በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 28

ማንን መታዘዝ እንዳለብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ማንን መታዘዝ እንዳለብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

አንዳንድ ጊዜ ማንን መታዘዝ እንዳለብን ማወቅ አስቸጋሪ ነው። እናትህ ወይም አባትህ አንድ ነገር እንድታደርግ ይነግሩህ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ግን አንድ አስተማሪ ወይም ፖሊስ ወላጆችህ ከነገሩህ ነገር ተቃራኒ የሆነ ነገር እንድታደርግ ይነግርህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ነገር ቢያጋጥምህ የምትታዘዘው ማንን ነው?—

ቀደም ሲል በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ላይ ኤፌሶን 6:1-3ን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብበን ነበር። ይህ ጥቅስ ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ እንዳለባቸው የሚናገር ሲሆን “ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል። ልጆች “ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ” ለወላጆቻቸው መታዘዝ አለባቸው ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— ወላጆቻቸው የአምላክን ሕጎች እንዲታዘዙ ሲያስተምሯቸው መታዘዝ አለባቸው ማለት ነው።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች በይሖዋ አያምኑም። ስለዚህ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ በትምህርት ቤት ፈተና ወቅት ብታጭበረብር ወይም ደግሞ ገንዘብ ሳትከፍል ከሱቅ አንድ ነገር ብትወስድ ምንም ችግር የለውም ቢልህ ምን ታደርጋለህ? አንድ ልጅ ቢያጭበረብር ወይም ቢሰርቅ ተገቢ ነው ማለት ነው?—

በአንድ ወቅት ንጉሥ ናቡከደነፆር ሁሉም ሰው እሱ ለሠራው የወርቅ ምስል እንዲሰግድ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደነበር አስታውስ። ሆኖም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለምስሉ አልሰገዱም። ያልሰገዱት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ማምለክ ያለባቸው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ ስለሚናገር ነው።—ዘፀአት 20:3፤ ማቴዎስ 4:10

ጴጥሮስ ለቀያፋ ምን እያለው ነው?

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሐዋርያቱ የአይሁዳውያን ዋነኛ ሃይማኖታዊ ፍርድ  ቤት በሆነው በሳንሄድሪን ፊት ቀርበው ነበር። ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ “[በኢየሱስ] ስም ማስተማራችሁን እንድታቆሙ በጥብቅ አዝዘናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል” አላቸው። ሐዋርያቱ ሳንሄድሪንን ያልታዘዙት ለምንድን ነው?— ጴጥሮስ ሐዋርያቱን በሙሉ ወክሎ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት ለቀያፋ መልስ ሰጠ።—የሐዋርያት ሥራ 5:27-29

በዚያን ጊዜ የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። ይሁን እንጂ አገራቸውን ይገዛ የነበረው የሮማ መንግሥት ነበር። የሮማ መንግሥት ገዥ ደግሞ ቄሳር ነበር። አይሁዳውያን ቄሳር እንዲገዛቸው ባይፈልጉም እንኳ የሮማ መንግሥት ለሕዝቡ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ያደርግላቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ መንግሥታትም ለሕዝቦቻቸው ብዙ ጥሩ ነገሮች ያደርጋሉ። ከእነዚህ ጥሩ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ልትጠቅስ ትችላለህ?—

መንግሥታት ለጉዞ ምቹ የሆኑ መንገዶች ይሠራሉ፤ እንዲሁም ፖሊሶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከአደጋ እንዲጠብቁን ደሞዝ ይከፍሏቸዋል። በተጨማሪም ልጆች እንዲማሩ፣ አረጋውያን ደግሞ የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ያሟላሉ። አንድ መንግሥት እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ገንዘብ ያስፈልገዋል። መንግሥት ገንዘቡን የሚያገኘው ከየት እንደሆነ  ታውቃለህ?— ከሕዝቡ ነው። ሕዝቡ ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ግብር ይባላል።

ታላቁ አስተማሪ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ አይሁዳውያን ለሮማ መንግሥት ግብር መክፈል አይፈልጉም ነበር። ስለዚህ አንድ ቀን ካህናት ኢየሱስን ችግር ውስጥ ለማስገባት ብለው አንድ ጥያቄ እንዲጠይቁት ሰዎችን ቀጥረው ላኩበት። ጥያቄው “ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል?” የሚል ነበር። ይህ ጥያቄ ተንኮል ያዘለ ነበር። ኢየሱስ ‘አዎ፣ ግብር መክፈል አለባችሁ’ ብሎ መልስ ቢሰጥ ብዙዎቹ አይሁዳውያን ደስ አይላቸውም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘ግብር መክፈል አያስፈልጋችሁም’ ሊል አይችልም። እንዲህ ብሎ መናገር ስህተት ነው።

ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ‘እስቲ አንድ ሳንቲም አሳዩኝ’ አላቸው። ሳንቲሙን ሲያመጡለት ‘በላዩ ላይ ያለው ምስልና የተጻፈው ስም የማን ነው?’ ብሎ ጠየቃቸው። ሰዎቹም “የቄሳር” ብለው መልስ ሰጡ። ስለዚህ ኢየሱስ “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” አላቸው።—ሉቃስ 20:19-26

ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡለትን ተንኮል ያዘለ ጥያቄ የመለሰው እንዴት ነበር?

