በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 38

ኢየሱስን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

ኢየሱስን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

እየሰመጠ ባለ ጀልባ ላይ ተሳፍረሃል እንበል። አንድ ሰው ከመስመጥ ቢያድንህ ደስ አይልህም?— አንድ ሰው የራሱን ሕይወት ሠውቶ ቢያድንህስ ምን ይሰማሃል?— ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አድርጓል። ምዕራፍ 37 ላይ እንደተማርነው ኢየሱስ እኛ መዳን እንድንችል ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ የሚያድነን ከመስመጥ አይደለም። እሱ ከምን እንደሚያድነን ታስታውሳለህ?— ከአዳም ከወረስነው ኃጢአትና ሞት ያድነናል። አንዳንድ ሰዎች በጣም መጥፎ የሆነ ነገር የሠሩ ቢሆኑም እንኳን ኢየሱስ ለእነሱም ጭምር ሞቶላቸዋል። አንተ ብትሆን ኖሮ መጥፎ ነገር የሠሩ ሰዎችን ለማዳን ብለህ ሕይወትህን ለአደጋ ታጋልጥ ነበር?—

መጽሐፍ ቅዱስ “ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ እርግጥ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል” በማለት ይናገራል። ሆኖም ኢየሱስ “አምላክን ለማይታዘዙ ሰዎች” እንደሞተ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህም አምላክን የማያገለግሉ ሰዎችን ይጨምራል! በመቀጠልም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ገና ኃጢአተኞች [ማለትም መጥፎ ነገር የምንሠራ ሰዎች ሆነን] ሳለን ክርስቶስ ለእኛ ሞተ’ ይላል።—ሮም 5:6-8

በአንድ ወቅት በጣም መጥፎ ነገር ይሠራ የነበረ ሐዋርያ ትዝ ይልሃል?— ይህ ሐዋርያ “ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ . . . ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ” በማለት ጽፎ ነበር። ይህን የተናገረው ሐዋርያ፣ ጳውሎስ ነው። ‘በአንድ ወቅት የማያመዛዝን’ እንደነበረና “በክፋት” ይኖር እንደነበረ ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 1:15፤ ቲቶ 3:3

አምላክ ልጁን መጥፎ ነገር ለሠሩ ሰዎች እንዲሞት የላከው ምን ያህል ፍቅር ቢኖረው እንደሆነ እስቲ አስበው! መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ዮሐንስ  ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 አምላክ ስላሳየው ታላቅ ፍቅር ምን እንደሚል ለምን አታነብም? ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

ኢየሱስ ለእኛ ሕይወቱን በሰጠበት ጊዜ ምን ሥቃይ ደርሶበታል?

ኢየሱስ አባቱ ለእኛ ያለው ዓይነት ፍቅር እንዳለው በተግባር አሳይቷል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 30 ላይ ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት የደረሰበትን ሥቃይ በጥቂቱ ተመልክተን እንደነበር ታስታውስ ይሆናል። ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ቤት ተወስዶ እዚያ ለፍርድ ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስ በውሸት የመሠከሩ የሐሰት ምሥክሮች ቀርበው የነበረ ሲሆን ሰዎችም በቡጢ መትተውታል። ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ የካደው በዚህ ጊዜ ነበር። አሁን እዚያ እንዳለን አድርገን እናስብና የሆነውን ነገር እንመልከት።

ሌሊቱ ነጋ። ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ምንም አልተኛም። ሌሊት የተካሄደው የፍርድ ሂደት ሕጋዊ ተቀባይነት ስላልነበረው ካህናቱ ሳንሄድሪንን ወይም የአይሁዳውያንን ከፍተኛ የፍርድ ሸንጎ በፍጥነት ሰበሰቡና ኢየሱስን እንደገና ፍርድ ፊት አቀረቡት። አሁንም ኢየሱስን በአምላክ ላይ ወንጀል ሠርቷል ብለው ከሰሱት።

ከዚያም ካህናቱ ኢየሱስን አስረው ሮማዊ ገዥ ወደነበረው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት። ጲላጦስንም ‘ኢየሱስ መንግሥትን ይቃወማል። መገደል አለበት’ አሉት። ጲላጦስ ግን ካህናቱ ውሸት እየተናገሩ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ጲላጦስ ‘በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘሁም። በነፃ እለቀዋለሁ’ አላቸው። ይሁን እንጂ ካህናቱና ሌሎች ሰዎች ‘አይሆንም! ግደለው!’ እያሉ ጮኹ።

በኋላም ጲላጦስ ኢየሱስን ሊለቀው እንደሆነ ለሕዝቡ ሊነግር ሞክሮ ነበር። ካህናቱ ግን ሕዝቡ ‘እሱን ከለቀቅከው አንተም የመንግሥት ተቃዋሚ ነህ ማለት ነው! ግደለው!’ እያለ እንዲጮኽ አደረጉ። ሕዝቡ በጣም መንጫጫት ጀመረ። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?—

