በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 ምዕራፍ 19

መጣላት ተገቢ ነው?

መጣላት ተገቢ ነው?

ትልቅ ሰው መስለው መታየትና ጉልበተኛ መሆን የሚፈልጉ ልጆች አይተህ ታውቃለህ?— ከእነሱ ጋር መሆን ትፈልጋለህ? ወይስ ደግና ሰላም ፈላጊ ከሆነ ልጅ ጋር መሆን ትመርጣለህ?— ታላቁ አስተማሪ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ‘የአምላክ ልጆች ይባላሉና’” ብሏል።—ማቴዎስ 5:9

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚያናድድ ነገር ሊያደርጉብን ይችላሉ። ይህ እውነት አይደለም?— ስለዚህ እነሱን ለመበቀል እንነሳሳ ይሆናል። በአንድ ወቅት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ሳሉ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሟቸው ነበር። እስቲ ያጋጠማቸውን ነገር ልንገርህ።

የተወሰነ መንገድ ከተጓዙ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጥቂቶቹን በአቅራቢያው ወዳለ የሳምራውያን መንደር ሄደው የሚያርፉበት ቦታ እንዲፈልጉ ላካቸው። ይሁን እንጂ በዚያ የሚኖሩት ሳምራውያን  የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ስለነበሩ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በመንደራቸው እንዲያርፉ አልፈለጉም ነበር። እንዲያውም ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድ ሰው አይወዱም ነበር።

ያዕቆብና ዮሐንስ ሳምራውያንን ለመበቀል ምን ሊያደርጉ ፈልገው ነበር?

ይህ በአንተ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ትናደድ ነበር? እነሱን ለመበቀል ትነሳሳ ነበር?— የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የነበሩት ያዕቆብና ዮሐንስ መበቀል ፈልገው ነበር። ኢየሱስን “እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈልጋለህ?” አሉት። ኢየሱስ እነሱን “የነጎድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራቸው ለዚህ ነው! ኢየሱስ ግን በሰዎች ላይ እንዲህ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ነገራቸው።—ሉቃስ 9:51-56፤ ማርቆስ 3:17

እርግጥ፣ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሊሆኑብን ይችላሉ። ሌሎች ልጆች አብረናቸው እንድንጫወት ላይፈልጉ ይችላሉ። እንዲያውም “ከእኛ ጋር እንድትሆን አንፈልግም” ይሉ ይሆናል። እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ሊያበሳጨን ይችላል፣ አይደል? በዚህ ጊዜ እነሱን ለመበቀል ልንነሳሳ እንችላለን። ታዲያ መበቀል ይኖርብናል?—

እስቲ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጣና ምሳሌ ምዕራፍ 24 ቁጥር 29ን እናንብብ። “‘በእኔ ላይ እንደሠራብኝ እሠራለታለሁ፤ ስለ አድራጎቱም የጁን እመልስለታለሁ’ አትበል” ይላል።

ይህ ጥቅስ ምን ያስተምረናል?— ሌሎችን ለመበቀል መሞከር እንደሌለብን ያስተምረናል። አንድ ሰው ክፉ ስለሆነብን ብቻ እኛም ክፉ ልንሆንበት አይገባም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከአንተ ጋር መጣላት ቢፈልግስ? እየተሳደበ ሊያናድድህ ይሞክር ይሆናል። ሊስቅብህና እንደፈራኸው ሊናገር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ፈሪ’ ይልህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ከእሱ ጋር መጣላት ይኖርብሃል?—

አሁንም እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት። ማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 39ን አውጣ። እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ክፉ ለሚያደርግባችሁ ሰው አጸፋ አትመልሱ፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።” ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ  ይመስልሃል? አንድ ሰው ቀኝ ጉንጭህን በቡጢ ሲመታህ ሌላውን ጉንጭህንም እንዲመታህ ፍቀድለት ማለቱ ነው?—

