በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 4

አምላክ ስም አለው

አምላክ ስም አለው

ከአንድ ሰው ጋር ስትተዋወቅ ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ የምትጠይቀው ምንድን ነው?— አዎ፣ ስሙን ትጠይቃለህ። ሁላችንም ስም አለን። አምላክ በምድር ላይ በመጀመሪያ ለፈጠረው ሰው ስም አውጥቶለታል። ይህ ሰው ስሙ አዳም ነበር። የአዳም ሚስት ደግሞ ሔዋን ትባል ነበር።

ይሁን እንጂ ስም ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። እስቲ ስም ያላቸውን ሌሎች ነገሮች አስብ። ውሻ ወይም ድመት ቢኖርህ ስም ታወጣለታለህ፣ አይደል?— አዎ፣ ስም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

ማታ በጨለማ የሚታዩትን በጣም ብዙ ከዋክብት ተመልከት። ስም ያላቸው ይመስልሃል?— አዎ፣ አምላክ በሰማይ ላለው ለእያንዳንዱ ኮከብ ስም አውጥቶለታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል” በማለት ይነግረናል።—መዝሙር 147:4

ሁሉም ከዋክብት ስም እንዳላቸው ታውቅ ነበር?

በመላው ጽንፈ ዓለም ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አካል ማን ይመስልሃል?— አዎ፣ አምላክ ነው። ታዲያ አምላክ ስም ያለው ይመስልሃል?— አምላክ ስም እንዳለው ኢየሱስ ተናግሯል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ወደ አምላክ ሲጸልይ ‘ስምህን ለተከታዮቼ አሳውቄያለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 17:26) የአምላክን ስም ታውቀዋለህ?— አምላክ ስሙ ማን እንደሆነ ራሱ ይነግረናል። “እኔ ይሖዋ ነኝ፣ ስሜ ይህ ነው” ብሏል። ስለዚህ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።—ኢሳይያስ 42:8 NW

ሰዎች ስምህን አስታውሰው ሲጠሩህ ምን ይሰማሃል? ደስ አይልህም?— ይሖዋም ሰዎች ስሙን እንዲያውቁ ይፈልጋል። ስለዚህ ስለ አምላክ ስንናገር ይሖዋ የሚለውን ስም መጠቀም አለብን። ታላቁ አስተማሪ ለሰዎች ሲናገር ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም ይጠቀም ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ . . . ውደድ” በማለት ተናግሯል።—ማርቆስ 12:30

 ኢየሱስ “ይሖዋ” የሚለው የአምላክ ስም በጣም አስፈላጊ ስም እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ተከታዮቹ በአምላክ ስም እንዲጠቀሙ አስተምሯቸዋል። በሚጸልዩበት ጊዜም እንኳን ስለ አምላክ ስም እንዲጸልዩ አስተምሯል። አምላክ ሰዎች ሁሉ ይሖዋ የሚለውን ስሙን እንዲያውቁ እንደሚፈልግ ኢየሱስ ያውቅ ነበር።

አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት ሙሴ ለተባለ አንድ እስራኤላዊ ሰው የስሙን አስፈላጊነት ገልጾለት ነበር። እስራኤላውያን ግብፅ በሚባል አገር ይኖሩ ነበር። በዚያ አገር የሚኖሩ ሰዎች ግብፃውያን ይባላሉ። ግብፃውያን እስራኤላውያንን ባሪያዎች አድርገዋቸው የነበረ ሲሆን በጭካኔ ይገዟቸው ነበር። ሙሴ ሲያድግ እንደ እሱ እስራኤላዊ ከሆኑት ሰዎች አንዱን ለመርዳት ሞክሮ ነበር። የግብፅ ንጉሥ የነበረው ፈርዖን ይህን ሲሰማ ተቆጣ። ፈርዖን ሙሴን ሊገድለው ፈለገ! ስለዚህ ሙሴ ከግብፅ ሸሽቶ አመለጠ።

ከዚያም ሙሴ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሄደበት አገር ምድያም ይባላል። እዚያም ሙሴ ሚስት  አግብቶ ልጅ ወለደ። በተጨማሪም እረኛ ሆኖ በግ ይጠብቅ ነበር። አንድ ቀን ሙሴ በአንድ ተራራ አጠገብ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ አንድ የሚያስገርም ነገር ተመለከተ። አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ሲነድ አየ፤ ነገር ግን ቁጥቋጦው አልተቃጠለም! ሙሴ ቀረብ ብሎ ለማየት ወደ ቁጥቋጦው ተጠጋ።

በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ታውቃለህ?— ሙሴ ከሚነደው ቁጥቋጦ መካከል አንድ ድምፅ ሲጠራው ሰማ። ድምፁ “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ተጣራ! የጠራው ማን ነበር?— አምላክ ነበር! አምላክ ለሙሴ የሚሰጠው ብዙ ሥራ ነበረው። አምላክ እንዲህ አለው:- ‘ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ።’ አምላክ፣ ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲያወጣ እንደሚረዳው ቃል ገባለት።

ሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ አጠገብ በነበረበት ጊዜ ምን አስፈላጊ ነገር ተምሯል?

ይሁን እንጂ ሙሴ ‘በግብፅ ወዳሉት የእስራኤል ልጆች ሄጄ አምላክ ላከኝ ስላቸው “ስሙ ማን ነው?” ቢሉኝ ምን እላቸዋለሁ?’ ብሎ አምላክን ጠየቀው። አምላክ ለሙሴ ‘ወደ እናንተ የላከኝ ይሖዋ ነው። ስሙም ለዘላለም ይሖዋ እንደሆነ ነግሮኛል’ ብሎ ለእስራኤል ልጆች እንዲነግራቸው አዘዘው። (ዘፀአት 3:1-15 NW) ይህ ደግሞ አምላክ፣ ይሖዋ በተባለው ስሙ ለዘላለም  እንደሚጠራ ያሳያል። ይህን ስም ፈጽሞ አይለውጠውም ማለት ነው። አምላክ ለዘላለም መታወቅ የሚፈልገው ይሖዋ በሚለው ስሙ ነው።

አምላክ በቀይ ባሕር ስሙን ያስታወቀው እንዴት ነው?

