በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 2

ከሚወደን አምላክ የተላከ ደብዳቤ

ከሚወደን አምላክ የተላከ ደብዳቤ

በጣም የምትወደው መጽሐፍ የትኛው ነው?— አንዳንድ ልጆች ስለ እንስሳት የሚናገር መጽሐፍ ይወዳሉ። ሌሎች ደግሞ ብዙ ሥዕሎች ያሉት መጽሐፍ ይወዳሉ። እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ማንበብ አስደሳች ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ በዓለም ላይ ካሉት መጽሐፎች ሁሉ የሚበልጡት ስለ አምላክ እውነተኛውን ነገር የሚነግሩን መጽሐፎች ናቸው። ከእነዚህ መጽሐፎች መካከል ደግሞ አንዱ ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ጠቃሚ ነው። ይህ መጽሐፍ የቱ እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?— አምላክ የሰጠን መጽሐፍ ስለሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ወደፊት አምላክ ለእኛ ስለሚያደርግልን ጥሩ ነገሮች ይነግረናል። በተጨማሪም እኛ እሱን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ይገልጽልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ልክ ከአምላክ እንደተላከልን ደብዳቤ ነው።

እርግጥ፣ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ በሰማይ ጽፎ ለሰዎች ሊልክ ይችል ነበር። ግን እንዲህ አላደረገም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች የተናገረው አምላክ ቢሆንም መጽሐፉን ያጻፈው ምድር ላይ ባሉ አገልጋዮቹ ነው።

አምላክ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?— ይህን መረዳት እንድትችል እስቲ የሚከተለውን ነገር ተመልከት። የአንድን ሰው ድምፅ በሬዲዮ በምንሰማበት ጊዜ ድምፁ የሚመጣው ከሩቅ ቦታ ሊሆን ይችላል። ቴሌቪዥን ስንመለከትም በሌላ አገር ያሉ ሰዎችን ምስል ልናይና የሚናገሩትን ልንሰማ እንችላለን።

እንዲያውም ሰዎች በመንኮራኩር ተሳፍረው በጣም ሩቅ ወደሆነችው ጨረቃ ሊጓዙና እዚያ ሆነው ወደ ምድር መልእክት ሊልኩ ይችላሉ። ይህን ታውቃለህ?— ሰዎች ይህን ማድረግ ከቻሉ አምላክ መልእክቱን ከሰማይ ወደ ምድር መላክ ያቅተዋል?— እንደማያቅተው የታወቀ ነው! ይህን ደግሞ ያደረገው ሰዎች ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ከመሥራታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው።

አምላክ ካለበት ሩቅ ቦታ ሆኖ ሊያናግረን እንደሚችል እንዴት እናውቃለን?

 አምላክ ሲናገር ከሰሙት ሰዎች አንዱ ሙሴ ነው። ሙሴ አምላክን ሊያየው ባይችልም ድምፁን ግን ሰምቷል። አምላክ ከሙሴ ጋር ሲነጋገር በጣም ብዙ ሰዎች በዚያ ቦታ ተሰብስበው ነበር። እንዲያውም አምላክ በዚያ ቀን አንድ ተራራ እንዲንቀጠቀጥ አድርጎ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ነጎድጓድ የተሰማ ሲሆን መብረቅም ታይቶ ነበር። ሰዎቹ አምላክ እየተናገረ መሆኑን ቢያውቁም በጣም ፈርተው ነበር። ስለዚህ ሙሴን “እግዚአብሔር እንዲናገረን አታድርግ፤ አለበለዚያ መሞታችን ነው” አሉት። በኋላም ሙሴ፣ አምላክ የተናገረውን ነገር ጻፈው። ሙሴ የጻፈው ነገር ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል።—ዘፀአት 20:18-21

የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች የጻፈው ሙሴ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈው እሱ ብቻ አይደለም። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጻፍ 40 የሚያህሉ ሰዎችን ተጠቅሟል። እነዚህ ሰዎች የኖሩት በድሮ  ጊዜ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ጽፎ ለመጨረስ ብዙ ዓመታት ፈጅቷል። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እስኪያልቅ 1,600 ዓመታት አልፈዋል! የሚያስገርመው ነገር፣ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው ባይተዋወቁም የጻፉት ነገር ሁሉ እርስ በርሱ ይስማማል።

የእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስም ማን ነው?

አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ ከተጠቀመባቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ታዋቂ ሰዎች ነበሩ። ሙሴ በግ ጠባቂ የነበረ ቢሆንም የእስራኤል ሕዝብ መሪ ሆኗል። ሰለሞን ንጉሥ የነበረ ሲሆን በዓለም ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛና ሀብታም ሰው ነበር። ሌሎቹ ጸሐፊዎች ግን ብዙም ታዋቂ ሰዎች አልነበሩም። አሞጽ የበለስ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን የሚንከባከብ ሰው ነበር።

በተጨማሪም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሐኪም ነበር። ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— ሉቃስ ነው። ሌላው ጸሐፊ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። ይህ ሰው ማቴዎስ ይባላል። ሌላው ደግሞ የአይሁዳውያንን ሃይማኖታዊ ሕግ በደንብ የተማረ ሕግ አዋቂ ሰው ነበር። ከሁሉም ይበልጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎችን የጻፈው እሱ ነው። ይህን ሰው ታውቀዋለህ?— ጳውሎስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሆኑት ጴጥሮስና ዮሐንስ የሚባሉት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ደግሞ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ።

ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አብዛኞቹ አምላክ ወደፊት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ጽፈዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች ሊያውቁ የቻሉት እንዴት ነው?— አምላክ ስለነገራቸው ነው።

ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተጻፈ በኋላ ነበር። ታላቁ አስተማሪ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ እንደነበረ አስታውስ። አምላክ በፊት ያደረጋቸውን ነገሮች ያውቅ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ እንደሆነ ያምን ነበር?— አዎ፣ ያምን ነበር።

ኢየሱስ ለሰዎች አምላክ ስለ ሠራቸው ሥራዎች በሚናገርበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነብላቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን ነገር በቃሉ ይነግራቸው ነበር። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ከአባቱ ያገኘውን ተጨማሪ እውቀት አምጥቶልናል። ኢየሱስ “ከእሱ የሰማሁትን ያንኑ ነገር ለዓለም እየተናገርኩ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 8:26) ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ስለኖረ ከአምላክ የሰማው ብዙ ነገር አለ። ታዲያ ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች የምናገኘው የት ነው?—  መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች ሁሉ ማንበብ እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈውልናል።

እርግጥ፣ አምላክ በሰዎች ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው በዚያን ጊዜ ይነጋገሩበት በነበረ ቋንቋ ነው። ስለዚህ አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈው በዕብራይስጥ ሲሆን ጥቂቱ በአረማይክ የቀረው በዛ ያለ ክፍል ደግሞ በግሪክኛ ተጽፏል። በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች እነዚያን ቋንቋዎች ስለማያውቋቸው መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም አስፈላጊ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከ2,260 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ይህ ምን ያህል ብዙ እንደሆነ አስብ! መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ያስጻፈው ደብዳቤ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የቱንም ያህል በብዙ ቋንቋዎች ቢገለበጥም መልእክቱ ከአምላክ የመጣ ስለሆነ አልተለወጠም።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ለእኛ አስፈላጊ ነው።  የተጻፈው ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ስላሉት ነገሮች ይገልጻል። በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ አምላክ ምን እንደሚያደርግ ይነግረናል። የሚናገረው ነገር በጣም አስደሳች ነው! ወደፊት አስደናቂ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ይናገራል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ምን ነገሮችን መማር ትችላለህ?

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንዴት እንድንኖር እንደሚፈልግ ይነግረናል። ትክክልና ስህተት የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ይገልጽልናል። አንተም ሆንክ እኔ ይህን ማወቅ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ነገር ስለሠሩ ሰዎችና እነዚህ ሰዎች ስለደረሰባቸው ነገር ስለሚነግረን እነሱ የገጠማቸው ችግር በእኛም ላይ እንዳይደርስ መጠንቀቅ እንችላለን። በተጨማሪም ትክክል የሆነውን ነገር ስላደረጉ ሰዎችና እነዚህ ሰዎች ስላገኙት ጥሩ ውጤት ይነግረናል። ይህ ሁሉ የተጻፈው ለእኛው ጥቅም ነው።

ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የቻልነውን ያህል ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ለአንድ ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል። ጥያቄው ‘መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ማን ነው?’ የሚል ነው። ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?— አዎ፣ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ነው። ታዲያ ጥበበኞች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?— አምላክን በማዳመጥና የሚናገረውን በተግባር በማዋል ነው።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ሆነን ለማንበብ ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። በጣም ከምንወደው ሰው ደብዳቤ ሲደርሰን ደብዳቤውን ደግመን ደጋግመን እናነበዋለን። እንዲህ ዓይነቱን ደብዳቤ በጣም እንወደዋለን። መጽሐፍ ቅዱስም ከማንም በላይ ከሚወደን አምላክ የተላከ ደብዳቤ ስለሆነ በጣም ልንወደው ይገባል።

አሁን ደግሞ ቀጥሎ ባሉት ጥቂት ደቂቃዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል እንደሆነና ለእኛ ጥቅም እንደተጻፈ የሚገልጹትን የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብቡ:- ሮም 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21