድርግ፤ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ’ አለው።

ይሁን እንጂ ይህ ሰው ከእሱ ለየት ላሉ ሰዎች ደግ ወይም አፍቃሪ መሆን አልፈለገም። በመሆኑም ከዚህ ነፃ ሊያደርገው የሚችል ሰበብ መፈለግ ጀመረ። ስለዚህ ኢየሱስን “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። ይህ ሰው ምናልባት ኢየሱስ “ባልንጀሮችህ ጓደኞችህ ናቸው” ወይም “ባልንጀሮችህ ከአንተ ጋር የሚመሳሰሉ ሰዎች ናቸው” እንዲለው ፈልጎ ይሆናል። ኢየሱስ ጥያቄውን ለመመለስ ስለ አንድ አይሁዳዊና ስለ አንድ ሳምራዊ የሚገልጽ ታሪክ ነገረው። ታሪኩ የሚከተለው ነው።

አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ከተማ ተነስቶ ወደ ኢያሪኮ እየሄደ ነበር። ይህ ሰው አይሁዳዊ ነው። በመንገድ ላይ እየሄደ ሳለ ሌቦች ያዙት። ከዚያም መትተው መሬት ላይ ከጣሉት በኋላ ገንዘቡንና ልብሱን ወሰዱበት። ሌቦቹ በጣም ደብድበውት ሊሞት ሲቃረብ መንገዱ ዳር ጥለውት ሄዱ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲመጣ በጣም የተደበደበውን  ሰው አየው። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?— ካህኑ ተሻግሮ በሌላኛው የመንገዱ ዳር መጓዙን ቀጠለ። የተደበደበውን ሰው ለማየት እንኳ አልቆመም። ሰውየውን ለመርዳት ምንም ያደረገው ጥረት የለም።

ከዚያም በጣም ሃይማኖተኛ የሆነ አንድ ሌላ ሰው በዚያ መንገድ መጣ። ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ የሚያገለግል ሌዋዊ ነበር። እሱስ ቆም ብሎ አደጋ የደረሰበትን ሰው ይረዳው ይሆን?— በፍጹም። እሱም እንደ ካህኑ ጥሎት ሄደ።

በመጨረሻም አንድ ሳምራዊ ሰው መጣ። እዚህ ሥዕሉ ላይ ከመንገዱ መታጠፊያ ሲመጣ ይታይሃል?— ይህ ሳምራዊ ሰው በጣም ተደብድቦ መንገድ ዳር የወደቀውን አይሁዳዊ ተመለከተው። አብዛኞቹ ሳምራውያንና አይሁዳውያን ደግሞ ፈጽሞ አይዋደዱም። (ዮሐንስ 4:9) ታዲያ ይህ ሳምራዊ ሰውየውን  ምንም ሳይረዳው ትቶት ይሄድ ይሆን? ሳምራዊው በልቡ ‘እኔ ይህን አይሁዳዊ የምረዳበት ምን ምክንያት አለ? የተደበደብኩት እኔ ብሆን ኖሮ እሱ አይረዳኝም ነበር’ ይል ይሆን?

ሳምራዊው ጥሩ ባልንጀራ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ይህ ሳምራዊ እንዲህ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ በመንገድ ዳር የወደቀውን ሰው አየውና አዘነለት። እዚያው ትቶት ሄዶ እንዲሞት አልፈለገም። ስለዚህ ከአህያው ላይ ወርዶ ወደ ሰውየው መጣና ቁስሉን ያክምለት ጀመር። በቁስሉ ላይ ዘይትና ወይን አፈሰሰበት። ዘይቱና ወይኑ ቁስሉ እንዲድን ይረዳል። ከዚያም ቁስሉን በጨርቅ አሰረለት።

ሳምራዊው የተደበደበውን ሰው ቀስ ብሎ አነሳውና አህያው ላይ አወጣው። ከዚያም ቀስ ብለው በመንገዱ ላይ ቁልቁል ወረዱና ወደ አንድ ማደሪያ ወይም አነስተኛ ሆቴል ደረሱ። እዚያም ሳምራዊው ለሰውየው ማደሪያ ተከራየለትና አስፈላጊውን እንክብካቤ አደረገለት።

ኢየሱስ ይህን ታሪክ ተናግሮ ሲጨርስ ጥያቄውን ላቀረበለት ሰው ‘ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል ጥሩ ባልንጀራ የሆነው ሰው የትኛው ይመስልሃል?’ ብሎ ጠየቀው። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን መልስ ትሰጥ ነበር? ጥሩ ባልንጀራ የሆነው ሰው ካህኑ ነው፣ ሌዋዊው ነው ወይስ ሳምራዊው?—

ሰውየውም ‘ጥሩ ባልንጀራ የሆነው መሄዱን ትቶ ለተጎዳው ሰው እንክብካቤ ያደረገለት ሰው ነው’ ብሎ መልስ ሰጠ። ኢየሱስም ‘ልክ ነህ። አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ’ አለው።—ሉቃስ 10:25-37

 ይህ ጥሩ ታሪክ አይደለም? ይህ ታሪክ ባልንጀሮቻችን እነማን እንደሆኑ ግልጽ ያደርግልናል። ባልንጀሮቻችን የቅርብ ጓደኞቻችን ብቻ አይደሉም። ወይም ደግሞ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የቆዳ ቀለም ወይም ቋንቋ ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። ሰዎች ከየትኛውም አገር የመጡ ቢሆኑ፣ ምንም ዓይነት መልክ ቢኖራቸው ወይም ማንኛውንም ቋንቋ ቢናገሩ ለሁሉም ደግ መሆን እንዳለብን ኢየሱስ አስተምሮናል።

ይሖዋ ለማንም የማያዳላ አምላክ ነው። እሱ ለማንም ጭፍን ጥላቻ የለውም። ኢየሱስ ‘በሰማይ ያለው አባታችሁ ፀሐዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል። ዝናቡንም ለጥሩ ሰዎችና ጥሩ ላልሆኑ ሰዎች ያዘንባል’ በማለት ተናግሯል። ስለዚህ እኛም እንደ አምላክ ለሰው ሁሉ ደግ መሆን ይኖርብናል።—ማቴዎስ 5:44-48

ጥሩ ባልንጀራ ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ታዲያ አንተ አንድ ሰው ጉዳት ደርሶበት ብታይ ምን ታደርጋለህ?— ሰውየው የሌላ አገር ሰው ቢሆን ወይም የቆዳ ቀለሙ ከአንተ የተለየ ቢሆንስ? እንደዚያም ቢሆን ባልንጀራህ ስለሆነ ልትረዳው ይገባሃል። እሱን ለመርዳት አቅም እንደሌለህ ቢሰማህ አንድ ትልቅ ሰው እንዲረዳው ልትጠይቅ ትችላለህ። አለዚያም ፖሊስ ወይም አስተማሪ ጠርተህ እንዲረዱት ልታደርግ ትችላለህ። እንዲህ ካደረግክ እንደ ሳምራዊው ሰው ደግ ሆነሃል ማለት ነው።

ታላቁ አስተማሪ ደጎች እንድንሆን ይፈልጋል። ሰዎቹ ማንም ሆኑ ማን፣ ሌሎችን እንድንረዳ ይፈልጋል። ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚገልጸውን ታሪክ የተናገረው ለዚህ ነው።

ሰዎች ዘራቸውም ሆነ አገራቸው ምንም ሆነ ምን ለሁሉም ደግ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጽ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምሳሌ 19:22፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 እና 17:26ን አንብቡ።