በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 11

ከአምላክ መላእክት የሚገኝ እርዳታ

ከአምላክ መላእክት የሚገኝ እርዳታ

አንዳንድ ሰዎች የሚያምኑት የሚያዩትን ነገር ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ግን ሞኝነት ነው። ብዙ ነገሮችን በዓይናችን አይተናቸው ባናውቅም እንዳሉ ግን እናውቃለን። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱን ልትጠቅስ ትችላለህ?—

የምንተነፍሰው አየር መኖሩ ይታወቅሃል?— እስቲ እጅህን ዘርጋና እፍ በልበት። የሚሰማህ ነገር አለ?— አዎ፣ አለ፤ ይሁን እንጂ አየሩን ልታየው አትችልም፣ አይደል?—

ቀደም ሲል በዓይናችን ስለማናያቸው መንፈሳዊ አካሎች ተነጋግረን ነበር። ከእነዚህ መንፈሳዊ አካሎች መካከል አንዳንዶቹ ጥሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ክፉ እንደሆኑ ተምረናል። እስቲ በዓይን ልናያቸው ከማንችላቸው ጥሩ መንፈሳዊ አካሎች ውስጥ አንዳንዶቹን ጥቀስ።— አዎ፣ ይሖዋ አምላክ አለ፤ ኢየሱስ አለ፤ በተጨማሪም ጥሩ መላእክት አሉ። ክፉ መላእክትስ አሉ?— መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መላእክትም እንዳሉ ይናገራል። እስቲ ስለ እነሱ የተማርከውን ነገር ንገረኝ።—

ጥሩዎቹም ሆኑ ክፉዎቹ መላእክት ከእኛ ይበልጥ ኃይለኞች እንደሆኑ እናውቃለን። ታላቁ አስተማሪ ስለ መላእክት ብዙ ነገር ያውቃል። ስለ መላእክት ብዙ ነገር ሊያውቅ የቻለው በምድር ላይ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት መልአክ ስለነበረ ነው። በሰማይ ሳለ ከሌሎች መላእክት ጋር ይኖር ነበር። በሚሊዮን የሚቆጠሩትን መላእክት ያውቃቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ መላእክት ስም አላቸው?—

አምላክ ለከዋክብት ስም እንዳወጣላቸው ተምረናል። ስለዚህ መላእክትም ስም እንዳላቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘መላእክት ቋንቋ’ ስለሚናገር መላእክት እርስ በርሳቸው እንደሚነጋገሩም እናውቃለን። (1 ቆሮንቶስ 13:1) መላእክት ስለምን ነገር የሚያወሩ ይመስልሃል? በምድር ላይ ስላለነው ሰዎች ይነጋገራሉ?—

 የሰይጣን መላእክት የሆኑት አጋንንት ይሖዋን እንዳንታዘዝ ለማድረግ እንደሚጥሩ እናውቃለን። ስለዚህ እኛን እንዴት አድርገው ሊያሳስቱን እንደሚችሉ ይነጋገራሉ ማለት ነው። ይሖዋ እኛንም እንዲጠላን ለማድረግ ስለሚፈልጉ እንደነሱ እንድንሆን ይፈልጋሉ። የአምላክ ታማኝ መላእክትስ ስለ እኛ የሚያወሩ ይመስልሃል?— አዎ፣ ያወራሉ። እኛን ሊረዱን ይፈልጋሉ። አንዳንዶቹ የአምላክ መላእክት ይሖዋን የሚወዱትንና የሚያገለግሉትን ሰዎች እንዴት እንደረዷቸው እስቲ ልንገርህ።

ለምሳሌ ያህል፣ በባቢሎን ይኖር የነበረ ዳንኤል የሚባል ሰው ነበር። በባቢሎን ይኖሩ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋን የማይወዱ ነበሩ። እንዲያውም ሰዎቹ ወደ ይሖዋ አምላክ የሚጸልይ ማንኛውም ሰው እንዲቀጣ የሚያደርግ ሕግ አውጥተው ነበር። ዳንኤል ግን ወደ ይሖዋ መጸለዩን አላቆመም። እነዚያ ሰዎች ዳንኤልን ምን እንዳደረጉት ታውቃለህ?—

አዎ፣ ክፉ ሰዎች ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል አደረጉ። በጉድጓዱ ውስጥ ዳንኤል ብቻውን ከተራቡ አንበሶች ጋር ነበር። ከዚያ በኋላ  የሆነውን ነገር ታውቃለህ?— ዳንኤል “አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ” በማለት ተናግሯል። ዳንኤል ምንም ጉዳት አልደረሰበትም! መላእክት ይሖዋን ለሚያገለግሉ ሰዎች ብዙ አስደናቂ ነገሮች ሊያደርጉላቸው ይችላሉ።—ዳንኤል 6:18-22

አምላክ ዳንኤልን ለማዳን ምን አደረገ?

በአንድ ወቅት ደግሞ ጴጥሮስ ታስሮ ነበር። ጴጥሮስ የታላቁ አስተማሪ የኢየሱስ ክርስቶስ ጓደኛ እንደነበረ ታስታውሳለህ። ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ጴጥሮስ ሲናገር አንዳንድ ሰዎች ደስ አላላቸውም ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስን ወደ እስር ቤት አስገቡት። ጴጥሮስ እንዳያመልጥ ወታደሮች እየጠበቁት ነበር። ታዲያ ጴጥሮስን ሊረዳው የሚችል ይኖር ይሆን?—

ጴጥሮስ እጆቹ በሰንሰለት ታስረው በሁለት ጠባቂዎች መካከል ተኝቶ  ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- ‘የይሖዋ መልአክ ድንገት መጣ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ። መልአኩም የጴጥሮስን ጎን ነካ ነካ አድርጎ ቀሰቀሰውና “ቶሎ ብለህ ተነሳ!” አለው።’

ጴጥሮስ ከእስር ቤት እንዲወጣ አንድ መልአክ የረዳው እንዴት ነበር?

