በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 17

ደስተኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ

ደስተኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ

ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነው ለምንድን ነው?

ሁላችንም ደስተኛ መሆን እንፈልጋለን፣ አይደል?— ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ደስተኞች አይደሉም። ደስተኞች ያልሆኑት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ደስተኛ መሆን የሚቻልበትን መንገድ ስላላወቁ ነው። እነዚህ ሰዎች ብዙ ቁሳዊ ነገር ማግኘት ደስታ የሚሰጥ ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ የሚፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ካገኙ በኋላ ደስታቸው ብዙ አይቆይም።

ደስተኛ ለመሆን የሚያስችለው ዋናው ነገር የሚከተለው ነው። ታላቁ አስተማሪ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ስለዚህ ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?— አዎ፣ ደስተኛ መሆን የሚቻለው ለሌሎች በመስጠትና መልካም ነገር በማድረግ ነው። ይህን ታውቃለህ?—

እስቲ ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለመመርመር እንሞክር። ኢየሱስ ስጦታ የተቀበለ ሰው ደስተኛ አይሆንም ማለቱ ነው?—  እንደዚያ ማለቱ አይደለም። አንተ ስጦታ መቀበል ትወዳለህ፣ አይደል?— ሁሉም ሰው ስጦታ መቀበል ይወዳል። ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሲሰጡን ደስ ይለናል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስንሰጥ የበለጠ ደስታ እንደምናገኝ ተናግሯል። ታዲያ ከማንም ይበልጥ ለሰዎች ብዙ ስጦታ የሰጠው ማን ይመስልሃል?— አዎ፣ ይሖዋ አምላክ ነው።

“ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው” አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከሰማይ ዝናብንና የፀሐይን ብርሃን ስለሚሰጠን ተክሎች አድገው የምንበላው ምግብ እናገኛለን። (የሐዋርያት ሥራ 14:17፤ 17:25) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ‘ደስተኛ የሆነው አምላክ’ ብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) አምላክን ደስተኛ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ለሌሎች የሚሰጥ መሆኑ ነው። እኛም ለሌሎች የምንሰጥ ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን።

ታዲያ ለሌሎች ምን ልንሰጥ እንችላለን? አንተ ምን ትላለህ?— አንዳንድ ጊዜ ስጦታ ገንዘብ ያስወጣል። ከሱቅ የሚገዛ ስጦታ ከሆነ ገንዘብ መክፈል ይጠይቅብሃል። ስለዚህ ከሱቅ የሚገዛ ስጦታ መስጠት የምትፈልግ ከሆነ ስጦታውን ለመግዛት የሚያስችል በቂ ገንዘብ እስክታገኝ ድረስ ገንዘብ ማጠራቀም ሊኖርብህ ይችላል።

ያለህን ብስኩት በሙሉ ብቻህን በልተህ ከመጨረስ ይልቅ ምን ብታደርግ ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ?

ሆኖም ሁሉም ስጦታ ከሱቅ የሚገዛ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ኃይለኛ ሙቀት ባለበት ቀን ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት በጣም እንደሚያረካ የታወቀ ነው። ስለዚህ ለተጠማ ሰው እንዲህ ያለ ስጦታ ብትሰጥ፣ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ልታገኝ ትችላለህ።

ምናልባት አንድ ቀን አንተና እናትህ ዳቦ ልትጋግሩ ወይም ብስኩት ልትሠሩ ትችላላችሁ። ይህ በራሱ ሊያስደስትህ ይችላል። ይሁን እንጂ ሁሉንም  ብቻህን በልተህ ከመጨረስ ይልቅ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን ምን ልታደርግ ትችላለህ?— አዎ፣ ለአንዱ ጓደኛህ ልታካፍለው ትችላለህ። ወደፊት እንዲህ ማድረግ ትፈልጋለህ?—

ታላቁ አስተማሪና ሐዋርያቱ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ያውቃሉ። እነሱ ለሌሎች ሰዎች ምን እንደሰጡ ታውቃለህ?— እነሱ የሰጡት በዓለም ካሉት ነገሮች ሁሉ የበለጠውን ስጦታ ነው! ስለ አምላክ እውነቱን ያውቁ ስለነበር ይህን የምሥራች ለሌሎች በደስታ አካፍለዋል። ይህንንም ያደረጉት ምንም ገንዘብ ሳያስከፍሉ ነበር።

አንድ ቀን፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ደቀ መዝሙር የሆነው ጓደኛው ሉቃስ በመስጠት መደሰት የምትፈልግ አንዲት ሴት አገኙ። ይህችን ሴት ያገኟት በወንዝ ዳር ነበር። ጳውሎስና ሉቃስ እዚያ የሄዱት የጸሎት ቦታ መሆኑን ሰምተው ነበር። እንደተባለውም እዚያ ሲደርሱ እየጸለዩ ያሉ ሴቶችን አገኙ።

