በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ከታላቁ አስተማሪ ተማር

 ምዕራፍ 30

ያለብንን ፍርሃት ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ

ያለብንን ፍርሃት ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ

ይሖዋን ማገልገል ቀላል ሆኖ አግኝተኸዋል?— ታላቁ አስተማሪ ይሖዋን ማገልገል ቀላል ነው አላለም። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ሐዋርያቱን “ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ” ብሏቸው ነበር።—ዮሐንስ 15:18

ጴጥሮስ ኢየሱስን ፈጽሞ ጥሎት እንደማይሄድ በጉራ ተናገረ፤ ሆኖም ኢየሱስ በዚያ ሌሊት ጴጥሮስ እሱን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ተናገረ። ደግሞም ጴጥሮስ ያደረገው ይህንኑ ነበር! (ማቴዎስ 26:31-35, 69-75) ይህ ነገር ሊደርስ የቻለው እንዴት ነው?— ይህ ነገር የደረሰው ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት ስለፈሩ ነበር።

ሐዋርያት የፈሩት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ሳያደርጉ በመቅረታቸው ነው። ይህን አስፈላጊ ነገር ማወቃችን፣ ማንም ሰው የፈለገውን ነገር ቢናገረን ወይም ቢያደርግብን፣ ይሖዋን እንድናገለግል ሊረዳን ይችላል። በመጀመሪያ ግን ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የተፈጸመውን ነገር ማወቅ ያስፈልገናል።

በመጀመሪያ አንድ ላይ ሆነው ፋሲካን አከበሩ። ፋሲካ የአምላክ ሕዝቦች ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ለማስታወስ በየዓመቱ የሚያዘጋጁት ልዩ ራት ነበር። ቀጥሎም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ስለ አንድ ልዩ ራት ነገራቸው። ይህ ራት ኢየሱስን እንድናስታውስ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ወደፊት በሌላ ምዕራፍ ላይ እንወያያለን። ይህን ልዩ ራት ከበሉና ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የማበረታቻ ቃላት ከተናገረ በኋላ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ወሰዳቸው። ይህ የአትክልት ሥፍራ ዘወትር ይሄዱበት የነበረ የሚወዱት ቦታ ነው።

 ኢየሱስ ለብቻው ሆኖ ለመጸለይ ትንሽ ራቅ ብሎ ሄደ። ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስም እንዲጸልዩ ነግሯቸው ነበር። እነሱ ግን እንቅልፍ ጣላቸው። ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ለብቻው ትንሽ ራቅ ብሎ እየሄደ ጸልዮ ሲመለስ በሦስቱም ጊዜያት ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ተኝተው አገኛቸው! (ማቴዎስ 26:36-47) ንቁ ሆነው መጸለይ የነበረባቸው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— እስቲ ስለዚህ ጉዳይ እንነጋገር።

ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ነቅተው መጠበቅ የነበረባቸው ለምን ነበር?

በዚያ ምሽት ትንሽ ቀደም ብሎ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የፋሲካን በዓል ሲያከብር የአስቆሮቱ ይሁዳም አብሮ ነበር። እንደምታስታውሰው ይሁዳ ሌባ ነበር። አሁን ደግሞ ከሃዲ ሆነ። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር አዘውትሮ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እንደሚሄድ ይሁዳ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ ኢየሱስን እንዲይዙት ወታደሮች ይዞ ወደዚህ ቦታ መጣ። ወታደሮቹ ወደዚህ ቦታ ሲደርሱ ኢየሱስ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ብሎ ጠየቃቸው።

ወታደሮቹም ‘ኢየሱስን’ ብለው መለሱ። ኢየሱስ ምንም ሳይፈራ “እኔ ነኝ” አላቸው። ወታደሮቹ በኢየሱስ ድፍረት ተደናግጠው ወደ ኋላቸው ሲያፈገፍጉ መሬት ላይ ወደቁ። ከዚያም ኢየሱስ ‘የምትፈልጉት እኔን ከሆነ ሐዋርያቴን ተዉአቸውና ይሂዱ’ አላቸው።—ዮሐንስ 18:1-9

ወታደሮቹ ኢየሱስን ይዘው እጁን ሲያስሩ ሐዋርያቱ ፈሩና ሸሽተው ሄዱ። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን የሚሆነውን ለማየት ስለፈለጉ በርቀት ይከታተሉ ነበር። በመጨረሻም ኢየሱስ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ቤት ተወሰደ። ሊቀ ካህናቱ ዮሐንስን ያውቀው ስለነበር በር ጠባቂዋ እሱንም ሆነ ጴጥሮስን ወደ ግቢው አስገባቻቸው።

ካህናቱ ፍርድ ለመስጠት አስቀድመው ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት መጥተው ነበር። ኢየሱስን ማስገደል ፈልገው ነበር። ስለዚህ በኢየሱስ ላይ በሐሰት የሚመሠክሩ ምሥክሮችን አመጡ። ሰዎቹ ኢየሱስን በቡጢና በጥፊ መቱት። ይህ ሁሉ ሲሆን ጴጥሮስ በአቅራቢያው ሆኖ ይመለከት ነበር።

ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ያስገባቻቸው በር ጠባቂ ወይም አገልጋይ ጴጥሮስን ለይታ አወቀችው። ‘አንተም ከኢየሱስ ጋር ነበርክ!’  አለችው። ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ጭራሽ አላውቀውም ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሌላ ሴት ጴጥሮስን አወቀችውና በዚያ ለቆሙት ሰዎች ‘ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ነበር’ አለች። ጴጥሮስ አሁንም አላውቀውም ብሎ ካደ። ከዚያም ትንሽ ቆይቶ በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ሰዎች “በእርግጥ አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አሉት። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም!” ብሎ ካደ። እንዲያውም ጴጥሮስ የተናገረው እውነት መሆኑን ለማሳየት ማለ፤ ኢየሱስም ዞር ብሎ ተመለከተው።—ማቴዎስ 26:57-75፤ ሉቃስ 22:54-62፤ ዮሐንስ 18:15-27

ጴጥሮስ በጣም ፈርቶ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ የዋሸው ለምን ነበር?

ጴጥሮስ የዋሸው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አዎ፣ ጴጥሮስ የዋሸው ፈርቶ ነው። ግን ለምን ፈራ? ድፍረት ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረበት? እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ ድፍረት ለማግኘት ምን አድርጓል?— ኢየሱስ ወደ አምላክ የጸለየ ሲሆን አምላክም ድፍረት እንዲኖረው ረድቶታል። ደግሞም ኢየሱስ ጴጥሮስን እንዲጸልይና ነቅቶ እንዲጠብቅ ሦስት ጊዜ ነግሮት እንደነበረ አስታውስ። ነገር ግን የሆነው ነገር ምን ነበር?—

ጴጥሮስ ሦስቱንም ጊዜ ተኝቶ ተገኝቷል። አልጸለየም፤ ነቅቶም  አልጠበቀም። ስለዚህ ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ ሁኔታው ለጴጥሮስ ያልተጠበቀ ነገር ሆኖበታል። በኋላም ኢየሱስ ለፍርድ ቀርቦ ሲመቱትና ሊገድሉት ሲያሤሩ ጴጥሮስ ደነገጠ። ሆኖም ከጥቂት ሰዓታት በፊት ኢየሱስ ሐዋርያቱን ምን ሁኔታ እንዲጠብቁ ነግሯቸው ነበር?— ኢየሱስ ዓለም እሱን እንደጠላው እነሱንም እንደሚጠላቸው ነግሯቸው ነበር።

እንደ ጴጥሮስ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥምህ የሚችለው እንዴት ነው?

አሁን ደግሞ በጴጥሮስ ላይ የደረሰውን ሁኔታ የሚመስል ምን ነገር ሊደርስብን እንደሚችል እናስብ። በትምህርት ቤት በክፍል ውስጥ ሆነህ ብሔራዊ መዝሙር ስለማይዘምሩና ገናን ስለማያከብሩ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲነገር ሰማህ እንበል። አንድ ሰው ወደ አንተ ዞር ብሎ “ብሔራዊ  መዝሙር አትዘምርም የተባለው እውነት ነው?” ቢልህ ምን ትላለህ? ወይም ደግሞ ሌሎቹ “ገናን እንኳ አታከብርም አሉ!” ቢሉህስ ምን ትላለህ? እውነቱን መናገር ትፈራለህ?— አንተም እንደ ጴጥሮስ መዋሸት ትፈልጋለህ?—

ጴጥሮስ ግን ከዚያ በኋላ ኢየሱስን በመካዱ በጣም አዝኖ ተጸጽቷል። ያደረገውን ነገር ሲያስበው ወደ ውጪ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። አዎ፣ ጴጥሮስ ንስሐ ገብቶ እንደገና ኢየሱስን መከተሉን ቀጥሏል። (ሉቃስ 22:32) ታዲያ እንዳንፈራና እንደ ጴጥሮስ ውሸት እንዳንናገር ምን ሊረዳን ይችላል?— ጴጥሮስ እንዳልጸለየና ነቅቶ እንዳልጠበቀ አስታውስ። ስለዚህ የታላቁ አስተማሪ ተከታዮች ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል ትላለህ?—

ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ እንደሚያስፈልገን የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ በጸለየ ጊዜ አምላክ ምን እንዳደረገለት ታውቃለህ?— የሚያበረታው መልአክ ልኮለታል። (ሉቃስ 22:43) የአምላክ መላእክት እኛንም ሊረዱን ይችላሉ?— መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 34:7) ይሁን እንጂ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ከመጸለይ በተጨማሪ ማድረግ ያለብን ሌላም ነገር አለ። ሌላ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ታውቃለህ?— ኢየሱስ ተከታዮቹን ዘወትር ነቅተው እንዲጠብቁ ነግሯቸዋል። ነቅተን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ይመስልሃል?—

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚነገረውን ነገር በደንብ ማዳመጥና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለምናነበው ነገር ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለይና እንድናገለግለው እንዲረዳን መጠየቅ ያስፈልገናል። እንዲህ ካደረግን ፍርሃታችንን ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ እናገኛለን። ከዚያም ስለ ታላቁ አስተማሪና ስለ አባቱ ለመናገር አጋጣሚ ስናገኝ እንደሰታለን።

የሚከተሉት ጥቅሶች ሰዎችን ፈርተን ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳንል ሊረዱን ይችላሉ:- ምሳሌ 29:25፤ ኤርምያስ 26:12-15, 20-24፤ ዮሐንስ 12:42, 43