በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 31

መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?

የሐዘንና የብቸኝነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል?— እኔን የሚወደኝ ሰው የለም የሚል ስሜትስ አድሮብህ ያውቃል?— አንዳንድ ልጆች እንዲህ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ ‘እኔ አልረሳህም’ በማለት ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 49:15) አምላክ እንደማይረሳን ማወቁ በጣም የሚያስደስት አይደለም?— አዎ፣ በእርግጥም ይሖዋ አምላክ ይወደናል!

ይህች የጠፋች ትንሽ በግ ምን የሚሰማት ይመስልሃል?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 27:10) ይህን ማወቃችን በእርግጥም ሊያጽናናን ይችላል፣ አይደል?— አዎ፣ ይሖዋ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . እረዳሃለሁ” ብሎናል።—ኢሳይያስ 41:10

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ፣ ሰይጣን መከራ እንዲያመጣብን ሊፈቅድ ይችላል። አልፎ ተርፎም ይሖዋ አገልጋዮቹን ሰይጣን እንዲፈትናቸው ይፈቅዳል። በአንድ ወቅት ዲያብሎስ ኢየሱስን በጣም ስላሠቃየው ኢየሱስ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውከኝ?” በማለት ወደ ይሖዋ ጮዃል። (ማቴዎስ 27:46) ኢየሱስ ሥቃይ እየደረሰበት ባለበት ወቅትም እንኳን ይሖዋ እንደሚወደው ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 10:17) ይሁን እንጂ ኢየሱስ አምላክ አገልጋዮቹን ሰይጣን እንዲፈትናቸውና እንዲያሠቃያቸው እንደሚፈቅድለትም ያውቅ ነበር። ሰይጣን ይህን እንዲያደርግ አምላክ የሚፈቅድለት ለምን እንደሆነ በሌላ ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

አንዳንድ ጊዜ ትንንሽ ልጆች ፍርሃት ያጠቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከወላጆችህ ጋር ተጠፋፍተህ ታውቃለህ?— በዚያን ጊዜ ደንግጠህ ነበር?— ብዙ ልጆች ይደነግጣሉ። ታላቁ አስተማሪም አንድ ጊዜ ስለ መጥፋት ተናግሮ ነበር። ነገር ግን እሱ የተናገረው ስለ ጠፋ ልጅ ሳይሆን ስለ ጠፋ በግ ነበር።

 በአንዳንድ መንገዶች ሲታይ አንተም እንደ በግ ነህ። እንዲህ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? በጎች በጣም ትልልቅ ወይም ጠንካራ እንስሳት አይደሉም። የሚንከባከባቸውና የሚጠብቃቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። በጎችን የሚንከባከብ ሰው እረኛ ይባላል።

ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ መቶ በጎች ያሉትን አንድ እረኛ የጠቀሰ ሲሆን ከበጎቹ መካከል አንዷ ጠፍታ ነበር። ይህች በግ ከተራራው ማዶ ያለውን ለማየት ፈልጋ ሄዳ ይሆናል። ነገር ግን ሳታስበው ከሌሎቹ በጎች ርቃ ሄደች። በጓ ዙሪያዋን ተመልክታ ብቻዋን እንደቀረች ስታውቅ ምን እንደሚሰማት መገመት ትችላለህ?—

እረኛው በጉ እንደጠፋች ሲገነዘብ ምን ያደርግ ይሆን? የጠፋችው በራሷ ጥፋት ስለሆነ የራሷ ጉዳይ ነው ይል ይሆን? ወይስ 99ኙን ደህና ቦታ ትቶ የጠፋችውን በግ ፍለጋ ይሄዳል? ለአንዲት በግ ይህን ያህል ሊለፋላት ይገባል?— የጠፋችው በግ አንተ ብትሆን ኖሮ እረኛው እንዲፈልግህ ትመኝ ነበር?—

የጠፋችውን በግ ፈልጎ ካገኛት እረኛ ጋር የሚመሳሰለው ማን ነው?

እረኛው የጠፋችውን በግ ጨምሮ ሁሉንም በጎች በጣም ይወዳቸዋል። ስለዚህ የጠፋችውን በግ ፍለጋ ሄደ። ይህች በግ እረኛዋ ወደ እሷ ሲመጣ ስታየው ምን ያህል እንደምትደሰት አስብ! እረኛው  የጠፋችበትን በግ ስላገኛት እንደተደሰተ ኢየሱስ ተናግሯል። ካልጠፉት 99 በጎች ይልቅ ጠፍታ በተገኘችው አንዲት በግ ይበልጥ ተደስቷል። ታዲያ ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ እንደተጠቀሰው እረኛ የሆነው ማን ነው? እረኛው ለበጓ እንዳደረገላት ሁሉ ለእኛም በጣም የሚያስብልን ማን ነው?— ለእኛ በጣም የሚያስብልን በሰማይ ያለው አባቱ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። የኢየሱስ አባት ደግሞ ይሖዋ ነው።

