በአንድ ወቅት ታላቁ አስተማሪ አንድ አስገራሚ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ጥያቄው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 12:48) ይህን ጥያቄ መመለስ ትችላለህ?— የኢየሱስ እናት ስም ማርያም እንደሆነ ሳታውቅ አትቀርም። የወንድሞቹንስ ስም ታውቃለህ?— እህቶችስ ነበሩት?—

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ወንድሞች “ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ” እንደሚባሉ ይናገራል። ኢየሱስ እህቶችም የነበሩት ሲሆን በሚሰብክበት ጊዜ በሕይወት ነበሩ። ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ ሁሉም ታናናሾቹ ነበሩ።—ማቴዎስ 13:55, 56፤ ሉቃስ 1:34, 35

የኢየሱስ ወንድሞች ደቀ መዛሙርቱም ጭምር ነበሩ?— መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ “አላመኑበትም ነበር” ይላል። (ዮሐንስ 7:5) በኋላ ግን ያዕቆብና ይሁዳ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ ሲሆን እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መጽሐፎችን ጽፈዋል። እነሱ የጻፏቸው መጽሐፎች የትኞቹ እንደሆኑ ታውቃለህ?— አዎ፣ የያዕቆብና የይሁዳ ደብዳቤዎች ናቸው።

ምንም እንኳን የኢየሱስ እህቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስማቸው ባይጠቀስም ቢያንስ ሁለት እህቶች እንደነበሩት እናውቃለን። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ከዚህም ሊበልጥ ይችላል። እህቶቹስ ተከታዮቹ ሆነዋል?— መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስለማይነግረን ማወቅ አንችልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” የሚለውን ጥያቄ ያቀረበው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— እስቲ እንዲህ ያለበትን ምክንያት ለማወቅ እንሞክር።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እያስተማረ ሳለ አንድ ሰው በመካከል ጣልቃ ገብቶ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው ውጭ ቆመዋል” አለው።  ስለዚህ ኢየሱስ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” የሚለውን አስገራሚ ጥያቄ በማቅረብ አጋጣሚውን አንድ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ለማስተማር ተጠቀመበት። እጁን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘረጋና “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!” በማለት መልስ ሰጠ።

ከዚያም ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ሲያብራራ “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 12:47-50) ይህ ደግሞ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ምን ያህል እንደሚወዳቸው ያሳያል። ኢየሱስ ይህን መናገሩ ደቀ መዛሙርቱ ለእሱ እንደ እውነተኛ ወንድሞቹ፣ እህቶቹና እናቶቹ እንደሆኑ ያስተምረናል።

ኢየሱስ ወንድሞቹና እህቶቹ እነማን መሆናቸውን ተናግሯል?

በዚያን ጊዜ የገዛ ራሱ ወንድሞች የነበሩት ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ አላመኑም ነበር። መልአኩ ገብርኤል ለእናታቸው ለማርያም የነገራትን ነገር አላመኑም ነበር ማለት ነው። (ሉቃስ 1:30-33) ስለዚህ ለኢየሱስ ክፉ ሆነውበት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ጠባይ የሚያሳይ ሰው እውነተኛ ወንድም ወይም እህት አይደለም። ለወንድሙ ወይም ለእህቱ ክፉ የሆነ ሌላ ሰው ታውቃለህ?—

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዔሳውና ያዕቆብ ሲናገር ዔሳው በጣም ተቆጥቶ “ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ እንደነበረ ይነግረናል። እናታቸው ርብቃ በጣም ከመፍራቷ የተነሳ ዔሳው እንዳይገድለው ያዕቆብን ወደ ሩቅ አገር ላከችው። (ዘፍጥረት 27:41-46) ይሁን እንጂ ከብዙ ዓመታት በኋላ ዔሳው አስተሳሰቡ ስለተለወጠ ያዕቆብን አቅፎ ስሞታል።—ዘፍጥረት 33:4

ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ወለደ። ይሁን እንጂ ትልልቆቹ የያዕቆብ ልጆች ታናሽ ወንድማቸው የሆነውን ዮሴፍን አይወዱትም ነበር። አባታቸው ከእነሱ አብልጦ ይወደው ስለነበረ ይቀኑበት ነበር። ስለዚህ ወደ ግብፅ ለሚሄዱ የባሪያ ነጋዴዎች ሸጡት። ከዚያም ለአባታቸው ዮሴፍን አውሬ ገደለው ብለው ነገሩት። (ዘፍጥረት 37:23-36) ይህ በጣም መጥፎ ድርጊት አይደለም?—

ከጊዜ በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች ባደረጉት ነገር ተጸጸቱ። ስለዚህ ዮሴፍ ይቅር አላቸው። ዮሴፍ ከኢየሱስ ጋር የሚመሳሰል ነገር እንዳደረገ አስተዋልክ?— ኢየሱስ የገዛ ራሱ ሐዋርያት እሱ ችግር ባጋጠመው ጊዜ ትተውት የሸሹ ሲሆን እንዲያውም ጴጥሮስ አላውቀውም ብሎ ክዶታል። ሆኖም ኢየሱስ እንደ ዮሴፍ ሁሉንም ይቅር ብሏቸዋል።

ቃየን በአቤል ላይ ከፈጸመው ድርጊት ምን መማር ይኖርብናል?