በዚህ ጊዜ ሰንሰለቱ ከጴጥሮስ እጅ ላይ ወደቀ! መልአኩም ‘ልብስህን ለብሰህና ጫማህን አድርገህ ተከተለኝ’ አለው። መልአኩ ጴጥሮስን እየረዳው ስለነበር ጠባቂዎቹ ሊያስቆሟቸው አልቻሉም። ከዚያም ጴጥሮስና መልአኩ ወደ ብረቱ በር ሲደርሱ አንድ ልዩ ነገር ተፈጸመ። በሩ ሳይነኩት ራሱ ተከፈተ! ጴጥሮስ መስበኩን እንዲቀጥል መልአኩ ነፃ አወጣው።—የሐዋርያት ሥራ 12:3-11

የአምላክ መላእክት እኛንም ሊረዱን ይችላሉ?— አዎ፣ ይችላሉ። ታዲያ ይህ ማለት ምንም ጉዳት እንዳይደርስብን ያደርጋሉ ማለት ነው?— በፍጹም፤ የሞኝነት ድርጊት የምንፈጽም ከሆነ መላእክት ምንም ጉዳት እንዳይደርስብን አይከላከሉልንም። ሆኖም የሞኝነት ድርጊት ባንፈጽምም እንኳን ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። መላእክት የሚላኩት ምንም ጉዳት እንዳይደርስብን እንዲከላከሉልን አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ አንድ ልዩ ሥራ እንዲሠሩ አዟቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ መልአክ በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ በመናገር ላይ እንዳለ ይገልጻል። (ራእይ 14:6, 7) መልአኩ ለሰዎቹ የሚነግራቸው እንዴት ነው? ሁሉም ሰው እንዲሰማው ሰማይ ላይ ሆኖ ይጮኻል ማለት ነው?— አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ ለሌሎች የሚናገሩት በምድር ላይ ያሉት የኢየሱስ ተከታዮች ሲሆኑ መላእክት ደግሞ ይመሯቸዋል። መላእክት ከልባቸው ስለ አምላክ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መልእክቱን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። እኛም በዚህ የስብከት ሥራ ልንካፈል እንችላለን፤ መላእክት ደግሞ ይረዱናል።

ሆኖም አምላክን የማይወዱ ሰዎች ችግር ቢፈጥሩብንስ? ቢያሳስሩንስ? መላእክት እኛንም ከእስር ሊያስለቅቁን ይችላሉ?— ይህን ለማድረግ ችሎታው አላቸው። ነገር ግን ሁልጊዜ ይህን ያደርጋሉ ማለት አይደለም።

መልአኩ ለጳውሎስ ምን እየነገረው ነው?

የኢየሱስ ተከታይ የሆነው ጳውሎስ በአንድ ወቅት ታስሮ ነበር። በባሕር ላይ በመርከብ እየተጓዘ ሳለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነስቶ ነበር። ነገር ግን መላእክት  ወዲያውኑ አላስለቀቁትም። ምክንያቱም ስለ አምላክ መስማት የሚያስፈልጋቸው ሌሎች ሰዎች ነበሩ። አንድ መልአክ “ጳውሎስ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል” አለው። አዎ፣ ጳውሎስ የዓለም ገዥ ለነበረው ለቄሳር እንዲሰብክ እሱ ፊት መቅረብ ነበረበት። መላእክት ምንጊዜም ጳውሎስ ያለበትን ቦታ ያውቁ የነበረ ሲሆን የሚያስፈልገውንም እርዳታ ያደርጉለት ነበር። እኛም በእርግጥ አምላክን የምናገለግል ከሆነ መላእክት ይረዱናል።—የሐዋርያት ሥራ 27:23-25

መላእክት ወደፊት የሚሠሩት አስፈላጊ የሆነ አንድ ሌላ ሥራ አለ፤ ይህን ሥራም በቅርቡ ይፈጽሙታል። አምላክ ክፉ ሰዎችን የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። እውነተኛውን አምላክ የማያመልኩ ሰዎች ሁሉ ይጠፋሉ። ያ ጊዜ ሲመጣ ‘መላእክትን ልናያቸው ስለማንችል መኖራቸውን አናምንም’ የሚሉ ሰዎች ምን ያህል እንደተሳሳቱ ይገነዘባሉ።—2 ተሰሎንቄ 1:6-8

ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?— የአምላክ መላእክት እነሱን የምንደግፍ ከሆነ ይረዱናል። ታዲያ እኛ እነሱን እንደግፋለን?— ይሖዋን የምናገለግል ከሆነ እነሱን እየደገፍን ነው ማለት ነው። ይሖዋን የምናገለግል ከሆነ ደግሞ ሌሎች ሰዎችም እሱን እንዲያገለግሉት እንናገራለን።

መላእክት ሰዎችን እንዴት እንደሚረዱ ይበልጥ ለመገንዘብ መዝሙር 34:7፤ ማቴዎስ 4:11፤ 18:10፤ ሉቃስ 22:43 እና የሐዋርያት ሥራ 8:26-31ን አንብቡ።