በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 42

ሥራ መሥራት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

ሥራ መሥራት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

ከሥራና ከጨዋታ በጣም የምትወደው የትኛውን ነው?— በእርግጥ፣ መጫወት ምንም ስህተት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር “የከተማዪቱም አደባባዮች እዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ” ይላል።—ዘካርያስ 8:5

ታላቁ አስተማሪ ልጆች ሲጫወቱ ማየት ደስ ይለው ነበር። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “የተካንኩ ሠራተኛ ሆኜ [ከአምላክ ጋር] እሠራ ነበር። . . . ሁልጊዜ በፊቱ እደሰት ነበር” ብሏል። ኢየሱስ በሰማይ ከይሖዋ ጋር ይሠራ እንደነበረ ልብ በል። በተጨማሪም በሰማይ ሳለ “በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር” ብሏል። አዎ፣ ከዚህ በፊት እንደተማርነው ታላቁ አስተማሪ ልጆችን ጨምሮ ሁሉንም ሰው ይወድ ነበር።—ምሳሌ 8:30, 31 NW

ታላቁ አስተማሪ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ይደሰት የነበረው በምንድን ነው?

 ኢየሱስ በልጅነቱ ይጫወት የነበረ ይመስልሃል?— ምናልባት ተጫውቶ ይሆናል። ይሁን እንጂ በሰማይ ሳለ ‘የተካነ ሠራተኛ’ የነበረው ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም ይሠራ ነበር?— ኢየሱስ “የአናጢው ልጅ” ተብሎ ይጠራ ነበር። ይሁን እንጂ “አናጺው” ተብሎም ተጠርቷል። ይህ ምን ያመለክታል?— ኢየሱስን ያሳደገው ዮሴፍ የአናጺነት ሥራ አስተምሮት መሆን አለበት። ስለዚህ ኢየሱስም አናጺ ሆኖ ነበር።—ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3

ኢየሱስ ምን ዓይነት አናጺ ነበር?— በሰማይ ሳለ የተካነ ሠራተኛ ስለነበረ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜም የተካነ ወይም ጎበዝ አናጺ የሆነ አይመስልህም?— በዚያን ጊዜ አናጺ መሆን ምን ያህል ከባድ ሥራ እንደሆነ አስበው። ምናልባት ኢየሱስ ወደ ጫካ ሄዶ ዛፍ መቁረጥ ሳይኖርበት አልቀረም። ከዚያም  እንጨቱን መቆራረጥ፣ ተሸክሞ ወደ ቤት መውሰድ እንዲሁም ጠረጴዛ፣ አግዳሚ ወንበርና ሌሎች ነገሮችን ለመሥራት እንጨቱን መቅረጽ ያስፈልገው ይሆናል።

ይህ ሥራ ለኢየሱስ ደስታ አምጥቶለት ነበር ብለህ ታስባለህ?— አንተ ሌሎች ሰዎች እንዲጠቀሙባቸው ጠረጴዛዎችንና ወንበሮችን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መሥራት ብትችል ደስ ይልህ ነበር?— መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ‘በሥራው መደሰቱ’ ጥሩ ነገር እንደሆነ ይናገራል። ሥራ መሥራት ከጨዋታ ልታገኘው የማትችለውን ደስታ ይሰጥሃል።—መክብብ 3:22

በእርግጥም ሥራ ለአእምሯችንም ሆነ ለአካላችን ጠቃሚ ነው። ብዙ ልጆች ምንም ሥራ ሳይሠሩ ቁጭ ብለው ያወራሉ፣ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ ወይም የቪድዮ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ። በዚህም የተነሳ ሰነፍና የማይታዘዙ ልጆች ይሆናሉ፤ ደግሞም ደስታ አይኖራቸውም። ሌሎችንም ቢሆን ደስታ ያሳጣሉ። ደስተኞች ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል?—

በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ መስጠትና አንዳንድ ነገሮችን በመሥራት ሌሎችን መርዳት ደስታ እንደሚያስገኝ ተምረን ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ‘ደስተኛ አምላክ’ ብሎ ይጠራዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) በተጨማሪም በምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ ‘ሁልጊዜ በፊቱ ይደሰት ነበር።’ ኢየሱስ ደስተኛ የነበረው ለምንድን ነው?— ደስተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱን ሲገልጽ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም መሥራቴን እቀጥላለሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 5:17

ኢየሱስ በምድር ሳለ አናጺ ሆኖ የሠራው ዕድሜውን ሙሉ አልነበረም። ይሖዋ አምላክ በምድር ላይ እንዲሠራው የሰጠው ሌላ ልዩ ሥራ ነበር። ይህ ሥራ ምን እንደነበረ ታውቃለህ?— ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) እዚህ ላይ የምታያት ሳምራዊት ሴት እንዳደረገችው አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ ለሰዎች በሚሰብክበት ጊዜ ሰዎቹ ያምኑት የነበረ ከመሆኑም በላይ የተናገረውን ነገር ለሌሎች ይናገሩ ነበር።—ዮሐንስ 4:7-15, 27-30

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የሠራቸው ሁለት ዓይነት ሥራዎች ምንድን ናቸው?

