በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 10

ኢየሱስ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው

ኢየሱስ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው

ከአምላክ መላእክት አንዱ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነበትን ምክንያት ታስታውሳለህ?— በአምላክ ላይ እንዲያምፅ ያደረገው ለመመለክ የነበረው የራስ ወዳድነት ፍላጎት ነው። የሰይጣን ተከታዮች የሆኑ ሌሎች መላእክት አሉ?— አዎ፣ አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መላእክት ‘የሰይጣን መላእክት’ ወይም አጋንንት ብሎ ይጠራቸዋል።—ራእይ 12:9

እነዚህ መጥፎ መላእክት ወይም አጋንንት በአምላክ ያምናሉ?— ‘አጋንንት አምላክ እንዳለ ያምናሉ’ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ያዕቆብ 2:19) በአሁኑ ጊዜ ግን አጋንንት በጣም ፈርተዋል። ምክንያቱም መጥፎ ነገር በመሥራታቸው አምላክ ሊቀጣቸው እንደሆነ ያውቃሉ። የሠሩት ጥፋት ምንድን ነው?—

እነዚህ መላእክት በሰማይ መኖር ሲገባቸው ሰው ሆነው በምድር ላይ ለመኖር ሲሉ መኖሪያቸውን ትተው እንደመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህን ያደረጉት በምድር ላይ ከነበሩ ቆንጆ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ነበር። (ዘፍጥረት 6:1, 2፤ ይሁዳ 6) የጾታ ግንኙነት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

 የጾታ ግንኙነት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልዩ በሆነ መንገድ በሚቀራረቡት ጊዜ የሚፈጸም ድርጊት ነው። ከዚያ በኋላ በእናቲቱ ሆድ ውስጥ ሕፃን ልጅ ሊፈጠር ይችላል። መላእክት ግን የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አልተፈቀደላቸውም። አምላክ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የሚፈቅደው ለተጋቡ ወንድና ሴት ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ልጅ ከተወለደ ባልና ሚስቱ ሊንከባከቡት ይችላሉ።

እነዚህ መላእክት ያደረጉት መጥፎ ነገር ምንድን ነው?

መላእክት የሰው አካል ለብሰው በምድር ካሉ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት በፈጸሙ ጊዜ የተወለዱላቸው ልጆች ሲያድጉ ግዙፎች ሆኑ። እነሱም በጣም ጨካኞችና ሰዎችን የሚጎዱ ነበሩ። ስለዚህ አምላክ እነዚያን ግዙፍ ሰዎችና ሌሎቹን ክፉ ሰዎች በሙሉ ለማጥፋት ኃይለኛ ጎርፍ አመጣ። ይሁን እንጂ አምላክ ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርጉ ጥቂት ሰዎችን ለማዳን ኖኅ መርከብ ወይም ትልቅ ጀልባ እንዲሠራ አደረገ። ታላቁ አስተማሪ ጎርፉ ወይም የጥፋት ውኃው በመጣ ጊዜ የሆነውን ነገር ማስታወስ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግሯል።—ዘፍጥረት 6:3, 4, 13, 14፤ ሉቃስ 17:26, 27

የጥፋት ውኃው በመጣ ጊዜ እነዚያ ክፉ መላእክት ምን እንደደረሰባቸው ታውቃለህ?— ለራሳቸው የሠሩትን የሰው አካል ትተው ወደ ሰማይ ተመለሱ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የአምላክ መላእክት መሆን ስለማይችሉ የሰይጣን መላእክት ወይም አጋንንት ሆኑ። ግዙፎቹ የአጋንንት ልጆችስ  ምን ሆኑ?— በጥፋት ውኃው ሞቱ። አምላክን ያልታዘዙ ሌሎች ሰዎችም ጠፉ።

በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ከምንጊዜውም የበለጠ ችግር የኖረው ለምንድን ነው?

የጥፋት ውኃው ከመጣ በኋላ አጋንንት እንደገና የሰው አካል እንዲለብሱ አምላክ አልፈቀደላቸውም። ይሁን እንጂ አጋንንት እኛ ልናያቸው ባንችልም አሁንም ቢሆን ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ችግር እያደረሱ ነው። ይህ የሆነው ከሰማይ ወደ ምድር ስለተወረወሩ ነው።

አጋንንትን ልናያቸው የማንችለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— መንፈስ ስለሆኑ ነው። ሆኖም አጋንንት እንዳሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን ‘በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ እያሳሳተ እንዳለ’ ይናገራል፤ አጋንንቱም እየረዱት ነው።—ራእይ 12:9, 12

ዲያብሎስና አጋንንቱ እኛንም ሊያሳስቱን ወይም ሊያሞኙን ይችላሉ?— አዎ፣ ካልተጠነቀቅን ሊያሳስቱን ይችላሉ። ይሁን እንጂ መፍራት አያስፈልገንም። ታላቁ አስተማሪ፣ ‘ዲያብሎስ በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም’ ብሏል። ወደ አምላክ ከቀረብን ከዲያብሎስና ከአጋንንቱ ይጠብቀናል።—ዮሐንስ 14:30