በፍጹም፤ ኢየሱስ ይህን ማለቱ አልነበረም። ጥፊ በቡጢ ከመማታት ጋር አንድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ መግፋት የሚቆጠር ድርጊት ነው። አንድ ሰው ሊጣላን ሲፈልግ በጥፊ ሊመታን ይችላል። ሊያናድደን ፈልጓል ማለት ነው። እኛ ደግሞ ተናደን መልሰን ብንገፋው ወይም ብንገፈትረው ምን ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል?— ምናልባት መደባደብ ልንጀምር እንችላለን።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጣሉ አይፈልግም። ስለዚህ አንድ ሰው በጥፊ ቢመታን እኛም መልሰን በጥፊ መምታት እንደሌለብን ተናግሯል። ተናደን ድብድብ ውስጥ መግባት የለብንም። እንዲህ ካደረግን፣ ነገር ከፈለገን ሰው አልተሻልንም ማለት ነው።

አንድ ሰው ነገር ሲፈልግህ ምን ብታደርግ የተሻለ ይመስልሃል?— የሚሻለው  ነገር ትቶ መሄድ ነው። ልጁ ደጋግሞ ይገፈትርህ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ግን ሊተውህ ይችላል። ትተህ መሄድህ ደካማ ነህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትክክል ለሆነው ነገር ጠንካራ አቋም እንዳለህ ያሳያል።

አንድ ሰው ሊጣላን ቢፈልግ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ሆኖም መጣላት ጀምረህ ብታሸንፍስ? ከዚያ በኋላ ምን ሊፈጠር ይችላል?— የመታኸው ልጅ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ይመጣብህ ይሆናል። በዱላ መትተው ወይም በጩቤ ወግተው ጉዳት ሊያደርሱብህ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ መጣላት እንደሌለብን የተናገረው ለምን እንደሆነ አሁን ገባህ?—

ሌሎች ሰዎች ሲጣሉ ብናይ ምን ማድረግ ይኖርብናል? አንዱን ወይም ሌላኛውን ማገዝ ይኖርብናል?— መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል የሆነውን ነገር ይነግረናል። ምሳሌ ምዕራፍ 26 ቁጥር 17ን አውጣ። “በሌሎች ጠብ ጥልቅ የሚል መንገደኛ፣ የውሻ ጆሮ እንደሚይዝ ሰው ነው” ይላል።

ሌሎች ሰዎች ሲጣሉ ጣልቃ መግባት የውሻን ጆሮ እንደመያዝ የሚቆጠረው እንዴት ነው?

የአንድን ውሻ ጆሮ ብትይዝ ውሻው ምን ያደርጋል? ስለሚያመው ይጮኽብሃል፣ አይደል? ውሻው ከእጅህ ለማምለጥ በሞከረ መጠን አንተም አጥብቀህ ስለምትይዘው ይበልጥ እየተናደደ ይሄዳል። ብትለቀው ደግሞ በኃይል ሊነክስህ ይችላል። ታዲያ ይህ እንዳይሆን የውሻውን ጆሮ እንደያዝክ ባለህበት ቦታ ቆመህ ትቀራለህ?—

ሌሎች ሰዎች ሲጣሉ ጣልቃ የምንገባ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ችግር ሊደርስብን ይችላል። ድብድቡን የጀመረው ማን እንደሆነ ወይም ለምን እንደተጣሉ ላናውቅ እንችላለን። አንዱ እየተመታ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እየመታው ካለው ሰው ላይ አንድ ነገር ሰርቆ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እየተደበደበ ያለውን ሰው የምናግዝ ከሆነ ለሌባ እያገዝን ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም፤ አይመስልህም?

 ስለዚህ ሰዎች ሲጣሉ ብታይ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?— ድብድቡ የተጀመረው በትምህርት ቤት ከሆነ ሮጠህ በመሄድ ለአስተማሪ ልትናገር ትችላለህ። ከትምህርት ቤት ውጪ ከሆነ ደግሞ ወላጅህን ወይም ፖሊስ ልትጠራ ትችላለህ። አዎ፣ ሰዎች ከእኛ ጋር መጣላት በሚፈልጉበት ጊዜም እንኳ ሰላማዊ መሆን ይኖርብናል።

ሰዎች ሲጣሉ ብታይ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሰዎች ጋር ላለመጣላት የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ትክክል ለሆነ ነገር ጠንካራ አቋም እንዳለን እናሳያለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ‘ሊጣላ አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር ሊሆን ይገባዋል’ በማለት ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24

ከሰዎች ጋር ከመጣላት እንድንቆጠብ የሚረዳ ተጨማሪ ምክር ለማግኘት ሮም 12:17-21 እና 1 ጴጥሮስ 3:10, 11ን እናንብብ።