በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 20

ሁልጊዜ ቅድሚያ ማግኘት ትፈልጋለህ?

ሁልጊዜ ቅድሚያ ማግኘት ትፈልጋለህ?

ሁልጊዜ ቅድሚያ ማግኘት ወይም አንደኛ መሆን የሚፈልግ ሰው አይተህ ታውቃለህ?— እንዲህ ዓይነት ሰው ሠልፍ ላይ አንደኛ ለመሆን ሲል ሌላውን ሰው ገፍትሮ ሊያስወጣ ይችላል። ሰዎች እንዲህ ሲያደርጉ አይተህ ታውቃለህ?— ታላቁ አስተማሪ ትልልቅ ሰዎችም እንኳን ሳይቀሩ ከሁሉ የተሻለውን የክብር ቦታ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ አይቶ ነበር። እሱ ግን እንዲህ በማድረጋቸው አልተደሰተም። እስቲ የሆነውን ነገር እንመልከት።

ሰዎች ቅድሚያ ለማግኘት ሲጣጣሩ አይተህ ታውቃለህ?

ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ የሆነ አንድ ፈሪሳዊ በቤቱ ባዘጋጀው ትልቅ ግብዣ ላይ ኢየሱስ ተጋብዞ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ኢየሱስ ወደ ግብዣው ቦታ ከደረሰ በኋላ ሌሎች እንግዶች ሲገቡና የተሻለ መቀመጫ  ሲመርጡ ተመለከተ። ስለዚህ ለተጋባዦቹ አንድ ታሪክ ነገራቸው። ታሪኩን መስማት ትፈልጋለህ?—

ኢየሱስ ‘አንድ ሰው በሠርግ ግብዣ ላይ እንድትገኝ ሲጠራህ የተሻለ ወይም የክብር ቦታ ላይ ሄደህ አትቀመጥ’ ብሎ ተናገረ። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ሌላ የበለጠ ክብር ያለው ሰው ተጋብዞ ሊሆን ስለሚችል እንደሆነ ገልጿል። ስለዚህ በሥዕሉ ላይ እንደምትመለከተው ጋባዡ መጥቶ የተሻለ ቦታ ላይ የተቀመጠውን ሰው ‘ቦታውን ለዚህ ሰው ልቀቅለት፤ አንተ ወደዚያ ሄደህ ተቀመጥ’ ሊለው ይችላል። በዚህ ጊዜ የተሻለ ቦታ ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰው ምን ይሰማዋል?— ዝቅተኛ ቦታ ላይ ሄዶ ሲቀመጥ ተጋባዦቹ ሁሉ ስለሚያዩት ማፈሩ አይቀርም።

ኢየሱስ ይህን የተናገረው የተሻለውን ቦታ መርጦ መቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ ፈልጎ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- ‘ለሠርግ ግብዣ በተጠራህ ጊዜ ዝቅተኛው ቦታ ላይ ተቀመጥ። ከዚያም ጋባዡ መጥቶ “ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል” ይልሃል። በዚህ ጊዜ የተሻለው ቦታ ላይ ሄደህ ስትቀመጥ በሌሎቹ እንግዶች ፊት ክብር ታገኛለህ።’—ሉቃስ 14:1, 7-11

ኢየሱስ የተሻለውን ቦታ ስለሚፈልጉ ሰዎች በተናገረ ጊዜ ምን ትምህርት አስተምሯል?

ኢየሱስ የተናገረው ይህ ታሪክ ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ ገብቶሃል?— እስቲ ገብቶህ እንደሆነ ለማየት አንድ ምሳሌ እንመልከት። ብዙ ሰው እያሳፈረ ወዳለ አውቶብስ ውስጥ ገባህ እንበል። ትልልቆቹ ሰዎች መቀመጫ ሳያገኙ አንተ መቀመጫ ለማግኘት መጣደፍ ይኖርብሃል?— እንዲህ ብታደርግ ኢየሱስ የሚደሰት ይመስልሃል?—

ምንም ነገር ብናደርግ ኢየሱስ ምንም አይመስለውም የሚል ሰው ይኖር ይሆናል። አንተ እንዲህ ብለህ ታስባለህ?— ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በዚያ ታላቅ ግብዣ ላይ በተገኘበት ጊዜ ሰዎቹ የሚቀመጡበትን ቦታ ሲመርጡ አይቷቸዋል። ታዲያ ዛሬም እኛ የምናደርገውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከት አይመስልህም?— እንዲያውም  አሁን ኢየሱስ የሚኖረው በሰማይ ላይ በመሆኑ እኛን ለመመልከት የሚያስችል ጥሩ ቦታ ላይ ይገኛል።

አንድ ሰው ቅድሚያ ማግኘት ወይም አንደኛ መሆን በሚፈልግበት ጊዜ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ብዙውን ጊዜ ጭቅጭቅ ሊነሳና ሰዎች ሊናደዱ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ልጆች አውቶብስ ሲሳፈሩ እንዲህ ዓይነት ችግር ያጋጥማል። የአውቶብሱ በር ገና ከመከፈቱ ልጆቹ ቀድመው ለመግባት ይሯሯጣሉ። መስኮት አጠገብ የሚገኝ የተሻለ ወንበር ለማግኘት ይፈልጋሉ። በዚህ ጊዜ ምን ሊፈጠር ይችላል?— አዎ፣ አንዱ በሌላው ሊናደድ ይችላል።