አጋንንት ምን መጥፎ ነገር እንድንሠራ ለማድረግ እንደሚጥሩ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ለማሰብ ሞክር። አጋንንት ወደ ምድር መጥተው እያለ ምን መጥፎ ነገር ሠርተው ነበር?— ከጥፋት ውኃው በፊት ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ሲሆን ይህ ደግሞ መላእክት ሊያደርጉት የሚገባ ነገር አልነበረም። በዛሬው ጊዜም አምላክ ስለ ጾታ ግንኙነት ያወጣውን ሕግ ሰዎች ሳይታዘዙ ሲቀሩ አጋንንት ደስ ይላቸዋል። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፣ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያለባቸው እነማን ብቻ ናቸው?— ልክ ነህ፤ የተጋቡ ወንድና ሴት ብቻ ናቸው።

በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሳይጋቡ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ፤ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። የወንዱንም ሆነ የሴቷን የጾታ ብልቶች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ እነዚህን የአካል ክፍሎች የፈጠረው ለአንድ ልዩ ዓላማ ሲሆን ይህንንም ልዩ ዓላማ መፈጸም ያለባቸው የተጋቡ ሰዎች ብቻ ናቸው። ሰዎች ይሖዋ የከለከለውን  ነገር ሲያደርጉ አጋንንት ይደሰታሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅ አንዳቸው በሌላው የጾታ ብልት ሲጫወቱ አጋንንት ደስ ይላቸዋል። እኛ ግን አጋንንትን ማስደሰት አንፈልግም፤ እንፈልጋለን እንዴ?—

አጋንንት የሚወዱት ይሖዋ ግን የሚጠላው ሌላም ነገር አለ። ይህ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ዓመፅ ነው። (መዝሙር 11:5) ዓመፅ፣ ሰዎች ጨካኞች በመሆን የሚፈጽሙት ሌሎችን የሚጎዳ ድርጊት ነው። ግዙፎቹ የአጋንንት ልጆችም ያደረጉት ይህንኑ እንደነበር አስታውስ።

አጋንንት ሰዎችን ማስፈራራትም ይወዳሉ። አንዳንድ ጊዜ የሞቱ ሰዎችን መስለው ይቀርባሉ። እንዲያውም የሞቱ ሰዎችን ድምፅ አስመስለው ሊናገሩም ይችላሉ። በዚህ መንገድ፣ አጋንንት የሞቱ ሰዎች ሕያው እንደሆኑና በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር መነጋገር እንደሚችሉ አድርገው እንዲያምኑ በማድረግ ብዙ ሰዎችን ያታልላሉ። አዎ፣ አጋንንት ብዙ ሰዎች በሙታን መናፍስት እንዲያምኑ ያደርጋሉ።

ስለዚህ ሰይጣንና አጋንንቱ እኛንም እንዳያሞኙን መጠንቀቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ይሞክራል፤ አገልጋዮቹም እንዲሁ ያደርጋሉ’ በማለት ያስጠነቅቃል።  (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አጋንንት ክፉ ናቸው። እኛም እንደነሱ እንድንሆን የሚሞክሩት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሰዎች ስለ ዓመፅና ተገቢ ስላልሆነ የጾታ ግንኙነት እንዲሁም ስለ መንፈሳዊ ፍጥረታትና የሙታን መናፍስት የሚማሩት ከየት ነው?— አንዳንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችንና ፊልሞችን በመመልከት፣ የኮምፒውተርና የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት፣ ኢንተርኔት በመጠቀም፣ የቀልድ መጽሐፎችን በማንበብ እንዲሁም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር በመዋል አይደለም? እነዚህን ነገሮች ማድረግ የሚያቀራርበን ከአምላክ ጋር ነው ወይስ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር? ምን ይመስልሃል?—

የዓመፅ ድርጊት መመልከት ምን ችግር ሊያስከትል ይችላል?

መጥፎ ነገሮችን እንድናዳምጥና እንድንመለከት የሚፈልጉት እነማን ናቸው?— አዎ፣ ሰይጣንና አጋንንቱ ናቸው። ስለዚህ እኔና አንተ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?— የሚጠቅሙንንና ይሖዋን እንድናገለግል የሚረዱንን ነገሮች ማንበብ፣ ማዳመጥና መመልከት ያስፈልገናል። ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ጥሩ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን መጥቀስ ትችላለህ?—

እኛ ልናደርገው የሚገባ ጠቃሚ ነገር ምንድን ነው?

ጥሩ የሆነውን ነገር የምናደርግ ከሆነ አጋንንትን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ኢየሱስ ከአጋንንት ይበልጥ ኃይለኛ ነው፤ እነሱም ይፈሩታል። አንድ ቀን አጋንንት ኢየሱስን “የመጣኸው ልታጠፋን ነው?” ብለውት ነበር። (ማርቆስ 1:24) ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን የሚያጠፋበት ጊዜ ሲደርስ አትደሰትም?— እስከዚያው ድረስ ከኢየሱስና በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር ተቀራርበን ከኖርን ኢየሱስ ከአጋንንት እንደሚጠብቀን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን የሚገልጹትን የሚከተሉትን ጥቅሶች እናንብብ:- 1 ጴጥሮስ 5:8, 9፤ ያዕቆብ 4:7, 8