በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 22

መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?

መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?

አንዲት ልጅ ለእናቷ “ከትምህርት ቤት እንደተለቀቅኩ ወዲያው እመጣለሁ” ብላ ተናገረች እንበል። ሆኖም ከትምህርት ቤት ስትለቀቅ ከጓደኞቿ ጋር እዚያው ስትጫወት ቆይታ ለእናቷ “ከትምህርት ቤት ከተለቀቅኩ በኋላ አስተማሪዬ እንድቆይ አደረገችኝ” ብላ ብትናገር ተገቢ ይሆናል?—

ይህ ልጅ የሠራው ጥፋት ምንድን ነው?

አንድ ልጅ ደግሞ ለአባቱ “ቤት ውስጥ ኳስ አልተጫወትኩም” ብሎ ተናገረ እንበል። ነገር ግን ልጁ ኳስ ተጫውቶ ከነበረስ? ኳስ አልተጫወትኩም ብሎ መናገሩ ትክክል ነው?—

ታላቁ አስተማሪ ማድረግ የሚገባንን ትክክለኛ ነገር ገልጾልናል። እንዲህ ብሏል:- “ቃላችሁ አዎ ከሆነ አዎ ይሁን፣ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው ነው።” (ማቴዎስ 5:37) ኢየሱስ ይህን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?— የምንናገረውን ነገር ማድረግ እንዳለብን መግለጹ ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነቱን መናገር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ታሪክ አለ። ታሪኩ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ነን ይሉ የነበሩ ሁለት ሰዎችን የሚመለከት ነው። እስቲ የሆነውን ነገር እንመልከት።

 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሁለት ወር ሊሞላው ሲል ብዙ ሰዎች ጴንጤቆስጤ የሚባለውን የአይሁዳውያን ታላቅ በዓል ለማክበር ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሰዎቹ ይሖዋ ከሞት ስላስነሳው ስለ ኢየሱስ የሚገልጽ ጥሩ ንግግር አቀረበ። በዚህ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ስለ ኢየሱስ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ መስማታቸው ነበር። በመሆኑም ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ፈልገው ነበር። ታዲያ ምን አደረጉ?

ካሰቡት በላይ በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ቆዩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የያዙትን ገንዘብ በሙሉ ስለጨረሱ ምግብ መግዛት እንዲችሉ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት እነዚህን እንግዶች ለመርዳት ፈለጉ። ስለዚህ ብዙዎቹ ያላቸውን ነገር እየሸጡ ገንዘቡን ወደ ኢየሱስ ሐዋርያት ያመጡ ነበር። ከዚያም ሐዋርያት ገንዘቡን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይሰጡ ነበር።

በኢየሩሳሌም የሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑት ሐናንያና ሚስቱ ሰጲራ መሬታቸውን ሸጡ። እነዚህን ሰዎች መሬቱን ሽጡ ብሎ ያዘዛቸው ሰው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መሬቱን የሸጡት በራሳቸው ውሳኔ ነበር። ነገር ግን ይህን ያደረጉት አዲሶቹን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለወደዷቸው አልነበረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሐናንያና  ሰጲራ ይህን ያደረጉት ከሌሎች የተሻሉ ሰዎች መስለው ለመታየት ስለፈለጉ ነበር። ስለዚህ ሌሎችን ለመርዳት ብለው ገንዘቡን በሙሉ እንደሰጡ አድርገው ለመናገር ወሰኑ። የሚሰጡት የተወሰነውን ገንዘብ ብቻ ቢሆንም ሁሉንም እንደሰጡ አድርገው ለመናገር ተስማሙ። እንዲህ ማድረጋቸው ትክክል ይመስልሃል?—

ሐናንያ ወደ ሐዋርያት መጣና ገንዘቡን ሰጣቸው። ይሁን እንጂ ሐናንያ ገንዘቡን በሙሉ እንዳልሰጠ አምላክ ያውቅ ነበር። ስለዚህ አምላክ ሐናንያ የተናገረው እውነቱን እንዳልሆነ ለሐዋርያው ጴጥሮስ አሳወቀው።

ሐናንያ ለጴጥሮስ ምን ውሸት እየነገረው ነው?

ስለዚህ ጴጥሮስ ሐናንያን እንዲህ አለው:- ‘ሐናንያ፣ ሰይጣን ይህን እንድታደርግ እንዲገፋፋህ የፈቀድከው ለምንድን ነው? መሬቱ ያንተው ነበር። የመሸጥ ግዴታ አልነበረብህም። ከሸጥከውም በኋላ ቢሆን በገንዘቡ ምን ብታደርግ እንደሚሻል ራስህ መወሰን ትችል ነበር። የሰጠኸው የተወሰነውን ገንዘብ ብቻ ሆኖ ሳለ ሁሉንም እንደሰጠህ አድርገህ ለማስመሰል የሞከርከው ለምንድን ነው? ይህን በማድረግህ የዋሸኸው እኛን ብቻ ሳይሆን አምላክን ጭምር ነው።’

የፈጸመው ድርጊት በጣም ከባድ ነበር። ሐናንያ እየዋሸ ነበር! ያላደረገውን ነገር እንዳደረገ አድርጎ ተናገረ። እያስመሰለ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሆነውን ነገር ሲናገር ‘ሐናንያ፣ ጴጥሮስ የተናገረውን ሲሰማ ወደቀና ሞተ’ ይላል። ሐናንያን እንዲሞት ያደረገው አምላክ ነው! ከዚያ በኋላ ሬሳውን ወደ ውጪ አውጥተው ቀበሩት።

ሐናንያ በመዋሸቱ ምን ሆነ?

