በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 27

አምላክህ ማን ነው?

አምላክህ ማን ነው?

አምላክህ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?— ይህ ጥያቄ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ሰዎች ብዙ አማልክትን ስለሚያመልኩ ነው። (1 ቆሮንቶስ 8:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ከይሖዋ ባገኘው ኃይል በእግሩ ተራምዶ የማያውቅ ሰው በፈወሰ ጊዜ ሰዎቹ “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ። ሕዝቡ ጳውሎስንና ጓደኛውን በርናባስን ሊያመልኳቸው ፈልገው ነበር። የሐሰት አማልክትን ስም በመስጠት ጳውሎስን ሄርሜስ፣ በርናባስን ደግሞ ዙስ ብለው ጠሯቸው።

ጳውሎስና በርናባስ ግን ሰዎቹ እንዲያመልኳቸው አልፈቀዱላቸውም። ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጠው በመግባት ‘ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሕያው ወደሆነው አምላክ ተመለሱ’ አሏቸው። (የሐዋርያት ሥራ 14:8-15) ሁሉንም ነገር የፈጠረው “ሕያው አምላክ” ማን ነው?— አዎ፣ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” የሆነው ይሖዋ ነው። ኢየሱስ ይሖዋን “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” በማለት ጠርቶታል። ስለዚህ ሊመለክ የሚገባው ማን ብቻ ነው?— ይሖዋ ብቻ ነው!—መዝሙር 83:18፤ ዮሐንስ 17:3፤ ራእይ 4:11

ጳውሎስና በርናባስ ሰዎቹ እንዲሰግዱላቸው ያልፈቀዱት ለምንድን ነው?

አብዛኞቹ ሰዎች የሚያመልኩት ‘ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ’ ሳይሆን ሌሎች አማልክትን ነው። ብዙውን ጊዜ የሚያመልኩት ከእንጨት፣ ከድንጋይ ወይም ከብረት የሠሯቸውን ነገሮች ነው። (ዘፀአት 32:3-7፤ ዘሌዋውያን 26:1፤ ኢሳይያስ 44:14-17) አንዳንድ ጊዜ ዝነኛ የሆኑ ወንዶችና ሴቶችም እንኳን ሳይቀሩ እንደ አማልክት የሚታዩ ሲሆን ኮከቦች ተብለው ይጠራሉ። ታዲያ ለእነሱ ልዩ ክብር መስጠት ተገቢ ነው?—

ሳኦል ሐዋርያው ጳውሎስ ከሆነ በኋላ “የዚህ ሥርዓት አምላክ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ ያሳወረው ይህ አምላክ ማን ነው?— አዎ፣ ሰይጣን  ዲያብሎስ ነው! ሰይጣን ሰዎች ብዙ ነገሮችንና ሰዎችን እንዲያመልኩ ማድረግ ችሏል።

ሰይጣን፣ ኢየሱስ እንዲሰግድለትና እንዲያመልከው ለማድረግ በሞከረበት ጊዜ ኢየሱስ ምን አለው?— “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” አለው። (ማቴዎስ 4:10) ስለዚህ ኢየሱስ መመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። መመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ መሆኑን ያውቁ የነበሩ ወጣቶችን ታሪክ እስቲ እንመልከት። ስማቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ይባላል።

እነዚህ ወጣት ዕብራውያን፣ የአምላክ ሕዝብ የነበሩት የእስራኤላውያን ተወላጆች ሲሆኑ ተማርከው ወደ ባቢሎን ተወስደው ነበር። እዚያም ናቡከደነፆር የተባለ ንጉሥ ግዙፍ የሆነ የወርቅ ምስል አሠርቶ ነበር። አንድ ቀን፣ ይህ ንጉሥ እያንዳንዱ ሰው የሙዚቃ ድምፅ ሲሰማ ለምስሉ እንዲሰግድ አዘዘ። ‘ለምስሉ የማይሰግድና ምስሉን የማያመልክ ሁሉ ወደሚነደው  እሳት ይጣላል’ ብሎ አስጠነቀቀ። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?—

እነዚህ ሰዎች ለምስሉ ያልሰገዱት ለምንድን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ንጉሡ ያዘዘውን ሁሉ ይፈጽሙ ነበር። አሁን ግን ለምስሉ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆኑም። ለምን እምቢ እንዳሉ ታውቃለህ?— የአምላክ ሕግ ‘ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። ለራስህ የተቀረጸ ምስል አትሥራ፤ እንዲሁም አትስገድለት’ ስለሚል ነው። (ዘፀአት 20:3-5) ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ንጉሡን ከመታዘዝ ይልቅ የይሖዋን ሕግ ታዘዙ።

ንጉሡ በጣም ስለተናደደ ወዲያውኑ ሦስቱን ዕብራውያን ወደ እሱ እንዲያመጧቸው አደረገ። ከዚያም እንዲህ አላቸው:- ‘የእኔን አማልክት አላገለገላችሁም የሚባለው እውነት ነው? እንደገና ሌላ ዕድል እሰጣችኋለሁ። አሁን የሙዚቃውን ድምፅ ስትሰሙ ተደፍታችሁ የሠራሁትን ምስል አምልኩ። አለዚያ ወደሚነደው እሳት ትጣላላችሁ። ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችለው አምላክ ማን ነው?’