ጲላጦስ በሕዝቡ ጩኸት ተሸነፈ። በመጀመሪያ ኢየሱስን አስገረፈው። ከዚያም እንዲገደል ለወታደሮቹ አሳልፎ ሰጠው። ወታደሮቹም በኢየሱስ ራስ ላይ የእሾህ አክሊል ደፍተው በፊቱ እየሰገዱ አሾፉበት። ከዚያም ኢየሱስን አንድ  ትልቅ ግንድ ወይም እንጨት አሸከሙትና ከከተማዋ ውጪ ወደሚገኝ የራስ ቅል ቦታ ወደሚባል ሥፍራ ወሰዱት። እዚያም የኢየሱስን እጆችና እግሮች እንጨቱ ላይ በምስማር መቷቸው። ከዚያም ኢየሱስ በእንጨቱ ላይ እንደተሰቀለ እንጨቱን ቀጥ አድርገው አቆሙት። ኢየሱስ ደሙ እየፈሰሰ ነበር። ሥቃዩም በጣም ከፍተኛ ነበር።

ኢየሱስ ወዲያውኑ አልሞተም። እዚያው እንደተሰቀለ ቆየ። የካህናት አለቆቹ ያሾፉበት ነበር። በዚያ የሚያልፉ ሰዎችም “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ውረድ!” ይሉት ነበር። ኢየሱስ ግን አባቱ ምን እንዲያደርግ እንደላከው ያውቃል። እኛ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበት አጋጣሚ እንዲኖረን ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በመጨረሻም ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት ገደማ  ወደ አባቱ ከጮኸ በኋላ ሞተ።—ማቴዎስ 26:36 እስከ 27:50፤ ማርቆስ 15:1፤ ሉቃስ 22:39 እስከ 23:46፤ ዮሐንስ 18:1 እስከ 19:30

ኢየሱስ ከአዳም በጣም የተለየ ነበር! አዳም ለአምላክ ፍቅር አላሳየም። የአምላክን ትእዛዝ ጥሷል። አዳም ለእኛም ቢሆን ፍቅር አላሳየም። እሱ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ተወልደናል። ኢየሱስ ግን ለአምላክም ሆነ ለእኛ ፍቅር አሳይቷል። እሱ ምንጊዜም አምላክን ይታዘዝ ነበር። እንዲሁም አዳም ያደረሰብንን ጉዳት ለማስወገድ ሕይወቱን ሰጥቷል።

ኢየሱስን እንደምንወደው ለማሳየት ምን ማድረግ እንችላለን?

ኢየሱስ የፈጸመውን በጣም ጥሩ የሆነ ተግባር ታደንቃለህ?— ወደ አምላክ በምትጸልይበት ጊዜ ልጁን ለእኛ በመስጠቱ ታመሰግነዋለህ?— ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ ያደረገለትን ነገር አድንቋል። ጳውሎስ የአምላክ ልጅ ‘ወዶኛል፤ እንዲሁም ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ ብሏል። (ገላትያ 2:20) ኢየሱስ ለአንተም ሆነ ለእኔ ሞቶልናል። እኛ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ፍጹም ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል! በእርግጥም ይህ ኢየሱስን እንድንወደው የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ ለነበሩ ክርስቲያኖች “የክርስቶስ ፍቅር ለተግባር ያነሳሳናል” በማለት ጽፎላቸዋል። የክርስቶስ ፍቅር ምን ዓይነት ተግባር እንድንፈጽም ያነሳሳናል? አንተ ምን ትላለህ?— ጳውሎስ የሰጠውን መልስ ልብ በል:- “ለእሱ እንዲኖሩ ሲል ክርስቶስ ለሁሉ ሞተ። ከእንግዲህ ራሳቸውን ለማስደሰት ብለው መኖር የለባቸውም።”2 ቆሮንቶስ 5:14, 15 ኒው ላይፍ ቨርዥን

 የምትኖረው ክርስቶስን ለማስደሰት መሆኑን ማሳየት የምትችልባቸውን መንገዶች መጥቀስ ትችላለህ?— አዎ፣ ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ስለ እሱ ያወቅከውን ነገር ለሌሎች መናገር ነው። የሚከተለውን ደግሞ እስቲ አስብበት:- ብቻህን ነህ እንበል፤ ስለሆነም የምታደርገውን ነገር እናትህ ወይም አባትህ ወይም ሌላ ማንም ሰው አያይ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የማያስደስቱ ነገሮች ታደርጋለህ ወይም በቴሌቪዥን ትመለከታለህ?— ኢየሱስ አሁን ሕያው እንደሆነና የምናደርገውን ነገር በሙሉ መመልከት እንደሚችል አስታውስ!

የምናደርገውን ነገር ሁሉ ማን ሊያይ ይችላል?

ኢየሱስን መውደድ አለብን የምንልበት ሌላው ምክንያት ይሖዋን መምሰል ስለምንፈልግ ነው። ኢየሱስ ‘አብ ይወደኛል’ ብሏል። ይሖዋ ኢየሱስን የሚወደውና እኛም ልንወደው የሚገባን ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ በመሆኑ ነው። (ዮሐንስ 10:17) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት የሚነግረንን ነገር ተግባራዊ እናድርግ:- “የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ፤ ክርስቶስ እንደወደዳችሁና . . . ራሱን ስለ እናንተ መባና መሥዋዕት አድርጎ ለአምላክ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ኤፌሶን 5:1, 2

ለኢየሱስና ላደረገልን ነገር ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ዮሐንስ 3:35፤ 15:9, 10 እና 1 ዮሐንስ 5:11, 12ን እናንብብ።