በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 23

ሰዎች የሚታመሙት ለምንድን ነው?

ሰዎች የሚታመሙት ለምንድን ነው?

የታመመ ሰው አይተህ ታውቃለህ?— ምናልባት አንተም አንዳንድ ጊዜ ትታመም ይሆናል። ጉንፋን ሊይዝህ ይችላል፣ አለዚያም ሆድህን ያምህ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች በጣም ከመታመማቸው የተነሳ ሰው ካልደገፋቸው መቆም እንኳ አይችሉም። በተለይ ሰዎች በጣም በሚያረጁበት ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል።

ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ይታመማል። ሰዎች የሚታመሙት፣ የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ ቀን ሰዎች መራመድ የማይችል ሰው ወደ ኢየሱስ አምጥተው ነበር፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ሰዎች የሚታመሙትና የሚሞቱት ለምን እንደሆነ ጠቁሞ ነበር። እስቲ በዚያ ወቅት የተፈጸመውን ነገር ልንገርህ።

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ መጡ። በጣም ብዙ ሰዎች መጥተው ስለነበር ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች ወደ ቤት መግባት አልቻሉም። ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ወደ በሩ ለመጠጋት የሚያስችል ቦታ እንኳ አልነበረም። ያም ሆኖ ሰዎቹ መምጣታቸውን አላቋረጡም ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎች መራመድ የማይችል ሽባ የሆነ ሰው አመጡ። ሰውየውን በትንሽ አልጋ ወይም በቃሬዛ ላይ አድርገው የተሸከሙት አራት ሰዎች ነበሩ።

ሰዎቹ ይህን የታመመ ሰው ወደ ኢየሱስ ማምጣት የፈለጉት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ ሊረዳውና ከበሽታው ሊፈውሰው እንደሚችል እርግጠኞች ስለነበሩ ነው። ታዲያ ያ ሁሉ ሰው እያለ ሽባውን ሰው እንዴት ኢየሱስ ፊት እንዳቀረቡት ታውቃለህ?—

እዚህ ላይ የምታየው ሥዕል ሽባውን ሰው ኢየሱስ ፊት ያቀረቡት እንዴት አድርገው እንደሆነ ያሳያል። በመጀመሪያ ሰውየውን ተሸክመው ጣሪያው ላይ ወጡ። ጣሪያው ለጥ ያለ ነበር። ከዚያም ጣሪያውን በስተው ሰውየውን ሊያሾልክ  የሚችል ትልቅ ቀዳዳ ሠሩ። በመጨረሻም የታመመውን ሰው ከነአልጋው በቀዳዳው በኩል አሾልከው ወደ ውስጥ አወረዱት። በእርግጥም ጠንካራ እምነት ነበራቸው!

በቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ ይህን ሲያዩ ተገረሙ። ሽባውን ሰው የተሸከሙት ሰዎች ከነአልጋው አውርደው በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል አደረጉት። ኢየሱስ ሰዎቹ ያደረጉትን ሲያይ ተቆጣ?— በጭራሽ! እንዲያውም ሰዎቹ ባሳዩት እምነት ተደስቶ ነበር። ሽባውን “ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው።

ኢየሱስ ሽባውን ሰው ምን እንዲያደርግ ነገረው?

በቦታው የነበሩት አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መናገሩ ትክክል አይደለም ብለው አሰቡ። ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል አልመሰላቸውም ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ማለት እንደሚችል ለማሳየት ሰውየውን “ተነስ፣ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።

 ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሰውየው ተፈወሰ። ሽባ መሆኑ ቀርቶ አሁን ያለማንም ድጋፍ ራሱ ቆሞ መሄድ ቻለ። ይህን ተአምር ያዩት ሰዎች በጣም ተገረሙ። በሕይወታቸው በሙሉ እንደዚህ ያለ አስገራሚ ነገር አይተው አያውቁም። ሰዎችን ከበሽታቸው መፈወስ የሚችል እንደዚህ ያለ ታላቅ አስተማሪ ስለሰጣቸው ይሖዋን አመሰገኑት።—ማርቆስ 2:1-12

እኛ ከዚህ ተአምር ምን እንማራለን?

እኛ ከዚህ ተአምር ምን እንማራለን?— ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ለማለትና የታመሙ ሰዎችን ለማዳን የሚያስችል ኃይል እንዳለው እንማራለን። ይሁን እንጂ ሌላም የምንማረው በጣም አስፈላጊ ነገር አለ። ሰዎች የሚታመሙት በኃጢአት ምክንያት እንደሆነ እንማራለን።

ታዲያ ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ የምንታመመው ኃጢአተኞች ስለሆንን ነው ማለት ነው?— አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን እንደተወለድን ይናገራል። ኃጢአተኛ ሆኖ መወለድ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— ሁላችንም ፍጽምና የሌለን ወይም ጉድለት ያለብን ሆነን ተወልደናል ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ሳንፈልግ ስህተት እንሠራለን። ሁላችንም ኃጢአተኞች ልንሆን የቻልነው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ሁላችንም ኃጢአተኞች ልንሆን የቻልነው የመጀመሪያው ሰው አዳም አምላክን ስላልታዘዘ ነው። አዳም የአምላክን ሕግ በጣሰ ጊዜ ኃጢአት ሠራ። እኛ ሁላችን ደግሞ ከአዳም ኃጢአትን ወረስን። ኃጢአት ከአዳም የተጋባብን እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? እስቲ ይህን ነገር ሊገባህ በሚችል መንገድ ላስረዳህ።

ሁላችንም ኃጢአተኞች የሆንነው እንዴት ነው?