ወጣቶቹ ምን ያደርጉ ይሆን? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?— ወጣቶቹ ንጉሡን ‘የምናገለግለው አምላካችን ሊያድነን ይችላል። ነገር ግን እሱ ባያድነንም እንኳን የአንተን አማልክት አናገለግልም። ለወርቁ ምስልህም አንሰግድም’ አሉት።

ንጉሡ እጅግ ተቆጣ። ‘እሳቱን ከበፊቱ የበለጠ ሰባት እጥፍ አንድዱት’  ብሎ አዘዘ። ከዚያም ኃይለኛ የሆኑ ሰዎች ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደ እሳቱ እንዲጥሏቸው አዘዘ። እሳቱ በኃይል እየነደደ ስለነበረ ወላፈኑ ወታደሮቹን ገደላቸው! ሦስቱ ዕብራውያንስ ምን ሆኑ?

ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እሳቱ መካከል ወደቁ። ከዚያ በኋላ ግን ተነስተው ቆሙ! ምንም አልተጎዱም። የታሰሩበትም ነገር ተፈቶ ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?— ንጉሡ ወደ እሳቱ ሲመለከት ያየው ነገር አስደነገጠው። ‘እሳቱ ውስጥ የጣልናቸው ሦስት ሰዎች አልነበሩም?’ ብሎ ጠየቀ። አገልጋዮቹም “ንጉሥ ሆይ፣ እውነት ነው” ብለው መለሱ።

ይሖዋ አገልጋዮቹን ከእሳት ያዳናቸው እንዴት ነው?

ከዚያም ንጉሡ ‘እነሆ፣ በእሳቱ ውስጥ አራት ሰዎች ወዲያ ወዲህ ሲሉ አያለሁ፤ እሳቱም አልጎዳቸውም’ አላቸው። አራተኛው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— የይሖዋ መልአክ ነበር። ሦስቱ ዕብራውያን ጉዳት እንዳይደርስባቸው መልአኩ ጠብቋቸዋል።

ንጉሡ ይህን ሲያይ ወደ እሳቱ ቀርቦ ከፍ ባለ ድምፅ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፤ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!” አላቸው። ከእሳቱ ውስጥ ሲወጡ ሁሉም ሰው እንዳልተቃጠሉ አየ። እሳቱ ጫፋቸውን እንኳን  አልነካቸውም። ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለ:- ‘ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማምለክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተባረከ ይሁን።’—ዳንኤል ምዕራፍ 3

በዛሬው ጊዜ እንደ ጣዖት ልዩ ክብር የሚሰጣቸው ምን ዓይነት ሰዎችና ነገሮች ናቸው?

እኛ በዚያን ጊዜ ከተፈጸመው ነገር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ዛሬም ቢሆን ሰዎች ለአምልኮ የሚሆኑ ምስሎች ወይም ጣዖቶች ይሠራሉ። አንድ መጽሐፍ “ባንዲራ እንደ መስቀል ቅዱስ ነው” ይላል። (ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና) ምስሎች ከእንጨት፣ ከድንጋይ፣ ከብረት ወይም ከጨርቅ ሊሠሩ ይችላሉ። የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለሮማ ንጉሠ ነገሥት አይሰግዱም ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዳንኤል ፒ ማኒክስ የቀድሞዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለሮማ ንጉሠ ነገሥት አለመስገዳቸው “ሰዎች ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ወይም ለአገራቸው ታማኝ እንደሆኑ የሚገልጽ ቃለ መሐላ ለመፈጸም እምቢተኛ ከመሆናቸው” ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ተናግረዋል።

ስለዚህ አንድ ሃይማኖታዊ ምስል ከጨርቅ፣ ከእንጨት፣ ከድንጋይ ወይም ከብረት መሠራቱ በአምላክ ዘንድ ልዩነት የሚያመጣ ይመስልሃል?— የይሖዋ አገልጋይ የሆነ ሰው ለእንዲህ ዓይነቱ ምስል መስገዱ ተገቢ ይሆናል?— ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንዲህ አላደረጉም፤ ይሖዋም ተደስቶባቸዋል። ታዲያ አንተ የእነሱን ምሳሌ ልትኮርጅ የምትችለው እንዴት ነው?—

ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች ማንኛውንም ሌላ ነገር ወይም ፍጡር ሊያመልኩ አይችሉም። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኢያሱ 24:14, 15, 19-22፤ ኢሳይያስ 42:8፤ 1 ዮሐንስ 5:21 እና ራእይ 19:10 ላይ የተገለጸውን አንብቡ።