በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 37

ይሖዋንና ልጁን ማስታወስ

ይሖዋንና ልጁን ማስታወስ

አንድ ሰው ልዩ የሆነ ስጦታ ሰጠህ እንበል። ምን ይሰማሃል?— አንዴ ምስጋናህን ከገለጽክ በኋላ ስጦታውን የሰጠህን ሰው ሙሉ በሙሉ ትረሳዋለህ? ወይስ እሱንም ሆነ ያደረገልህን ነገር ታስታውሳለህ?—

ይሖዋ አምላክ ልዩ የሆነ ስጦታ ሰጥቶናል። ለእኛ እንዲሞትልን ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ ለእኛ መሞት ያስፈለገው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ይህ ልናውቀው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

በምዕራፍ 23 ላይ እንደተማርነው አዳም የአምላክን ፍጹም ሕግ ሲጥስ ኃጢአት ሠርቷል። እኛም የሁላችን አባት ከሆነው ከአዳም ኃጢአት ወርሰናል። ስለዚህ ምን የሚያስፈልገን ይመስልሃል?— በምድር ላይ ፍጹም ሆኖ የኖረ አዲስ አባት ያስፈልገናል። ታዲያ ለእኛ እንዲህ ያለ አባት ሊሆንልን የሚችለው ማን ይመስልሃል?— ኢየሱስ ነው።

ይሖዋ ኢየሱስን በአዳም ምትክ እንደ አባት እንዲሆንልን ወደ ምድር ልኮታል። መጽሐፍ ቅዱስ “‘የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ’ . . . የኋለኛው አዳም ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” በማለት ይናገራል። የመጀመሪያው አዳም ማን ነበር?— አዎ፣ አምላክ ከምድር አፈር የፈጠረው ሰው ነበር። ሁለተኛው አዳምስ ማን ነው?— ኢየሱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ይህን ያረጋግጥልናል:- “የመጀመሪያው ሰው [አዳም] ከምድር የተገኘና ከአፈር የተሠራ ነው፤ ሁለተኛው ሰው [ኢየሱስ] ደግሞ ከሰማይ ነው።”1 ቆሮንቶስ 15:45, 47፤ ዘፍጥረት 2:7

አምላክ የኢየሱስን ሕይወት ከሰማይ ወስዶ በማርያም ሆድ ውስጥ ስላስቀመጠው ኢየሱስ ከአዳም የመጣው ኃጢአት አልተላለፈበትም። ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 1:30-35) በተጨማሪም ኢየሱስ ሲወለድ መልአኩ እረኞቹን ‘በዛሬው ዕለት አዳኝ ተወልዶላችኋል’ በማለት  የነገራቸው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 2:11) ይሁን እንጂ ሕፃኑ ኢየሱስ ለእኛ አዳኝ ለመሆን በመጀመሪያ ምን መሆን ያስፈልገው ነበር?— ማደግና ትልቅ ሰው መሆን ያስፈልገው ነበር። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ‘ሁለተኛው አዳም’ መሆን ይችላል።

በተጨማሪም አዳኛችን ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ይሆንልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የዘላለም አባት” ተብሎ ተጠርቷል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) አዎ፣ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ፍጽምናውን ባጣው በአዳም ምትክ ፍጹም የሆነው ኢየሱስ አባታችን መሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ‘ሁለተኛውን አዳም’ አባት አድርገን መምረጥ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ራሱ የይሖዋ አምላክ ልጅ ነው።

አዳምና ኢየሱስ የሚመሳሰሉት በምን መንገድ ነው? መመሳሰላቸው አስፈላጊ የነበረውስ ለምንድን ነው?

ስለ ኢየሱስ በመማር እሱን እንደ አዳኛችን አድርገን መቀበል እንችላለን። መዳን የሚያስፈልገን ከምን እንደሆነ ታስታውሳለህ?— አዎ፣ ከአዳም ከወረስነው ኃጢአትና ሞት ነው። ኢየሱስ ትልቅ ሰው ሆኖ ለእኛ የሠዋው ወይም የሰጠው ፍጹም ሕይወት ቤዛ ተብሎ ይጠራል። ይሖዋ ቤዛ ያዘጋጀልን ኃጢአታችን ይቅር እንዲባል ነው።—ማቴዎስ 20:28፤ ሮም 5:8፤ 6:23

አምላክና ልጁ ያደረጉልንን ነገር መርሳት አንፈልግም፣ አይደል?— ኢየሱስ፣ እሱ ያደረገልንን ነገር ማስታወስ እንድንችል የሚረዳ አንድ ልዩ መንገድ ለተከታዮቹ አሳይቷል። እስቲ አሁን ስለዚህ ጉዳይ እንነጋገር።

በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ  እንዳለህ አድርገህ አስብ። ጊዜው ማታ ነው። ኢየሱስና ሐዋርያቱ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል። የተጠበሰ የበግ ጠቦት ሥጋ፣ ቂጣና ቀይ ወይን ጠጅ በጠረጴዛው ላይ ቀርቧል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ልዩ ራት እየተመገቡ ነው። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ይህ ራት ይሖዋ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች እያሉ ያደረገላቸውን ነገር የሚያስታውሳቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን ‘ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ የበግ ጠቦት እረዱና ደሙን በቤታችሁ መቃን ላይ ቀቡት’ በማለት ነግሯቸው ነበር። ከዚያም ‘ቤት ውስጥ ሆናችሁ ጠቦቱን ብሉት’ አላቸው።

የበጉ ደም የእስራኤልን ሕዝብ ሊጠብቅ የቻለው እንዴት ነው?