ዳቦ ሲጋገር አይተህ ታውቃለህ? የዳቦ መጋገሪያ ዕቃው የተሰረጎደ ከሆነ የሚጋገረው ዳቦ ሁሉ ምን እንደሚሆን ታውቃለህ?— በዚህ ዕቃ የሚጋገረው  ዳቦ ሁሉ ልክ እንደ ዕቃው የተሰረጎደ ይሆናል፣ አይደል?—

አዳም እንደ ዳቦ መጋገሪያ ዕቃው ሲሆን እኛ ሁላችን ደግሞ እንደ ዳቦው ነን። አዳም የአምላክን ሕግ ሲጥስ ፍጽምና የጎደለው ሆነ። ልክ እንደ ዕቃው የተሰረጎደ ወይም መጥፎ ምልክት የወጣበት ያህል ነበር። ስለዚህ እሱ የሚወልዳቸው ልጆች እንዴት ያሉ ይሆናሉ?— ልጆቹ በሙሉ ያንኑ የአለፍጽምና ምልክት ወይም ጉድለት ይዘው ይወለዳሉ።

አብዛኞቹ ልጆች ሲወለዱ በዓይን የሚታይ ትልቅ ጉድለት አይኖርባቸውም። እጅ ወይም እግር የሌላቸው ሆነው አይወለዱም። ሆኖም ያለባቸው አለፍጽምና ወይም ጉድለት ከባድ በመሆኑ ይታመሙና ከጊዜ በኋላ ይሞታሉ።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ቶሎ ቶሎ ይታመማሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ኃጢአተኛ ሆነው ስለሚወለዱ ነው?— አይደለም፤ ሁሉም ሰው ይዞት የሚወለደው ኃጢአት መጠን እኩል ነው። ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ተወልደናል። ስለዚህ ከጊዜ በኋላ ሁሉም ሰው በሆነ ዓይነት በሽታ መታመሙ አይቀርም። የአምላክን ሕግ በሙሉ ለመታዘዝ የሚጥሩና ምንም ዓይነት ክፉ ነገር የማይሠሩ ሰዎችም እንኳን ሊታመሙ ይችላሉ።

ኃጢአታችን ሲወገድ ምን ዓይነት ጤንነት ይኖረናል?

ታዲያ አንዳንዶቹ ሰዎች ከሌሎቹ ይበልጥ ቶሎ ቶሎ የሚታመሙት ለምንድን ነው?— ይህ የሚሆንበት ብዙ ምክንያት አለ። ምናልባት የሚመገቡት በቂ ምግብ ላይኖራቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ለጤንነታቸው ጠቃሚ የሆነ ምግብ አይመገቡ ይሆናል። እንደ ኬክና ከረሜላ ያሉ ብዙ ጣፋጭ ነገሮች ይበሉ ይሆናል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ማታ ቶሎ ስለማይተኙና በቂ እንቅልፍ ስለማያገኙ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በዝናብና በብርድ ሰዓት የሚሞቅ ልብስ አይለብሱ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ  ራሳቸውን ለመንከባከብ ቢጥሩም ሰውነታቸው ከሌሎቹ ይበልጥ ደካማና በሽታን መከላከል የማይችል ነው።

ታዲያ ፈጽሞ የማንታመምበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ከኃጢአት ነፃ መሆን እንችል ይሆን?— ኢየሱስ ለሽባው ሰው ያደረገለት ነገር ምን ነበር?— ኢየሱስ ኃጢአቱን ይቅር ብሎታል፤ እንዲሁም ፈውሶታል። ኢየሱስ ይህን መፈጸሙ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ለሚጥሩ ሰዎች ሁሉ አንድ ቀን ምን እንደሚያደርግላቸው ያሳያል።

እኛም ኃጢአት መሥራት እንደማንፈልግና መጥፎ የሆነውን ነገር እንደምንጠላ የምናሳይ ከሆነ ኢየሱስ ይፈውሰናል። ወደፊት አሁን ያለብንን አለፍጽምና ሁሉ ያስወግድልናል። ይህን የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ጊዜ ነው። ኃጢአታችን የሚወገድልን በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ ነው። ከዚያም ኃጢአታችን ሙሉ በሙሉ ሲወገድ ዳግመኛ አንታመምም። ሁላችንም ፍጹም ጤንነት ይኖረናል። ይህ በጣም የሚያስደስት ይሆናል!

ኃጢአት በሁላችንም ላይ ምን እንደሚያስከትል ይበልጥ ለመረዳት ኢዮብ 14:4፤ መዝሙር 51:5፤ ሮም 3:23, 5:12 እና 6:23ን አንብቡ።