ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት አንድ ለየት ያለ ሕፃን ተወለደ፤ ይህ ልጅ ካደገ በኋላ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ሆነ። በዚያ ዘመን አውሮፕላን ወይም መኪና አልነበረም። እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር ወይም ኢንተርኔት የመሳሰሉ ነገሮችም አልነበሩም።

ይህ ሕፃን ኢየሱስ ይባላል። ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ጥበበኛ ሰው ሆነ። በተጨማሪም ተወዳዳሪ የሌለው ጎበዝ አስተማሪ ሆነ። ኢየሱስ ለመረዳት ከባድ የሆኑ ነገሮችን ቀላል በሆነ መንገድ ለሰዎች ያስረዳ ነበር።

ኢየሱስ በሄደበት ቦታ ሁሉ ያገኛቸውን ሰዎች ያስተምር ነበር። በባሕር ዳርቻዎች አካባቢና ጀልባ ላይ ሆኖ አስተምሯል። በቤታቸውም ሆነ በመንገድ ላይ በሚሄድበት ጊዜ ሰዎችን ያስተምር ነበር። ኢየሱስ መኪና አልነበረውም፤ ደግሞም በአውቶብስም ሆነ በባቡር ተጉዞ አያውቅም። ከቦታ ወደ ቦታ በእግር እየሄደ ሰዎችን አስተምሯል።

ከሌሎች ሰዎች የምንማረው ብዙ ነገር አለ። በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን መማር የምንችለው ግን ታላቅ አስተማሪ ከሆነው ከኢየሱስ ነው። እሱ የተናገራቸውን ቃላት የምናገኘው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። ኢየሱስ የተናገራቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ቃላት የምናነብ ወይም ሲነበብልን የምናዳምጥ ከሆነ ልክ ኢየሱስ እያናገረን እንዳለ ይቆጠራል።

ኢየሱስ እንዲህ ታላቅ አስተማሪ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ሊሆን የቻለበት አንዱ ምክንያት እሱ ራሱ በደንብ ስለተማረ ነው። ማዳመጥ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያዳምጥ የነበረው ማንን ነው? እሱን ያስተማረው ማን ነው?— አባቱ ነው። የኢየሱስ አባት ደግሞ አምላክ ነው።

 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአምላክ ጋር በሰማይ ይኖር ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተለየ ነበር፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ከመወለዱ በፊት በሰማይ የኖረ ሌላ ማንም ሰው የለም። ኢየሱስ በሰማይ እያለ አባቱን የሚያዳምጥ ታዛዥ ልጅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ከአባቱ የተማረውን ነገር ለሌሎች ሰዎች ሊያስተምር ይችላል። አንተም አባትህንና እናትህን በማዳመጥ እንደ ኢየሱስ መሆን ትችላለህ።

ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ሊሆን የቻለበት ሌላው ምክንያት ሰዎችን ይወድ ስለነበረ ነው። ሰዎችን ስለ አምላክ እንዲማሩ መርዳት ያስደስተው ነበር። ኢየሱስ ትልልቅ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ልጆችንም ይወድ ነበር። ልጆችም ኢየሱስ ያዋራቸውና ያዳምጣቸው ስለነበር ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር።

ልጆች ከኢየሱስ ጋር መሆን የሚያስደስታቸው ለምን ነበር?

አንድ ቀን፣ ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ አመጡ። የኢየሱስ ጓደኞች ግን ታላቁ አስተማሪ ከልጆች ጋር ለማውራት ጊዜ የለውም ብለው አሰቡ። ስለዚህ ልጆቻቸውን ይዘው እንዲሄዱ ነገሯቸው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አለ?— “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” አላቸው። አዎ፣ ኢየሱስ እነዚህ ልጆች ወደ እሱ እንዲመጡ ፈልጎ ነበር።  ኢየሱስ ጥበበኛና የተከበረ ሰው ቢሆንም እንኳ ትንንሽ ልጆችን ለማስተማር ጊዜ መድቧል።—ማርቆስ 10:13, 14

ኢየሱስ ልጆችን ያስተምርና ያዳምጥ የነበረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አንዱ ምክንያት፣ በሰማይ ስላለው አባቱ ማለትም ስለ አምላክ በመንገር እነሱን ማስደስት ይፈልግ ስለነበር ነው። አንተስ፣ ሰዎችን ማስደሰት የምትችለው እንዴት ነው?— ስለ አምላክ የተማርካቸውን ነገሮች በመንገር ነው።

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለጓደኞቹ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ለማስተማር በአንድ ትንሽ ልጅ ተጠቅሟል። ልጁን አምጥቶ በደቀ መዛሙርቱ ማለትም በእሱ ተከታዮች መሃል አቆመው። ከዚያም ኢየሱስ እነዚህ ትልልቅ ሰዎች አስተሳሰባቸውን ለውጠው እንደ ሕፃኑ ልጅ መሆን እንዳለባቸው ነገራቸው።

ትልልቅ ልጆችና ትልልቅ ሰዎች ከአንድ ትንሽ ልጅ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ ትልቅ ሰው፣ ሌላው ቀርቶ አንድ ትልቅ ልጅ እንደ ሕፃን መሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ ሕፃን ልጅ ትልቅ ሰው የሚያውቀውን ያህል የማያውቅ በመሆኑ ለመማር ፈቃደኛ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንደ ሕፃናት ትሑት መሆን እንደሚያስፈልጋቸው መናገሩ ነበር። አዎ፣ ሁላችንም ከሌሎች ሰዎች ብዙ ነገር መማር እንችላለን። ደግሞም ሁላችንም ብንሆን የኢየሱስ ትምህርት ከእኛ ሐሳብ እንደሚበልጥ ማወቅ ይኖርብናል።—ማቴዎስ 18:1-5

ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ሊሆን የቻለበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰዎችን በሚያስደስት መንገድ እንዴት ማስተማር እንደሚቻል ያውቅ ስለነበር ነው። ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ያስረዳቸው ነበር። ሰዎች ስለ አምላክ በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ስለ ወፎች፣ ስለ አበቦችና አብዛኞቹ ሰዎች ስለሚያውቋቸው ሌሎች ነገሮች ይነግራቸው ነበር።

 አንድ ቀን፣ ኢየሱስ በተራራ ላይ እያለ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ መጡ። በሥዕሉ ላይ እንደምትመለከተው ኢየሱስ ተቀምጦ ንግግር ሰጠ። ይህ ንግግር የተራራው ስብከት ተብሎ ይጠራል። ኢየሱስ ይህን ንግግር በሰጠበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር:- ‘የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ። አትክልት አይተክሉም፤ ምግብ አያከማቹም። ሆኖም በሰማይ ያለው አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከእነሱ አትበልጡም?’

ኢየሱስ ስለ ወፎችና ስለ አበቦች የተናገረው ምን ለማስተማር ፈልጎ ነበር?

በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ አለ:- ‘እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ። ምንም ሳይሠሩ እንዲሁ ያድጋሉ። ደግሞ እንዴት እንደሚያምሩ ተመልከቱ! ንጉሥ ሰለሞን ሀብታም የነበረ ቢሆንም እንኳ ከሜዳ አበቦች የበለጠ የሚያምር ልብስ አለበሰም። ስለዚህ አምላክ በሜዳ ለሚያድጉት አበቦች የሚያስብ ከሆነ ለእናንተስ አያስብም?’—ማቴዎስ 6:25-33

ኢየሱስ ይህን ሲናገር ምን ለማስተማር እንደፈለገ ገብቶሃል?— ‘የምንበላው ምግብና የምንለብሰው ልብስ ከየት እናገኛለን’ እያልን እንድንጨነቅ አይፈልግም። አምላክ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንደሚያስፈልጉን ያውቃል። ኢየሱስ  ምግብና ልብስ ለማግኘት መሥራት የለብንም አላለም። ይሁን እንጂ ለአምላክ አንደኛ ቦታ መስጠት እንዳለብን ተናግሯል። ይህን ካደረግን አምላክ የምንበላው ምግብና የምንለብሰው ልብስ እንድናገኝ ያደርጋል። ይህን ታምናለህ?—

ኢየሱስ ተናግሮ ሲጨርስ ንግግሩን ያዳመጡት ሰዎች ምን ተሰማቸው?— ሰዎቹ በማስተማር ችሎታው እንደተገረሙ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እሱን ማዳመጥ በጣም ያስደስታል። ኢየሱስ ያስተማረው ነገር ሰዎች ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።—ማቴዎስ 7:28

 ስለዚህ እኛም ከኢየሱስ መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከእሱ መማር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— እሱ የተናገራቸው ነገሮች በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው እናገኛቸዋለን። ይህን መጽሐፍ ታውቀዋለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምናነባቸው ነገሮች ትኩረት በመስጠት ኢየሱስ ሲናገር ማዳመጥ እንችላለን ማለት ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ራሱ ኢየሱስን እንድናዳምጠው እንዳዘዘን የሚገልጽ አስደሳች ታሪክ ይዟል። እስቲ ይህን ታሪክ እንመልከት።

አንድ ቀን፣ ኢየሱስ ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ወደ ተራራ ወጣ። የጓደኞቹ ስም ያዕቆብ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ ይባላል። እነዚህ ሦስት ሰዎች ኢየሱስ በጣም የሚወዳቸው ጓደኞቹ ስለነበሩ ወደፊት ስለ እነሱ የምንማረው ብዙ ነገር ይኖራል። ወደ ተራራው በወጡበት በዚህ ጊዜ አንድ ልዩ ነገር ተፈጸመ፤ የኢየሱስ ፊት በጣም ያበራ ጀመር። በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው ልብሱም እንደ መብራት አንጸባረቀ።

“ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት”

ከዚያ በኋላ ኢየሱስና ጓደኞቹ ከሰማይ አንድ ድምፅ ሰሙ። ድምፁም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት” አለ። (ማቴዎስ 17:1-5) የሰሙት የማንን ድምፅ እንደሆነ ታውቃለህ?— የአምላክን ድምፅ ነበር! አዎ፣ ልጁን መስማት እንዳለባቸው የተናገረው አምላክ ነበር።

እኛስ? አምላክን በመታዘዝ ታላቅ አስተማሪ የሆነውን ልጁን እንሰማለን?— ሁላችንም ልጁን መስማት ያስፈልገናል። ልጁን መስማት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ቀደም ሲል የተነጋገርነው ትዝ ይልሃል?—

አዎ፣ የአምላክን ልጅ መስማት የምንችለው ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በማንበብ ነው። ታላቁ አስተማሪ የሚነግረን ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፉትን እነዚህን ነገሮች በመማር ልትደሰት ትችላለህ። በተጨማሪም እነዚህን የምትማራቸውን ጥሩ ነገሮች ለጓደኞችህ የምትናገር ከሆነ ደስታ ታገኛለህ።

ኢየሱስን በማዳመጥ የሚገኙትን ጥሩ ነገሮች በሚመለከት ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ግለጡና ዮሐንስ 3:16፤ 8:28-30 እና የሐዋርያት ሥራ 4:12ን አንብቡ።