በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 46

ዓለም በውኃ ጠፋ—ዳግመኛ በውኃ ይጠፋ ይሆን?

ዓለም በውኃ ጠፋ—ዳግመኛ በውኃ ይጠፋ ይሆን?

ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲነገር ሰምተህ ታውቃለህ?— በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለ ዓለም ፍጻሜ ያወራሉ። አንዳንድ ሰዎች በኑክሌር ቦምብ አማካኝነት በሚደረግ ጦርነት ዓለም ትጠፋለች ብለው ያስባሉ። አምላክ፣ ውብ የሆነችውን ምድራችንን ሰዎች እንዲያጠፏት የሚፈቅድ ይመስልሃል?—

ቀደም ብለን እንደተማርነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓለም በማለፍ ላይ ነው’ ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) የዓለም ፍጻሜ ማለት የምድር ፍጻሜ ማለት ይመስልሃል?— አይደለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምድርን የሠራት ‘መኖሪያ እንድትሆን’ ማለትም ሰዎች እየተደሰቱ የሚኖሩባት  ቦታ እንድትሆን ብሎ እንደሆነ ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ለዘላለም ጸንታ እንደምትኖር ይናገራል።—መዝሙር 104:5፤ መክብብ 1:4

ታዲያ የዓለም ፍጻሜ የምድር ፍጻሜ ማለት ካልሆነ ምን ማለት ነው?— በኖኅ ዘመን የተፈጸመውን ነገር በደንብ ብንመረምር የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፍቷል” በማለት ይናገራል።—2 ጴጥሮስ 3:6

በኖኅ ዘመን በተከሰተው በዚያ የውኃ መጥለቅለቅ ወይም ታላቅ ጎርፍ ወቅት ከደረሰው የዓለም ፍጻሜ የተረፈ ሰው ነበር?— አምላክ “የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ” እንዳመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ጴጥሮስ 2:5

ታዲያ የጠፋው ዓለም የትኛው ነው? ምድር ናት ወይስ ክፉ ሰዎች?— መጽሐፍ ቅዱስ የጠፋው ‘ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች የተሞላው ዓለም’ እንደሆነ ይናገራል። በተጨማሪም ኖኅ “ሰባኪ” ተብሎ እንደተጠራ ልብ በል። ኖኅ ይሰብክ የነበረው ስለ ምን ይመስልሃል?— ኖኅ “በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም” ስለሚደርስበት ጥፋት ሰዎቹን እያስጠነቀቀ ነበር።

በኖኅ ዘመን የጠፋው ዓለም የትኛው ነው?

ኢየሱስ ስለ ታላቁ ጎርፍ በተናገረ ጊዜ ፍጻሜው ከመምጣቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ሰዎቹ ምን ያደርጉ እንደነበረ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። እንዲህ ብሏል:- “ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም።” ከዚያም ኢየሱስ የአሁኑ ዓለም ፍጻሜ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ልክ በኖኅ ዘመን ከኖሩት ሰዎች ጋር የሚመሳሰል ነገር እንደሚያደርጉ ተናገረ።—ማቴዎስ 24:37-39

ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ሰዎች ሲያደርጉት ከነበረው ነገር የምናገኘው ትምህርት እንዳለ ያመለክታሉ።  በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ላይ እንዳነበብከው በዚያ ጊዜ የነበሩት ሰዎች ምን ያደርጉ እንደነበረ ታስታውሳለህ?— አንዳንዶቹ የዓመፅ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ጉልበተኞች ነበሩ። በተጨማሪም ኢየሱስ እንደተናገረው አብዛኞቹ ሰዎች ኖኅ፣ አምላክ የላከውን መልእክት በሚሰብክበት ጊዜ አያዳምጡም ነበር።