 ወንድማማቾች የነበሩትን የቃየንንና የአቤልን ታሪክም መመልከት እንችላለን። ከእነሱም የምናገኘው ትምህርት አለ። አምላክ፣ ቃየን ወንድሙን እንደማይወደው አስተዋለ። ስለዚህ አምላክ ቃየን አመለካከቱን መለወጥ እንዳለበት ነገረው። ቃየን በእርግጥ አምላክን ቢወደው ኖሮ የነገረውን ነገር ይሰማ ነበር። ይሁን እንጂ ቃየን ለአምላክ ፍቅር አልነበረውም። አንድ ቀን ቃየን አቤልን “ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው። አቤልም አብሮት ሄደ። ሜዳው ላይ ብቻቸውን ሳሉ ቃየን ወንድሙን በኃይል መታውና ገደለው።—ዘፍጥረት 4:2-8

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ልንማረው የሚገባ ልዩ የሆነ ትምህርት እንዳለ ይነግረናል። ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— “ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነው፤ ከክፉው ወገን እንደሆነው . . . እንደ ቃየን መሆን የለብንም።” ስለዚህ ወንድማማቾችና እህትማማቾች እርስ በርስ ሊዋደዱ ይገባል። እንደ ቃየን መሆን የለባቸውም።—1 ዮሐንስ 3:11, 12

እንደ ቃየን መሆን መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?— ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ቃየን “ከክፉው” ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ “ወገን” እንደሆነ ይናገራል። ቃየን ከዲያብሎስ ጋር የሚመሳሰል ድርጊት በመፈጸሙ ዲያብሎስ አባቱ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

ወንድሞችህንና እህቶችህን መውደድ ያለብህ ለምን እንደሆነ አሁን ገባህ?— የማትወዳቸው ከሆነ እንደ ማን ልጆች እየሆንክ ነው?— እንደ ዲያብሎስ ልጆች እየሆንክ ነው። እንዲህ መሆን ደግሞ አትፈልግም፣ አይደል?— ስለዚህ የአምላክ ልጅ መሆን እንደምትፈልግ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?— ለወንድሞችህና ለእህቶችህ እውነተኛ ፍቅር በማሳየት ነው።

ይሁን እንጂ ፍቅር ምንድን ነው?— ፍቅር ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ነገር እንድናደርግላቸው የሚገፋፋ ከውስጥ የሚመነጭ ኃይለኛ ስሜት ነው። ለሌሎች ፍቅር እንዳለን የምናሳየው ለእነሱ ጥሩ ስሜት ሲኖረንና ጥሩ ነገር  ስናደርግላቸው ነው። ለመሆኑ ልንወዳቸው የሚገባን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እነማን ናቸው?— ኢየሱስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የትልቁ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን እንደተናገረ አስታውስ።

ወንድምህን እንደምትወድ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መውደዳችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?— መጽሐፍ ቅዱስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:20) ስለዚህ ከዚህ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ መውደድ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ሁሉንም መውደድ አለብን። ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) ታዲያ ሁሉንም ወንድሞችና እህቶች ትወዳለህ?— የማትወዳቸው ከሆነ አምላክን እወደዋለሁ ማለት እንደማትችል አስታውስ።

ታዲያ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በእርግጥ እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?— የምንወዳቸው ከሆነ አኩርፈን አንርቃቸውም። ለሁሉም የወዳጅነት መንፈስ እናሳያለን። ሁልጊዜ ጥሩ ነገር እናደርግላቸዋለን፤ እንዲሁም ያለንን ለእነሱ ለማካፈል ፈቃደኞች እንሆናለን። በተጨማሪም ሁላችንም እንደ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ስለሆንን ወንድሞቻችን ችግር ሲደርስባቸው እንረዳቸዋለን።

ሁሉንም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከልብ የምንወዳቸው ከሆነ ይህ ምን ያሳያል?— የታላቁ አስተማሪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ያሳያል። ደግሞስ መሆን የምንፈልገው እንዲህ አይደለም?—

ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየት እንዳለብን ገላትያ 6:10 እና 1 ዮሐንስ 4:8, 21 ላይም ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ እነዚህን ጥቅሶች አንብቧቸው።