ይሖዋ አምላክ የሕዝቦቹ ታላቅ እረኛ ነው። እንደ አንተ ያሉትን ትንንሽ ልጆች ጨምሮ እሱን የሚያገለግሉትን ሁሉ ይወዳቸዋል። ማንኛችንም ብንሆን እንድንጎዳ ወይም እንድንጠፋ አይፈልግም። አምላክ ይህን ያህል እንደሚያስብልን ማወቅ በእርግጥም የሚያጽናና ነው!—ማቴዎስ 18:12-14

አባትህ ወይም አንድ ሌላ ሰው ለአንተ እውን የሆኑትን ያህል ይሖዋ ለአንተ እውን ነው?

ይሖዋ አምላክ እንዳለ በእርግጥ ታምናለህ?— እሱ ልክ እንደ አባትህ ወይም እንደ አንድ ሌላ ሰው ለአንተ እውን አካል ነው?— ይሖዋን ልናየው እንደማንችል የተረጋገጠ ነው። ልናየው የማንችለው እሱ መንፈስ ስለሆነ ነው። መንፈስ ደግሞ በሰው ዓይን ሊታይ አይችልም። ይሁን እንጂ እሱ እውን አካል ከመሆኑም  በላይ እኛን ሊያየን ይችላል። እርዳታ የሚያስፈልገን መቼ እንደሆነ ያውቃል። እኛም በምድር ላይ ከሚኖር አንድ ሰው ጋር እንደምንነጋገር ሁሉ አምላክንም በጸሎት ልናነጋግረው እንችላለን። ይሖዋ በጸሎት እንድናነጋግረው ይፈልጋል።

ስለዚህ ሐዘንና ብቸኝነት ቢሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?— ይሖዋን አነጋግረው። ወደ እሱ ቅረብ፤ እሱም ያጽናናሃል፤ እንዲሁም ይረዳሃል። ብቸኛ እንደሆንክ በሚሰማህ ጊዜም እንኳ ሳይቀር ይሖዋ እንደሚወድህ አስታውስ። አሁን እስቲ መጽሐፍ ቅዱሳችንን እናውጣ። መዝሙር 23 ላይ ከቁጥር 1 ጀምሮ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል።”

ጸሐፊው ቀጥሎ ቁጥር 4 ላይ የተናገረውንም ልብ በል:- “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል።” ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። ችግር ሲደርስባቸው ይጽናናሉ። አንተም እንደዚህ ይሰማሃል?—

አንድ አፍቃሪ እረኛ በጎቹን እንደሚንከባከብ ሁሉ ይሖዋም ሕዝቡን በጥሩ ሁኔታ ይንከባከባል። የሚሄዱበትን ትክክለኛ መንገድ የሚያሳያቸው ሲሆን እነሱም በደስታ ይከተሉታል። ብዙ ችግሮች በሚያጋጥሟቸው ጊዜም እንኳ የሚፈሩበት ምክንያት የለም። አንድ እረኛ በጎቹን ሊጎዷቸው ከሚችሉ  እንስሳት ለመጠበቅ በበትሩ ወይም በምርኩዙ ይጠቀማል። ወጣቱ እረኛ ዳዊት በጎቹን ከአንበሳና ከድብ እንዴት እንደጠበቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ሳሙኤል 17:34-36) የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋ እነሱንም እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉ። አምላክ ከእነሱ ጋር ስለሆነ ደህንነት ይሰማቸዋል።

አንድ እረኛ በጎቹን እንደሚጠብቅ ሁሉ እኛም ችግር ላይ ስንወድቅ ማን ሊረዳን ይችላል?

ይሖዋ በእርግጥም በጎቹን ይወዳል፤ ደግሞም በርኅራኄ ይንከባከባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በጎቹን እንደ እረኛ ይመራል፤ ትንንሾቹን በጎች በክንዱ ይሰበስባል’ በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 40:11

ይሖዋ እንደዚህ ዓይነት አምላክ መሆኑን ማወቅህ ደስ አያሰኝህም?— ከይሖዋ በጎች አንዱ መሆን ትፈልጋለህ?— በጎች የእረኛቸውን ድምፅ ይሰማሉ። ወደ እረኛቸው ይጠጋሉ። አንተም ይሖዋን ትሰማለህ?— ወደ እሱ ተጠግተህ ትኖራለህ?— እንዲህ ከሆነ የምትፈራበት ምክንያት አይኖርም። ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሆናል።

ይሖዋ የሚያገለግሉትን ሰዎች በፍቅር ይንከባከባል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር 37:25 እና ሉቃስ 12:29-31 ላይ ምን እንደሚል እንመልከት።