ስለዚህ ይሖዋ ለኖኅ በነገረው መሠረት ክፉ ሰዎችን በጎርፍ የሚያጠፋበት ጊዜ ደረሰ። ውኃው መላዋን ምድር፣ ተራሮችንም እንኳን ሳይቀር የሚሸፍን ነበር። ይሖዋ ለኖኅ ትልቅ መርከብ እንዲሠራ ነግሮት ነበር። ገጽ 238 ላይ እንደምታየው መርከቡ ግዙፍና ረጅም ሣጥን ይመስል ነበር።

አምላክ፣ ኖኅ እሱንና ቤተሰቡን እንዲሁም ብዙ እንስሳትን የሚይዝና ከጥፋት ውኃው እንዲተርፉ የሚያስችል ትልቅ መርከብ እንዲሠራ ነግሮት ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ጠንክረው መሥራት ጀመሩ። ትልልቅ ዛፎችን እየቆረጡ እንጨቶቹን በማገጣጠም መርከቡን መሥራት ቀጠሉ። የሚሠሩት መርከብ በጣም ትልቅ ስለነበር ብዙ ዓመታት ፈጀባቸው።

ኖኅ መርከቡን እየሠራ በነበረባቸው በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ምን ተጨማሪ ሥራ ይሠራ እንደነበረ ታስታውሳለህ?— ሰዎቹን ስለሚመጣው ጎርፍ እያስጠነቀቀ ይሰብክ ነበር። ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ እርምጃ የወሰደ ሰው ነበር? ከኖኅ ቤተሰብ በስተቀር አንድም ሰው አልነበረም። ሌሎቹ ሰዎች በሙሉ ሌሎች ነገሮችን በመሥራት ተጠምደው ነበር። ኢየሱስ ምን ያደርጉ እንደነበር የተናገረውን ታስታውሳለህ?— ጊዜያቸው ሁሉ የተያዘው በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም በማግባትና በመጋባት ነበር። ክፉ ሰዎች ነን ብለው አያስቡም ነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ ጊዜ ሰጥተው ኖኅን ለማዳመጥ ፈቃደኞች አልነበሩም። በዚህ የተነሳ ምን እንደደረሰባቸው እስቲ እንመልከት።

ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ውስጥ ከገቡ በኋላ ይሖዋ በሩን ዘጋው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ከመርከቡ ውጪ ያሉት ሰዎች ጎርፍ እንደሚመጣ አላመኑም ነበር። ይሁን እንጂ በድንገት ውኃ ከሰማይ መውረድ ጀመረ! ይህ የተለመደው ዓይነት ዝናብ አልነበረም። ዶፍ ዝናብ ነበር! ወዲያውኑ ውኃው ትልቅ ወንዝ ሆኖ ኃይለኛ ድምፅ እያሰማ ይጎርፍ ጀመር። ውኃው ትልልቅ ዛፎችን ከመገንደሱም በላይ ትልልቅ ድንጋዮችን እንደ ትንንሽ ጠጠሮች እያንከባለለ  ይወስድ ጀመር። ከመርከቡ ውጪ የነበሩት ሰዎችስ ምን ሆኑ?— ኢየሱስ ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ ወሰዳቸው’ በማለት ተናግሯል። ከመርከቡ ውጪ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ሞቱ። ለምን?— ምክንያቱም ኢየሱስ እንደተናገረው “ምንም አላስተዋሉም” ነበር። የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አልሰሙም!—ማቴዎስ 24:39፤ ዘፍጥረት 6:5-7

ስለ መዝናናት ብቻ ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው?

በእነዚያ ሰዎች ላይ የደረሰው ነገር በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ሰዎች ትምህርት እንደሚሆነን ኢየሱስ መናገሩን አስታውስ። ታዲያ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?— አብዛኞቹ ሰዎች የጠፉት ክፉ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ስለ አምላክና እሱ ሊያደርገው ስላሰበው ነገር ለመማር ጊዜ እስኪያጡ ድረስ በሌላ ነገር ተጠምደው ስለነበር ነው። እኛም እንደነሱ እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልገናል፣ አይደል?—