በዚህ መልስ ላይ ማንም ስህተት ሊያገኝ አይችልም። ቄሳር ለሕዝቡ ጠቃሚ ነገሮች የሚያደርግ ከሆነ ቄሳር ላደረገው ነገር ራሱ የሠራውን ገንዘብ  መልሶ መክፈል ተገቢ ነው። ስለዚህ በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለምናገኛቸው ነገሮች ለመንግሥት ግብር መክፈል ተገቢ እንደሆነ ገልጿል።

አሁን ግብር ለመክፈል ዕድሜህ ገና አልደረሰም። ነገር ግን ለመንግሥት ልታደርገው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ለመንግሥት ሕጎች ታዛዥ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለበላይ ባለሥልጣናት ታዘዙ’ በማለት ይናገራል። እነዚህ ባለሥልጣናት በአንድ አገር መንግሥት ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የመንግሥትን ሕጎች መታዘዝ እንዳለብን የተናገረው አምላክ ራሱ ነው።—ሮም 13:1, 2

በመንገድ ላይ ወረቀት ወይም ሌላ ነገር መጣል የሚከለክል ሕግ ሊኖር ይችላል። ታዲያ ይህን ሕግ መታዘዝ ይኖርብሃል?— አዎ፣ አምላክ እንድትታዘዝ ይፈልጋል። ለፖሊሶችስ ታዛዥ መሆን ይኖርብሃል?— ፖሊሶች ሕዝብን እንዲጠብቁ መንግሥት ደሞዝ ይከፍላቸዋል። ስለዚህ ፖሊሶችን መታዘዝ መንግሥትን መታዘዝ ማለት ነው።

ስለዚህ መንገድ ልታቋርጥ ስትል አንድ ፖሊስ “ቆይ!” ቢልህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?— ሌሎች የፖሊሱን ትእዛዝ ጥሰው ሲሻገሩ ብታይ መሻገር ይኖርብሃል?— የፖሊሱን ትእዛዝ ተቀብለህ የቆምከው አንተ ብቻ ብትሆንም እንኳን ፖሊሱ እንድታልፍ እስኪፈቅድልህ ድረስ መቆየት ይኖርብሃል። እንድትታዘዝ የሚነግርህ አምላክ ነው።

በሰፈር ውስጥ ችግር ቢኖርና ፖሊስ “ወደ መንገድ አትውጡ። ቤታችሁ ቆዩ” ቢልስ ምን ታደርጋለህ? የሰዎች ጩኸት ብትሰማና ምን እንደሆነ ለማየት ብትፈልግስ? ለማየት ወደ ውጪ መውጣት ይኖርብሃል?— ብትወጣ ‘ለበላይ ባለ ሥልጣናት’ ተገዝተሃል ሊባል ይችላል?—

በብዙ ቦታዎች መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ይሠራል፤ እንዲሁም ለአስተማሪዎች ደሞዝ ይከፍላቸዋል። ታዲያ አምላክ ለአስተማሪ እንድትታዘዝ የሚፈልግብህ ይመስልሃል?— እስቲ ጉዳዩን ትንሽ አስብበት። መንግሥት፣ ሕዝቡን እንዲጠብቅ ለፖሊስ ደሞዝ እንደሚከፍል ሁሉ አስተማሪውም እንዲያስተምር ደሞዝ ይከፍለዋል። ስለዚህ ለፖሊስ ወይም ለአስተማሪ ታዛዥ መሆን ለመንግሥት ከመታዘዝ ጋር አንድ ነው።

ለፖሊስ መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

 ይሁን እንጂ አንድ አስተማሪ ለምስል እንድትሰግድ ቢነግርህስ? በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ?— ሦስቱ ዕብራውያን ለምስሉ እንዲሰግዱ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሲነግራቸው አልሰገዱም። ያልሰገዱት ለምን እንደሆነ ታስታውሳለህ?— የአምላክን ትእዛዝ መጣስ ስላልፈለጉ ነበር።

ዊል ዱራንት የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሲጽፉ ክርስቲያኖች ‘ከፍተኛ ታማኝነት የሚያሳዩት ለቄሳር እንዳልነበረ’ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ ከፍተኛ ታማኝነት የሚያሳዩት ለይሖዋ ነበር! ስለዚህ በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ መያዝ ያለበት አምላክ መሆን እንደሚኖርበት አስታውስ።

ለመንግሥታትም እንድንታዘዝ የሚፈልገው አምላክ ስለሆነ እንታዘዛቸዋለን። ይሁን እንጂ አምላክ አታድርጉ የሚለንን ነገር አድርጉ ቢሉን ምን መልስ መስጠት አለብን?— ሐዋርያት ለሊቀ ካህናቱ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” ብለው የሰጡትን መልስ መመለስ ይኖርብናል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

ሕግ መከበር እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ማቴዎስ 5:41፤ ቲቶ 3:1 እና 1 ጴጥሮስ 2:12-14 ላይ የተጻፈውን አንብቡ።