 እስራኤላውያንም እንደታዘዙት አደረጉ። በዚያው ሌሊት የአምላክ መልአክ በግብፅ ምድር አለፈ። መልአኩ በአብዛኞቹ ቤቶች ውስጥ የነበሩትን የመጀመሪያ ልጆች ገደለ። ይሁን እንጂ መልአኩ የጠቦቱን ደም በመቃኑ ላይ ሲመለከት ያንን ቤት አልፎ ይሄድ ነበር። በመሆኑም በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ምንም ልጅ አልሞተም። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን የይሖዋ መልአክ ባደረገው ነገር ደንግጦ ነበር። ስለዚህ ፈርዖን እስራኤላውያንን ‘መሄድ ትችላላችሁ፤ ከግብፅ ውጡ!’ አላቸው። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ዕቃቸውን በግመሎቻቸውና በአህዮቻቸው ላይ ጭነው ሄዱ።

ይሖዋ፣ ሕዝቡ እነሱን ነፃ ያወጣበትን መንገድ እንዲረሱ አልፈለገም ነበር። ስለዚህ ‘በዓመት አንድ ጊዜ ዛሬ ማታ እንደበላችሁት ዓይነት ራት መብላት አለባችሁ’ ብሎ ነገራቸው። ይህን ልዩ ራት ፋሲካ ብለው ጠሩት። ፋሲካ የሚለው ቃል “አልፎ መሄድ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። በዚያ ዕለት ማታ የአምላክ መልአክ ደም የተቀቡትን ቤቶች ‘አልፎ ሄዷል።’—ዘፀአት 12:1-13, 24-27, 31

ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፋሲካን ራት ሲበሉ ይህን እያሰቡ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ኢየሱስ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር አደረገ። ይሁን እንጂ ይህን ከማድረጉ በፊት ከሃዲ ሐዋርያ የሆነው ይሁዳ ከክፍሉ እንዲወጣ ተደረገ። ከዚያም ኢየሱስ ከተረፉት ቂጣዎች አንዱን አንስቶ ከጸለየ በኋላ ቆራርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው። “እንኩ፣ ብሉ” አላቸው። ከዚያም ‘ይህ ለእናንተ በምሞትበት ጊዜ የምሰጠውን ሥጋዬን ይወክላል’ አላቸው።

ቀጥሎም ኢየሱስ ቀዩን ወይን የያዘውን ጽዋ አነሳ። አሁንም የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቶ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ” አላቸው። ከዚያም እንዲህ አላቸው:- ‘ይህ ወይን ደሜን ይወክላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናንተን ከኃጢአታችሁ ነፃ ለማውጣት ደሜን አፈስላችኋለሁ። እኔን ለማስታወስ ሁልጊዜ ይህን አድርጉ።’—ማቴዎስ 26:26-28፤ 1 ቆሮንቶስ 11:23-26

ኢየሱስ በወይን የመሰለው ደሙ ለእኛ ምን ሊያደርግልን ይችላል?

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሱን ለማስታወስ ሁልጊዜ እንዲህ ማድረግ እንዳለባቸው መናገሩን አስተዋልክ?— ከዚያን ጊዜ አንስቶ የፋሲካን ራት  በመብላት ፋንታ በዓመት አንድ ጊዜ ኢየሱስንና ሞቱን ለማስታወስ ይህን ልዩ ራት ይበላሉ። ይህ ራት የጌታ ራት ተብሎ ይጠራል። በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የመታሰቢያው በዓል ብለን እንጠራዋለን። ለምን?— ኢየሱስና አባቱ ይሖዋ አምላክ ያደረጉልንን ነገር እንድናስብ ወይም እንድናስታውስ ስለሚያደርገን ነው።

ቂጣው የኢየሱስን ሥጋ እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል። ኢየሱስ፣ እኛ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ሥጋውን መሥዋዕት አድርጎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። ስለ ቀዩ ወይንስ ምን ማለት ይቻላል?— ቀዩ ወይን ደግሞ የኢየሱስን ደም ዋጋማነት ሊያስታውሰን ይገባል። የኢየሱስ ደም በግብፅ ከፈሰሰው የፋሲካ በግ ደም የበለጠ ውድ ነው። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ደም የኃጢአት ይቅርታ ሊያስገኝልን እንደሚችል ይናገራል። ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ስንሆን ደግሞ አንታመምም፣ አናረጅም እንዲሁም አንሞትም። በመታሰቢያው በዓል ላይ ስንገኝ ይህን ማሰብ ይኖርብናል።

በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኘ ሰው ሁሉ ከቂጣው መብላትና ከወይኑ መጠጣት ይኖርበታል?— ኢየሱስ ቂጣውን የሚበሉትንና ወይኑን የሚጠጡትን ‘በመንግሥቴ ድርሻ ይኖራችኋል፤ እንዲሁም ከእኔ ጋር በሰማይ በዙፋን ትቀመጣላችሁ’ ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:19, 20, 30) ይህ ማለት ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ለመሆን ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለት ነው። ስለዚህ ቂጣውን የሚበሉትና ወይኑን የሚጠጡት በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የመግዛት ተስፋ ያላቸው ብቻ ናቸው።

ይሁን እንጂ ቂጣውን የማይበሉና ወይኑን የማይጠጡ ሰዎችም እንኳ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት አለባቸው። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ ሕይወቱን የሰጠው ለእኛም ጭምር ስለሆነ ነው። በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘት እንዳልረሳነው እናሳያለን። በዚህ መንገድ የአምላክን ልዩ የሆነ ስጦታ እናስታውሳለን።

የኢየሱስን ቤዛ አስፈላጊነት ከሚገልጹት ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- 1 ቆሮንቶስ 5:7፤ ኤፌሶን 1:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19