ኢየሱስ ይህን ሥራ በመሥራቱ ምን ተሰምቶት ነበር? ሥራውን የሠራው በፍላጎት ነው?— ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን  መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) በጣም የምትወደውን ምግብ መብላት ምን ያህል ያስደስትሃል?— ኢየሱስ፣ አምላክ እንዲሠራው የሰጠውን ሥራ ምን ያህል ይወደው እንደነበረ ከዚህ መረዳት ትችላለህ።

አምላክ የፈጠረን ሥራን በመሥራት እንድንደሰት አድርጎ ነው። ሰው ‘በሥራው መደሰት’ መቻሉ የአምላክ ስጦታ ነው። ስለዚህ ከልጅነትህ ጀምሮ ሥራ መሥራት ከለመድክ መላው ሕይወትህ በጣም አስደሳች ይሆንልሃል።—መክብብ 5:19

ይህ ሲባል አንድ ትንሽ ልጅ የትልቅ ሰው ሥራ መሥራት ይችላል ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሁላችንም የሆነ ዓይነት ሥራ መሥራት እንችላለን። ወላጆችህ፣ ቤተሰባችሁ የሚበላው ምግብና የሚኖርበት ቤት እንዲኖረው የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ዘወትር ወደ ሥራ ይሄዱ ይሆናል። ደግሞም እንደምታውቀው በቤት ውስጥ ዕቃዎቹ ሳይዝረከረኩ በሥርዓት እንዲቀመጡ ለማድረግና ለማጽዳት መሠራት ያለበት ብዙ ነገር አለ።

መላውን ቤተሰብ የሚጠቅም አንተ ልትሠራው የምትችል ምን ሥራ አለ?— ምግብ የሚበላበት ሰዓት ሲደርስ ዕቃ ልታቀራርብ፣ ዕቃዎቹን ልታጣጥብ፣ ቆሻሻ ልትደፋ፣ የምትተኛበትን ክፍል ልታጸዳና አሻንጉሊቶችህን ከወዳደቁበት ልታነሳ ትችላለህ። ምናልባትም ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዳንዶቹን እየሠራህ ይሆናል። የምትሠራው ሥራ ለቤተሰቡ ጥቅም እንደሚያስገኝ የተረጋገጠ ነው።

ከተጫወትክ በኋላ መጫወቻዎችህን ሰብስበህ ማስቀመጥህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ጠቃሚ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ስትጫወት ከቆየህ በኋላ መጫወቻዎችህን ሰብስበህ ማስቀመጥ ይኖርብሃል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምን ይመስልሃል?— እንዲህ ማድረግ ቤቱ እንዳይዝረከረክ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ከአደጋም ይጠብቃል። መጫወቻዎችህን ካላነሳሳሃቸው አንድ ቀን እናትህ በእጆቿ የሆነ ነገር ተሸክማ ስትመጣ ልትረግጣቸው ትችላለች። ከዚያም ተደናቅፋ ልትወድቅና ጉዳት ሊደርስባት ይችላል። አልፎ ተርፎም ሆስፒታል መሄድ ሊያስፈልጋት ይችላል። ታዲያ ይህ መጥፎ ነገር አይደለም?— ስለዚህ ከተጫወትክ በኋላ መጫወቻዎችህን አንስተህ በቦታቸው ማስቀመጥህ ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ነው።

ልጆች የሚሠሩት ሌላም ሥራ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ በትምህርት ቤት  የሚሰጥህን ሥራ እንውሰድ። በትምህርት ቤት እንዴት ማንበብ እንደምትችል ትማራለህ። አንዳንድ ልጆች ማንበብ የሚወዱ ሲሆን ሌሎች ልጆች ግን ከባድ ነው ይላሉ። መጀመሪያ ላይ ከባድ ቢሆንብህም እንኳ በደንብ አድርገህ ማንበብ ከቻልክ ትደሰታለህ። ማንበብ ስትችል ደግሞ ልትማራቸው የምትችላቸው ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉ። የአምላክ መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስንም እንኳን ሳይቀር ራስህ ማንበብ ትችላለህ። ስለዚህ በትምህርት ቤት የሚሰጥህን ሥራ በጥሩ ሁኔታ መሥራትህ ጠቃሚ ነው፣ አይደል?—

አንዳንድ ሰዎች ሥራ መሥራት አይወዱም። ምናልባት አንተም ሥራ የማይወድ ሰው ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ ሥራ እንድንሠራ አድርጎ ስለፈጠረን ሥራ በመሥራት መደሰትን መልመድ ያስፈልገናል። ታላቁ አስተማሪ በሥራው ምን ያህል ይደሰት ነበር?— ሥራው ለእሱ የሚወደውን ምግብ እንደ መብላት ያህል ነበር። ኢየሱስ የተናገረው ስለ የትኛው ሥራ ነው?— ኢየሱስ የጠቀሰው ሥራ ለሌሎች ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚችሉበት መንገድ መናገር ነው።

እንግዲያው የሚከተለው ሐሳብ በሥራ መደሰት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። ‘ይህ ሥራ መሠራት ያለበት ለምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። አንድ ነገር መሠራት ያለበት ለምን እንደሆነ ከገባህ ሥራውን ለመሥራት ትነሳሳለህ። ከዚህም በላይ ሥራው ከባድም ይሁን ቀላል በደንብ ሥራው። እንዲህ ካደረግክ ልክ እንደ ታላቁ አስተማሪያችን አንተም በምትሠራው ሥራ ልትደሰት ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው ጥሩ ሠራተኛ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል። ምሳሌ 10:4፤ 22:29፤ መክብብ 3:12, 13 እና ቆላስይስ 3:23 ላይ ምን እንደሚል ተመልከቱ።