 ከሦስት ሰዓት ገደማ በኋላ ሰጲራ መጣች። ባሏ የደረሰበትን ነገር አላወቀችም። ስለዚህ ጴጥሮስ ‘መሬቱን የሸጣችሁት በዚህ በሰጣችሁን ገንዘብ ብቻ ነው?’ ብሎ ጠየቃት።

ሰጲራም ‘አዎ፣ መሬቱን የሸጥነው በዚህ ገንዘብ ብቻ ነው’ ብላ መለሰች። ሆኖም ውሸቷን ነበር! መሬቱ ከተሸጠበት ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለራሳቸው አስቀርተው ነበር። ስለዚህ አምላክ ሰጲራም እንድትሞት አደረገ።—የሐዋርያት ሥራ 5:1-11

በሐናንያና በሰጲራ ላይ ከደረሰው ነገር ምን እንማራለን?— ይህ ታሪክ አምላክ ውሸታሞችን እንደማይወድ ያስተምረናል። አምላክ ሁልጊዜ እውነቱን እንድንናገር ይፈልጋል። ብዙ ሰዎች ግን ውሸት መናገር ምንም ችግር የለውም ብለው ይናገራሉ። እንዲህ ብለው የሚናገሩ ሰዎች ትክክል ናቸው ብለህ ታስባለህ?— በምድር ላይ ያለው በሽታ፣ ሥቃይና ሞት የመጣው በውሸት ምክንያት መሆኑን ታውቃለህ?—

ኢየሱስ በመጀመሪያ ውሸት የተናገረው ማን ነው ብሏል? ውጤቱስ ምን ነበር?

ዲያብሎስ ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን ውሸት እንደነገራት አስታውስ። አምላክን ባትታዘዝና እንዳትበላ ከከለከላት ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት ነገራት። ሔዋን ዲያብሎስ የተናገረው እውነት መስሏት የተከለከለውን ፍሬ በላች። አዳምንም እንዲበላ አደረገችው። ይህን በማድረጋቸውም ኃጢአተኞች ሆኑ፤ ልጆቻቸው በሙሉም ኃጢአተኞች ሆነው ይወለዳሉ። የአዳም ልጆች በሙሉ ኃጢአተኞች ስለሆኑም ይሠቃያሉ፤ እንዲሁም ይሞታሉ። ይህ ሁሉ ችግር የጀመረው በምን የተነሳ ነው?— በውሸት የተነሳ ነው።

ኢየሱስ ዲያብሎስን “ውሸታምና የውሸት አባት” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው! ለመጀመሪያ ጊዜ ውሸት የተናገረው ዲያብሎስ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ውሸት ሲናገር ዲያብሎስ በመጀመሪያ ያደረገውን ነገር እያደረገ ነው ማለት ነው። ውሸት እንድንናገር የሚገፋፋ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይህ ትዝ ሊለን ይገባል።—ዮሐንስ 8:44

 ውሸት እንድትናገር የሚገፋፋ ሁኔታ ሊያጋጥምህ የሚችለው መቼ ነው?— አንድ ጥፋት ስትሠራ አይደለም?— ሳታስበው አንድ ነገር ወድቆ ተሰብሮብህ ይሆናል። ማን እንደሰበረው ስትጠየቅ ወንድምህ ወይም እህትህ እንደሰበሩት አድርገህ ትናገራለህ? ወይም ደግሞ እንዴት እንደተሰበረ እንደማታውቅ ለማስመሰል ትሞክራለህ?—

ውሸት እንድትናገር የሚገፋፋ ሁኔታ ሊያጋጥምህ የሚችለው መቼ ነው?

የቤት ሥራህን መሥራት ሲኖርብህ የሠራኸው ግማሹን ብቻ ቢሆንስ? ሁሉንም ሳትሠራ ሠርቻለሁ ብለህ ትናገራለህ?— ሐናንያንና ሰጲራን ማስታወስ ይኖርብናል። እውነቱን ሙሉ በሙሉ አልተናገሩም። ውሸት በመናገራቸው ምክንያት አምላክ እነሱን እንዲሞቱ በማድረግ ውሸት መናገር ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ አሳይቷል።

ስለዚህ ምንም ነገር ብናደርግ፣ መዋሸት ምንጊዜም የባሰ ችግር ከማምጣት በቀር ምንም ስለማይጠቅመን ግማሹን እውነት ደብቀን ግማሽ እውነት ብቻ እንኳ መናገር የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነትን ተነጋገሩ” ይላል። በተጨማሪም “አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ” ይላል። ይሖዋ ምንጊዜም እውነትን ስለሚናገር እኛም እውነት እንድንናገር ይፈልጋል።—ኤፌሶን 4:25፤ ቆላስይስ 3:9

ምንጊዜም እውነቱን መናገር አለብን። ዘፀአት 20:16፤ ምሳሌ 6:16-19፤ 12:19፤ 14:5፤ 16:6 እና ዕብራውያን 4:13 ላይ የተገለጸው ሐሳብ ይህ ነው።