አምላክ ዓለምን እንደገና በውኃ ያጠፋል ብለህ ታስባለህ?— በጭራሽ፤ አምላክ እንዲህ እንደማያደርግ ቃል ገብቷል። “ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም . . . ምልክት ይሆናል” ብሏል። ይሖዋ ቀስተ ደመናው “ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም” ብሎ ለገባው ቃል ምልክት እንደሚሆን ተናግሯል።—ዘፍጥረት 9:11-17

ስለዚህ አምላክ ዓለምን ዳግመኛ በውኃ እንደማያጠፋ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሆኖም ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ይናገራል። አምላክ በዚህ ዓለም ላይ ጥፋት በሚያመጣበት ጊዜ የሚያድነው እነማንን ነው?— ሐሳባቸው በሌሎች ነገሮች ተይዞ ስለ አምላክ ለመማር ምንም ፍላጎት የሌላቸውን ሰዎች ነው? ወይም ደግሞ ሁልጊዜ  መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ የለኝም የሚሉ ሰዎችን ነው? ምን ይመስልሃል?—

አምላክ ከሚያድናቸው ሰዎች መካከል መሆን እንፈልጋለን፤ አይደለም እንዴ?— ቤተሰባችን እንደ ኖኅ ቤተሰብ ቢሆንና አምላክ ሁላችንንም ቢያድነን በጣም አስደሳች አይሆንም?— ከዓለም ፍጻሜ በሕይወት መትረፍ እንድንችል አምላክ ይህን ዓለም አጥፍቶ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳንኤል ምዕራፍ 2 ቁጥር 44 ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ይህ ጥቅስ እኛ ስላለንበት ዘመን ሲናገር እንደሚከተለው ይላል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

ይህ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲናገር የአምላክ መንግሥት ሁሉንም የምድር መንግሥታት እንደሚያጠፋ መግለጹ ነው። መንግሥታት የሚጠፉት ለምንድን ነው?— አምላክ ለሾመው ንጉሥ ስለማይታዘዙ ነው። አምላክ የሾመው ንጉሥ ማን ነው?— አዎ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!

አምላክ የመረጠው ንጉሥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም በአርማጌዶን ያጠፋዋል

ይሖዋ አምላክ፣ ምድርን መግዛት ያለበት ምን ዓይነት መንግሥት እንደሆነ የመወሰን መብት ስላለው ልጁን ኢየሱስን ንጉሥ እንዲሆን መርጦታል። በቅርቡ የዚህ ዓለም መንግሥታት በሙሉ የሚጠፉት አምላክ በመረጠው ገዥ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራእይ ምዕራፍ 19 ከቁጥር 11 እስከ 16 ላይ ኢየሱስ ይህን የማጥፋት እርምጃ እንደሚወስድ ይገልጻል፤ ሥዕሉም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። አምላክ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ የሚያጠፋበት ጦርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን ተብሎ ይጠራል።

አምላክ የእሱ መንግሥት የሰዎችን መንግሥታት እንደሚያጠፋ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የዓለምን መንግሥታት እንድናጠፋ እኛን ያዝዘን  ይሆን?— በፍጹም፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አርማጌዶን ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 16:14, 16) አዎ፣ አርማጌዶን የአምላክ ጦርነት ሲሆን በሰማይ ያለውን ሠራዊት አስከትሎ ውጊያውን እንዲያካሂድ ኢየሱስ ክርስቶስን መሪ አድርጎ ይጠቀምበታል። የአርማጌዶን ጦርነት የሚካሄድበት ጊዜ ቀርቧል? ይህን እንዴት ማወቅ እንደምንችል ቀጥሎ እንመለከታለን።

አምላክ ክፉዎችን በሙሉ አጥፍቶ እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎች ስለሚያድንበት ጊዜ የሚገልጹትን የሚከተሉትን ጥቅሶች አብረን እናንብብ:- ምሳሌ 2:21, 22፤ ኢሳይያስ 26:20, 21፤ ኤርምያስ 25:31-33፤ ማቴዎስ 24:21, 22