ቅድሚያ ለማግኘት መፈለግ ብዙ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ይህ ነገር በኢየሱስ ሐዋርያት መካከልም እንኳን ችግር አስከትሎ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ እንደተማርነው ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ከሁሉ የሚበልጠው ማን እንደሆነ ተከራክረው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ?— አዎ፣ እንዲህ ብለው መከራከራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ነግሯቸዋል። ይሁን እንጂ ሌላ ጊዜም እንደገና  ተከራክረዋል። ክርክሩ የጀመረው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ እየተጓዙ ነበር። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ነግሯቸው ስለነበር ያዕቆብና ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው ስለመግዛት እያሰቡ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ ለእናታቸው ለሰሎሜም ነግረዋታል። (ማቴዎስ 27:56፤ ማርቆስ 15:40) በመሆኑም ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ እንዳሉ ሰሎሜ መጣችና በኢየሱስ ፊት ተንበርክካ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።

ኢየሱስ “ምንድን ነው የፈለግሽው?” ብሎ ጠየቃት። እሷም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ሲጀምር ልጆቿን አንዱን በቀኙ ሌላውን በግራው እንዲያስቀምጥላት እንደምትፈልግ ተናገረች። የቀሩት አሥር ሐዋርያት፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እናታቸው እንዲህ ብላ እንድትጠይቅላቸው እንዳደረጉ ሲሰሙ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል?—

ሰሎሜ ኢየሱስን ምን ጠየቀችው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

አዎ፣ በያዕቆብና በዮሐንስ ላይ በጣም ተቆጡ። ስለዚህ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ  በሙሉ አንድ ጠቃሚ ምክር ሰጠ። የአሕዛብ ገዢዎች ታላቅ መሆንና የክብር ቦታ ማግኘት እንደሚፈልጉ ነገራቸው። ሁሉም ሰው እነሱን እንዲታዘዝ ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ማግኘት ይፈልጋሉ። ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲህ መሆን እንደሌለባቸው ነገራቸው። ከዚህ ይልቅ “ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባዋል” በማለት ተናገረ። እስቲ አስበው።—ማቴዎስ 20:20-28

አንድ ባሪያ ምን እንደሚሠራ ታውቃለህ?— እሱ ሌሎች ሰዎችን ያገለግላል እንጂ ሌሎች እሱን እንዲያገለግሉት አይጠብቅም። አንድ ባሪያ ለራሱ የተሻለውን ቦታ ሳይሆን ዝቅተኛውን ቦታ ይመርጣል። ራሱን የበላይ እንደሆነ አድርጎ ሳይሆን የበታች እንደሆነ አድርጎ ይቆጥራል። ደግሞም ኢየሱስ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሰው በሌሎች ፊት እንደ ባሪያ መሆን እንዳለበት መናገሩን አስታውስ።

እኛ ከዚህ ምን ትምህርት የምናገኝ ይመስልሃል?— አንድ ባሪያ የተሻለውን ቦታ እኔ ማግኘት አለብኝ ብሎ ከጌታው ጋር ይከራከራል? ወይም ደግሞ መጀመሪያ መብላት ያለብኝ እኔ ነኝ ብሎ ይከራከራል? ምን ይመስልሃል?— ኢየሱስ፣ አንድ ባሪያ ምንጊዜም ከራሱ ይልቅ ጌታውን እንደሚያስቀድም ተናግሯል።—ሉቃስ 17:7-10

ስለዚህ ቅድሚያ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?— አዎ፣ አንድ ባሪያ በሌሎች ፊት የሚያሳየው ዓይነት ባሕርይ ማሳየት አለብን። ይህ ማለት ደግሞ ከራሳችን በፊት ሌሎችን ማስቀደም ማለት ነው። ሌሎች ሰዎችን ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን እንመለከታቸዋለን ማለት ነው። ሌሎችን ማስቀደም የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች መጥቀስ ትችላለህ?— ወደ ገጽ 40 እና 41 ተመልሰህ ሌሎችን በማገልገል እነሱን ማስቀደም የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ለምን አትመለከትም?

ታላቁ አስተማሪ ሌሎችን በማገልገል ከራሱ ይልቅ እነሱን እንዳስቀደመ ታስታውሳለህ። ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻው ምሽት ላይ ራሱን ዝቅ አድርጎ እግራቸውን እስከማጠብ ደርሷል። እኛም ሌሎችን በማገልገል ቅድሚያ የምንሰጣቸው ከሆነ ታላቁን አስተማሪና አባቱን ይሖዋ አምላክን ማስደሰት እንችላለን።

ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ እንድንሰጥ የሚያበረታቱ አንዳንድ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እናንብብ:- ሉቃስ 9:48፤ ሮም 12:3፤ ፊልጵስዩስ 2:3, 4