ይህ ሰው ማን ነው? የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነውስ እንዴት ነው?

ተወዳዳሪ የሌለው የአምላክ አገልጋይ ማን ነው?— ልክ ነህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንደ ኢየሱስ መሆን የምንችል ይመስልሃል?— አዎ፣ ኢየሱስ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌያችን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ደግሞም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንድንሆን ጋብዞናል።

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ይጠይቃል። በመጀመሪያ ከኢየሱስ መማር አለብን። ሆኖም ሌላም ነገር ማድረግ ይኖርብናል። የሚነግረንን ነገር ከልብ ማመን አለብን። የሚነግረንን ነገር ካመንን ደግሞ በሥራ ላይ እናውለዋለን።

ብዙ ሰዎች በኢየሱስ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ታዲያ በኢየሱስ እናምናለን የሚሉ ሰዎች ሁሉ በእርግጥ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይመስሉሃል?— አብዛኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አይደሉም። እነዚህ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ጊዜ መድበው ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር አይማሩም። እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚባሉት የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ብቻ ናቸው።

እስቲ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በኖረበት ጊዜ የእሱ ደቀ መዛሙርት ስለሆኑት ሰዎች እንነጋገር። በመጀመሪያ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑት አንዱ ፊልጶስ ነው። ፊልጶስ በሥዕሉ ላይ ዛፍ ሥር ተቀምጦ የምታየውን ጓደኛውን ናትናኤልን (ወይም በርቶሎሜዎስን) ፈልጎ አገኘው። ኢየሱስ ናትናኤል ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” በማለት ተናገረ። ናትናኤል በመደነቅ “እንዴት ልታውቀኝ ቻልክ?” ብሎ ጠየቀው።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ እየጠራ ያለው እነማንን ነው?

 ኢየሱስም “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ” አለው። ናትናኤል የነበረበትን ቦታ ኢየሱስ በትክክል ማወቁ በጣም አስገርሞት “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው።—ዮሐንስ 1:49

የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ ይሁዳ (ታዴዎስ ተብሎም ይጠራል)፣ ስምዖን

ፊልጶስና ናትናኤል ደቀ መዛሙርት ከመሆናቸው ከአንድ ቀን በፊት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። እነሱም እንድርያስና ታላቅ ወንድሙ ጴጥሮስ እንዲሁም ዮሐንስ ናቸው፤ የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብም ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐንስ 1:35-51) ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነዚህ አራቱ ሰዎች ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራቸው ተመለሱ። ከዚያም አንድ ቀን ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳር ሲሄድ ጴጥሮስና እንድርያስ ዓሣ የሚያጠምዱበትን መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። ኢየሱስ ጠራቸውና “ኑ፣ ተከተሉኝ” አላቸው።

ያዕቆብ (የእልፍዮስ ልጅ)፣ ቶማስ፣ ማቴዎስ

ከዚያም ኢየሱስ ትንሽ ከሄደ በኋላ ያዕቆብንና ዮሐንስን አገኛቸው።  እነሱም መረባቸውን እየጠገኑ ከአባታቸው ጋር ጀልባ ላይ ነበሩ። ኢየሱስ እነሱም እንዲከተሉት ጠራቸው። ኢየሱስ አንተን ጠርቶህ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ወዲያውኑ ተከትለኸው ትሄድ ነበር?— ኢየሱስ እንዲከተሉት የጠራቸው ሰዎች እሱ ማን እንደሆነ አውቀው ነበር። አምላክ ልኮት እንደመጣ አውቀዋል። ስለዚህ ወዲያውኑ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው ተከተሉት።—ማቴዎስ 4:18-22

ናትናኤል፣ ፊልጶስና ዮሐንስ

እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች ከሆኑ በኋላ ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ ያደርጉ ነበር ማለት ነው?— አይደለም። እነዚህ ሰዎች ከእነሱ መካከል ከሁሉ የሚበልጠው ማን እንደሆነ ተከራክረው እንደነበረ ትዝ ይልህ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስን ያዳምጡት ስለነበር የጠባይና የአመለካከት ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበሩ። እኛም ለመለወጥ ፈቃደኞች ከሆን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆን እንችላለን።