ጳውሎስ ለእነዚህ ሴቶች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን ምሥራች መናገር ጀመረ። ከሴቶቹ አንዷ ሊዲያ የምትባል ሲሆን ጳውሎስ የተናገረውን በትኩረት አዳመጠች። ከዚያ በኋላ ሊዲያ የሰማችውን ምሥራች በጣም እንደወደደችው የሚያሳይ ነገር ለማድረግ ፈለገች። ስለዚህ ጳውሎስንና ሉቃስን “ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንኩ አድርጋችሁ ከቆጠራችሁኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ በእንግድነት ዕረፉ” ብላ በጣም ለመነቻቸው። ከዚያም ወደ ቤቷ እንዲመጡ አደረገች።—የሐዋርያት ሥራ 16:13-15

ሊዲያ ጳውሎስንና ሉቃስን ምን እያለቻቸው ነው?

ሊዲያ እነዚህን የአምላክ አገልጋዮች ወደ ቤቷ በማምጣቷ ተደስታ ነበር። ጳውሎስና ሉቃስ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ እንዲሁም ሰዎች ለዘላለም መኖር ስለሚችሉበት መንገድ እንድትማር ስለረዷት ወደደቻቸው። ለጳውሎስና ለሉቃስ ምግብና ማረፊያ ቦታ መስጠት መቻሏ አስደስቷታል። ሊዲያ ከልቧ ፈልጋ ያደረገችው ነገር በመሆኑ መስጠቷ ደስታ አስገኝቶላታል። እኛም ይህን ማስታወስ አለብን። አንድ ሰው ስጦታ መስጠት እንዳለብን ሊነግረን ይችላል። ነገር ግን ሳንፈልግ የምንሰጥ ከሆነ መስጠታችን ደስታ ሊያስገኝልን አይችልም።

ሊዲያ ጳውሎስንና ሉቃስን ማስተናገዷ ያስደሰታት ለምንድን ነው?

ለምሳሌ ያህል፣ ከረሜላ አለህ እንበል፤ ከረሜላውን ራስህ ልትበላው ፈልገህ ይሆናል። ከረሜላውን ለሌላ ልጅ እንድታካፍል ብነግርህ ደስ ይልሃል?—  ይሁን እንጂ ከረሜላ ይዘህ ሳለ በጣም የምትወደው ጓደኛህ ቢመጣስ? ራስህ አስበህ ከረሜላውን ለጓደኛህ ብታካፍለው ደስ አይልህም?—

አንዳንድ ጊዜ አንድን ሰው በጣም የምንወደው ከሆነ ለራሳችን ምንም ሳናስቀር ያለንን ሁሉ ለእሱ መስጠት እንፈልጋለን። ለአምላክ ያለን ፍቅርም እያደገ ሲሄድ ለእሱ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል።

ይህች ድሃ ሴት የነበራትን ሁሉ መስጠቷ ያስደሰታት ለምንድን ነው?

ታላቁ አስተማሪ፣ አምላክን በጣም ከመውደዷ የተነሳ ያላትን ሁሉ ለመስጠት የፈለገችን አንዲት ድሃ ሴት ተመልክቶ ነበር። ይህችን ሴት ያያት በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ነበር። ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ይዛ ነበር፤ የነበራትም ይኸው ብቻ ነበር። ሆኖም ለቤተ መቅደሱ ስጦታ እንዲሆኑ ሁለቱንም ሳንቲሞች መዋጮ ሣጥኑ ውስጥ ከተተች። ይህን እንድታደርግ ያስገደዳት ሰው የለም። በዚያ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ምን እንዳደረገች እንኳን አላወቁም። ይህች ድሃ መበለት ይህን ያደረገችው ራሷ ማድረግ ስለፈለገችና ይሖዋን በጣም ስለምትወደው ነው። መስጠት መቻሏ ደስተኛ አድርጓታል።—ሉቃስ 21:1-4

እኛም መስጠት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። መስጠት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች መጥቀስ ትችላለህ?— ራሳችን ፈልገን የምንሰጥ ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን። ታላቁ አስተማሪ “ሰጪዎች ሁኑ” ያለን ለዚህ ነው። (ሉቃስ 6:38) የምንሰጥ ከሆነ ሌሎች ሰዎች ደስተኞች እንዲሆኑ እናደርጋለን። ከሁሉም ይበልጥ ደስተኛ የምንሆነው ግን እኛ ራሳችን ነን!

መስጠት ደስታ የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት ማቴዎስ 6:1-4፤ ሉቃስ 14:12-14 እና 2 ቆሮንቶስ 9:7ን እናንብብ።