ሙሴ ወደ ግብፅ ተመልሶ ሲሄድ ግብፃውያን ይሖዋ አንድ አነስተኛ የእስራኤላውያን አምላክ መስሏቸው ነበር። ይሖዋ የምድር ሁሉ አምላክ መሆኑን አላወቁም ነበር። ስለዚህ ይሖዋ የግብፁን ንጉሥ ‘ስሜ በምድር ሁሉ ላይ እንዲታወቅ አደርጋለሁ’ አለው። (ዘፀአት 9:16) በእርግጥም ይሖዋ ስሙ እንዲታወቅ አድርጓል። ይሖዋ ስሙ እንዲታወቅ ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?—

ይሖዋ፣ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እየመራ ከግብፅ እንዲያወጣቸው አደረገ። ቀይ ባሕር ጋር ሲደርሱ ይሖዋ ባሕሩን ሰንጥቆ ደረቅ መንገድ አዘጋጀላቸው። እስራኤላውያን ያለምንም ችግር ባሕሩን ተሻገሩ። ፈርዖንና ወታደሮቹ በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ደረቁ መንገድ ሲገቡ በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ የነበረው ውኃ እላያቸው ላይ ፈሶ አሰመጣቸውና ሞቱ።

ወዲያውኑ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ይሖዋ በቀይ ባሕር ያደረገውን ነገር ሰሙ። ሰዎቹ ይህን ነገር እንደሰሙ እንዴት እናውቃለን?— ይህ ነገር ከተፈጸመ ከ40 ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን ይሖዋ እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል ወደገባላቸው ወደ ከነዓን ምድር መጡ። እዚያም ረዓብ የምትባል ሴት ‘ከግብፅ በወጣችሁ  ጊዜ ይሖዋ ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ ሰምተናል’ ብላ ለሁለት እስራኤላውያን ነግራቸው ነበር።—ኢያሱ 2:10

በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች በዚያን ጊዜ እንደነበሩት ግብፃውያን ናቸው። ይሖዋ የምድር ሁሉ አምላክ መሆኑን አያምኑም። ስለዚህ ይሖዋ የራሱ ሕዝቦች ስለ እሱ ለሌሎች ሰዎች እንዲነግሩ ይፈልጋል። ኢየሱስም ስለ ይሖዋ ለሌሎች ሰዎች ተናግሯል። ኢየሱስ በምድር ላይ እያለ፣ የሚሞትበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ስምህን ለእነሱ አሳውቄአለሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 17:26

ኢየሱስ የአምላክን ስም አስታውቋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም ያለበትን ጥቅስ አውጥተህ ማሳየት ትችላለህ?

 እንደ ኢየሱስ መሆን ትፈልጋለህ? እንደ እሱ መሆን የምትፈልግ ከሆነ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ለሌሎች ሰዎች ንገር። የአምላክን ስም የማያውቁ ብዙ ሰዎች ልታገኝ ትችላለህ። ስለዚህ የ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ዘፀአት 6:3ን አውጥተህ የአምላክን ስም ልታሳያቸው ትችል ይሆናል። እስቲ ይህን ጥቅስ እናውጣና አብረን እናንብበው። እንዲህ ይላል:- “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።”

ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን?— የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ እንማራለን። ይህ ስም ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችለውና ሁሉን የፈጠረው አምላክ ማለትም የኢየሱስ አባት ስም ነው። ደግሞም ኢየሱስ ይሖዋ አምላክን በሙሉ ልባችን መውደድ እንዳለብን እንደተናገረ አስታውስ። ታዲያ አንተ ይሖዋን ትወደዋለህ?—

ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?— ይሖዋን እንደምንወደው ማሳየት ከፈለግን እሱን ልክ እንደ ጓደኛችን አድርገን በደንብ ማወቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም ስሙን ለሌሎች ሰዎች በማሳወቅ እሱን እንደምንወደው ማሳየት እንችላለን። ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን ልናሳያቸው እንችላለን። እንዲሁም ይሖዋ ስለፈጠራቸው አስደናቂ ነገሮችና ስላደረጋቸው መልካም ነገሮች ልንናገር እንችላለን። ይህ ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሰዎች ስለ እሱ እንዲያውቁ ይፈልጋል። እኛም ለሰዎች ስለ ይሖዋ በመናገሩ ሥራ ልንካፈል እንችላለን፣ አይደል?—

ስለ ይሖዋ ስንናገር መስማት የማይፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ እንኳ ስለ ይሖዋ ሲናገር ብዙ ሰዎች መስማት አልፈለጉም ነበር። ሆኖም እነሱ መስማት አለመፈለጋቸው ኢየሱስ ስለ ይሖዋ መናገሩን እንዲያቆም አላደረገውም።

ስለዚህ እኛም እንደ ኢየሱስ እንሁን። ስለ ይሖዋ መናገራችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን ለስሙ ፍቅር በማሳየታችን ይሖዋ አምላክ ይደሰትብናል።

አሁን የአምላክን ስም አስፈላጊነት የሚያሳዩ ተጨማሪ ጥቅሶችን አውጥታችሁ አንድ ላይ አንብቡ:- ኢሳይያስ 12:4, 5፤ ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6፤ ሮም 10:13