ያዕቆብ (የዮሐንስ ወንድም)፣ እንድርያስና ጴጥሮስ

ኢየሱስ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ ጋብዟል። በአንድ ወቅት፣ አንድ ሀብታም ወጣት የሕዝብ አለቃ ወደ ኢየሱስ መጣና የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንደሚችል ጠየቀው። ሀብታሙ አለቃ የአምላክን ትእዛዛት ከልጅነቱ ጀምሮ እንደሚታዘዝ ሲናገር ኢየሱስ ‘መጥተህ ተከታዬ ሁን’ ብሎ ጋበዘው። ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ሰውየው የኢየሱስ ተከታይ መሆንን ሀብታም ከመሆን አስበልጦ መመልከት እንዳለበት ሲነገረው አልተደሰተም። ይህ ሰው ገንዘቡን ከአምላክ አስበልጦ ይወድ ስለነበር የኢየሱስ ተከታይ ሳይሆን ቀረ።—ሉቃስ 18:18-25

ኢየሱስ ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ያህል ሲሰብክ ከቆየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል 12 ሐዋርያት መረጠ። ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ልዩ ሥራ እንዲሠሩ የላካቸው ሰዎች ነበሩ። የእነዚህን ሐዋርያት ስም ታውቃለህ?— እስቲ ስማቸውን ለማወቅ እንሞክር። ሥዕሎቹን እያየህ ስማቸውን ለመጥራት ሞክር። ከዚያም ስማቸውን በቃልህ አጥንተህ ለመጥራት ሞክር።

ኢየሱስ ለመስበክ በሚሄድበት ጊዜ ይረዱት የነበሩት እነዚህ ሴቶች እነማን ናቸው?

የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ክፉ ሆነ። ይህ ሰው የአስቆሮቱ ይሁዳ ይባላል። ከጊዜ በኋላ በአስቆሮቱ ይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው ተመርጦ ሐዋርያ ሆነ። ስሙን ታውቀዋለህ?— ማትያስ ይባላል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያት ሆኑ፤ ቢሆንም እነሱ ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አልነበሩም።—የሐዋርያት ሥራ 1:23-26፤ 14:14

 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንደተማርነው ኢየሱስ ትንንሽ ልጆችን ይወድ ነበር። ኢየሱስ ልጆችን ይወድ የነበረው ለምንድን ነው?— እነሱም ደቀ መዛሙርቱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያውቅ ስለነበር ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ልጆች ትልልቅ ሰዎችም እንኳን እንዲያዳምጡና ስለ ታላቁ አስተማሪ ብዙ ለመማር እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ።

ብዙ ሴቶችም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። አንዳንዶቹ ሴቶች ኢየሱስ ለመስበክ ወደ ሌሎች ከተሞች ሲሄድ አብረውት ይሄዱ ነበር። ከኢየሱስ ጋር አብረው ይሄዱ ከነበሩት ሴቶች መካከል መግደላዊት ማርያም፣ ዮሐናና ሶስና ይገኙበታል። ኢየሱስን ምግብ በማዘጋጀትና ልብሱን በማጠብ ጭምር ረድተውት ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 8:1-3

 የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ትፈልጋለህ?— የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነኝ ስላልን ብቻ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን እንደማንችል አስታውስ። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነኝ የምንል ከሆነ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስንሄድ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ቦታ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆናችንን በተግባር ልናሳይባቸው ከሚገቡ ቦታዎች መካከል አንዳንዶቹን ልትጠቅስልኝ ትችላለህ?—

አዎ፣ በቤት ውስጥ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆናችንን በተግባር ማሳየት አለብን። የእሱ ደቀ መዝሙር መሆናችንን ልናሳይበት የሚገባ ሌላው ቦታ ደግሞ ትምህርት ቤት ነው። እኔም ሆንኩ አንተ የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር መሆን ከፈለግን በማንኛውም ቦታ ቀኑን ሙሉ የኢየሱስ ዓይነት ተግባር መፈጸም እንደሚኖርብን መርሳት የለብንም።

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆናችንን በተግባር ልናሳይበት የሚገባ አንዱ ቦታ የት ነው?

አሁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚናገረውን ነገር ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሉቃስ 6:13-16፤ ዮሐንስ 8:31, 32 እና 1 ጴጥሮስ 2:21 ላይ አብራችሁ አንብቡ።